Saturday, 06 June 2015 14:14

ተቃዋሚና ኢህአዴግን በዳዊትና ጐልያድ መነፅር!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(15 votes)

ገዢው ፓርቲ ለምን ምርጫውን አሸነፈ?
                  የዛሬ 3ሺ ዓመት ገደማ ነው፡፡ በጥንታዊቷ ፍልስጤም እምብርት ሼፕሄላህ በተባለ ሥፍራ ነበር ፍልስጤሞች የሚኖሩት፡፡ ለብዙ ዘመናት ሥፍራውን ለመቆጣጠር በሚደረጉ ጥረቶች በርካታ ጦርነቶች በአካባቢው ተካሂደዋል፡፡ የእስራኤላውያን ታሪካዊ ጠላቶች ናቸው የሚባሉት ፍልስጤሞች፤ በጦርነት የተፈተኑ አደገኛ ተዋጊዎች ነበሩ፡፡ ፍልስጤሞች ከሰፈሩበት የባህር ዳርቻ ወደ ምስራቅ አቅጣጫ የተንቀሳቀሱበት ብቸኛ ዓላማ እስራኤሎች ሰፍረውበት የነበረውን ቤተልሄም አቅራቢያ የሚገኝ ተራራ በመቆጣጠር የንጉስ ሳኡልን ግዛት ለሁለት ለመክፈል ነበር፡፡ በዚህ የተደናገጠው ሳኡል፤ ተዋጊዎቹን አሰባስቦ በፍጥነት ከተራራው ላይ ቁልቁል ወረደ - ፍልስጤሞችን በውጊያ ለመግጠም። ከዚያም ሁለቱ ባላጋራዎች ማዶ ለማዶ ተፋጠው ተቀመጡ፡፡ ማናቸውም  ለመንቀሳቀስ አልደፈሩም፡፡ በመጨረሻ ግን ፍልስጤሞቹ መፋጠጡም መጠባበቁም ታከታቸው፡፡
በዘመኑ እንደዚህ ዓይነት ጦርነት ውስጥ ከመገባቱ በፊት አሰቃቂ ደም መፋሰስን ለማስቀረት ሁለቱ ቡድኖች አንድ አንድ ተዋጊዎቻቸውን በመወከል ማፋለም የተለመደ ነበር፡፡ እናም ፍልስጤሞች ታላቁን ተዋጊያቸውን ወደ እስራኤሎች ዘንድ ላኩት፡፡ ቁመቱ ከ6 ጫማ በላይ ነው፡፡ የነሐስ ቆብ (ሄልሜት) ጭንቅላቱ ላይ አጥልቋል፡፡ ሙሉ ሰውነትን የሚሸፍን ጥሩር አድርጓል፡፡  በእጁ ሁለት ጦር ይዟል፡፡ ወገቡ ላይ ጐራዴ ታጥቋል፡፡ ትልቅ ጋሻ የያዘ አጃቢም ነበረው፡፡ ይሄ የሰማይ ስባሪ የሚያህል ሰው ወደ እስራኤላውያኑ እያየ፤ “የሚፋለመኝን ሰው መርጣችሁ ወደ እኔ ላኩት፤ በፍልሚያው አሸንፎ ከጣለኝ እኛ የናንተ ባሮች ሆነን እናገለግላለን፡፡ እኔ አሸንፌ ከጣልኩት ግን እናንተ የእኛ ባሮች ሆናችሁ ታገለግሉናላችሁ” ሲል በድንፋታ ጮሆ ተናገረ፡፡
ከእስራኤል ካምፕ ለፍልሚያው አንድም ንቅንቅ ያለ ሰው አልነበረም፡፡ ለነገሩ እንደዚያ ያለ አስፈሪ ባላጋራን ማን ገጥሜ አሸንፈዋለሁ ሊል ይችላል፡፡ በዚህ ፀጥ እረጭ  ባለበት ድባብ ነበር ድንገት አንድ ከቤተልሄም ለወንድሞቹ ምሳ ይዞ የመጣ የበግ እረኛ ብድግ ያለው፡፡ ለፍልሚያው ፈቃደኝነቱን ገለፀ፡፡ ንጉስ ሳኡል ግን አይደረግም ብሎ ተቃወመ፡፡ “ከዚህ ሰው ጋር ልትፋለም አትችልም፤ አንተ ብላቴና ነህ፤ ለእሱ ግን ፍልሚያ ጥርሱን የነቀለበት ነው” ሲል መከረው ንጉሡ። ብላቴናው እረኛ ግን ፍንክች አላለም፤ እፋለመዋለሁ ብሎ ድርቅ አለ፡፡
