Saturday, 13 June 2015 14:57

10ሺህ ጐበዝና ድሃ ሕፃናትን የማስተማር ውጥን

Written by  መንግስቱ አበበ
Rate this item
(2 votes)

በአዲስ አበባ 36ሺ የምግብ ድጋፍ የሚፈልጉ ህፃናት አሉ
በአትሌት ኃይሌ ሚመራ “አንድ ልጅ ይርዱ” ቅስቀሳ ይጀመራል


አገር በቀሉ “ቪዥን ፎር ጀነሬሽን” መሥራችና የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ያሬድ ግርማ ከ4 ዓመት በፊት ለሥራ ጉዳይ ወደ ድሬዳዋ ሄዶ ነበር፡፡ በጨዋታ ጨዋታ “ለመማር ከፍተኛ ፍላጐት ያላቸውና የትምህርት አቀባበላቸውም በጣም ጥሩ የሆኑ ልጆች በመንግሥት አንደኛ ደረጃ ት/ቤት እየተማሩ ነው፡፡ እነዚህ ጐበዝ ልጆች ጥሩ እውቀት የሚያገኙበት ት/ቤት ቢማሩ የተሻለ እውቀት ቀስመው፣ የነገዋን ኢትዮጵያ ተረክበው የተጀመረውን ዕድገት ያፋጥኑ ነበር፡፡ ነገር ግን ጥሩ እውቀት የሚቀስሙበት ት/ቤት እንዳይማሩ የቤተሰቦቻቸው ድህነት እንቅፋት ሆነባቸው፡፡…” የሚል አሳዛኝ ነገር ሰማና ከልቡ አዘነ።
በአዲስ አበባ የጐስቋሎች መናኸሪያ በሆነችው ጨርቆስ አካባቢ ተወልዶ ያደገው አቶ ያሬድ፤ የድህነትን አበሳና ጠባሳ በሚገባ ያውቃል፡፡ አቶ ያሬድ ሰሞኑን በጽ/ቤቱ በሰጠው መግለጫ፤ “ሀብታም ሰው ሳናይ ነው ያደግነው፡፡ ቂርቆስ የተወለደ ልጅ ትምህርት የሚያገኘው በዕድል ነው።” ብሏል፡፡ በመላ አገሪቱ ከድሃ ቤተሰብ የተወለዱና የትምህርት አቀባበላቸው ከፍተኛ የሆነ በርካታ ልጆች እንዳሉ ያምናል፡፡ እነዚህ ልጆች ድጋፍ ቢያገኙ በቀሰሙት እውቀት አገራቸውን በማበልፀግ ውለታ መላሽ ይሆናሉ፡፡ ድጋፍ ካላገኙ የነበራቸውን ጥሩ የትምህርት አቀባበል ችሎታ አጥተው (ተነጥቀው) የአገርና የኅብረተሰቡ ሸክም ሲሆኑ ታየውና ከማኅበሩ አባላት ጋር የዜግነት ኃላፊነታቸውን ለመወጣት መንቀሳቀስ ጀመሩ፡፡
ችግሩን በግላቸው ብቻ መወጣት ስለማይችሉ፣ ደርባ ሲሚንቶ ፋብሪካ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠየቁ፡፡ ድርጅቱም በሐሳባቸው ተስማምቶ 100 ሺህ ብር ፈቀደላቸው፡፡ አቶ ያሬድ ወደ ድሬዳዋ ተመልሶ ከተለያዩ 5 የመንግሥት ት/ቤት ከፍተኛ የትምህርት አቀባበል ችሎታ ያላቸውን 12 የድሃ ቤተሰብ ልጆች ከ5ኛ፣ ከ6ኛ፣ ከ7ኛ ክፍል መርጦ፣ በድሬዳዋ እንደ አዲስ አበባው ቅዱስ ዮሴፍ በሚቆጠረው ኖተርዳም ካቶሊክ ት/ቤት አስገብቶ ለት/ቤቱና ለትምህርት መርጃ መሳሪያዎች ለዩኒፎርም በወር 1,000 ብር እየከፈሉ አስተማሩ፡፡
ልጆቹ ከአራት ልጆች ዓመት በኋላ ያስመዘገቡት ከፍተኛ ውጤት ጮቤ የሚያስረግጥ እንደሆነ አቶ ያሬድ በኩራትና በደስታ ገልጿል፡፡ አምና አራቱ የ10ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ወስደው ሦስቱ ልጆች ከፍተኛውን 4፡00 ማምጣታቸውን ተናግሯል። ልጆቹ ያመጡት ውጤት ከፍተኛ ሞራል ስለሰጠው፣ ከፍተኛ የትምህርት አቀባበል ያላቸውን የድሃ ቤተሰብ ልጆች ማስተማሩን ለመቀጠል አበረታታው፡፡
