Saturday, 06 June 2015 14:00

ሞጋች ቃለምልልስ ከ“አንድነት”ሊቀመንበር ጋር

Written by 
Rate this item
(2 votes)

የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ፕሬዚዳንት አቶ ትዕግስቱ አወሉ፤ በቅርቡ በተካሄደው አገራዊ ምርጫ ፓርቲያቸው ያገኘውን ውጤት በፀጋ እንደሚቀበለው ጠቁመው ፓርቲው ስኬት ያላስመዘገበው በራሱ ችግር እንጂ በገዢው ፓርቲ ተጭበርብሮ እንዳልሆነ ሰሞኑን ለኢቢሲ ብቻ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ አቶ ትዕግስቱ አወሉ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ባደረጉት ሞጋች ቃለምልልስ ለተለያዩ አወዛጋቢ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ምክትል ፕሬዚዳንት ስለሌለው ካቢኔያቸው፣ የፓርቲውን ውድቀት ከሚሹ አካላት ገንዘብ ተቀብለው መኪና ገዝተዋል ተብሎ ስለሚናፈሰው ወሬ፣ በዘንድሮ ምርጫ ፓርቲያቸው ባገኘው ውጤት ከመጨረሻዎቹ ተርታ ስለመሠለፉ ተጠይቀዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ የሰጧቸውን ምላሾች ያንብቡ፡፡
              ለአወዛጋቢ ጥያቄዎች መልስ ሰጥተዋል

     “አንድነት” ምን ውጤት ጠብቆ ነበር ወደ ምርጫው የገባው? ያገኛችሁትን ውጤትስ እንዴት አያችሁት?
አንድነት ህጋዊና ሠላማዊ ተቃዋሚ ፓርቲ ነው። ምርጫ የሠላማዊ ትግል አንዱ መገለጫ እንደመሆኑ ወደ ምርጫው ሲገባም አሸንፋለሁ ብሎ ነው፡፡ መንግስት ለመሆን የሚያበቃ በቂ ውጤት ያገኘ ፓርቲ ባይኖርና አንድነት ቢያሸንፍ ከማንኛውም ያሸነፈ ፓርቲ ጋር በጥምረት መንግስት የመመስረት አላማ ይዞ ነው ወደ ምርጫው የገባው። አንድነት ከሁሉም በላይ ግን ለዲሞክራሲያዊ ስርአት መጐልበት አስተዋጽኦ ለማድረግና በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ትርጉም ባለው ሁኔታ ወንበር ለማግኘት በማሰብ ነው ወደ ምርጫ የገባው፡፡
የምርጫ ውጤቱን በተመለከተ እስካሁን የተገለፀው የ442 ወንበሮች ነው፡፡ በዚህም ኢህአዴግና አጋሮቹ እንዳሸነፉ ነው የተነገረው። ስለዚህ እኛ ውጤት አላገኘንም ማለት ነው፡፡ ያገኘነው የምክር ቤት ወንበር  የለም፡፡
“አንድነት” ከሌሎቹ ተቃዋሚዎች አንፃር ያገኘው የድምጽ ብዛት ለምን ዝቅተኛ ሆነ? ቀደም ሲል ፓርቲው በተሻለ አቋም ላይ እንደነበር ይነገራል። ይሄን ጥያቄ ያነሣሁት፤ እርስዎም በተወዳደሩበት የምርጫ ክልል እጅግ ዝቅተኛ ድምጽ ማግኘትዎን ስላየሁ ነው?
ስንት ጣቢያ ላይ ነው ያየኸው?
የተወሰኑትን አይቻለሁ፡፡
እንግዲህ 57 ጣቢያ ነው ያለው፡፡ ምን ያህሉን አይተህ “ዝቅተኛ ውጤት ነው ያገኘኸው” እንዳልከኝ አላውቅም። እኔም ምን ያህል እንደሆነ ገና መረጃ እያሰባሰብኩ ነው፡፡ ግን ከአዲስ አበባ ውጪ በሌሎች እጩዎች ከኢህአዴግ ቀጥሎ ከፍተኛ ድምጽ ያገኘንባቸው ቦታዎች አሉ፡፡
ቦታዎቹን ሊጠቅሱልኝ ይችላሉ?
