Saturday, 06 June 2015 14:02

አገጭህን ይዞ የሚለምንህ፣ እምቢ ብትል በጥፊ ሊልህ (መንከስካ ሒዙ ዝልምነካስ፣ እንተኣበቸ ብፅፍዒት)

Written by 
Rate this item
(8 votes)

  ከዕለታት አንድ ቀን ቹዌንጌር የሚባል አንድ የቺን ልዑል ነበረ፡፡ ይህ ልዑል ቀን ጐሎበት ወደሌላ ቼንግ ወደሚባል አገር ተሰደደ፡፡ ወደ አገሩ እስኪመለስም በድህነት፤
“ካገሩ የወጣ አገሩ እስኪመለስ
ቢጭኑት አህያ ቢለጉሙት ፈረስ”
እያለ በቻይኒኛ አሳዛኝ ህይወቱን ይመራ ጀመር፡፡
አንድ ቀን በተሰደደበት አገር በቼንግ ቤተመንግሥት አጠገብ ሲያልፍ ድንገት ንጉሡ ሲወጣ ይደርሳል፡፡ ንጉሡ የዚህን ልዑል ማንነት ሳያውቅ፤
“የማን ነው ቡቱቷም! እንደነዚህ ዓይነት ሰዎች በመንገድ ላይ እንዳላይ አላልኩም?! ይሄን ጭርንቁሳም ከመንገዴ አስወግዱልኝ!” አለ፡፡
የንጉሡ ባለሟል ግን ሰውዬው ማን እንደሆነ ስለገባው፤
“ንጉሥ ሆይ! ይሄ ሰው ጊዜ ጥሎት ነው እንጂ የተከበረ ልዑል ነበር፡፡ በታላቅ አክብሮት ብንይዘው ጥሩ ይመስለኛል፡፡ ደህና ቦታ አስቀምጠንም በዐይነ - ቁራኛ ብናየው ይሻላል!” አለ፡፡
ንጉሡ ግን የዚያን ሰው ጉስቁልናና ጨብራራ ፀጉር ብቻ ነበርና የተመለከተው የቧለሟሉን ምክር ከመጤፍ ሳይቆጥር ልዑሉን ክፉኛ ሰደበው፡፡
ባለሟሉም፤ እንደገና፤
“ንጉሥ ሆይ! ግርማዊነትዎ በአክብሮት ሊይዘው ካልቻለ፣ ነገ የሚመጣውን ማናቸውንም ነገር ከወዲሁ ለመቅጨት ወይ ይሄን ሰው ማስወገድ ይኖርብዎታል!” አለና አስጠነቀቀ፡፡
ንጉሡ ግን፤
“በእንደዚህ ያለ ቆሻሻ ላይ እጄን አላሳርፍም!” ብሎ አንቋሾት ሄደ፡፡ ከጊዜ በኋላ ልዑል ወደ አገሩ ተመለሰ፡፡
ሁኔታዎች ሁሉ ተለዋወጡ፡፡ ያ ልዑል ማ ደግ እንደሆነለት፣ ማ ክፉ እንደሠራበት ያውቃል፡፡ ከሰው ሁሉ ግን ያንን ንጉሥ አልረሳውም፡፡ ስለሆነም ጦሩን ሁሉ አደራጅቶ ወደ ቼንግ ዘመተ፡፡ ስምንት ግዛቶች ያዘ፡፡ ግዛተ - መንግሥቱን አፈራረሰ፡፡ የቼንግን ንጉሥም ወደራሱ ወደ ልዑሉ አገር እንዲሰደድ አደረገ፡፡
*   *   *
ሰው ነገ ምን እንደሚሆን አይታወቅም፡፡ ዛሬ ምናምኒት አቅም የሌለው ሰው፣ ወደፊት ትልቅ ሥልጣን ያለው ሰው ሊሆን ይችላል፡፡ በህይወታችን ብዙ ነገር ልንሸከም፣ ልንረሳም እንችላለን፡፡ መናቅና መሰደብን ግን አንረሳም፡፡ ቅስም የሚያም ነገር በቶሎ ከልባችን አይወጣም፡፡ ፈረንጆች “ረዥም የማስታወስ ችሎታ ካለው እባብ ጋር አትጣላ” ይላሉ፡፡ አላስፈላጊ የሆነ ሌሎችን የማጐሳቆል ተግባር ጥቅም የለውም፡፡ ሌላው ሰው፤ ጊዜ የገፋው አንሶ እኛ ተጨምረን “የወደቀ ዛፍ ምሣር ይበዛበታል” የሚለውን ብናስዘምር የማታ ማታ፤ ለጊዜያዊ እርካታ ብለን አሁን የፈፀምነው ኋላ መዘዙ ብዙ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ዓለምን በተለይም አገራችንን የቂም ቀለበት መሽከርከሪያ ምህዋር አናድርጋት፡፡ አርቀን እናስብ፡፡ ሼክስፒር በሐምሌቱ፤ በፀጋዬ ገ/መድህን ብዕር ልሣን፤
