Saturday, 06 June 2015 14:16

ናሽናል አቪዬሽን ኮሌጅ ከአፍሪካ ቀዳሚ ሆኖ በአይኤቲኤ ተሸለመ

Written by  መንግስቱ አበበ
Rate this item
(2 votes)

 ናሽናል አቪዬሽን ኮሌጅ ከአፍሪካ አቪዬሽን ማሰልጠኛ ማዕከላት አንደኛ ሆኖ መሸለሙንና የበረራ አስተናጋጆችን (ሆስቴሶች) ለማሰልጠን ከኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ለመጀመሪያ ጊዜ እውቅና ያገኘ የግል ተቋም መሆኑን የኮሌጁ ዲን አስታወቁ፡፡
ዲኑ አቶ ገዛኸኝ ብሩ ከትናት በስቲያ በተለይ ለጋዜጣው ሪፖርተር በሰጡት መግለጫ፤ ኮሌጃቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ ከሆኑ ተቋማት ጋር እንደሚሰራ ጠቅሰው፣ መቀመጫው ሞንትሪያል - ካናዳ የሆነውና የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ኳታር ኤርዌይስን…. ጨምሮ በመላው ዓለም 87 በመቶ አየር መንገዶች በአባልነት የያዘው ዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር (አይ ኤ ቲ ኤ - IATA)፤ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ለበርካታ ወጣቶች ዓለም አቀፍ ደረጃና ጥራት ያለው ሥልጠና በመስጠታቸው “Africa Top Performing Authorized Training Center (ATC)-2015” በማለት እንደሸለማቸው ገልፀዋል፡፡
አቶ ገዛኸኝ ኮሌጁ እንዴት ለሽልማት እንደበቃ ሲስረዱ፣ ከዓለም አቀፉ ተቋም አይኤቴኤ አገልግሎት አንዱ በአቪዬሽን ዘርፍ ለኢንዱስትሪው አገልግሎት የሚሰጥ ብቁ የሰው ኃይል በዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃ ማሠልጠን እንደሆነ ጠቅሰው፤ ይህን ኃላፊነት የሚወጣው ለብቻው ሳይሆን በየአህጉሩ በትብብር (በፓርትነርሺፕ) አብረውት ከሚሰሩ የአቪዬሽን ማሰልጠኛ ተቋማት ጋር በሚገባው ውል እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
አይኤቲኤ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለው ወይም የሚሰራበትን የአቪዬሽን ትምህርት ማሰልጠን ለሚችሉ ተቋማት ፈቃድና የሚያሰለጥኑበትን የትምህርት ፕሮግራም (የሥልጠና ማኑዋል) አዘጋጅቶ ለተባባሪዎቹ እንደሚሰጥ ጠቅሰው፣ ሠልጣኞቹ የተሰጣቸውን ትምህርት ሲጨርሱ፣ ራሱ የሚያዘጋጀውን ፈተና ላለፉት፣ “በአገር ውስጥም ሆነ በመላው ዓለም አቪዬሽን ኢንዱስትሪ መሥራት ይችላሉ” የሚል የብቃት ማረጋገጫ እንደሚሰጥና በዓመት 4 ጊዜ እንደሚፈትን አስረድተዋል፡፡
አይኤቲኤ በመላው ዓለም እንደ ናሽናል አቪዬሽን ኮሌጅ ካሉ 240 የአቪዬሽን ማሰልጠኛ ተቋማት ጋር በትብብር እንደሚሰራ፣ በየአኅጉሩ ብዙ ሰልጣኝ ተቀብሎ ያስተናገደ፣ ፈተናውን ከወሰዱት ውስጥ ብዙ ሰልጣኞችን ያሳለፈና ፈተናውን በጥራት ያለፉ በርካታ ሙያተኞች ያበረከተ በሚል በየዓመቱ ውድድር እንደሚያካድ የገለጹት ዲኑ፤ ኮሌጃቸው ለሽልማት የበቃው በአፍሪካ ካሉ ተመሳሳይ የአቪዬሽን ተቋማት ጋር ተወዳድሮ በመመዘኛዎቹ ብልጫ በማግኘቱ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
አቶ ገዛኸን አያይዘውም ኮሌጃቸው በበረራ አስተናጋጅነት (ሆስቴስ) ሙያ ለሚሰጠው ሥልጠና ከኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የፋዊ እውቅና በማግኘት የመጀመሪያው የግል ተቋም በመሆኑ በጣም መደሰታቸውን ገልፀዋል፡፡
ናሽናል አቪዬሽን ኮሌጅ በአሁኑ ወቅት ከዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር ባገኘው እውቅና ፓሲንጀር ኤርፌይር (ቲኬቲንግ)፣ ካስተም ክሊራንስ፣ ካስተም ቫሉዬሽን፣ ሎጂስቲክስና ትራንስፖርት ፍላይት ፎርዋርዲንግ፣ ከአዲስ አበባ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኤጀንሲ በተሰጠው እውቅና በመደበኛ ከደረጃ 1-4 በ11 የትምህርት ዘርፎችና በ8 አጫጭር ኮርሶች እንዲሁም ከእንግሊዙ ኢንስቲትዩት ኦፍ ኮመርሻል ማናጅመንት ጋር በመተባበር በሆቴልና ቱሪዝም መስክ እያሰለጠነ መሆኑ ታውቋል፡፡
ኮሌጁ ከሁለቱ ተቋማት ያገኘው እውቅና በኢትዮጵያ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ብቁና የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት የጀመረውን ጥረት የበለጠ አጠናክሮ ለመቀጠል አቅም ይፈጥርለታል ያሉት ዲኑ አቶ ገዛኸኝ ብሩ፤ ተቋሙ የሚሰጣቸውን ስልጠናዎች በተሻለ ጥራት ብቃት በማከናወን ዓለም አቀፍ ግዴታዎችን ከመወጣት ባሻገር በኢትዮጵያ እያደገ ለመጣው የአቪዬሽን ሆቴልና ቱሪዝም ኢንዱስትሪ የሰለጠነ የሰው ኃይል በማቅረብ የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት እንደሚያስችለው ገልጸዋል፡፡
ኮሌጁ በበረራ ስምሪት፣ በፓይለቶች ስልጠና፣ በአውሮፕላን ጥገና እንዲሁም በሌሎች ተያያዥ ዘርፎች ሥልጠና ለመስጠት አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎችን አሟልቶ ለሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን በማቅረቡ በቅርቡ እውቅና አገኛለሁ ብሎ እንደሚጠብቅና በአቪዬሽን ሳይንስ በአውሮፕላን ዲዛይን፣ በአውሮፕላን ጥገና፣ በኤሮናውቲካል ኢንጂነሪንግና በኤሮስፔስ ኢንጂነሪንግ፣ በሆቴልና ቱሪዝም ማኔጅመንት ዘርፎች በቅድመና ድህረ ምረቃ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማሰልጠን እየተዘጋጀ መሆኑን ዲኑ አስታውቀዋል፡፡

Read 2788 times