Print this page
Saturday, 06 June 2015 13:57

የአቶ ሙሼ ትንታኔ - በዘንድሮ ምርጫና በምርጫ ሥርዓቱ ዙሪያ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(10 votes)

  አቶ ሙሼ ሰሙ የኢትዮጵያውያን ዲሞክራቲክ ፓርቲ (ኢዴፓ) መስራች ሲሆኑ የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊና የፓርቲው ዋና ጸሐፊ በመሆን አገልግለዋል። በመጨረሻም ለ3 ዓመታት ፓርቲውን በፕሬዚዳንትነት የመሩ ሲሆን በአሁን ሰዓት ከኢዴፓም ሆነ ከማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት አባልነት ራሳቸውን አግልለዋል። ለረዥም ዓመታት  ባካበቱት ፖለቲካዊ እውቀትና ልምድ በተለያዩ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ትንታኔ የሚሰጡት አቶ ሙሼ፤ በቅርቡ በተካሄደው 5ኛ ሃገር አቀፍ ምርጫ ላይ ትኩረት በማድረግ፣በአጠቃላይ በምርጫ ስርዓቱ ዙሪያ እንዲሁም ፖለቲካዊ እንቅስቃሴውን በተመለከተ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ተከታዩን ቃለምልልስ አድርገዋል፡፡

    በዘንድሮ ምርጫ እስካሁን ባለው ውጤት ገዥው ፓርቲ ሙሉ ለሙሉ ማሸነፉ ታውቋል፡፡ የምርጫውን ሂደትና ውጤት እንዴት አዩት?
በፊት የማጭበርበሩ ነገር ቴክኒካል ነበር - ኮሮጆ የመስረቅ፣ ቆጠራ ላይ የማጭበርበር ወዘተ--- አሁን ግን ነገሩ የስነልቦና ጨዋታ ሆኗል፡፡ እርግጥ ነው አሁንም በአንዳንድ የምርጫ ወረዳዎች ላይ ከቦርዱ አሠራር ውጪ ከ1ሺህ በላይ መራጮች ድምጽ የሠጡበት ሁኔታ እንዳለ ሪፖርቶችና መረጃዎች እያመለከቱ ነው፡፡ ይሄ ማለት ከመራጩ ህዝብ ቁጥር በላይ ካርድ ተሠራጭቷል ማለት ነው፡፡ በኔ እምነት ግን ምርጫው ኢህአዴግ በሚፈልገው ቅርፅና መልክ እንዲጠናቀቅ ያደረገው ከምርጫው እለት ጋር በተያያዙ ሁኔታዎች አይመስለኝም፤ ቀድሞ በተሠራ ስራ ነው፡፡ ኢህአዴግ ካለፉት 3 አመታት ወዲህ በማህበረሰቡ ውስጥ እየተብሰለሰሉ፣ እያደጉ የመጡ በርካታ ጥያቄዎች እንዳሉ በቅጡ የገመገመ ይመስለኛል፡፡ እነዚህን ጥያቄዎች ደግሞ ኢህአዴግ በሚፈለገው ፍጥነት እየመለሳቸው እንዳልሆነ ይረዳዋል፡፡
ኢህአዴግ ሠራኋቸው የሚላቸው ነገሮች፣ በማህበረሰቡ ህይወት ላይ ቀጥተኛ ለውጥ ያመጡ አይመስለኝም፡፡ ያ ለምን ሆነ? ከተባለ፣ እየተፈጠሩ ያሉ የስራ እድሎች ቋሚ ሳይሆኑ ጊዜያዊ መሆናቸው አንዱ ነው፡፡ ኮብልስቶን፣ የኮንስትራክሽን ስራ የመሳሰሉት ወቅታዊ ስራ ናቸው፡፡ በዓለም አቀፉ የሥራ ድርጅት (ILO) “ስራ” ተብለው አለማቀፍ እውቅና የተሠጣቸው አይደሉም፡፡ በርካታ ወጣቶች