Saturday, 13 June 2015 14:22

በምርጫው መድረክ በሁለተኛነት፣ ሰማያዊ በሶስተኛነት ኢህአዴግን ይከተላሉ

Written by  ኤልሳቤት እቁባ
Rate this item
(1 Vote)

ተቃዋሚዎች ውጤቱን አልተቀበሉትም

         በዘንድሮው አምስተኛ አገር አቀፍ ምርጫ፣ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የ442 ጣቢያዎችን ጊዜያዊ ውጤት ይፋ ማድረጉ የሚታወቅ ሲሆን በአገር አቀፍ ደረጃ መድረክ በሁለተኛነት፣ ሰማያዊ በሶስተኝነት ኢህአዴግን ይከተላሉ፡፡ በአዲስ አበባ የምርጫ ውጤት መሰረት፤ ሰማያዊ የሁለተኛነት፣ መድረክ ደግሞ የሦስተኝነት ደረጃ አግኝተዋል፡፡
በአገር አቀፍ ደረጃ ኢህአዴግ 26,007410 በማግኘት በአብላጫ ድምፅ ማሸነፉን የገለፀው ቦርዱ፤ መድረክ በ5መቶ 56ሺ 85 ሰማያዊ ፓርቲ በ3መቶ 79 ሺ 211 ድምፅ ሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃን እንደያዙ ስታውቋል፡፡ መኢአድ አራተኛ፣ ቅንጅት አምስተኛ፣ ኢዴፓ ስድስተኛና አንድነት ሰባተኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡
በአዲስ አበባ ኢህአዴግ 737ሺ 547 በማግኘት አብላጫውን ድምጽ ሲያሸንፍ፣ ሰማያዊ በ186ሺ 907 ድምፅ ሁለተኛ እንዲሁም መድረክ በ145ሺ 434 ድምፅ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል፡፡ የምርጫ ቦርድ የገለፀውን ጊዚያዊ ውጤት ተከትሎ መድረክ የዘንድሮ ምርጫ ከ2002 የባሰ የሀገሪቱን ዲሞክራሲ ያጨለመ ነው በማለት የምርጫውን ውጤት እንደማይቀበለው ሲገልፅ ሰማያዊ ፓርቲም፤ ምርጫው ኢ-ፍትሀዊ ፣ ወገንተኛ እና ተአማኒነት የሌለው በመሆኑ የምርጫውን ውጤት እንደማይቀበለው ገልጿል፡፡ አራተኛ ደረጃን ያገኘው መኢአድ፤ በምርጫው ወቅት አጋጠሙኝ ያላቸውን ችግሮች በመዘርዘር፣ የምርጫውን ውጤት እንደማይቀበል የገለፀ ሲሆን በስድስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ኢዴፓም፤ ምርጫው ዲሞክራሲያዊ ፣ ፍትሀዊና በህብረተሰቡም ዘንድ ተአማኒ አልነበረም በማለት የምርጫውን ውጤት እንደማይቀበል አስታውቋል፡፡ በውጤቱ የአምስተኛ ደረጃን ያገኘው ቅንጅትና የሰባተኛ ደረጃን ያገኘው አንድነት የምርጫውን ውጤት በፀጋ እንደሚቀበሉ ገልፀዋል፡፡ ሄራዊ ምርጫ ቦርድ የተቃዋሚዎችን ክስ “መሰረተቢስ ውንጀላ ነው” ሲል ማጣጣሉ ይታወሳል፡፡

Read 1781 times