“ዛሬ ለወግ ያደረግሺው፣ ወይ ለነገ ይለምድብሻል
ልማድ ፊት እንዳሳዩት ነው፣ ወይ ይጠፋል ወይ ያጠፋል”…ይለናል፡፡ እንደወግ የምናደርገውን ነገር ሁሉ እንመርምር፡፡ አንድም፤ ማታለልና ማጭበርበር የደህንነት -ማጣት፣ የሥጋት እናት ነው ይሏልና አበው፡፡ ደረጃው ይለያይ እንጂ ራስን አደጋ ላይ መጣል መሆኑን ለአፍታም አለመዘንጋት ብልህነት ነው፡፡
ለሀገራችን ፖለቲካ ብቻ ሳይሆን ለአጠቃላይ ህይወታችን፤ አንድ ተረት እጅግ ጠቃሚ ፋይዳ አለው፡፡ ይኸውም፤ “ዋናው መንገድ ቢጠፋብህ፣ መጋቢ መንገድ ፈልግ” የሚለው ነው፡፡ በሀገራችን የትግል ሂደት ውስጥ ዋናው መንገድ የጠፋበት በርካታ ጊዜ እንደነበረ የኖረና የታዘበ ሁሉ ያውቀዋል፡፡ አማራጭ መንገድ ወይም አማራጭ ዕቅድ (Plan B- እንዲሉ) የሌለው ሰው፤ ዓለም ባንድ ጊዜ የጨለመበት ይመስለዋል፡፡ “ከእንግዲህ መሄጃ መራመጃ የለም፤ ሁሉ ነገር አበቃለት” ይላል፡፡ ሌላው ቀርቶ ግን ዋናው መንገድ በዕድሳት ላይ ቢሆንስ? ብሎ እንኳ ማሰብምኮ ያባት ነው፡፡ ከሁሉ ቀዳሚው ነገር ግን ለራስ የዝግጅት ጊዜ መስጠት መሆኑን ከልብና ጥንቅቅ ባለ ሁኔታ አጢኖ መጓዝ ነው፡፡ የሚመጣውን አምስት ዓመት መንገድ  ከአሁኗ ሰዓት መጀመር ተገቢ ነው፡፡ ዋናና መጋቢ መንገዶችን በቅጡ መለየት ከአሁኑ ነው፡፡ ጊዜ የማያላላው ሰንሰለት የለም ይባላል፡፡ የለውጥ ህግ ብቻ ይቀራል እንጂ ሁሉም ነገር ይለወጣል፡፡ ስለዚህ በፅንዓት መቀጠል ይገባል፡፡ አገር በአንድ ጀንበር እንዳልተገነባች ሁሉ፣ ለውጥም በአንድ ጀንበር አይመጣም፡፡ ለውጥ አዳጊ ሂደት መሆኑን ምኔም አለመርሳት ነው፡፡ ቀና ውድድርና ፉክክር፣ የፖለቲካ ንግግርና ክርክር በማድረግ አስተሳሰብን መለወጥ የአንድ ሰሞን የቴሌቪዥን ፍጆታ አይደለም፡፡ ቻይናዎች፤
“ዕቅድህ የዓመት ከሆነ ሩዝ ዝራ፡፡
ዕቅድህ የአምስት ዓመት ከሆነ ባህርዛፍ ትከል
ዕቅድህ የዘለዓለም ከሆነ ግን ልጅህን አስተምር!”
ይላሉ፡፡ የሁልጊዜ ሥራችን ህዝብን ማስተማር መሆን አለበት፡፡ ከአሁኗ ደቂቃ ጀምሮ፡፡ በዚህ የፖለቲካ መማር ማስተማር ሂደት ውስጥ እንቅፋት አያጋጥመንም ማለት አይደለም፡፡ መስዋዕትነት የለበትም ማለት አይደለም፡፡ እንኳን የፖለቲካ መንገድ ተራውም ህይወት እንኳ በእሾክ በአረንቋ የተሞላ መሆኑን አለመዘንጋት ነው፡፡ “አገጭህን ይዞ የሚለምንህ፣ እምቢ ብትል በጥፊ ሊልህ” የሚለው ተረትም እዚህ ውስጥ እንደሚካተት አለመዘንጋት ብልህነት ነው!

Read 3813 times