ከዩኒቨርሲቲ እየተመረቁ ነው:: እነዚህ ወጣቶች ስራ አለማግኘታቸው በማህበረሰቡ ዘንድ ብዙ ጥያቄ እያስነሳ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከሃገራዊ የሃብት ክፍፍል አኳያ ማህበረሰቡ ጥያቄ አለው፡፡ ጥቂት ሃብታሞች ብዙ ድሆች እየፈጠረ ያለ ስርአት ነው። ለዚህ ደግሞ የሙስና ሚና ከፍተኛ ነው ብለው የሚያምኑ ዜጐች አሉ፡፡
በተለያዩ ክልሎች የሚፈጠሩ ግጭቶችን መነሻ በማድረግ፣ “ኢትዮጵያ ህልውናዋን ጠብቃ ትቀጥል ይሆን?” የሚለው ስጋት በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ለምሣሌ የአማራ ተወላጆች ከተለያዩ ክልሎች መፈናቀል የመሳሰሉት እንደ ኢትዮጵያዊ ለመኖርና ተዘዋውሮ ለመስራት ያለውን የመብት ጥያቄ ሲያስነሳ ቆይቷል፡፡ አገሪቱ በከባድ (ስታግፍሌሽን) ውስጥ ነው ያለችው፡፡ ኢኮኖሚው አንድ ቅርቃር ውስጥ ነው ያለው፤ ግሽበቱም አለ፡፡ እነዚህ በህብረተሰቡ ውስጥ ያሉ ችግሮችና ጥያቄዎቹ በኢህአዴግ ግምገማ የተለዩ ይመስለኛል፡፡ እናም እነዚህ ችግሮች ኢህአዴግን ስጋት ውስጥ ሳይከቱት አልቀሩም፡፡ ስለዚህ ምርጫ በኮሮጆ ማጭበርበር የሚቻልበት ሁኔታ ከሌለ፣ ማህበረሰቡን በፍርሃት ውስጥ ማስቀመጥ እንደ አማራጭ ስትራቴጂ የተወሰደ ይመስለኛል፡፡
ለዚህም መጀመሪያ መሠረታዊ የህዝብ ጥያቄን አንግበው አንገታቸውን ቀና ቀና ያደረጉ ሰዎችን ከማህበረሰቡ የመነጠል ስራ ነው የተሠራው፡፡ የታሠሩ ሰዎች አሉ፡፡ እነዚያ ሰዎች በማህበረሰቡ ውስጥ የጐመሩ ናቸው፡፡ እነሱን አስሮ ሌላ አንገቱን ቀና ያደረገን ሰው እንዲያጐነብስ ለማስገደድ ነው ጥረት የተደረገው፡፡ ወደ ምርጫው እየተቃረብን ስንመጣ ደግሞ ያለማቋረጥ የፖለቲካ ስራ ተሠርቷል። “መጪው ምርጫ ሠላማዊና ዲሞክራሲያዊ ሆኖ ሊጠናቀቅ ይችላል” ማለት ሲገባ፣ “ምርጫን ተከትሎ የሚፈጠርን ችግር ሁሉ እቋቋመዋለሁ” ብሎ መናገር ምን ማለት እንደሆነ የቅኔ ሊቅ መሆንን አይጠይቅም፡፡ እንደ መንግስት ለህዝብ በራስ መተማመንን ነበር መፍጠር የሚገባው፡፡ ችግር ሊከሰት ይችላል፣ ከተከሰተ እቋቋመዋለሁ ማለቱ፣ ብጥብጥ ሊነሳ ይችላል፤ ያንን አከሽፈዋለሁ ማለት ነው። ፖሊስ፤ ደህንነት፣ መከላከያ የሚደራጀው እኮ ቅድመ መከላከል ለማድረግ ነው እንጂ ችግር ሲፈጠር ጠብቆ በጥይት ለመመለስ አይደለም፡፡ ይሄ በማህበረሰቡ ስነልቦና ውስጥ የፈጠረው ነገር ቀላል አይደለም፡፡ ችግር ሊፈጠር ይችላል የሚል ስነልቦናዊ ተፅዕኖ በማህበረሰቡ ውስጥ ስላደገ፣ ከምርጫው በፊት አንዳንድ ሰዎች ስንቅም መሰነቅ ጀምረው ነበር፡፡