በደቡብ አካባቢ እንዲሁም በአማራ ክልል ከፍተኛ ውጤት አግኝተን 2ኛ የሆንባቸው ጣቢያዎች አሉ፡፡ ግን ውጤት መግለፅ አይፈቀድም፣ ምርጫ ቦርድ ማጠቃለያ ሠርቶ ውጤቱን ይፋ ያደርጋል፡፡ ለቀጣይ ምርጫ በአንድ ምርጫ ክልል የእጩዎችን ቁጥር ከ12 ያልበለጠ ለማድረግ አሁን የሚገኘው ውጤት ወሣኝነት አለው፡፡ እስከ 6ኛ ደረጃ የያዙት በቀጥታ እንዲወዳደሩ ይደረጋል፡፡ እኛም እዚያ ደረጃ ውስጥ መግባታችንን ለማወቅ የቦርዱን ጠቅላላ ውጤት መጠበቅ  ይኖርብናል፡፡
አንዳንድ ወገኖች፤ የፓርቲው የምርጫ ውጤት ዝቅ ማለት “አንድነት” በህዝብ ዘንድ ተቀባይነቱ መቀነሱን ያሳያል ይላሉ በተለይ ከቀድሞው የአንድነት ተቀባይነት አንፃር በማለት፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?
ከነችግሩም ቢሆን ህዝቡ ልብ ውስጥ እንዳለን በድፍረት መናገር ይቻላል፡፡ የአንድነት ችግር መነጋገሪያ የሆነው እኮ በህዝቡ ውስጥ ስላለን ነው፡፡ እኛ በህዝቡ ውስጥ ነን ብለን እናምናለን። የእርስ በእርስ ውዝግቡ ለትግሉ ስኬት በጐ ያልሆነ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ይሄን ሁሉ ታግሎ ማለፍ ይጠይቃል፡፡ እኛ በተለያዩ አደረጃጀቶቻችን አማካኝነት በህዝቡ ውስጥ እንዳለን እናውቃለን፡፡ ለዚህ ማሣያው የምርጫ ውጤት ብቻ አይደለም። ሀገራችን ለዲሞክራሲ ገና ጀማሪ እንደመሆኗ ነገሮችን ከነችግሩ መቀበል ያስፈልጋል፡፡
“አንድነት” ከአመራር ውዝግቡ በፊት ከሁሉም ተቃዋሚዎች የበለጠ በርካታ እጩዎችን እንደሚያቀርብ አስታውቆ ነበር፡፡ እናንተ 92 እጩዎች ብቻ ነው ያቀረባችሁት፡፡ ይሄ ከአመራር ለውጡ በኋላ ፓርቲው መዳከሙን ወይም ብዙዎች ከፓርቲው መሻሻቸውን አያሳይም?