“አንበሳ ሁሌ ወይም ድብ ከበጐቼ መንጋ አንዱን አፈፍ አድርጐ ሲወስድብኝ ተከትዬ  ማጅራቱን እለውና በጊቱን ከአውሬው መንጋጋ ነጥቄ አተርፋታለሁ!” በማለት የጀግንነቱን ልክ ገለፀ፡፡ ለነገሩ ንጉሱም ሌላ አማራጭ አልነበረውም፡፡ እናም ፈቀደለት እረኛውም ከመቅጽበት ግዙፉን የፍልስጤም ጦረኛ ለመፋለም   ቁልቁለቱን እየሮጠ ወረደ፡፡
“ና ወደ እኔ፤ ሥጋህን ለሰማይ አሞሮችና ለዱር አውሬዎች ነው የምሰጠው” ሲል አምባረቀ የባላጋራውን ወደሱ መምጣት ከርቀት የተመለከተው ተዋጊው። በታሪክ ከሚጠቀሱት ታዋቂ ፍልሚያዎች መካከል አንዱ የተደረገውም ይሄኔ ነው፡፡ በዚያች ቅፅበት በዚያች ሥፍራ፡፡ ግዙፉ ተዋጊ ጐልያድ ሲሆን የበግ እረኛው ብላቴና ደግሞ ዳዊት ነበር፡፡
እስካሁን ያነበባችሁትን ትረካ የወሰድኩት አፃፃፉ በእጅጉ ከሚማርከኝ አሜሪካዊ ደራሲ ማልኮልም ግላድዌል መፅሃፍ ላይ ነው - “David and Goliath” ከሚለው፡፡ ከዚህ ቀደም እንደነገርኳችሁ የግላድዌል መፃሕፍት በሙሉ ከፍተኛ የሽያጭ ሪከርድ ያስመዘገቡ ናቸው፡፡  እንደውም ትዝ ይላችሁ እንደሆነ… የ97 ምርጫ የወለደው “ቅንጅት” ፓርቲን (“መንፈስ ነው” ይሉት ነበር!) ከ “Tipping point” መጽሐፍ በወሰድኩት ፅንሰ ሃሳብ ልተነትን ሞክሬ ነበር፡፡ (የማይተነተን ፓርቲ እኮ አለ!)
በነገራችን ላይ “David and Goliath” የተሰኘው የግላድዌል መፅሃፍ እንደሌሎቹ ድንቅ ሥራዎቹ ሁሉ በመረጃና በጥናት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ የአፃፃፍ ስታይሉ ግን ይማርካል፤ እንደልብወለድ ይመስጣል፡፡ ያሳምናል፡፡ ያስደስታል፡፡
ይሄን መፅሃፍ የማስቃኛችሁ የአገራችንን ተቃዋሚዎችና ገዢው ፓርቲን በአዲስ መነፅር እንድናያቸው ፈልጌ ነው፡፡ ዳዊትና ጐልያድን እንደ ተቃዋሚ እና ገዢ ፓርቲ ቁጠሯቸው፡፡ የሰማይ ስባሪ የሚያህለውን “ኢህአዴግ” በሉት፣ ኮስማናውን ደግሞ በተቃዋሚ ፓርቲ ወክሉ፡፡ ምርጫውንና ውጤቱንም አብራችሁ እዩት፡፡ ለምን ኢህአዴግ በዝረራ አሸነፈ? (ምርጫ ቦርድ በ100% አላሸነፈም ብሏል!) ለምን የተቃዋሚው ጐራ በዝረራ ተሸነፈ? ቀጥሉ ማንበባችሁን። ለመሆኑ የግላድዌል “David and Goliath” ጠቅላላ ጭብጥ ምንድን ነው? ተራና ደካማ ሰዎች ከሃያላንና ግዙፎች ጋር ፍልሚያ ወይም ጠብ ሲገጥሙ ምን ይከሰታል የሚለውን ነው በዝርዝር እየተነተነ የሚያሳየን - በአሳማኝ ማስረጃዎች እያስደገፈ። የመፅሃፉ የመጀመሪያ ምዕራፍም ታሪካቸው በመጽሐፍ ቅዱስ የሰፈረላቸው የዳዊትና ጎልያድ ታሪክን ነው የያዘው፡፡