ሶስተኛ፤ ኢህአዴግ ማዕከላዊነቱን የጠበቀውን አሠራሩን በማላላቱ፣ እያንዳንዱ እጩ ተወዳዳሪ በራሱ መንግስት ሆኖ ነበር፡፡ ማዕከላዊነት ስለሌለ እያንዳንዱ ተወዳዳሪ የመንግስት መዋቅርን የመጠቀም ጉልበትና አቅም ነበረው። አነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞችን፣ በተለያየ ምክንያት ወደ ወረዳ ጽ/ቤት የሚሄድ ተገልጋይን እንደ ሠራዊት አሰልፎ ነው ለምርጫው ቅስቀሳ ያደረገው። መንግስት ትልቁ ጃንጥላ ውስጥ ሆኖ የሚሠራው አለ፤ እንደገና ደግሞ እያንዳንዱ ካድሬ የሚፈለገው ውጤት እንዲመጣ የተጠቀመው አቅም ቀላል አልነበረም፡፡ ቤት ለቤት እየተዞረ፣ መቼና እንዴት መምረጥ እንዳለበት እየተነገረው ነው ብዙ ሰው የመረጠው፡፡ ይሄ የሚያሳየው ምርጫው በአጠቃላይ “ማሽን ፖለቲክስ” መሆኑን ነው - ልክ እንደ ፋብሪካ በሚፈለገው የቁጥር መጠን ማምረት ነው የተጀመረው። እያንዳንዱ የኢህአዴግ ተወዳዳሪ በምርጫው ውጤት ካላገኘ፣ ምን እንደሚከተለው ስለሚያውቅ በዚያም በዚህም ብሎ ውጤት የሚያመጣበት ስሌት ውስጥ እንዲገባ ነው የተገደደው፡፡ ይሄ ምርጫውን የምርጫነት ባህሪ አሳጥቶታል፡፡ በድርጅት፣ኢህአዴግ የተንቀሳቀሰው ብቻ ሣይሆን፣ በግለሰብ ደረጃ በተናጥል የተንቀሳቀሰው ራሱ የምርጫውን ገጽታ ለውጦታል ብዬ ነው የማስበው።
ሌላው ወጣቱ ማህበረሰብ ውስጥ ያደረው ፍርሃት ደግሞ የተለየ መልክ አለው፡፡ በ97 የቀመሰው ገፈት አለ። በወቅቱ በጉዳዩ ላይ ተሣትፎ ይኑረውም አይኑረውም የቀመሰው ገፈት ቀላል አይደለም፡፡ አዲስ አበባ ላይ ብቻ እስከ 30 ሺህ ወጣቶች ታስረው ነበር፡፡ ይሄ የፈጠረው ፍርሃትና ስጋት አሁንም አለ፡፡ “የግጭቱ የመጀመሪያ ሠለባ እኔ ነኝ የምሆነው፤ ስለዚህ ኢህአዴግን መርጬ አርፌ እቀመጣለሁ” የሚል አስተሳሰብ ነው የሠረፀበት። ብዙ ወጣቶች አነጋግሬ የተረዳሁት ይሄንን ነው። ወጣቱ የደህንነት ስሜት ስለሌለው ኢህአዴግን መርጦ በሠላም መቀመጥን ነው የመረጠው፡፡ ከዚህ አንፃር “ኢህአዴግ ኮሮጆ ሠርቋል” የሚለው አይደለም ይበልጥ የሚታየኝ፤ የሰውን ስነልቦና አስቀድሞ በዚህ መልኩ ሠርቋል የሚል ሃሳብ ነው ያለኝ። ሰው ከሚያምንበት አማራጭ እና ከሚደርስበት ጉዳት የተሻለውን እንዲመርጥ ነው የተደረገው። በፍርሀት ድባብ ውስጥ ስለሆነ መራጩ እራሱን እንዲጭበረብር ነው የተደረገው፡፡
 በምርጫው በርካታ ፓርቲዎች ተወዳድረዋል ቢባልም የቀረበው አማራጭ ግን “አሁን ያለውን ስርአት በሠላም ማስቀጠል ወይም ደግሞ በምርጫው ውጤት ሳቢያ የሚመጣውን ሁሉ ለመቀበል መዘጋጀት” የሚል አማራጭ ነው ለህብረተሰቡ የቀረበለት፡፡ ይህ ማለት ወይ ጦርነትን ወይ ሰላምን ምረጥ ማለት ነው፡፡ በዚህ መልኩ ነበር ቅስቀሳ የተደረገው፤ ስለዚህ ሰው ሠላምን መርጧል። ምርጫውም በሠላም እንዲጠናቀቅ የሆነው በዚህ ምክንያት ነው፡፡
የምርጫ ሂደቱ ተሻሽሏል ማለት ይቻላል?
