Saturday, 06 June 2015 14:15

ነርሷ “በህክምና ስህተት” የወለደችውን ህጻን ማጣቷን ገለጸች

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(6 votes)

 “ለ6 ዓመት ባገለገልኩበት ሆስፒታል የሚያዋልደኝ አጣሁ”
  ለጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ቅሬታ ሰሚ አካል አቤት ብላለች
         
            በተማረችበት የነርስነት ሙያዋ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ከሐምሌ 2001 ዓ.ም ጀምሮ ለስድስት ዓመታት በተለያዩ ክፍሎች ውስጥ ተመድባ ስትሰራ ቆይታለች። የሰውን ልጅ ክቡር ህይወት ለመታደግ ከሚያስችሉት ሙያዎች አንዱ በሆነው የነርስነት ሙያዋ ያገለገለችበትና የአገሪቱ ከፍተኛ ሪፈራል ሆስፒታል የሆነው የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ከፍተኛ የአልጋ እጥረት እንዳለበት እንዲሁም በተገልጋዮች እጅግ የተጨናነቀ እንደሆነ ጠንቅቃ ታውቃለች፡፡
በሆስፒታሉ በቆየችባቸው ዓመታት ግን ሆስፒታሉ በውስጣዊ አደረጃጀት፣ በሙያተኞች ሙያዊና ሥነ - ምግባራዊ ብቃት ትልቅ ችግር ላይ መውደቁን ለአፍታም አስባው አታውቅም፡፡ ለዚህም ነበር የእርግዝና ክትትሏን እዚያው በምትሰራበት ሆስፒታል ውስጥ እንዲሆን የወሰነችው፡፡ እርግዝናዋ እየገፋ ሲሄድ ግን ሃሳብ ያዛት። በሆስፒታሉ ሁልጊዜም የምትሰማው የ“አልጋ የለም” እሮሮ ምናልባት እሷ በምጥ በተያዘችበት ወቅት ሊያጋጥም ቢችል ምን ይውጡኛል የሚል ስጋቷን ለመቀነስ፣ ቀዳሚ የህክምና ታሪኳን አውቆ እርዳታ ሊያደርግላት የሚችል የግል የጤና ተቋም ማዘጋጀት ነበረባት፡፡ እናም ተጨማሪ የእርግዝና ክትትል ለማድረግ ወደ አንድ የግል የጤና ተቋም አመራች፡፡
ከአርባ ሳምንታት ጤናማና ደስተኛ የእርግዝና ጊዜዋ በኋላ እጅግ የጓጓችለትን ጊዜ ደረሰ፡፡ ግንቦት 2 ቀን 2007 ዓ.ም ረፋድ ላይ የጀመራት ምጥ ሲበረታ ወደ ሆስፒታል ለመሄድ ተነሳች፡፡ ለዓመታት የሰራችበት የነርስነት ሙያዋ እያንዳንዱን የምጥ ስሜት እንድትረዳና ያለችበትን ሁኔታ እንድትገነዘብ ስላስቻላት በየደቂቃው የሚለዋወጠውን የምጥ ስሜት ተከትላ ራሷን እየረዳች ከባለቤቷ ጋር የህክምና ባለሙያ እገዛ ለማግኘት በረረች፡፡ ምጡ አጣዳፊ ስለነበር ቀድማ ደተዘጋጀችበት የግል የጤና ተቋም ለመሄድ ጊዜ አልነበራትም፡፡ ባለቤቷ ያለፉት 6 ዓመታትን ስታገለግል ወደቆየችበት የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል እንዲወስዳት ነገረችው፡፡ የሆስፒታሉ ሰራተኛ መሆኗ ለዚህች የጭንቀትና የምጥ ጊዜ እንደሚረዳት ቅንጣት አልተጠራጠረችም፡፡ ምጥ እያጣደፋት፣ መጣሁ መጣሁ እያለ የሚያስጨንቃት ፅንስ አጉል ቦታ ላይ ወድቆ አጉል እንዳይሆን እየታገለች ወደ ሆስፒታሉ የድንገተኛ ክፍል የገባችውን ነፍሰጡር ሴት ለመታደግና ከጭንቀቷ ለመገላገል ፍላጎት ያሳየ አንድም ሙያተኛ ማግኘት አልቻለችም፡፡  የዕለቱን አሳዛኝ ክስተት ባለጉዳይዋ ሲስተር ቤተልሔም ሽፈራው እንዲህ ትገልፀዋለች፡-