የእስራኤሉ ንጉስ ኮስማናውን ዳዊት ወደ ፍልሚያ እንዳይገባ የከለከለው የጎልያድን ግዙፍነት አይቶ ነው፡፡ ንጉሱ ብቻ ሳይሆን መላ እስራኤላውያንም ዳዊት በፍልሚያው እንደሚረታ ቅንጣት ጥርጣሬ አልነበራቸውም፡፡
እርግጠኛነቱ የመነጨው ከጐልያድ አካላዊ ግዝፈት ነው፡፡ በዓይናቸው ያዩትን አመኑ፡፡ በነገራችን ላይ ንጉሱ የራሱን ጐራዴ ጦር አውጥቶ ለዳዊት ሲሰጠው “አልመድኩትም፤ ምቾት አይሰጠኝም” በማለት ባዶ እጁን ነው ለፍልሚያ የሄደው፡፡  
ማልኮም ግላድዌል እንደሚለው፤ በዳዊትና ጎልያድ ፍልሚያ ሁሉም የጎልያድን አሸናፊነት፣ የዳዊትን ተሸናፊነት ደምድሞ ነበር፤ ያኔ ቅድመ ትንበያ ይቻላል፡፡ (ምርጫ ቦርድ አልነበረማ!) በዘንድሮ የአገራችን ምርጫስ? ተቃዋሚዎችንና ገዢውን ፓርቲ በደራሲው አዲስ ፅንሰ ሃሳብ ቅኝት ተመልከቷቸው ስላችሁ፤ በአገራችን ሰላማዊ ትግል እንጂ የትጥቅ ትግል እንደማይፈቀድ ለአፍታ እንኳን እንዳትዘነጉ፡፡ ስለዚህ እንደነ ጐልያድ ፍልሚያ ምናምን የለም፡፡ የምርጫ ፍልሚያ ግን ይቻላል፡፡ በእሱ ላይ ብቻ አተኩሩልኝ። ዋናው የምንዘነጋው ቁምነገር ግዙፎች ወይም ኃያላን ሁሌ እኛ እንደምናስባቸው አለመሆናቸውን ነው ይላል - ደራሲው፡፡ ለአሸናፊነት ያበቃቸዋል ብለን ያሰብነው ግዝፈታቸው ወይም ጥንካሬያቸው፣ አሊያም የጦር መሳሪያ ብዛትና ዘመናዊነታቸው … የድክመታቸው ምንጭም ሊሆን እንደሚችል ማሰብ ይገባል፡፡ ጐልያድን ለግዙፍነት ያበቃው ነገር የዕይታ ሃይሉን እንዳዳከመው ግላድዌል ጠቅሷል፡፡ ይሄም ለሽንፈት ዳርጐታል ባይ ነው፡፡
ባለፉት 200 ዓመታት በሃያላንና ደካማ አገራት መካከል የተደረጉ ጦርነቶችን እስቲ እናስብ የሚለን ደራሲው፤ ኃያላን አገራት ምን ያህል ጊዜ፣ ደካሞቹስ ስንቴ ያሸነፉ ይመስላችኋል? ሲል ይጠይቃል፡፡ (አያድርገውና ቻይናና አትዮጵያ ቢዋጉ ብላችሁ አስቡ!) አብዛኞቻችን የአሸናፊነቱን ድርሻ ወደ 100 ፐርሰንት የምናደርሰው  ይመስለኛል ይላል - ግላድዌል፡፡ እውነቱ ግን ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት አይቫን አሬጉይን-ቶፍት የተባለው የፖለቲካ ሳይንቲስት በሰራው ስሌት መሰረት፤ በጦርነቱ ሃያላን አገራት 71.5 በመቶ ሲያሸንፉ፣ 28.5 በመቶ ያህል ደግሞ ደካማ አገራት አሸንፈዋል ብሏል፡፡