የኢትዮጵያ የምርጫ ሂደት ተሻሽሏል ወይ ካልከ፣ አዎ በአንድ ነገር ተሻሽሏል፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ የአንድ ፓርቲን አመራር በማረጋገጥ ብዙ ርቀት ሄዷል፡፡ ከዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እና አማራጭ ሃሳቦችን አቅርቦ ከመደመጥ አንፃር ከታየ ግን በየጊዜው ውድቀቱ እየባሰበት ነው የመጣው፡፡ ከመድብለ ፓርቲ ስርአት ወደ አውራ ፓርቲ ስርአት፣ አሁን ደግሞ ወደ አንድ ፓርቲ ስርአት በመግባት ረገድ ተሳክቶለታል፡፡
የምርጫ ቦርድ የማስፈፀም ብቃትስ ?
ነጋዴ በሌለበት ሀገር ውስጥ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርን ማቋቋም ትርጉም የለውም፡፡ ምርጫ ቦርድ የተቋቋመበት አላማ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የመድብለ ፓርቲ ስርአትን እውን ለማድረግ እንዲሁም የመድብለ ፓርቲ ስርአቱ ሚዛናዊና ቀጣይነት ያለው መሆኑን ለማረጋገጥ ነው፡፡ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ እንደምናየው---ቦርዱ የማይከሰስ ጥያቄ የማይነሣበት፣ የማይተች ተቋም ከሆነ ግን የገለልተኝነት ሚናው ትርጉም ያጣብኛል። የተቋቋመበት መሠረት ይናዳል፡፡ ተቃዋሚዎች ትርጉም ባለው ሁኔታ መኖር ሲችሉ ነው የምርጫ ቦርድ አስፈላጊነቱ፡፡ ምርጫ የሚካሄደው በአንድ ፓርቲ እና በአጋሮቹ መካከል አይደለም፡፡ በተቃዋሚ እና በገዥው ፓርቲ ወይም እርስ በእርስ በተቃዋሚዎች መካከል ነው። የተቃዋሚዎች ትርጉም ባለው ሁኔታ አለመጠንከር የምርጫ ቦርድ መዘባበቻ ሊሆን አይገባም፡፡ ባለቤቱ ማን ሆነና ነው የሚዘባበተው? ችግሩ ምንድን ነው ብሎ መፈተሽ፣ የመፍትሔ አቅጣጫ ማስያዝ፣ የመድብለ ፓርቲ ስርአት እንዴት ይጐለብታል? አሁን ያለው ውጥንቅጥ በምን ይፈታል? የሚለውን መነሻ አድርጐ፣ ሲምፖዚየሞችና ውይይቶች ማዘጋጀት የቦርዱ ሃላፊነት ነው፤ እንጂ ደካማ ናቸው ብሎ ሊዘባበት የሚገባው ተቋም አይደለም፡፡ ገዥው ፓርቲ ፍፁም የበላይ ከሆነ፣ ተቃዋሚዎቹ ያለባቸውን ችግር ፈተው ወደ ተፎካካሪነት እንዲመጡ መንገዱን ማመቻቸት የቦርዱ ሃላፊነት ነው፡፡
“ውጤቱ ምንም ይሁን ምን ምርጫውን ኮሽ ሳይል አሣክቼ ጨርሻለሁ” ብሎ ሊቀመጥ አይችልም። የምርጫውን ሂደት በጊዜ ቀመሩ መሠረት አጠናቆ ሊሆን ይችላል፤ ግን ያ የተሠራው ነገር መስፈርቶች ወጥቶለት ሊመዘን ይገባል፡፡ ምርጫው የመድብለ ፓርቲ ስርአትን አረጋግጧል? ሃሳብ በበቂ ሁኔታ ተሠራጭቷል? ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በዘንድሮ ምርጫ ምንም ወንበር ማግኘት ያልቻሉት ለምንድን ነው? ተብሎ ሊጠየቅ ይገባል፡፡ “ምርጫው በሠላም አልቋል” የሚለው ብቸኛ የስኬት መስፈርት ተደርጐ ሊወሰድ አይገባም፤ በተለይ ለምርጫ ቦርድ፡፡ ተቃዋሚዎች የቤት ስራቸውን መስራት እንዳለባቸው እረዳለሁ፤ ነገር ግን “ለመስራት የሚያስችለን ሁኔታ የለም” የሚል ቅሬታ ሲያሰሙ፣  “የምትናገሩት ሁሉ ውሸት ነው” ከሚል መልስ መነሳት በራሱ ጤናማ አይደለም፡፡ ቢያንስ 20 እና 30 በመቶ ድጋፍ ያገኙትን ፓርቲዎች የመረጠውን ህዝብም መናቅ ነው የሚመስለኝ፡፡ ይሄ ህዝብ እምነት ያሳደረባቸውን ፓርቲዎች ጥያቄ፣ በጨለምተኝነት ውሸት ነው ማለት፣ የደገፋቸውንና የመረጣቸውን ማህበረሰብ መናቅ ነው፡፡ ጥያቄው የፓርቲዎቹ ብቻ ሳይሆን የመረጣቸው ህዝብም ጥያቄ መሆኑን መገንዘብ ያሻል፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠር ማህበረሰብን ጥያቄ እንደ ጥያቄ አለመቀበል፣ ምርጫ ቦርድ ራሱን እንዲፈትሽ የሚያስገድደው ይመስለኛል፡፡
ፓርቲዎች፤ ፖሊሲያቸውን እንዳያቀርቡ የክርክርና የምረጡኝ ቅስቀሳ አየር ሰአት ማነስ ፈታኝ እንደሆነባቸው በተደጋጋሚ ገልፀዋል፡፡ በዚህ ላይ የእርስዎ ሃሳብ ምንድነው?
በምርጫው ክርክር ወቅት የአየር ሰአት ሰፋ ቢል፤ አወያዮች ከተለያየ የሙያ መስክ ቢሆኑ፣ ክርክሩ የቀጥታ ስርጭት ቢሆን … ኖሮ እጅግ የተሻለ ነበር፡፡ እንዲያም ሆኖ ኢህአዴግ ከተቃዋሚዎች ይበልጥ እሮሮና ብሶት ያሰማበት ክርክር ነው፡፡ ከኢህአዴግ ሲቀርብ ከነበረው እሮሮና ውጭ ምንም የረባ ሃሳብ ያልቀረበበት መድረክ ነው፡፡
ከኢህአዴግ የቀረበው ሃሳብ፣ አሁን ኢኮኖሚው እንዴት ከቅርቃር ውስጥ ወጥቶ መጓዝ ይቻላል፤የመለሠ አልነበረም፡፡ ከዚህ በኋላ እንዴት ቋሚ ስራዎች ለዜጐች ይፈጠራሉ የሚለው አልጠቆመም፡፡ አሁን ያለው የፓርቲዎች ችግር የሚፈታበት፣ ጠንካራ የሙያ ማህበራትና ተቋማት እንዴት ይፈጠሩ የሚለውን የመለሰ አልነበረም፡፡ ዝም ብሎ እሮሮ ብቻ የተደመጠበት ነው፡፡
በተቃዋሚዎች በኩል ድሮም የሃሳብ እጥረት አለ። የአሁኑ ደግሞ ከ97 አንፃር የባሰ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ህዝቡ ተቃዋሚዎችን ሲመርጥ፣ ቁጣው አሸንፎ ወጥቶ ነው እንጂ ባቀረቡት የመከራከሪያ ሃሳቦች መሠረት መንግስት ሆነው ሃገር ይመሩልኛል፤ ያስተዳድሩኛል ብሎ አይመስለኝም፡፡ ህዝቡ ከባድ የሆነ ቁጣና ቁጭት በውስጡ አለ፡፡ እከሌን ለምን መረጥክ ሲባል፣ “በቃ ማንም ይሁን ማን አያገባኝም፤ ኢህአዴግን አለመምረጤን ብቻ ነው የማውቀው” ይላል፡፡ ይሄ ማለት ህዝብ አማራጭን አይቶ ለመምረጥ እድል አላገኘም ማለት ነው፡፡ አሳዛኙ ግን ኢህአዴግ ተቃዋሚዎችን የሃሳብ ድሃ ናችሁ ብሎ ለክርክር ሲመጣ፣ የራሱ ሃሳብ በእሮሮ ተጀምሮ በእሮሮ የተጠናቀቀ መሆኑ ነው፡፡ ተቃዋሚዎችን በማውገዝ ነው ጊዜውን የፈጀው፡፡