“የእርግዝና ጊዜያቶቼ እጅግ ሲበዛ ጤናማና ሰላማዊ ነበሩ፡፡ እንደነገርኩሽ በሁለቱም ተቋማት በየጊዜው የእርግዝና ክትትል አደርግም ነበር፡፡ እያንዳንዱ ስሜቴን በአግባቡ ስከታተል ቆይቻለሁ፡፡ አርባ ሳምንታት ከሁለት ቀን ከሆነኝ በኋላ ግንቦት 2/2007 ዓ.ም እሁድ ረፋድ ላይ ምጥ ጀመረኝ፡፡ የመጀመሪያዎቹን የምጥ ሂደቶች እቤቴ ሆኜ ካሳለፍኩ በኋላ ምጤ እየገፋ መምጣቱን ሳውቅ ከባለቤቱ ጋር ወደ ሆስፒታል ለመሄድ ተነሳሁ፡፡ እያንዳንዱን የምጥ ስሜቴን በሚገባ ስከታተል ስለቆየሁ ያለሁበትን ደረጃ አውቀው ነበር፡፡ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ድንገተኛ የማህፀንና ፅንስ ክፍል ስንገባ ምጤ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር፡፡ በሆስፒታሉ ለነበሩት ተረኛ ሃኪሞች (ኢንተርንናሬዚደንሶች) እንዲሁም ለነርሶቹ ልወልድ መቃረቤንና ምጤ እየገፋ መሆኑን ብነግራቸውም ማንም ከቁብ የቆጠረኝ አልነበረም። ይልቁንም ስለህክምና ታሪኬ ለመፃፍ ወንበር ላይ አስቀምጠውኝ እስኪሪብቶ መፈለግ ጀመሩ፡፡
መቀመጥ እንደማልችል፣ የህክምና ታሪኩን አቆይተው እኔን እንዲያዋልዱኝ ተማፀንኳቸው፡፡ ማንም የሰማኝ አልነበረም፡፡ ይልቁንም ነርሶቹ በመስታወት ፊታቸውን እያዩ ፀጉራቸውን እያበጃጁ እርስ በርስ እያወሩ ይሳሳቁ ነበር፡፡ ጭንቀቴ እጅግ በረታ፡፡ የሆስፒታሉ ነርስ መሆኔን፣ ስለወሊድ እንደማውቅ፣ ልጄ እየታፈነችብኝ እንደሆነና እኔም አደጋ ላይ መሆኔን እየጮህኩ በመናገር እርዳታቸውን ተማፀንኩ፡፡
የፅንሱ ጭንቅላት ማህፀኔ አፍ ላይ ደርሶ የተመለከተው ሃኪም እንኳ “ስድስተኛ ፎቅ ላይ ሂጂና እዚያ እናዋልድሻለን” ነው ያለኝ፡፡ እኔ በጭንቅ ተይዣለሁ፡፡ ልጄ ታፍናብኛለች፤ ግን ይህ ሁሉ ነገር ደንታ የሰጠው አንድም ባለሙያ አልነበረም፡፡ በመጨረሻ እኔ ከምሰራበት ክፍል ሊረዱኝ በመጡ ነርስ ጓደኞቼ ጉትጎታና ልመና በስንት ጭንቅ ልጄን ተገላገልኩ፡፡
ልጅቷ ከሆዴ ከወጣች በኋላ ሊደረግ የሚገባውን እያንዳንዱን ነገር እኔ እየነገርኳቸው ነበር ነርሶቹ ሲያከናውኑ የነበረው፡፡ የልጄን አለማልቀስ ተመልክቼ በዚያ ጭንቀት መሃል እባካችሁ ልጄን ዘቅዝቋት፣ እባካችሁ የህፃናት ሙቀት ክፍል ውሰዱልኝ፣ እባካችሁ እትብቷ አልተቆረጠም… እያልኩ ስጮህ ነበር፡፡ ለሰዓታት የቆየብኝ ምጥ እጅግ ቢያደክመኝም ልጄ እንዳትሞትብኝ ስለሰጋሁ ሁኔታውን በትኩረት ከመከታተል አልቢዞንኩም፡፡
ሆኖም ጥረቴ ከንቱ ሆነ፡፡ ከደቂቃዎች በኋላ ልጄ ህይወቷ እንዳለፈ ተነገረኝ፡፡ ይህን መርዶ እንዴት ልቀበለው እንደምችል መገመት ከባድ ነው፡፡ እያወቅሁ፣ እያየሁና፣ እየተናገርኩ ልጄን በሙያዊ ብቃት ማነስ ሲገሉብኝ ምን ለማለት እችላለሁ፡፡
ከዚህ ሁሉ ነገር እጅግ አሳዛኙ ደግሞ በሆስፒታሉ ውስጥ ምንም የህክምና መስጫ መሳሪያዎች አለመኖሩ ነው፡፡ በማዋለጃ ክፍል በአብዛኛዎቹ ጤና ጣቢያዎች ውስጥ ያሉት ለህፃኑ መቀበያ የሚያስፈልጉ የእትብት መቁረጫና ማሰሪያ ነገሮች እንዲሁም፡፡ ኦክስጂን፣ ማደንዘዣና መሰል መሰረታዊ መድኀኒቶች የሉም፣ በየጤና ተቋማቱ የእናቶች የወሊድ አገልግሎት በነፃ ይሰጣል በሚባልበት አገር ልጄ ህይወቷን ማጣቷ ሳያንስ፣ በልመና ለተደረገልኝ የህክምና እርዳታ፣ እያንዳንዷን መድኀኒትና ማደንዘዣ በግዥ እንዳመጣ ተደርጌአለሁ። በሆስፒታሉ ወላድ ሴቶችን