Saturday, 06 June 2015 14:04

“ዕንቁላሉ አየር ላይ…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(12 votes)

 እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ከአውሮፓና ከአሜሪካ የመጡ ተዋናዮች እያወሩ ነበር፡፡ የአውሮፓው ተዋናይ…
“አውሮፓ ውስጥ ትያትር ቤቶች ከትልቅነታቸው የተነሳ ከኳስ ሜዳ የሚበላልጡ ናቸው፣” ይላል፡፡ አሜሪካዊው በተራው ምን ቢል ጥሩ ነው…
“አሜሪካ ውስጥ ያሉ ትያትር ቤቶች ከትልቅነታቸው የተነሳ ከኋላ መቀመጫ ሆነህ ዕንቁላል ብትወረውር መድረኩ ላይ ከመድረሱ በፊት አየር ላይ ጫጩት ይፈለፈላል፡፡”
እኛ ዘንድም “ዕንቁላሉ አየር ላይ ይፈለፈላል…” አይነት ነገር ከማሳፈር ይልቅ ነገር እንደገባን ማሳያ እየሆነ ነው፡፡
አንዳንድ ጊዜ… አለ አይደል…አለመስማት ቢያቅታችሁ እንኳን… ውስጣችሁ… “በቃ ዝም ብትልስ!” የሚል ስሜት ያድርባችኋል፡፡ “እንቁላሉ አየር ላይ ይፈለፈላል…” አይነት ክርክር የሚገጥማችሁ ሰው ጋር… “ወይ አሳምነኝ፣ ወይ ላሳምንህ!” አይነት ክርክር ቆሽት ማድበን ነው፡፡
ስሙኝማ…የዝምታን ነገር ካነሳን አይቀር የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ…‘ዝምታ ወርቅ ነው’ የሚሏት የከረመች አባባል አለች፡፡ አባባሏ ትከለስልን፡ አሀ…አሁን፣ አሁን እዚህ አገር ‘ዝምታ ወርቅ…’ ሲሆን እያየን አይደለማ!፡፡ …አንድ ነገር በተፈጠረ ቁጥር አገሩ ሁሉ የቴሌቪዥን ካሜራና የሬድዮ ማይክ የሚያሳድደው ‘ዝምታ ወርቅ’ ስለሆነ አይደለም። ልጄ ዘንድሮ ‘ቸስ’ የሚሉት ዝም ያሉት ሳይሆኑ ‘ጮክ’ የሚሉት ናቸው፡፡
ሰውየው የሆነ መጽሐፍ ይጽፋል፡፡ ለጓደኞቹና በቅርቡ ላሉት ረቂቁን ያስነብባል፡፡ እና… “አድናቂህ ነኝ…” ይጎርፍለታል፡፡ (ስሙኝማ…አንዳንዱ… “አድናቂሀ ነኝ… እዚች ላይ ፈርምልኝ…” ሲባል… አለ አይደል… የእኔ አይነቱ ደግሞ “በሁለት ወር የምከፍለው ሁለት ሺህ ብር ተበድሬያለሁ ስትል እዚች ላይ ፈርም…” ይባላል፡፡ የአርባ ቀን ዕድል ጉዳይ ነው፡፡ የፊርማ ‘ዲስክሪሚኔሽን’ ይጥፋልን! ቂ...ቂ…ቂ…)
“አንተ ይሄን አይነት ታለንት ይዘህ እስከዛሬ ዝም ብለህ ተቀምጠሀል!”    “ምን አለ በለኝ፣ ይሄ መጽሐፍ እዚህ አገር የልብ ወለድ ሪቮሉሽን ባያስጀምር!”