ዳዊት ከግዙፍ ጎልያድ ጋር ፊት ለፊት አይደለም የገጠመው፡፡ ወደሱ ቀረብ እንዳለ ብዙ ሳይጠጋው በጠፍጣፋ ጠጠር  በወንጭፍ ነው ግንባሩን ያለው። ደካማ አገራት ከትላልቆቹ ጋር ጦርነት ሲገጥሙ በተለመደው መንገድ (ፊት ለፊት) ከመዋጋት ይልቅ የሽምጥ ውጊያን ቢመርጡ የአሸናፊነት ዕድላቸው በእጅጉ ይጨምራል ይላል - ደራሲው የጠቀሰው የፖለቲካ ሳይንቲስት፡፡ “ይሄን ጊዜ የደካማውን ወገን የማሸነፍ ዕድል ከ28.5 በመቶ ወደ 63.6 በመቶ ያድጋል” የአሜሪካ የህዝብ ቁጥር የካናዳን አስር እጥፍ ያህላል፡፡ ሁለቱ አገራት (“አያድርግባቸውና!”) ጦርነት ቢገጥሙና ካናዳ ባልተለመደ መንገድ ለመዋጋት ብትመርጥ ማን የሚያሸንፍ ይመስላችኋል? አትጠራጠሩ! ካናዳ ታሸንፋለች ይላል - የ“ዴቪድና ጎልያድ”  ደራሲ፡፡
ዳዊት ጎልያድን ያሸነፈው የጨዋታውን ህግ በመቀየር ነው፡፡ ጎልያድ ከባላጋራው ጋር ፊት ለፊት ገጥሞ በጎራዴ ለመፋለም ነበር ያቀደው፡፡ የያዛቸው ሶስት መሳሪያዎችም ለዚህ ዓይነቱ በቅርበት የሚደረግ ፍልሚያ የሚስማሙ ነበሩ፡፡ ዳዊት ግን ያንን ዕድል አልሰጠውም፡፡ ዳዊት ተራ እረኛ ነው፡፡ እንደ ባለጋራው ሶስት ዓይነት የፍልሚያ መሳሪያም አልታጠቀም፡፡ ጥሩርና ጋሻም አልነበረውም፡፡ የእሱ መሳሪያ ወንጪፍ ብቻ ነበር፤ ግን ፍጥነት፣ ብልጠት፣  ወኔና እምነት የዳዊት ንብረቶቹ ነበሩ፡፡ እስራኤላውያኑ እነዚህን ሁሉ አላስተዋሉም፡፡ የሚታዩ፣ የሚጨበጡና የሚዳሰሱ አይደሉማ፡፡ እናም ዳዊት በቀላሉ ይሸነፋል ብለው ደመደሙ፡፡ ዛሬም ከ3ሺ ዓመት በኋላ ይሄ እምነታችን አልተቀየረም የሚለው ግላድዌል፤ በዚህም የተነሳ በህይወታችን ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያደረሰብን ይገኛል ባይ ነው፡፡
በአሬጉይን - ቶፍት መዘርዝር ወስጥ ከተካተቱት ደካሞች (underdogs) ውስጥ እንግሊዛዊው የውጊያ መሪ ቲ.ኢ ሎውረንስ ተጠቃሽ ነው፡፡ (“የአረቡ ዓለም ሎውረንስ” በሚል መጠሪያው የበለጠ ይታወቃል) ሎውረንስ በቱርክ የጦር ሰራዊት ላይ የተነሳውን አመፅ በመምራት በአንደኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ላይ አረብን የተቆጣጠረ የጦር መሪ ነው፡፡
እንግሊዞች የአረቦችን አመፅ ይደግፉ የነበረ ሲሆን ግባቸውም ቱርኮች ከደማስቆ እስከ ሄጃዝ የዘረጉትን ረዥም የባቡር ሃዲድ ማውደም ነበር፡፡ ኃላፊነቱ የተሰጠው ደግሞ ለሎውረንስ ነው፡፡ ቱርክ በወቅቱ ከባድ ዘመናዊ የጦር ሰራዊት ነበራት፡፡ በተቃራኒው ሎውረንስ ደግሞ ምንም ዓይነት የውትድርና ስልጠናና ሥርዓት የሌላቸው የአረብ ዘላኖችን (ቦዴይን) ይዞ ነበር የተሰለፈው፡፡  
አንድ የቤዶይን ወታደር ከአንድ ጠብመንጃና 45 ፓውንድ ዱቄት በላይ ትጥቅና ስንቅ አይዝም፡፡  በበጋ ወራትም ቢሆን እንኳ በቀን እስከ 110 ማይልስ በረሃ እያቋረጠ ይጓዛል፡፡