አሁን ተዳክሟል፣ አልተዳከመም ለማለት ያስቸግራል። እኔ አመራሩን ስለያዝኩት ተዳክሟል ሊባል አይችልም፡፡ የበፊቱ አመራር ውስጥም ነበርኩበት፤ ዝም ብዬ መጥቼ የተቀመጥኩ ሰው አይደለሁም፡፡ ፓርቲው መጀመሪያም ድክመት አለው፡፡ ምናልባት በወቅቱ እዚያም እዚህም  የነበሩ ጩኸቶችን ሳታዳምጡ አልቀራችሁም። ያ ጥንካሬን አያሣይም፡፡ ፓርቲው ድክመት ነበረበት። አሁንም ፓርቲው ወደቀ አይባልም፤ በመካከለኛ ደረጃ እየተጓዘ ነው፡፡ በአመራር ደረጃ የተፈጠረው ችግር አሉታዊ ነገሮች አሉት፡፡ ውዝግቡ የወሰደው ጊዜ በቂ እጩዎች ማቅረብ እንዳንችል አድርጐናል። ፓርቲው ለሁለት አመት ያቀደውን ማከናወን አልቻለም፡፡ እቅዱ የጨነገፈበት ምክንያት የአመራሩ ውዝግብ ነው፡፡ እጩዎችን ለማቅረብ 7 ቀን ብቻ ነው የተሠጠን፡፡ ስለዚህ የተፈጠረው ችግር እቅዳችንን አፋልሶታል፡፡ እጩዎችንም በበቂ ሁኔታ እንዳናቀርብ አድርጐናል፡፡ በችግር ውስጥ እያለን በአጭር ጊዜ 92 እጩዎችን ማስመዝገብ በራሱ ትልቅ ስኬት ነው፡፡
ያለ ፓርቲው ሙሉ አባላት ተቀባይነት የእርስዎ ወደ አመራር መምጣት “አንድነት”ን እንዳልነበር አድርጐታል፣ የፓርቲውን መዋቅርም አፈራርሶታል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ እርስዎ ለፓርቲው መዳከም ተጠያቂ አይደለሁም ነው የሚሉት?
ተጠያቂ አይደለሁም፤ ምክንያቱም በህግ አግባብ የተሸነፉት ሰዎች አይደሉም እንዴ “አንድነት ፈርሷል የለም” ብለው አባላትን ወደ “ሠማያዊ” ያስኮበለሉት። “የሠማያዊ” አብዛኞቹ እጩዎች የማን ናቸው? የ “አንድነት” ናቸው፡፡
ግን እኮ አባላቱ ወደ “ሠማያዊ” የኮበለሉት የእርሶን አመራር ባለመቀበል እንደሆነ ነው የሚነገረው…?
ይሄንማ የኔ ተቀባይነት ማጣት ማሳያ ሆኖ ሊቀርብ አይገባም፡፡ የቀሩትንም አባላት ማሰብ አለብን፡፡
የቀሩ አባላት ቢኖሩም ፓርቲውን ከምስረታ ጀምሮ በአመራርነት ለረጅም ጊዜ ያገለገሉና ያደራጁ ሰዎች በአብዛኛው የእርስዎን አመራር አልተቀበሉትም ይባላል…
ተው እንደሱ አይደለም… ዋናዎቹ አልሄዱም። እስቲ ቁጠርልኝ… የትኛው አመራር የኔን አመራር አልቀበልም ብሎ ሄደ? አመራር ሳይሆን “እኛ ብቻ” የሚሉት ናቸው የሄዱት፡፡ ከዚያ ውጪ የቢሮ ሠራተኞች ሄደው ሊሆን ይችላል፡፡ በተረፈ ሚዲያውም ሆነ ሌላው የራሱን ስሜት ብቻ ነው የሚያራግበው፡፡
አሁን በእርስዎ አመራር ስር ምን ያህል አባላት አሉ?