“እኔ ጓደኛዬ ስለሆንክ አይደለም፡፡ በቃ አንተ የእኛ ዶስቶቭስኪያችን ነህ…”
“ይሄማ ተተርጉሞ ለዓለም አንባብያን መድረስ የሚገባው ነው…”
እያሉ ሰማየ ሰማያት ያወጡታል፡፡ እነማ…የትኛው ከልብ፣ የትኛው ረገጣ እንደሆነ አንድዬ ይወቀው፡፡ (የመጀመሪያ ሥራዎቻቸውን እያጋነንን እየነገርናቸው መሀል ላይ የተሰናከሉ ሰዎች ብዙ ናቸው፡፡)
እናማ… እንዲህ አይነት ለኖቤል ሽልማት የሚያበቁ አስተያየቶች የደረሱት ጸሀፊ ረቂቁን ለአሳታሚ ያሳያል፡፡ አሳታሚውም ካነበበ በኋለ አንድ ቀን ይጠራዋል፡፡
“ይህንን የጻፈከው አንተ ራስሀ ትመስለኛለህ፡፡”
“አዎ፡፡”
“ልትበረታታ ይገባል፡፡”
“አዎ፡፡”
“ወደ ገጠር አካባቢ መሄድ አለብህ፡፡”
“እሺ፡፡”
“ከዓለም ላይ ትልቁ የሆነው ተራራ ጫፍ ላይ መውጣት አለብህ፡፡”
“እሺ፡፡”
“እና… ከዛ ላይ ተወርውረህ መፈጥፈጥ አለብህ!”
ከዚህ አይነት አሳታሚ ይሰውራችሁ፡፡
ጸሀፊውን ጉድ ያደረጉት… “ዕንቁላሉ አየር ላይ ይፈለፈላል…” አይነት ነገር ሲሉት የከረሙ ወዳጆቹ ናቸው፡፡
“ምግብ በአዲስ መልክ ጀምረናል…” የሚሏት ነገር … ከሆነ የቀልድ መጽሐፍ ላይ የተወሰደች ትመስለን ጀምሯል፡፡ አሁንማ ምግብ ቤቱ ብቻ ሳይሆን…ሁለም አገልግሎት ምናምን ነገር ላይ “...በአዲስ መልክ ጀምረናል…” የሚሏት ነገር ተለምዳለች፡፡ የማጋነንና ‘የረገጣ’ አሪፍ ምሳሌዎች የሆነ ነገር “… በአዲስ መልክ ጀምረናል” የሚሉት ናቸው፡፡
እናላችሁ…“ምግብ በአዲስ መልክ ጀምረናል…” የሚለው ቤት ‘‘አዲሱ ነገር’ ምን መሰላችሁ… የጠረጴዛው ጨርቅ! ግን በር ላይ የተለጠፈው ማስታወቂያ የማማሩ ነገር ግን ምግብ ቤቱ የባለ አምስት ኮከብ ሆቴሎችን ምግብ በ‘ሰፊው ህዝብ አቅም’ ማቅረብ የጀመረ ነው የሚመስለው፡፡ አንዳንዱ ደግሞ “…በአዲስ መልክ…” የሚለው አዲስ የተቀባውን የግድግዳ ቀለም ነው፡፡
“የ24 ሰዓት አገልግሎት እንሰጣለን…” የሚሉት መደበኛ ሰዓቱን እንኳን በደንብ ሲያስተናግዱ አይገኙም፡፡ ግን የማያደርጉትን እናደርጋለን የማለት ‘ረገጣ’ ስለተለመደ ጠያቂም የለም፡፡
“ዕንቁላሉ አየር ላይ ይፈለፈላል…” አይነት ነገር በሁሉም ቦታ ስለለመድን መደናገጥም ተውን መሰለኝ፡፡ አብዛኞቹ ማስታወቂያዎች ላይ የምናየውና የምንሰማው ‘ዕንቁላሉ አየር ላይ ሲፈለፈል’ ነው፡፡   
የምር ግን… አለ አይደል… ሞኝ ሊያደርጓችሁ ሲሞክሩ… “የተለመደ ነው” ብትሉም ትንሽ በሸቅ ማለታችሁ አይቀርም፡፡
የሞኝነት ነገር ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ… እሱዬው ማንበብ አይችልም አሉ፡፡ እናላችሁ… ከእንትናዬው ደብዳቤ ይደርሰዋል፡፡ ይሄኔ ጓደኛውን እንዲያነብለት ይጠይቀዋል፡፡ እያነበበለት እያለም ሰውየው የጓደኛውን ጆሮዎች ግጥም አድርጎ በእጆቹ ይደፍናቸዋል፡፡ የሆነ ሰው በዛ ሲያልፍ ሁኔታቸው ገርሞት “ምን እያደረጋችሁ ነው?” ሲል ይጠይቃል። ሰውየውም “ከእጮኛዬ የደረሰኝን ደብዳቤ እያነበበልኝ ነው፣” ይለዋል፡፡
“ታዲያ ለምንድነው ጆሮዎቹን እንደሱ ግጥም አድርገህ የያዝከው?” ሲለው ምን ቢለው ጥሩ ነው… “ምን እንዳለች እንዳይሰማብኝ ነዋ!