በአግባቡ ሊረዳ የሚችል ብቃት ያለው ባለሙያ የለም፣ ነርሶቹ የሙያና የሥነ ምግባር ችግር አለባቸው፤ ለማዋለድ አገልግሎት የሚውል በቂ የህክምና መሳሪያ የለም፡፡ እኒህ ባልተሟሉበት ሁኔታ አንዲት እናት ምን ልታደርግ ነው ወደዚህ ሆስፒታል የምትመጣው? እኔ ቤቱ እንዲህ ባዶ መሆኑን ባውቅ ኖሮ አላደርገውም ነበር፡፡ “የማህፀንና ፅንስ ዲፓርትመንቱ ተማሪዎች ማስተማርና ማሰልጠን እንጂ ብቁ መሆናቸውን የሚፈትሽበት አሰራር የለውም፡፡ ብዙ ሰዎች ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የተሻለ ህክምና የሚሰጥበት፣ የተሻሉ ሃኪሞች ያሉበት ቦታ እንደሆነ ነው የሚያስበው፤ ነገሩ ግን የተገላቢጦሽ ነው፡፡ በየትኛውም የጤና ጣቢያ በቀላሉ ለሚከናወን የወሊድ አገልግሎት ነው ወደዚህ ሆስፒታል መጥቼ ልጄን ያጣሁት፤ ስለዚህም ሆስፒታሉ ራሱን መፈተሽ ይገባዋል፣ የሙያተኞች ብቃት ላይ ትኩረት ማድረግ፣ ሥነ - ምግባራቸውን መከታተልና በየጊዜው ለሚያጋጥሙ ችግሮች ጆሮ መስጠት ይኖርበታል፡፡
በሆስፒታሉ የጨቅላ ህፃናት ሞት የተለመደ ጉዳይ ነው፡፡ ለምን ብሎ የሚጠይቅ የለም፡፡ እናትየዋ የእሷን መትረፍ ከትልቅ ዕድል ቆጥራ በልጇ ሞት ምክንያት ላይ ጥያቄ ሳታነሳ ትሄዳለች፡፡ ይህ መቀጠል የለበትም፡፡ ጤና ጥበቃም የሆስፒታሉን አሰራር መፈተሸና ችግሮቹን ለይቶ እርምጃ መውሰድ ይኖርበታል፡፡ ‹አንዲትም እናት ከወሊድ ጋር በተያያዘ ችግር መሞት የለባትም› የሚለው መፈክር ልጇንም መጨመር ይገባዋል፡፡”
የጥቁር አንበሳዋ ነርስ ሲስተር ቤተልሄም ሽፈራው፤ ወደ በሆስፒታሉ ለወሊድ በገባችበት ወቅት የገጠማት ሁኔታና ልጇን በህክምና ጉድለት ማጣቷ እጅግ ያንገበግባታል፡፡ ምነው ደሜን እያፈሰስኩም ቢሆን ለድንገተኛ ብዬ ወዳዘጋጀሁት የግል የጤና ተቋም በሄድኩ ነበር፡፡ አሊያም እዚያው መኪና ውስጥ ብገላገል ኖሮ … ልጄን አላጣትም ነበር” ትላለች በቁጭት፡፡
ጉዳዩን በተመለከተ ማራሪያ ለመጠየቅ ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ብንሄድም፡፡ የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር አብዱልቃድር አህመድ ከአገር ውጪ መሆናቸው የተነገረን ሲሆን እሳቸው የወከሉአቸው ሰው ደግሞ በግል ችግር ምክንያት በሥራ ገበታቸው ላይ እንደሌሉ ተገልጿል፡፡ ሲስተሯ ጉዳያቸውን ለሆስፒታሉ የቅሬታ ሰሚ አካል አቤት ማለታቸውን ሰማንና የሆስፒታሉ ቅሬታ ሰሚ ወ/ሮ ወርቄን አነጋገርን፡፡ ሲስተሯ ደረሰብኝ ያሉትን ችግር አስመልክቶ ያቀረቡት ቅሬታ እንደደረሳቸውና ጉዳዩን አስመልክቶ የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር በሁለት ቀናት ውስጥ ምላሽ እንዲሰጧቸው ጠይቀው እየተጠባበቁ መሆኑንና የገለፁት ወ/ሮ ወርቄን አነጋገርን፡፡ በአሁኑ ወቅት ዳይሬክተሩ በአገር ውስጥ  ባለመኖራቸው ምክንያት ምላሹ ሊዘገይ እንደቻለ ተናግረዋል፡፡ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች ስለጉዳዩ ምላሽ እንዲሰጡን ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ ግን  ሳይሳካልን ቀርቷል፡፡   

Read 7110 times