Saturday, 13 June 2015 14:58

ኮካኮላ “እንችላለን፤ ቢሊዮን ምክንያቶች አሉን” የሚል የስኬት ዘመቻ ጀመረ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ኮካኮላ ኢትዮጵያ ከተለያዩ የአዲስ አበባ ት/ቤቶች ከተውጣጡ 50 ታዳጊ ተማሪዎች ጋር “በራስ ለመተማመን ቢሊዮን ምክንያቶች አሉን” በሚል መርህ ባለፈው ረቡዕ በሻላ መናፈሻ ዘመቻ ጀመረ፡፡
“በራስ ለመተማመን ቢሊዮን ምክንያቶች” በሚል መሪ ቃል ኮካኮላ በመላው አፍሪካ የጀመረው ዘመቻ አካል ሲሆን ዓላማውም ወጣት አርቲስቶች የተለያዩ ችግሮችን አልፈው ለስኬት የበቁበትን ተሞክሮ ለታዳጊዎች በማካፈል የአህጉሩን ቀና አስተሳሰብና አስደናቂ ታሪኮች በመሰብሰብ፣ የአፍሪካን ልዩ ታሪኮች ለማክበር መንገድ መክፈት እንደሆነ የኮካኮላ ኢትዮጵያ ማናጀር ሚ/ር ኬንጐሪ ማቻሪያ ገልፀዋል፡፡
ድርጅቱ ከተለያዩ የሕይወት ዘርፎች አራት ተፅዕኖ ፈጣሪ አርቲስቶች ያጋጠሟቸውን ፈታኝ ችግሮች እንዴት አልፈው ለስኬት እንደበቁ ለኢትዮጵያ ታዳጊዎች እንዲያካፍሉ የመረጠ ሲሆን እነሱም በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያተረፈችው ዲዛይነር ማኅሌት አፈወርቅ (ማፊ)፣ በኢትዮጵያ የሬጌ አልበም ያወጣው ስኬታማ ሙዚቀኛ ዮሐንስ በቀለ (ጆኒራጋ) ከፍተኛ እውቅና ካላቸው ሴት ዲጄዎች አንዷ የሆነችው የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ ማርሼት ፍሰሐ (ዲጄ የሚ) እና አካል የሚያደክም በሽታ ቢኖርበትም በፅናት ተቋቁሞ ለስኬት የበቃውና በአነቃቂ ንግግሮቹ የሚታወቀው ሰዓሊ ብሩክ የሺጥላ ናቸው፡፡
በዝግጅቱ ወቅት ታዳጊዎች በተለያዩ ምድቦች ተከፋፍለው እንዲሁም በግለሰብ ደረጃ ከተፅዕኖ ፈጣሪዎቹ ዝነኞቹ ጋር ተነጋግረዋል፡፡ ይህም ታዳጊዎች ውጤታማ አርአያ ሞዴሎች ለማግኘት ልዩ ዕድል የፈጠረላቸው ከመሆኑም በላይ የሥራ ፈጠራ፣ ከባድ ሥራ፣ የሕይወት ተድላና ስኬት በቀላሉ እንደማይገኝ የሚያሳይ እውነታ ተምረውበታል ብለዋል የኮካኮላ ኃላፊ፡፡

Read 2595 times