ሌላኛው ደግሞ ለጓደኛው ምን ይላል… “እኔ በምኖርበት ከተማ ሁሉም ነገር በፍጥነት ነው የሚሠራው፡፡ ለምሳሌ ህንጻዎች የሚገነቡበት ፍጥነት የሚያስገርም ነው፡፡ አንድ ቀን ባለ ሀያ ፎቅ ህንጻ ይጀምሩና በሳምንቱ ያልቃል፡፡” ጓደኝዬውም ‘ተመጣጣኝ’ መልስ ይሰጠዋል፡፡
“አንተ እሱን ትላለህ፣ የእኛን ልነግርህ፡፡ ጠዋት ወደ ሥራ ስሄድ የአንድ ግዙፍ ህንጻ መሰረት ድንጋይ እየተጣለ ነበር፡፡ ማታ ከሥራ ስመለስ አከራዩ ኪራያቸውን በወቅቱ ያልከፈሉ ተከራዮችን እያስወጣ ነበር፡፡”
በቃ፣ ‘ከረገጡ’ አይቀር እንደዚሀ እስከ ጥግ ድረስ ‘መርገጥ’ ነው፡፡ ‘የረገጣ’ ሀምሳ ፐርሰንት፣ ሲሦ ምናምን የትም አያደርስማ! ቂ…ቂ…ቂ… አንድ ዕንቁላል ሳይሆን አሥራ ምናምን ‘ዕንቁላል አየር ላይ ማስፈልፈል’ ነው!
በዛ ሰሞን አራት ልጆች የወለደችው ጀርመናዊትን አንድ ወዳጃችን… “የሚባለው ወለደች ሳይሆን ፈለፈለች ነው…” ብሎናል፡፡ ፈለፈለች ለሰው ሲሆን አሪፍ ድምጽ የለውም፣ አይደል!
ይቺን የሆነች ቦታ ያነበብኳትን ስሙልኝማ…
ሀብታሙ ሰውዬ ኑዛዜውን ሊያጽፍ ጠበቃውን ይጠራል፡፡ ጠበቃውም…
“ስንት ልጆች አሉዎት?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው…
“እሱን እንግዲህ በክርክር ወቅት ፍርድ ቤት የሚወስነው ይሆናል፡፡” ይሄ ዲ.ኤን.ኤ. የሚሉት ነገር ቀደም ብሎ ቢመጣ ኖሮ ይሄኔ ስንት ‘ወንደላጤ’ የአምስት ልጆች አባት ይሆን ነበር፡፡ “ግንባሩ አካባቢ ልክ እሱን ይመስላል…”፣ “ዓይኖቹ ያ ጋዜጣ ላይ የሚዘባርቀውን ሰውዬ አይመስልም!” አይነት ማመሳከሪያ ዘንድሮ አይሠራም፡፡
እናላችሁ….“ዕንቁላሉ አየር ላይ ይፈለፈላል…” አይነት ነገር ብዙ ጊዜ ተቋማዊ መልክም ይይዛል፡ በፐርሰንትና በ‘ዘመኑ አብዮት’ ቃላት ለመሸፋፋን የሚሞከር “ዕንቁላሉ አየር ላይ ይፈለፈላል…” ነገር በየዕለቱ በሚባል ድግግሞሽ የምንሰማው ነው፡፡
“ዕንቁላሉ አየር ላይ ይፈለፈላል…” ከሚያሰኝ ባህሪይ ይሰውረንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 2777 times