Saturday, 13 June 2015 14:24

ፀረሙስና ከ81 ኪ.ግ በላይ ወርቅና ሌሎች ንብረቶችን ማስመለሱን አስታወቀ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(8 votes)

በሰባት ዩኒቨርሲቲዎች ሊፈፀም የታቀደ የሙስና ወንጀልን መከላከሉን ጠቁሟል
የመከላከያ ሚኒስቴር 171ኛ ሬጅመንት መኮንኖች፤ ስኳር አውጥተው በመሸጥ ወንጀል ተከሰዋል

     የፀረ - ሙስና ኮሚሽን ባለፉት አስራ አንድ ወራት ውስጥ በህገወጥ መንገድ የተመዘበሩ ያላቸውን ከ81 ኪሎ ግራም በላይ ወርቅ፣ ከ26ሺ ካሬ ሜትር በላይ የከተማ መሬት፣ አራት ህንፃዎች፣ ከ74 ሚሊዮን ብር በላይ ጥሬ ገንዘብና ሌሎች ንብረቶች ማስመለሱን ገለጸ፡፡ ኮሚሽኑ ባለፈው ሳምንት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው የአስራ አንድ ወር ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ላይ እንደገለፀው፤ ከሙስና ወንጀል ጋር በተያያዘ ተፈፀሙ ባላቸው ጉዳዮች ላይ ምርመራ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ምርመራ ከተደረገባቸው የመንግስት ተቋማት መካከል ዩኒቨርሲቲዎች፣ ሆስፒታሎች፣ ባንኮች እና ጉምሩክ እንደሚገኙበትም በሪፖርቱ ተጠቁሟል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሚካሄድ የህንፃ ግንባታ ሥራ በህገወጥ መንገድ ሊወጣ የነበረውን 135
ሚሊዮን ብር ማዳኑን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ በጅማ ዩኒቨርሲቲ፣ አምቦ፣ አዳማ፣ አርባምንጭ፣
ደብረማርቆስና ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲዎች ግልፅነት በሌላቸውና ከሥርዓት ውጪ የሆኑ አሰራሮችን
በመከተል ሊባክን የነበረ ከ645 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ማዳኑንም አመልክቷል፡፡ ኮሚሽኑ በመንግስት ትላልቅ ግዥና ሽያጭ ላይ ባደረገው ምርመራ፤ የመከላከያ ሚኒስቴር 171ኛ ሬጅመንት መኮንኖች፣ ከነጋዴዎች ጋር ተመሳጥረው ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ስኳር አውጥተው በመሸጥ ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸውን ጠቁሞ በወንጀሉ ተሳታፊ በሆኑ መኮንኖች ላይ ምርመራ ተደርጐ ክስ መመስረቱንም አስታውቋል፡፡ በሀሰተኛ የቀበሌ ነዋሪነት መሸኛ፣ መታወቂያና ውክልና የግለሰብ ቤትን 12 ሚሊዮን ብር የሸጡ ግለሰቦች፣ በቦሌ ክፍለ ከተማ በሀሰተኛ ማስረጃ መሬት እንዲያገኙ የተደረጉ 89 ሰዎች፣ በአምስት
የግል ኩባንያዎች የተፈፀመ የ361.6 ሚሊዮን ብር የመንግሥት ታክስ አለመክፈል ወንጀል፣ በሁለት
አስመጪ ነጋዴዎች የተፈፀመና መንግስትን 301.9 ሚሊዮን ብር ገቢ ያሳጣ የሙስና ወንጀል፣ እንዲሁም በኢትዮቴሌኮም ሰራተኞችና በሌሎች የግል ሰራተኞች የተፈፀመና በመንግስት ላይ የ45 ሚሊዮን ብር ጉዳት ያደረሰ የሙስና ወንጀል ላይ ምርመራ አከናውኖ ክስ መመስረቱንም ኮሚሽኑበሪፖርቱ አስታውቋል፡፡    

Read 1833 times