በቁጥር ይሄን ያህል አልልህም፤ አንተም የሄዱትን በቁጥር ልትጠቅስልኝ አትችልም፡፡ ስለዚህ ያሉን አባላት ይሄን ያህል ናቸው ልልህ አልችልም። ፓርቲው እኮ አሁንም አደረጃጀቱንና መዋቅሩን አጠናክሮ እየሠራ ነው።
በክልሎች ያለው መዋቅራችሁ በአብዛኛው እንደፈራረሰ ይነገራል…
መዋቅር ቢኖረን አይደለም እንዴ 92 እጩዎችን በ7 ቀናት ማስመዝገብ የቻልነው፡፡ መዋቅራችንም ሆነ አደረጃጀታችን እንዳለ ነው ያለው፡፡ ያ ሁሉ “አንድነት”ን አፍርሱና ውጡ ጉትጐታ ሣይበግራቸው አባላቱ አብረውን አሉ፡፡ በየፕሬሱ ፓርቲውን እንዲለቁ ሲጐተጐት ነበር። ለነገሩ ፕሬሱ ምን አይነት አዝማሚያ እንደነበረው እኛ እናውቃለን፡፡ አንዳንድ ጊዜ ነፃ ሃሳብ ሣይሆን ግለሰብን በመውደድ የህዝብ ግንኙነት ስራ የሚሠሩ ፕሬሶች አሉ፡፡ ግን ያሁሉ ከሽፎ ምርጫው ተካሂዷል፡፡ የምርጫ ውጤት ማጣት የኛ ችግር ብቻ አይደለም፤ ሌሎችም ፓርቲዎች በዜሮ ድምር ተባዝተዋል፡፡
የአመራር ውዝግቡ ባይፈጠር ግን “አንድነት” ከየትኛውም ፓርቲ በተሻለ ዝግጅት ወደ ምርጫው ገብቶ ውጤት ማስመዝገብ ይችል ነበር ብለው የሚቆጩ ወገኖች አሉ፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?
የተሳሳተ ግንዛቤ ነው፡፡ “አንድነት” ሠዎች እንደሚሉት አይደለም፡፡ የግለሰቦች ችግር የነበረበት ፓርቲ ነው። ፕሮግራሙን ከማስፈፀም አንፃር ሌላ ችግር የነበረበት ፓርቲ ነው፡፡ ምንም ውዝግብ ባይፈጠር እንደውም በራሱ ችግሮቹ ምክንያት ወደ ምርጫው ሁሉ ላይገባ ይችል ነበር፡፡ የአስተሳሰብ ችግር በውስጡ የነበረበት ፓርቲ ነው፡፡ እነዚያ ሰዎች እኮ ፓርቲውን አድምተውታል፤ አቁስለውታል፡፡ አሁን እያገገመ ነው ያለው፡፡
አንድነት እኮ አሁን ብቻ አይደለም አመራሩ የተቀየረው፡፡ ከዶ/ር ነጋሶ በኋላ እንኳ እኔ ሦስተኛ ሰው ነኝ፡፡ እነዚህ ጠንካራ ነበሩ የሚባሉት ግለሰቦች የ3 ወር የአመራር እድሜ ነው የነበራቸው፡፡ እንዴት ነው በ3 ወር ጊዜ ውስጥ ተገምተው ጠንካራ ናቸው የሚባሉት? እንደገና የመጡትም በአሻጥር ነው፡፡ በአመራር ላይ ሲሰሩ የነበረው አሻጥር ነው እነሱኑ መልሶ የበላቸው። “አንድነት” ተዳክሟል የሚባል ከሆነ፣ በኔ አመራር ሳይሆን ተያይዞ በመጣ ችግር ነው የደከመው፡፡ ችግሩ የጀመረው በዶ/ር ነጋሶ አመራር ጊዜ ነው፡፡ “እሣቸው ጠንካራ ስለነበሩ  አቻችለው ይዘው ቆዩ፤ ዛሬ ትዕግስቱ ስለያዘው ወደቀ” ማለት አይቻልም፡፡
እርስዎ ከዚህ በፊት ለፓርቲው ፕሬዚዳንትነት ተወዳድረው 1 ድምጽ ብቻ ነው ያገኙት ይባላል፡፡ እውነት ነው?
ይሄ ብዙ ጊዜ ይባላል፡፡ በዲሞክራሲ የማያምኑ ሰዎች የሚያወሩት ነው፡፡
እርስዎ 1 ድምጽ ብቻ ማግኘትዎ ግን እውነት ነው?
