Saturday, 13 June 2015 14:48

“እንደምንም ብሎ ይሄስ ቀን…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(6 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ልጀቷ አባቷን…“አባዬ ማንን ላግባ፣ መልከ መልካሙን አበበን ወይስ ታማኙን ከበደን?” ትለዋለች፡ አባትም…
“ከበደን አግቢው፣” ይላታል፡፡
“ለምን?” ስትለው ምን ቢል ጥሩ ነው…
“ላለፉት ሰባት ወራት በመጣ ቁጥር ገንዘብ ስበደረው ቆይቻለሁ፡፡ ግን ይህ ሆኖ በሳምንት ሁለት ጊዜ አንቺ ዘንድ መምጣቱን አላቋረጠም፡፡”
ልጄ¸..ኑሮ ሲከፋ አባትም የልጁን ትዳር ጓኛ ከራሱ ‘ናሽናል ኢንተረስት’ (ቂ…ቂ…ቂ…) ማየት ቢጀምር ምን ይገርማል!
ነገርዬው… “እንደምንም ብሎ ይሄስ ቀን ባለፈ!” ሆኗላ!
ስሙኛማ… የምር ግን ኑሮ ከባድ፣ በጣም ከባድ እየሆነ ነው፡፡ አብዛኛውን ህዝብ ጧት ማታ ስለ ኑሮ የሚያማርረው ‘አልቃሻ’ ስለሆነ ወይም ‘ወተት ሲያቀርቡለት ፋንዲያ የሚል’ ስለሆነ አይደለም፡፡ ወይም “እነ እከሌ አማረባቸው፣ አለጠለጡ!” ብሎ ‘ስለሚመቀኝ’ አይደለም፡፡ ግራ ስለገባው ነው። ከቤቱ ሲወጣ መሳቀቅ፣ እቤቱ ሲመለስ ይበልጥ መሳቀቅ ስለበዛበት ነው፡፡ በየእምነታችን ስፍራ እየሄድን ተደፍተን… “እንደምንም ብሎ ይሄስ ቀን ባለፈ!” የምንለው…ችጋር ጠሪ ስለሆንን አይደለም፡፡
የምር እኮ የመሠረታዊ ዕቃዎች ዋጋ በየሁለትና ሦስት ቀኑ ሲያሻቅብ ‘ሀይ’ የሚል አለመኖሩ… አለ አይደል… “እረኛ የሌለን መንጋ…” መሆናችን ያሳዝናል፡፡ እናማ…“እንደው መጨረሻችን ምን ይሆን የምንለው ወደን ሳይሆን የምንለው ሲጠፋን ነው፡፡
“እንደምንም ብሎ ይሄስ ቀን ባለፈ!” የምነለው ቢቸግረን ነው፡፡
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል……ኑሮን በተመለከተ ዛሬ የኤፍ.ኤም. ጋዜጠኛ መሆን አምሮኛል፡፡
የኑሮን ነገር በተመለከተ ዛሬ ቃለ መጠይቅ ልናደርግ ስቱዲዮአችን አንድ እንግዳ አሉ፡፡ ወ/ሮ እንደልቧ አገሬ ሲሆኑ የቤት እመቤትና የአምስት ልጆች እናት ናቸው፡፡ አድማጫቾቸን በቀጥታ የስልክ መስመር ወይም በጽሁፍ መልእክተ ሀሳባቸሁብን ግለጡልን፡፡
ስምዎን ቢነገሩኝ፡፡
(ይሄኔ በልቧ “ማማሲያዬን ይዤ በመጣሁ ኖሮ፣ አናቱን የቻይና ብርጭቆ አደርገው ነበር!” ሳትል አትቀርም፡፡)
“እንደልቧ አገሬ እባላለሁ፡፡”
“ኑሮን እንዴት ይዘውታል?”
“ምን አልከኝ?”
“ኑሮን እንዴት ይዘውታል?”
“እንዴት ይዘውታል ብሎ ነገር ምንድነው! ኑሮ ጉሮሯችን አንቆ ትንፋሽ አሳጥቶን እንዴት ይዘውታል ትለኛለህ!”
“ይቅርታ…ኑሮ እንዴት ይዞዎታል?”
“እንዴት የያዘኝ ይመስለሀል…በርበሬ ኪሎ መቶ ሠላሳ ብር ገብቶ፣ ቅቤ ሁለት መቶ ሰባ ብር ገብቶ…ሦስት ራስ ሽንኩርት ዋጋው ራስ ላይ ወጥቶ እንዴት ይዞሻል ትለኛለህ!”
(“እንደምንም ብሎ ይሄስ ቀን ባለፈ!” የሚያሰኙ ነገሮች ብዙ ናቸው፡፡)
“ማለት የፈለግሁት…ይቅርታ አድማጭ መስመር ላይ አለ…ሀሎ አድማጫችን!
“ሀሎ! ‘ወይ ኑሮ፣ ወይ ኑሮ’ ፕሮግራም ነው?”
“ነው፡፡”
“አስተያየት ለመስጠት ነበር…”
“እሺ ማን እንበል ከየት ነው?”
“ቹቹ ነኝ፣ ከሀያ ሁለት…ምን ለማለት ፈልጌ ነው፣፣ ሴትዮዋ አምስት ልጅ ወልደው እሰካሁን በኑሮ ክፋት ገዳም አለመግባታቸው አድናቂያቸው እንደሆንኩ ለመግለጽ ነው፡፡”
“እርሶስ ኑሮ እንዴት ነው ይላሉ...”
“እነሱ ምን ቸገራቸው፣ ገበያ አይወጡ መርካቶና አትክልት ተራ የት እንዳለስ ያውቁታል?  ውስኪያቸውን እያንቃረሩ…“ ቀጭ!
