Saturday, 13 June 2015 14:35

ሃሳቤን ተዘርፌያለሁ ያሉት ዶ/ር ዳኛቸው ክስ ሊመሠርቱ ነው

Written by 
Rate this item
(7 votes)

መኖሪያ ቤታቸውን በ15 ቀን ውስጥ እንዲለቁ ታዘዋል

 “እኔ ሣላውቅ በስሜ በታተመ መፅሃፍ ሃሳቤን ተዘርፌያለው” ያሉት የፍልስፍና ምሁሩ ዶ/ር ዳኛቸው አሠፋ፤ መብቴን ለማስከበር በፍ/ቤት ክስ እመሰርታለሁ አሉ፡፡ መሐመድ ሀሰን በተባለ ፀሐፊ አማካኝነት “የዳኛቸው ሃሳቦች” በሚል ርዕስ ታትሞ በ80 ብር እየተሸጠ ነው የተባለው መፅሃፍ፤ ላለፉት 7 ዓመታት በተለያዩ የስልጠና መድረኮች፣ በሬዲዮ፣ በጋዜጦችና መፅሄቶች ያቀረቧቸው ሃሳቦች መሆናቸውን የጠቆሙት ምሁሩ፤ የመጽሐፉ አዘጋጅ “ትንታኔ” የሚል ቁንፅል አረፍተ ነገሮችን እየጨመረ ሃሳቦቼን ገልብጦ አትሞታል ሲሉ ከሰዋል፡፡ በመፅሃፉ ውስጥ ያሉት ሃሳቦች በሙሉ በ7 አመታት ውስጥ የተናገርኳቸው ናቸው ያሉት ዶ/ር ዳኛቸው፤ ግጥሞቹ ሳይቀሩ የራሳቸው እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡ መፅሃፉ በግልፅ የኔን ሃሳብ በመዝረፍ የተዘጋጀ ነው የሚሉት ዶ/ሩ፤ “ከህግ ባለሙያዎች ጋር ተማክሬ በፍ/ቤት ካሣ እጠይቅበታለሁ፤ ይህን መሰል የሃሳብ ዝርፊያ እንዳይፈፀምም ለሌላው መቀጣጫ እንዲሆን እፈልጋለሁ” ብለዋል፡፡”
መፅሀፉ የታተመበት ማተሚያ ቤት አይታወቅም የሚሉት ምሁሩ፤ የኔን ፎቶግራፍ ለጥፎ፣ ‹የዳኛቸው
ሃሳቦች› ብሎ ማውጣት ትልቅ ወንጀል ነው ሲሉ ወቅሰዋል፡፡ዶ/ር ዳኛቸው፤ የራሳቸውን መፅሃፍ ለማሳተም ከአሳታሚዎች ጋር ተዋውለው እንደነበር ጠቁመው የዚህ መፅሀፍ በስማቸው መውጣት ሊያሳትሙ ባቀዱት መፅሃፍ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳድር ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡በሌላ በኩል ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ፤ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መባረራቸውን ተከትሎ ላለፉት 7 ዓመታት ዩኒቨርሲቲው ሰጥቷቸው ይኖሩበት የነበረውን መኖሪያ ቤት በ15 ቀን ውስጥ ያለባቸውን 3300 ብር ውዝፍ እዳና የመብራትና ውሃ አገልግሎት ክፍያ ፈፅመው እንዲለቁ የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ባለፈው ግንቦት 28 በፃፈላቸው ደብዳቤ ያስታወቀ ሲሆን ዶ/ር ዳኛቸው በበኩላቸው፤ በዩኒቨርሲቲው ያስተማሩበትንና የምርምር ስራዎች የሰሩበትን ወደ 56 ሺህ ብር ክፍያ ቢፈፀምላቸው እዳቸውን ከፍለው መልቀቅ እንደሚችሉ ጠቁመው የተሰጣቸው የጊዜ ገደብም በቂ አለመሆኑን ገልፀዋል - ለዩኒቨርሲቲው በደብዳቤ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡   

Read 7799 times