እሱን የሚያውቀው በወቅቱ የነበረው አስመራጭ ኮሚቴ ነው፡፡ ለፕሮፓጋንዳ ተብሎ የሚወራ ነገር ነው። ይሄን ጥያቄ ደግሞ በዚህ ሰአት እንድጠየቅ ፈጽሞ አልፈልግም፡፡ ቆይ ለምን አሁን ስለተመረጥኩበት 160 ድምጽ አታነሳም፡፡ እሱን ለምን አትናገሩትም፡፡ ደግሞ አሁን ያለፈ ታሪክ አይደለም ማውራት ያለበን፡፡
ወደሱም ልመጣ ነበር እኮ… በውድድሩ አንድ ድምጽ ብቻ አግኝተው ብዙም ሣይቆዩ እንዴት በ160 ድምጽ ተመረጡ… የሚለውን የሚጠይቁ ወገኖች አሉ…
ይሄ ፍፁም ዲሞክራሲያዊ ያልሆነ፣ የፀለምተኝነት አስተሳሰብ ነው፡፡ እንዲህ አይነት ነገር የለም፡፡ ትናንት 1 ድምጽ አግኝቶ፣ ዛሬ እንዴት 160 ድምፅ ሊያገኝ ይችላል? የሚለው አያስኬድም። ይሄ የሂሣብ ጉዳይ አይደለም፡፡ ነገሩ ለፕሮፓጋንዳ ዓላማ የሚውል ስለሆነ አሁን ምንም የምለው ነገር የለኝም።
ቀደም ሲል ፓርቲው ከአሜሪካና በተለያዩ ሃገራት ካሉ ደጋፊዎቹ ሰፊ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያገኝ ሲገለፅ ነበር፡፡ አሁንስ ድጋፉ ሳይቋረጥ ቀጥሏል? ወይስ…
ፓርቲው በፊት ስንት ያገኝ እንደነበር ስለማናውቅ ይሄን ለመግለጽ ይከብደናል፡፡ እኛ የምናገኘውን የድጋፍ መጠን በተመለከተም ለመናገር የምንገደድ አይመስለኝም፡፡ ፓርቲው ተቋም እንደመሆኑ ድጋፍ አለው፡፡ በአመራር ደረጃ የግለሰቦችን መፈራረቅ ተመልክተው የሚሸሹ ሰዎች የሉም፡፡ “እኔ ፓርቲውን ካልመራሁት ደክሟል” ማለት፣ የጨለምተኝነት አስተሳሰብ ነው እንጂ ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ አይደለም፡፡ “አንድነት” ደግሞ እነዚህን ሰዎች ሠርጐ ገቦች አድርጐ ነው የሚወስዳቸው፡፡ ባህሪው አይደለማ!
ከምርጫ ቦርድ ለምርጫው ማስፈፀሚያ የተሰጣችሁን ግማሽ ሚሊዮን ብር ገደማ ለምን ተግባር ነው ያዋላችሁት?
ሙሉ ለሙሉ ለምርጫው ቅስቀሳ ነው  ያዋልነው፡፡
አንዳንድ የፓርቲው እጩዎች ግን በገንዘብ እጦት የቅስቀሳ ፖስተራቸውን እንኳ
ሳይለጥፉ እንደቀሩ ይነገራል…
የተሳሳተ መረጃ ነው፡፡ ለእጩዎች ገንዘብ ሰጥተናል። በስንፍና ያልለጠፈ ሊኖር ይችላል፡፡ እኛ ግን ገንዘቡን ለፓርቲው ሙሉ እንቅስቃሴ ነው ያዋልነው፡፡ ሌላው የጀነራል ኦዲተር ስራ ነው፡፡
አሁንም በመካከላችሁ የአመራርና የአባላት ቅራኔና መከፋፈል እንዳለ ይወራል…?
የለብንም፡፡ ችግር ያለበት አመራር ካለ ሊጠየቅ ይችላል፤ እኔ እስከማውቀው ድረስ የአመራር መከፋፈል  የለም፡፡
ፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት የለውም፡፡ ለምንድን ነው?
አልሾምንም!!
እስካሁን ያልተሾመበት የተለየ ምክንያት አለው?