ኢህአዴግ አምስቱንም አመት ሚዲያውን ተጠቅሞ እየሠራ፣ እንደገና በድልድሉም የበለጠውን ጊዜ መውሰዱ አስገራሚ ነው፡፡ ፓርቲዎች ለክርክር ሲቀርቡ ፈተና እየተፈተኑ ነው፡፡ ለተፈታኝ ደግሞ እኩል ሰዓት ነው የሚሠጠው፡፡ ለክርክር እኩል ሰአት አለመሰጠቱ የፈተናውን ሚዛናዊነት ያሳጣዋል፡፡ እኔ የአየር ሠአት ድልድል በእጩ ቁጥር መደረጉ ያስገርመኛል፡፡ ለገንዘብ ክፍፍሉ እሺ ይሁን… ለሚዲያ ግን እንዴት? ሃሳብ እኮ ነው የምታንሸራሽረው፡፡ ለኢህአዴግ የበለጠ ሰአት ተሰጥቶት፣ ለሌሎቹ ትንሽ ሰአት ሲሰጥ እንዴት ነው ሚዛናዊ የሚሆነው? ይሄ የሚያሳየው የመንግስት ቁርጠኝነት ያለመኖርን ነው፡፡ በቴሌቪዥን አዞና አሣማ በኢንስትሩመንት ሙዚቃ ታጅበው ከሚቀርቡበት ሰአት ላይ ቀንሰው ለፓርቲዎች እድል መስጠት እየተቻለ፣ ትርጉም በሌለው ጉዳይ ላይ ጊዜን ማጥፋት ያሳዝናል። ኢህአዴግ በስልጣን ላይ የቆየበት ጊዜና የሠራው ስራ ስለማይጣጣምለት፣ ሁልጊዜ እድል እንዲሠጠው የሚፈልግ ነው የሚመስለኝ፡፡ በተደጋጋሚ የሚሠጠው እድል ግን የትም እንደማያደርሰው ማወቅ አልቻለም። ሰው እድሜ የተሠጠው በገደብ ነው፡፡ ኢህአዴግም በተሠጠው እድሜ መስራት ካልቻለ መታገስ አያሻም፡፡ መስራት ከቻለ ደግሞ ሠርቶ ማሳየት ነው ያለበት፡፡
 ቦርዱ ምርጫን በገለልተኝነት የማስፈፀም አቅም አለው ብለው ያምናሉ?
የቦርዱ አደረጃጀት ነው ችግሩ ወይንስ ህጐቹና ደንቦቹ? የሚለው ተለይቶ መታየት አለበት፡፡ እኔ ከግለሰቦች ጋር ጉዳይ የለኝም፡፡ ቦርዱን የሚመሩት የተማሩ ሰዎች ናቸው፤ በደንብ ያውቃሉ፡፡ አቅም የሚባለውም ነገር አቅምን መገንባት ይቻላል፡፡ ትልቁ ችግር ግን ቁርጠኝነቱ ነው፡፡ ፍላጐቱ አለ ወይ ነው?  ቁርጠኝነቱ ካለ ባለው ህግ መስራት ይቻላል። ከዚህ በፊትም በ97 ተሠርቷል፡፡ እንደኔ ዋናው ጥያቄ የቁርጠኝነት ጉዳይ ነው፡፡
የምርጫው አለማቀፍ ትኩረት ማጣትስ ምክንያቱ ምን ይመስልዎታል?
ኢትዮጵያ ከአፍሪካ በህዝብ ብዛት 2ኛ ሀገር ስትሆን፣ የአፍሪካ መቀመጫ ነች፡፡ እነዚህና ሌሎች ጉዳዮች ኢትዮጵያን በተለየ አይን እንድትታይ የማድረግ አቅም አለው፡፡ እኔ ምርጫውን ነጮቹ እንዲታዘቡልን ፈልጌ ሳይሆን ትኩረት ያለማግኘቱ ጉዳይ ግን አሳሳቢ ነው፡፡ እውነቱን ለመናገር ምርጫ ለመታዘብ የሚመጡት ነጮች የሚታዘቡት ትንሽ ነው፡፡ ከጠቅላላው የምርጫ ጣቢያ ብዛት አንፃር ሲታይ ማለቴ ነው፡፡ መንግስት የመለወጥ ጫና ይዘው አይመጡም፡፡ እኔም እንደተቃዋሚ መንግስት በውጭ ሃይል እንዲለወጥ የምፈቅድ አይደለሁም፡፡ ቁምነገሩ ነጮቹ መጡም አልመጡም ማንም ከህዝብ ፍርድ አያመልጥም፡፡ “ምርጫው ተጭበርብሯል” የሚለውን እነሱ አይደሉም ለኔ የሚያረጋግጡት፤ መራጩ ህዝብ የሚሰጠኝ መረጃ በቂዬ ነው፡፡
ከጊዜ ወደ ጊዜ ተቃዋሚዎች የፓርላማ ወንበር ማጣታቸው የመድብለ ፓርቲ ስርአቱን አደጋ ውስጥ እንደሚከተው … ሠላማዊ ታጋዮችንም ተስፋ እንደሚያስቆርጥ የሚናገሩ ወገኖች አሉ፡፡ የእርስዎ ሃሳብስ?