“እኛ የነበረን ብልጫ - የውጊያ አይደለም፤ ፍጥነትና ጊዜ ነው” ሲል የፃፈው ሎውረንስ፤ “ትልቁ ሃብታችንም የጎሰ አባላት ነበሩ” ብሏል፡፡ ጥይት ተኩሰው የማያውቁት እኒህ  ዘላኖች፤ ከዘመናዊ ውጊያ ጋር አይተዋወቁም። ተንቀሳቃሽነታቸው፣ ፅናታቸው፣ ብልሃታቸው፣ የአገር ዕውቀታቸውና ወኔያቸው ግን የጥንካሬያቸው መገለጫዎች ነበሩ፡፡
የሎውረንስ ምርጥ ታክቲክ በቱርክ የወደብ ከተማ አቋባ ላይ ጥቃት መሰንዘሩ ነው፡፡  ቱርኮች ጥቃት የጠበቁት በስተምዕራብ የአቋባ ሰላጤን ባህር ከሚቃኙት የእንግሊዝ መርከቦች ነበር፡፡ ሎውረንስ ግን በምስራቅ በኩል በረሃ አቋርጦ ከች አለባቸው፡፡ ከዚያም  በመቶዎች የሚገመቱ የሎውረንስ ተዋጊዎች በሰነዘሩት ጥቃት 1200 ቱርኮችን የገደሉና የያዙ ሲሆን ከእነሱ ወገን ሁለት ሰዎች ብቻ ነበር የሞቱት፡፡ ቱርኮች ላልታሰበ ሽንፈት የተዳረጉት ጠላቶቻቸው በበረሃው በኩል የመምጣት ድፍረት (እብደት) ይኖራቸዋል ብለው ባለመገመታቸው ነበር፡፡
እንደቱርክ ብዙ የሰለጠኑ ወታደሮች፣ ዘመናዊ የጦር መሳሪያና በቂ የቁሳቁስ ሃብት ሲኖር ይጠቅማል፡፡ ሁልጊዜ ግን አይደለም፡፡ አንዳንዴ ሊያሸንፍም ይችላል። አጥቂ ሳይሆን ተከላካይ  ያደርጋል፡፡ ቱርክም የሆነችው እንዲያ ነው፡፡ ዘመናዊ ጦር ይዛ ባልሰለጠነ ዘላን ተዋጊ ድባቅ ተመታች፡፡
የቶፍት የመረጃ ጥንቅርም ሆነ የዓለማችን ታሪክ በግልፅ እንደሚያሳየው፤ ከኃያላን አገራት ጋር ውጊያ የገጠሙ ደካማ አገራት በአብዛኛው ድል የሚቀዳጁት የዳዊትን የፍልሚያ ስልት ከተጠቀሙ ብቻ ነው። ሽምቅ ውጊያ ልትሉት ትችላላችሁ፡፡ ኢህአዴግ ከአፍሪካ ግዙፍ የተባለ የጦር ሠራዊት የነበረውን ደርግን ያሸነፈው በዚሁ ስልት አይደል?! እንደተባባልነው አሁን የትጥቅ ትግል የለም፡፡ ጊዜው የሰላማዊ ትግል ነው (Cheers!!) እናም ሁሉን ነገር በሰላማዊ ትግል ውስጥ ነው እንድትፈትሹልኝ የምፈልገው፡፡ እናላችሁ በዘንድሮ ምርጫ ለምን ኢህአዴግ አሸነፈ? 7 ሚ. አባላት ስላሉት? አያስኬድም! ከ14 ሚ ብር በላይ የምርጫ በጀት ስለነበረው? አያሳምንም! መንግስትና ገዢ ፓርቲ ስለሆነ? ይሄም አያዋጣም! ደራሲው ግላድዌል፤ ኃያልነት ብቻ ለድል እንደማያበቃ ከዳዊትና ጐልያድ ታሪክ ተማሩ ይለናል፡፡ በተለይ ተቃዋሚዎች ይሄን ጉዳይ ሊያጤኑት ይገባል፡፡ ተቃዋሚዎች፤ ኢህአዴግንና ራሳቸውን እንዲሁም ምርጫውንና ውጤቱን በዚህ ፅንሰ ሃሳብ ቢፈትሹት ለቀጣዩ ምርጫ ሊጠቅማቸው ይችላል ባይ ነኝ፡፡ ጊዜ ካላቸው መፅሃፉንም ያንብቡት!! (Cheers!)

Read 3418 times