ምንም ምክንያት የለውም፡፡ በቃ ለቦታው የሚሆን ብቃት ያለውን ሰው ፈልገን እስከምናገኝ ድረስ ነው፡፡ እኛ እኮ ገና አሁን ነው ከችግር ውስጥ የወጣነው፡፡
የእርስዎን ካቢኔ ሊነግሩኝ ይችላሉ፡፡ እነማንን ያካትታል?
አሁን ካቢኔውን ማሳወቅ የሚጠበቅብኝ አይመስለኝም፡፡
ግን ፓርቲው ካቢኔ አለው?
አዎ አለው! ግን አሁን ማሳወቅ አይጠበቅብኝም፡፡
ፓርቲው ግልጽ አሠራር የሚከተል ከሆነ፣ ደጋፊዎቹና ህዝቡ ካቢኔውን ቢያውቁ ምን አለበት?
ተወው እሱን! ከአመራርነት ወጣን የሚሉ ሰዎች “የካቢኔ አባል ነን” የሚሉ ከሆነ፣ እነሱን አግኝተህ ጠይቅ። በ“አንድነት” ውስጥ መከፋፈል ተፈጥሯል የምትለኝም አያስደንቀኝም፤ ብዙ ፍላጐት ያለበት ቤት ስለሆነ ሰዎች የየራሳቸውን ነገር ሊፈጥሩ ይችላሉ፤ ነገር ግን የምንመራው በስርአት ስለሆነ ስርአቱ ራሱ ይገዛናል፡፡
ቀደም ሲል “አንድነት” አልፈርምም ያለውን የስነ ምግባር ደንብ ፈርማችሁ,ኧ የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የመግባት እቅድ አላችሁ?
አሁን እቅድ አለን የሚል መልስ የለኝም፡፡ ምክንያቱም ቀደም ሲል ከ “መድረክ” ጋር ስለነበርን የመድረክን አቋም ነው ፓርቲው ያራመደው፤ አሁን ከመድረክ ጋር አይደለንም፡፡ በሌላ በኩል ከመድረክ ጋር ያለን ግንኙነትም አለ፡፡ እስካሁን ግን በምርጫ ሂደት ውስጥ ስለነበርን በጉዳዩ ላይ ተወያይተን ውሳኔ አልሰጠንበትም። በቀጣይ የሚታይ ይሆናል። የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባል መሆን ያለመሆን ጉዳይም ሆነ መድረክ መልሶ በመቀላቀል ላይ የተወሰነ ነገር የለም፡፡
“አንድነት በአመራር ሽኩቻ ምክንያት ተቀባይነት እያጣ መጥቷል” የሚለው ጉዳይ ከፓርቲው የወደፊት እጣ ፈንታ አንፃር አያሳስቦትም?
አያሳስበኝም፡፡ ምክንያቱም “አመራር ነን” ብለው “አመራር አይደላችሁም” የተባሉት ሰዎች፣ ትክክል ናቸው የሚል አዝማሚያ ስላለ ነው፡፡ ፓርቲዎች ለህግ ተገዢ መሆን አለባቸው፡፡ እኛ በህግ አሸነፍን፤ እነሱ ግን በኔትወርክ ለመጓዝ ነበር ሃሳባቸው፡፡
አንዳንድ ወገኖች ከመንግስት ከፍተኛ ድጋፍ እንዳለዎት ይናገራሉ፡፡ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
ምንም ድጋፍ የለኝም! ህግን ከማስከበር አኳያ መንግስት ድጋፍ በማድረጉ ሃላፊነቱን ነው የተወጣው። እንዴ! እነሱ በኔትወርክ የሄዱት እኮ ለባለስልጣኖች ድጋፍ ነበር፤ ግን አልተሳካም። እዚህ ቤት ከዚህ በኋላም ባለፈው የተፈጠረው ስሜት ሊፈጠር ይችላል፤ ማንም ዋስትና የለውም። አሁንም የቡድን ስሜቶች ያሉበት ቤት ነው፡፡ አሁን “አንድነት”ን የሚመራው አንድ አመራር ነው። እነዚህ ሰዎች በፓርቲው ስም እንንቀሳቀሳለን ቢሉ በህግ ይጠየቃሉ፡፡ ይሄን የሚያራግብ የሚዲያ አካልም ከተጠያቂነት አያመልጥም፡፡
የአንድነትን አመራር ለመከፋፈል ላደረጉት ውለታ የፓርቲውን መዳከም ከሚፈልጉ ወገኖች  ገንዘብ ተሰጥቶታል፣ መኪናም ገዝተዋል…” የሚሉ መረጃዎች ይናፈሳሉ
ማን ነው ያለው?