ነገር ግን አንድ ችግር ታየው፡፡ ልጆቹን ያስተማሩት በወር 1000 ብር እየከፈሉ ነበር፡፡ የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርግ ድርጅት ቢጠፋ ልጆቹ ትምህርታቸው ስለሚቋረጥ ለምን ት/ቤት አንሰራም? አሉ፡፡ እኛ እንጀምረውና ካልሆነልን ኅብረተሰቡ ይጨርሰዋል በማለት አዳሪ ት/ቤት ለመሥራት ተንቀሳቅሰው በጐንደር 20ሺህ ካ.ሜ ቦታ አገኙ፡፡  የት/ቤቱ ግንባታ 117 ሚሊዮን ብር ይፈጃል፡፡ ለት/ቤቱ ማሰሪያ በሸራተን ሆቴል የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም አዘጋጅተው፣ 10 ሚሊዮን ብር ቃል ተገብቶላቸዋል፡፡ ሌላ ችግር ደግሞ  ታያቸው፡፡ ለት/ቤቱ ግንባታ የሚያስፈልገው ገንዘብ እስኪሟላና ቃል የተገባውም እስኪሰበስብ ድረስ ብዙ ጊዜ ይፈጃል፡፡ በዚህ ሂደት ት/ቤት አሠርቶ ልጆቹን ተቀብሎ የማስተማር ዕቅዳቸው ብዙ ጊዜ ይቆያል። ከድሃ ቤተሰብ የሚወለዱ ልጆች አንዱና ዋነኛው ችግር የምግብ እጦት ስለሆነ ለምን ልጆቹ ባሉበት ት/ቤት እየተረዱ፣ እንዲማሩ ከቋሚ ድርጅቶች ጋር አናገናኝም? በማለት እንቅስቃሴ ጀመሩ፡፡
ዓላማቸውን የሚገልጽ ፕሮፖዛል አዘጋጅተው፣ ለመከላከያ ሚኒስቴር አስገቡ፡፡ ሚኒስትሩም ሐሳቡን በደስታ ተቀብሎ በአራዳና በቂርቆስ ክፍለ ከተማ በሚገኙ 14 ት/ቤቶች የትምህርት አቀባበላቸው ከፍተኛ የሆኑ 315 ተማሪዎች ለመደገፍ በዓመት 1.4 ሚሊዮን ብር መደበ፡፡ ልጆቹ የምግብ አቅርቦቱን የሚያገኙት በሚማሩበት ት/ቤት መዝናኛ ክበብ ነው፡፡ በየቀኑ እንዲመገቡ ለአንድ ልጅ 12 ብር ለክበቡ ይከፍላሉ፡፡ ልጆቹ በትምህርታቸው ጥሩ ውጤት ካመጡ በመከላከያ ተቋማት ትምህርታቸውን ለማስቀጠል፣ ከዚህም በላይ በውጭ አገር ነፃ የትምህርት ዕድል (ስኮላርሺፕ) እንዲያገኙ ለማድረግ መ/ቤቱ ቃል ገብቷል፡፡ ሌላው በሐሳባቸው ተስማምቶ ሊደግፋቸው ቃል የገባው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነው፡፡ አየር መንገዱ በቦሌ ክፍለ ከተማ የሚገኙ 150 የድሃ ቤተሰብ ልጆች ለመመገብ ተስማምቷል፡፡ ለዚህም ለአየር መንገዱ ለሠራተኞች የተዘጋጀውን ምግብ ከክበቡ እየወሰዱ በየት/ቤቱ የሚያደርሱ 5 ተሽከርካሪዎች የመደበ ሲሆን ምገባው ዛሬ እንደሚጀመር አቶ ያሬድ ገልጿል፡፡ ከምግቡ በተጨማሪ ተማሪዎቹ በትምህርታቸው ጥሩ ውጤት ካመጡ በአየር መንገዱ አካዳሚ ገብተው የመሠልጠንና የማገልገል ዕድል ለመስጠት ቃል ገብቷል፡፡ በቅርቡ በአትሌት ኃይሌ ገ/ሥላሴ የሚመራ “አንድ ልጅ ይርዱ” የሚል ቅስቀሳ እንደሚጀመር አቶ ያሬድ ገልጿል፡፡
በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ 36‚000 የምግብ ድጋፍ የሚፈልጉ ሕፃናት እንዳሉ የጠቀሰው የድርጅቱ መስራችና የቦርድ ሰብሳቢ፤ የሁሉንም ሕፃናት የምግብ ችግር መፍታት ባይችሉም በ13 ዓመት (በኢትዮጵያ አቆጣጠር እስከ 2020 ዓ.ም) 10 ሺህ ሕፃናት፣ 1ኛ፣ 2ኛ እና የመሰናዶ ትምህርታቸውን እስኪጨርሱ እየመገበ እንደሚያስተምርና በአሁኑ ወቅት 470 እንደሚረዳ አስታውቋል፡፡
“ቪዥን ፎር ጀነሬሽን” ከ4 ዓመት በፊት ሲቋቋም የመጪው ትውልድ አገር ተረካቢ ሕፃናት ጥሩ አገር ኖሯቸው፣ አገር ወዳድ ዜጋ እንዲሆኑ ማስተማር ነበር ራዕዩ፡፡ ባለፈው 3 ዓመት ሲሰራ የቆየው ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገቡ ሴት ተማሪዎች ከፍተኛ ችግር ስለነበረባቸው እነሱን መርዳት ነበር። ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከገቡት መካከል 70 በመቶ ትምህርት የሚያቋርጡት ሴቶች ነበሩ፡፡
በት/ቤቶቹ አካባቢ ከፆታ ትንኮሳ አልፎ ከባህል ያፈነገጡ አስነዋሪ ተግባራት ይፈፀሙ ነበር። ድርጅቱ ችግሮቹ ከምን እንደመጡ ለማወቅ ባደረገው ጥናት ሦስት ችግሮች ለይቷል፡፡ አንደኛው ችግር ለተመደቡበት አካባቢ አዲስ መሆን፣ የግንዛቤ ማነስና ከቤተሰብ ቁጥጥር ነፃ መሆን ነበር፡፡
ሁለተኛው የገንዘብ ችግር ነው፡፡ ብዙቹ ሴት ተማሪዎች ከገጠር የመጡ የአርሶ አደሩ ልጆች ስለሆኑ ከፍተኛ የገንዘብ ችግር ነበረባቸው፡፡ ለደብተር መግዣ እንኳ ይቸግራቸው ነበር፡፡ አገር በቀል በመሆናቸው የሁሉንም ሴቶች ችግር መቅረፍ ባይችሉም፣ ከአገር ውስጥ ባገኙት 10 ሚሊዮን ብር ለ1000 ሴት ተማሪዎች ትምህርታቸውን እስኪጨርሱ በየወሩ 200 ብር እየሰጡ እያስተማሩ እንደሆነ አቶ ያሬድ ገልጿል፡፡  ስለዚህ ሴት ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ ከመግባታቸው በፊት መስከረም 5 ቀን በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ስኬታማ የሆኑ ሴት ተማሪዎች ላለፈው 3 ዓመት ተሞክሯቸውን እንዲያካፍሉ አድርገናል ብሏል፡፡ ይህን የልምድ ልውውጥ ያደረጉት በአዲስ አበባ፣ በድሬዳዋና በሐረሪ ሲሆን በአዲስ አበባ ብቻ 27 ሺህ ሴት ተማሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የሴቶች ችግር ውስብስብ ስለሆነ ለብቻው በማውጣት፣ ጥቅምት 5 ቀን 2007 ቀዳማይ እመቤት ሮማን ተስፋዬ በተገኙበት “ዘር ኢትዮጵያ” የተባለ ድርጅት ማቋቋማቸውን አቶ ያሬድ ግርማ ተናግሯል፡፡    

Read 2504 times