ፓርቲዎች በተግባር ተስፋ ያጡት ዛሬ አይደለም - በ97 ነው፡፡ አንድ ሰው ፓርላማ በመግባቱ ተስፋ ነበራቸው ማለት አይደለም፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች ሃሳባቸውን ለህዝብ የሚያደርሱበት አማራጭ ከሌላቸው እኮ አሉ ለማለት ይከብዳል፡፡ በሀገር ግንባታ ላይ ምንድን ነው አስተዋጽኦ የሚያደርጉት? የህዝብ ብሶትን ለህዝብ የሚያደርሱበት እድል ከሌላቸው፣ አማራጭ ሃሳቦቻቸውን ለገበያ ማቅረብ ካልቻሉ… አሉ ማለት እንዴት ይቻላል፡፡ ኢህአዴግ “ታሪክ ሠሪ ነኝ” ማለት ይወዳል፡፡ ተቃዋሚዎችን አቀጭጮ ልማትን ከግብ አደርሳለሁ ብሎ አስቦ ከሆነ ትልቅ ስህተት ነው፡፡ ምክንያቱም ፓርቲዎቹ የወጡት ከማህበረሰቡ ነው፡፡ ኢህአዴግ ፓርቲዎቹን ባቀጨጫቸው ቁጥር ጉልበት አገኛለሁ ካለ ስህተት ነው፡፡ የበለጠ የተቆጡ ተስፋ የቆረጡና በሀገራቸው ደስተኛ ያልሆኑ ዜጐችን ነው የሚፈጥረው፡፡ ምክንያቱም መንግስት የሁሉንም ዜጐች ፍላጐት ማሟላትና ማስደሰት አይችልም፡፡ ብዙ ውስብስብ ችግር ባለበት ሃገር ውስጥ አማራጭ ሃሳብ እንደሌለ አድርጐ ማሰብ የሚያስቅ ነገር ነው የሚሆነው፡፡
በኛ ሀገር የሚደረገው ምርጫ ከጊዜ ወደ ጊዜ ትርጉም አጥቷል የሚሉ ወገኖች  አሉ… የእርሶ አቋም ምንድን ነው?
አዎ ምርጫ ትርጉም አጥቷል፡፡ ምርጫ ትርጉም የሚኖረው በሂደቱ ብቻ ሳይሆን በውጤቱም ነው። ውጤቱም ሂደቱም ተስፋ ያለው ሲሆን ነው ትርጉም የሚኖረው፡፡ ምርጫ ትርጉም አጥቷል ከሚለው ይልቅ የምርጫ ስርአቱ የመቀልበስ አደጋ ላይ ነው የሚለው ይበልጥ ገላጭ ነው፡፡ እንዳይቀለበስ ትግሉ ተጠናክሮ መጓዝ አለበት፡፡ ተቃዋሚዎች አመራራቸውንና ከማህበረሰቡ ጋር ያላቸውን ግንኙነት በቅጡ መገምገም አለባቸው፡፡ ከመንግሥት ጋርም መቀራረብ አለባቸው፡፡ መለወጥ ያለበት እንዲለወጥ ቀርበው ሊታገሉ ይገባል፡፡ አለበለዚያ ምርጫው በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ፣ ትርጉም ያጣና የአንድን ስርአት መቀጠል ማረጋገጫ ብቻ ሆኖ ይቀራል፡፡
ቀጣዩ  ፓርላማ ምን አይነት ገፅታ ይኖረዋል ብለው ያስባሉ?