(“እንደምንም ብሎ ይሄስ ቀን ባለፈ!” የሚያሰኙ ነገሮች ብዙ ናቸው፡፡)
“ይቅርታ ስልኩ ተቋርጧል…ወ/ሮ እንደልቧ…አሁን ያለውን የኑሮ ጫና ለመቀነስ ምን መደረግ አለበት ይላሉ?”
“እና ምን አውቃለሁ…ነጋዴውን አንድ ይበሉልና! መንግሥት ስንበዘበዝ ዝም ብሎ የሚያየው ለምንድነው?”
“ቴክኒሻኗ አድማጭ ገብቷል እያለችኝ ነው…ሀሎ!”
“ሀሎ፣ ማን እንበል?”
“ቲቲ ነኝ ከአዲስ አበባ…”
“እሺ ቲቲ ሀሰብዎ ምንድነው?”
“ኸረ አንቱ አይደለሁም!”
“ተማሪ ነሽ ቲቲ?”
“አዎ…ግን ለምንድነው ኬክ ቤቶች አንድ የማይሏቸው! አንድ ፎርስት ኬክ ሠላሳ ብር እየሸጡ…እማዬ ትሙት ሲያስጠሉ!”
“እሺ ቲቲ መልእክትሽን አስተላልፈናል፡፡”
(እነ ቲቲ ዘንድም “እንደምንም ብሎ ይሄስ ቀን ባለፈ!” የሚያሰኙ ነገሮች ብዙ ናቸው፡፡)
“ደዋያችን ስለሰጠሽው ሀሳብ እናመሰግናለን… ወ/ሮ እንደልቧ በአሁኑ ጊዜ አምስት ልጆች ማስተዳደር አስቸጋሪ አይሆንም?”
“ተው እባክህ… እንኳን ለእነሱ ለዘመድ እንተርፍ ነበር…ክፉ ዘመን መጣና…”
“ይቅርታ አድማጭ ገብቷል…ሀሎ አድማጫችን ማን እንበል?”
“ስሜ ይቆይልኝ፡፡”
“እሺ ስለ ኑሮ ያለዎትን ሀሳብ ቢያካፍሉን፡፡”
“መጀመሪያ ነገር ለማሰብ መብላት ያስፈልጋል፣ ምኑን በልተን እናስብ! አገሩ ሁሉ ወሮበላ…”
“ይቅርታ አድማጫችን ከርእሳችን ባይወጡ…”
“አልኩህ እኮ… በየቦታው ያለው ሌባ ብቻ ነው…”
“አሁን እየተነጋገርን ያለነው ስለ ኑሮ ነው፡ አጠቃለይ ሃሳብዎን ቢገልጹልን፡፡”
“እኔም እኮ ስለ ኑሮ ነው የማወራው፣ ስማ ቀበሌያችን እንደ ቀንድና ጭራ የሌለው የሸማቾች…” ቀጭ!
(“እንደምንም ብሎ ይሄስ ቀን ባለፈ!” የሚያሰኙ ነገሮች ብዙ ናቸው፡፡)
“ይቅርታ ስልኩ ተቋርጧል፡፡ ከቻልን ደዋያችንን ደግመን ልናገኛቸው እነሞከራለን፡፡” (“እሱን እንኳን ተወው!” በሉኛ፡፡)
እናማ የዕለት ከዕለት ኑሯችንን በተመለከተ… “እንደምንም ብሎ ይሄስ ቀን ባለፈ!” የሚያሰኙን ነገሮች መአት ናቸው፡፡
ሦስትና አራት ብር ሲጨመር… አለ አይደል… “ቁ!…ቁ!…” (“እሪ!” እንደማለት) ልንል ምንም አይቀረን ነበር፡፡ አሁን ግን አምጥተው ‘ሲዘረግፉብን’ ዝም ብለን እያያን ነው፡ የእኛ ትከሻ ለመልመድ ማን ብሎት! በርበሬ በአጭር ወራት ወደ ሁለት መቶ ከመቶ ሲያድግ “ቁ!…ቁ!…” ማለት አቅቶናል፡፡
ስሙኝማ… ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ይቺን ስሙኝማ…ሴትዮዋ ሱፐርማርኬት ውስጥ እያንጎራጎረችና እየዘፈነች ነበር፡፡
“ዛሬ በጣም ደስ ብሎሻል፡፡ ምን ተገኘ?”
“አዎ…ትልቅ ቤት አለኝ፣ ሁለት ቆንጆ ልጆች አሉኝ፡ ባንክ ገንዘብ አለኝ፣ የባሌ የህይወት ኢንሹራንስ መቶ ሺህ ዶላር ነው…እሱ ደግሞ ጤናው ተቃውሶ አንድ ሐሙስ ነው የቀረው፡፡”
ሱፐርማርኬት ውስጥ የምታንጎራጉር ሴት ከገጠመቻችሁ ወይ ‘ሲንግል’ ለመልቀቅ እየተዘጋጀች ነው፣ ወይ የህይወት ኢንሹራንስ የገባው ባሏ ታሞ አልጋ ላይ ነው፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…
እናላችሁ…የዕለት በዕለት ኑሯችንን በተመለከተ… አለ አይደል… “እንደምንም ብሎ ይሄስ ቀን ባለፈ!” የሚያሰኙ ነገሮች በላይ በላይ እየተከመሩብን ነው፡
ጫንቃችን ነጻ የሚሆንበትን ዘመን ያቅርብልንማ!
ደሀና ሰንብቱልኝማ!

Read 3577 times