Saturday, 13 June 2015 14:46

አንገቷን ደግፈው ቢያስጨፍሯት፣ ያለች መሰላት

Written by 
Rate this item
(6 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ በአለቃው የተመረረ ቻይናዊ፣ ቢሮ ይገባና ለአለቃው እንዲህ ይላቸዋል፡-
“ከእንግዲህ እንደ በረዶ ዳክዬ ወደሩቅ አገር መሄድ ይሻላል”
አለቅዬውም፤
“ምን ለማለት ፈልገህ ነው?” ይሉታል፡፡
ቻይናዊው እንዲህ ሲል መለሰ፣
“አውራ ዶሮን ልብ ብለው ተመልክተዋል? የአምስት ምግባረ ሰናይ ተምሳሌት ነው፡-
ጭንቅላቱ ላይ ያለው ጉትያ የጥሩ ዜግነት ምልክት ነው፡፡
የእግር ጥፍሮቹ የኃይለኛነትና የጥንካሬ ምልክት ናቸው፡፡
ማንኛውንም ጠላት ለመጋፈጥ ያለው ቁርጠኝነት የድፍረት ምልክት ነው፡፡ ምግብ ባገኘ ሰዓት ለሌሎች ለማካፈል መቻሉ የደግነትና የቸርነት ምልክት ነው፡፡
በመጨረሻም በየሌሊቱ ሰዓቱን አክብሮ የሚጮህልን ደግሞ የዕውነተኝነት ተምሳሌት ነው፡፡
እነዚህን የመሰሉ አምስት ተምሳሌትነት ያለውን ዶሮ፣ እኛ የገበታ ሳህናችንን ለመሙላት ስንል በየቀኑ እናርደዋለን፡፡ ይሄ ለምን ይመስልዎታል? ከእዚሁ ቅርብ፣ አጠገባችን ስለምናገኘው ነው፡፡ በሌላ በኩል የበረዶ ዳክዬ በሺ ኪሎ ሜትር የሚቆጠር ርቀት ውቂያኖስ አቋርጣ ትበርራለች፡፡ ሲሻት በየአትክልቱ ማህል ታርፋለች፡፡ ሲሻትም በየወንዙ ዳር አሣ ታድናለች፡፡ ቢሻት ደግሞ ትናንሽ የውሃ ዔሊ ትመገባለች፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ የእርሻ ማሽላ ትበላለች፡፡ እንደ አውራ ዶሮ አምስት ምግባረ ሰናይ ባይኖራትም ትልቅ ዋጋ እንዳላት አድርገን እናደንቃታለን። ለምን? በእጃችን ስለሌለች! ይሄ ስለሆነ እኔም የበረዶ ዳክዬ ሆኜ መብረርን መረጥኩ”
*             *            *
“በእጅ ያለ ወርቅ እንደ መዳብ ይቆጠራል” እንደማለት ነው፡፡ በቅርባችን እጃችን ውስጥ ያለን ሀብት እንዴት እንደምንገለገልበት አለማወቅ ብቻ ሳይሆን አጎሳቁለንና ከአግባቡ ውጪ ስለምናዛባው ለድህነት ራሳችንን እናጋልጣለን፡፡ የበላይ ኃላፊዎች የበታች ሰራተኞችን ማጉላላትን የሥልጣን ማሳያ ካደረጉት መልካም አስተዳደር ስም ብቻ ሆኖ ይቀራል፡፡ በእጃችን ያለውን የሰው ኃይል ማባከንን የሚያህል የድህነት መነሾ የለም፡፡ ከአያያዝ ይቀደዳል ነው፡፡ ጉዳቱ እያደር የሚታወቀው፤ የመልካም አስተዳደር መጥፋት፣ ባለብን ድህነት ላይ ሲደረብ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ነው፡፡ በየውስጣችን አገርን የማሰብ ጥንካሬ ከሌለ፣ ላይ ላዩን ብቻ ማውራት እስክንጋለጥ ብቻ ነው የሚያበላን፡፡
ሾፐንአወር፤ “አዕምሮ ወደ ውስጥ አስቦ የመጠንከር ጉዳይ እንጂ ወደ ውጪ የመስፋፋት ጉዳይ አይደለም” ይለናል፡፡ አንጎል የተሰጠን ውስጣችንን እንድናጠናክርበት ነው ማለት ነው፡፡
በአካባቢያችን ያለውን አዕምሮ በቅጡ ካልተገለገልንበት ኑሮ ውሃ ወቀጣ ይሆናል፡፡ ራዕይ ይሟጠጣል፡፡ ምሁሮቻችንን አናርቃቸው፡፡ አንግፋቸው። ይልቁንም በአግባቡ እንጠቀምባቸው፡፡ የሚቆጨን፤ ጊዜው ካለፈና አዋቂዎች ከራቁ በኋላ ነው፡፡ ላሮቼፎኮ የተባለ ፀሐፊ፤
“በቅርብ አለመገኘት ትናንሽ መውደዶችን የባሰ ያሳንሳቸዋል፡፡ ትላልቆቹን ግን ያቀጣጥላቸዋል፡፡ ልክ ንፋስ ሻማን እንደሚያጠፋውና ትላልቅ ቃጠሎን ግን እንደሚያራግበው፡፡” ይለናል፡፡ በተቻለ መጠን የመቻቻልን ዕሳቤ ማስፋት ተገቢ ነው፡፡ ሆደ ሰፊነት ከብዙ አባዜ ያድናል፡፡ ሩቅ ለመጓዝም ዋና መሳሪያ ነው። የፖለቲካችን ውሃ ልክ የመቻቻልንና የዲሞክራሲን ባህሪ በቅጡ ማወቅ ነው፡፡ ይህ ዕውቀት ነው፤ ከተንኮል፣ ከበቀልና ከማናለብኝ አካሄድ የሚገላግለን፡፡ “ቆይ ነገ ባልሰራለት!” ዓይነት አስተሳሰብ፤ ከየትኛውም ወገን ቢመጣ ደግ አስተሳሰብ አይደለም፡፡
ስትራቴጂያችንን የሰመረ የሚያደርገው በወቅቱ ስንጀምረው ነው፡፡ በቅንነት፣ በጠዋት ካልተንቀሳቀስን ማታ መቸገራችን አይቀሬ ነው፡፡
“…. ያለንን ኃይል/አቅም አሰባስበን በአትኩሮት ወደሥራ እንደመግባት ኃያል ስትራቴጂ የለም” ይለናል፤ ካርል ፎን ክላውስዊዝ፡፡ በተለይ በምርጫ ማግሥት እንዲህ ማሰብ መልካም ነው፡፡ በሁሉም ወገን ያለው ችግር በራስ አለመቆም ነው። መደጋገፍ ትልቅ ፋይዳ ያለው ይሁን እንጂ ሁሌ ደግፉኝ ግብ አይደለም፡፡ ሁሌ ተሸከሙኝም ጤና አይሆንም፡፡ የሚመረጠው በራስ መተማመን፣ በተግባር ራስን ማወቅና በራስ መቆም ነው፡፡ አለበለዚያ “አንገቷን ደግፈው ቢያስጨፍሯት ያለች መሰላት” የሚለው ተረት ዕውን ይሆናል፡፡  

Read 4456 times