Saturday, 13 June 2015 15:00

3ኛው ሆቴል ሾው ኢትዮጵያ 2007 ነገ ይዘጋል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

      ከትናንት በስቲያ በድምቀተ የተከፈተው 3ኛው ሆቴል ሾው ኢትዮጵያ 2007 የሆስፒታሊቲ ቱሪዝም ፎረምና ኤክስፖ ነገ ይዘጋል ሲሉ የኦዚ ቢዝነስና ሆስፒታሊቲ ግሩፕ መስራችና ማኔጂንግ ዳይሬክተር አስታወቁ፡፡
ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ አቶ ቁምነገር ተከተል በተለይ ለጋዜጣው ሪፖርተር በሰጡት መግለጫ፤ ነገ ለአካባቢ ጥበቃ የሚቆረቆሩና የሚጨነቁ ሆቴሎች ተወዳድረው አሸናፊውን በመሸለም የንግድ ትርኢትና ኤክስፖው ይዘጋል ብለዋል፡፡
ለሦስተኛ ጊዜ ከሰኔ 4 ጀምሮ በሚሊኒየም አዳራሽ ሲካሄድ የቆየው የንግድ ትርኢትና ኤክስፖ  ዓላማ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው፣ በአፍሪካ ታዋቂ የሆነና በኢትዮጵያዊ ባህላዊ መሠረት ላይ የተገነባ የሆስፒታሊቲና የቱሪዝም መድረክ መፍጠር ነው ያሉት አቶ ቁምነገር፤ ባለድርሻ አካላት መድረክ ፈጥረው በዓለም አቀፍ መስፈርት መሰረት በአገር ውስጥ የሚታዩ ኢንዱስትሪ ነክ ጉዳዮችን ለመዳሰስ፣ አዳዲስ አሰራሮችን ለመጋራትና ለልምድ ልውውጥ አመቺ ሁኔታ መፍጠር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በ3ኛው ሆቴል ሾው ኢትዮጵያ ከኢጣሊያ፣ ፈረንሳይ፣ ዩ.ኤስ.ኤ፣ ታይላንድ፣ ቱርክ ደቡብ አፍሪካ፣ ግብፅ፣ ዱባይና ቻይና የመጡ 145 አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶች፣ የቢዝነስ ሀሳቦች (አይዲያ) የያዙና የገበያ አፈላላጊ ኩባያዎች እየተሳተፉ እንደሆነ ታውቋል፡፡
በንግድ ትርኢትና ኤክስፖው ላይ ሁለት ጥናታዊ ጽሁፎች እንደሚቀርብ የጠቀሱት ማኔጂንግ ማናጀሩ፣ ትናንት ቤልጂየማዊው የ “ሄድ ኳተር ማጋዚን” ማኔጂንግ ዳይሬክተር፣ የኢትዮጵያን የሆስፒታሊቲ ኢንዱስትሪ ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር በሚል ርዕስ ጥናታዊ ፅሑፍ ማቅረባቸውን፣ ዛሬ ደግሞ ደቡብ አፍሪካዊው የቢዝነስ ቱሪዝም  ኩባንያ ፕሬዚዳንት፤ የኢትዮጵያ የስብሰባ የኢንሼዬንቲቭ፤ (ኮንፈረንስ፣ ኤግዚቢሽን ወይም ኤቨንት) እምቅ የቱሪዝም ገበያ ዕድሎችና አጠቃቀማቸው በሚል ርዕስ ጽሑፍ ያቀርባሉ፡፡ እስካሁን በኢትዮጵያ ስብሰባዎች የሚካሄዱት በመንግስት አዘጋጅነት ብቻ ሳይሆን ቢዝነሱ ራሱ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት እንዳለበት ጠቅሰው፤ ለምሳሌ ቢልጌት 2 ሚሊዮን ዶላር መድቦ በኤድስ ላይ ዓለም አቀፍ ጉባኤ እንዲያዘጋጅ ዕድሉ ለግል ኮንፈረንስ አዘጋጅ ድርጅቶች ቢሰጥ፣ የአዘጋጅቱን ኃላፊነት የወሰደው ድርጅት በኤድስ በብዛት የተጎዳችው አፍሪካ ስለሆነች ስብሰባውን በአፍሪካ ለማድረግ ወስኖ በየትኛዋ አገር ይካሄድ? ብሎ ሲፈልግ፣ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ማዘጋጀት እንደምትችል ታውቆ ከቢዝነሱ የሚገኘው ገቢ (ማይስ MICE) መጠቀም በምትችልበት አሰራር ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀርባሉ ብለዋል፡፡  የንግድ ትርኢቱና ኤክስፖው በተከፈተበት ሥነ-ሥርዓት በሚቀጥለው ዓመት በመጋቢት ወር ስራ የሚጀምረው የስብሰባ፣ ኢንሴንቲቭ፣ ኮንፈረንስ (ኮንግረስ) ኤግዚቢሽን (ኢቨንት) አዘጋጅ ማይስ MICE ምሥራቅ አፍሪካ 2008 ፎረምና ኤክስፖ መቋቋሙን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ሚኒስትር ክቡር ሬድዋን ሁሴንና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተወካይ አቶ ተወልደ ወ/ማርያምን በመወከል አቶ ኢሳያስ ወ/ማርያም ይፋ አድርገዋል፡፡
ነገ ቨ3ኛው ሆቴል ሾው ኢትዮጵያ 2007 የንግድ ትርኢትና ኤክስፖ ከመዘጋቱ በፊት በተለያዩ ሆቴሎችና ሪዞርቶች መካከል የሙያ ውድድርና የልምድ ለውውጥ እንደሚካሄድ፣ እንዲሁም በዲዛይንና ግንባታ ወቅት ለአካባቢ ጥበቃ ክብካቤ ከፍተኛ ትኩረት በሰጡ ሆቴሎችና ሪዞርቶች መካከል ውድድር ተካሂዶ አሸናፊዎቹ እንደሚሸለሙ አቶ ቁምነገር ተከተል አስታውቀዋል፡፡  

Read 2568 times