“ከአንድነት” የወጡ የቀድሞ አባላት በማህበራዊ ሚዲያው በስፋት እየፃፉበት ነው
ማህበራዊ ሚዲያው ሃላፊነት የሚሠማው ስላልሆነ አላምንበትም፡፡ በሶሻል ሚዲያ ለሚወራው ነገር ብዙም ትኩረት ስለማልሰጠው በዚህ ላይ ጊዜዬን ማጥፋት አልፈልግም፡፡ በማላምንባቸው ሚዲያዎች የቀረበ ስም ማጥፋት ስለሆነ አልቀበለውም፡፡
ግን እኮ ይሄን የሚሉት የፓርቲው የቀድሞ አመራሮች ናቸው፡፡ እናንተም በሬዲዮ የፓርቲውን ገንዘብ ለግል ጥቅማቸው አውለዋል ብላችሁ ስትወነጅሉ ነበር፡፡ የእርስዎን በተመለከተ ለምን ቀጥተኛ ምላሽ አይሰጡኝም?  
እኔ የገዛሁት መኪናም የለም፡፡ ያገኘሁት የውለታ ገንዘብም (Reward) የለም፡፡ “ሪዋርድ” ላገኝ የምችልበት መንገድም የለም፤ በዚያ ላይ ፓርቲውን አላፈረስኩም፤ ይዤ ነው የቀጠልኩት።
ለ20 አመት ያህል በተቃዋሚ ውስጥ ያለሁ ሰው ነኝ። ከኢህአዴግ ጉርሻ አግኝቷል የሚሉት  በሃሳብ የበላይነት ተሸንፈው የወጡት ናቸው፡፡
“ሠማያዊ” ፓርቲን የመሠረቱት ሰዎችም ዛሬ ጀግና ሊባሉ በፊት እንዲህ ተብለው ነበር፡፡ እዚህ ፓርቲ ውስጥ ሲታገሉ ለእስር የተዳረጉት እነ ሃብታሙ አያሌውም ታስረው እንኳ አያምኗቸውም ነበር…ከነዚህ ሰዎች ጋር ነው እንዴ የኖርነው፡፡
እናንተ የታሠሩትን የአንድነት አባሎችና አመራሮች ትጠይቃላችሁ?
አዎ፤ እኔ አልቻልኩም እንጂ የኛ ልጆች ሄደው ይጠይቃሉ፡፡
የታሠሩት የፓርቲው አመራሮች ለእርሶ ድጋፍ እንዳላቸው አረጋግጠዋል?
እነሱ በህግ ጥላ ስር ስለሆኑ በዚህ ፓርቲ ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ ለማወቅ ያስቸግራል። የነሱን ፍላጐት ለመረዳት ግን አልሞከርንም፡፡ እኔ እንደምረዳው… “አንድነት” የታገሉለት ፓርቲ እንደመሆኑ… ከሱ ውጪ ሌላ አተያይ አላቸው የሚል እምነት የለኝም፡፡ እኛ የምናስበው፤ የኛ አርአያና የትግል ጽናት ተምሣሌዎች መሆናቸውን ነው፡፡ ትግላችንም እንዲፈቱ ነው፡፡

Read 3677 times