እኔ ከኢህአዴግ ማዕከላዊ ምክር ቤት የሚለይ አይመስለኝም፡፡ ሁለተኛ ምክር ቤት ለምን እንደሚያስፈልጋቸው አልገባኝም፡፡ ኢህአዴግ ምክር ቤት የተወሰነ ጉዳይ አምጥቶ ማስወሰን ነው፡፡ ይሄን ሃሳብ ለምን እዚያው የፓርቲ ምክር ቤታቸው ውስጥ አይሰሩትም የሚል ሃሳብ ይመጣብኛል፡፡ በማዕከላዊ ም/ቤት የወሰኑት ወደ ፓርላማ መጥቶ ህዝባዊ ቀለም ለመስጠት ብቻ ነው የሚሰራው፡፡ ሌላው ችግር ደግሞ ገዢው ፓርቲ ብቻውን ሲሆን  ብዙ ነገሮችን  ከህዝብ ሊደብቅ ይችላል፡፡ ተቃዋሚ መኖሩ ሚስጥር ከጀርባ እንዳይቀር ያደርጋል፡፡ እንደኔ እንደኔ የስራ መደራረብና የተቋም ብዜት ከምንፈጥር እዚያው ማዕከላዊ ምክር ቤት ቢያልቅና ማስፈፀሙ ላይ ትኩረት ቢሰጠው እላለሁ፡፡
የግል ፕሬሱ መዳከም፣ የፓርላማው በአንድ ፓርቲ ብቻ መያዝ --- የብዝ ሃሳብ መንሸራሸርን አደጋ ውስጥ ይከተዋል የሚሉ ወገኖችም አሉ፡፡  እርሶ በዚህ ላይ ምንድነው አቋምዎ?
እኔ ከምንም በላይ የሚያሰጋኝ እሱ ነው፡፡ የምንም ነገር መሰረት ሃሳብ ነው፡፡ ልማት ብንል ሌላውም የሃሳብ ውጤት ነው፡፡ ሃሳቦች በቀጨጩ ቁጥር አንድ ሃገር የሚሄድበት መንገድ አስጊ ነው የሚሆነው። አንዳንዴ ኢህአዴግ ምንድን ነው የሚፈልገው ብዬ ራሴን እጠይቃለሁ፡፡ በተለይ ደግሞ ለምንድን ነው ሆደ ሰፊነት የሌለው? ለምሳሌ ጋዜጠኞችን ለምን ያስራል? እነዚህ ዜጎች የገዛ አገራቸውን ለማፍረስ ታጥቀው የተነሱ ናቸው ለማለት እቸገራለሁ፡፡ አብዛኛው ጋዜጠኛ በገባው መንገድ፣ ሃገሪቱ ወደ ተሻለ ደረጃ እንድትመጣ የራሱን ሃሳብ ነው የሚያቀርበው፡፡ ኢህአዴግም በረሃ እያለ “ሀገር አጥፊ ነው” ተብሎ ነበር፡፡ ጋዜጠኛው ግን መሳሪያ ሳይዝ በሃሳብ የሚታገል ብቻ እንደመሆኑ፣ ለምንድን ነው እነሱም በሃሳብ የማይታገሉት? በስርጭታቸው ትንሽ የሆኑ ጋዜጠኞችና ጋዜጠኞችን እንዴት በሃሳብ መታገል ያቅተዋል? እንደውም ይሄን ቢያደርግ ፅናቱን ያሳይ ነበር። እነዚህን የሃሳብ መንሸራሸሪያ መድረኮች በዘጋ ቁጥር ኢህአዴግ በህዝቡ ላይ እምነት አይኖረውም። ህዝቡ እኮ ህፃን አይደለም፤ እሳት እና ውሃውን ለይቶና መዝኖ፣ ለምን አማራጩን እንዲወስድ ለራሱ አይተውለትም?
ስለ ወደፊቱ ምርጫችን ምን ይሁን?
በኢትዮጵያ ውስጥ የዲሞክራሲ ስርአቱ ወደ ኋላ  እንዳይቀለበስ የሚታገሉ አሉ፡፡ ወደ ኋላ እንዲጎተት፤ ባለበት እንዲቀርም የሚፈልጉ አሉ፡፡ አንዳንዴ ዲሞክራሲ ገፅታው እንደ ዘመናዊ ምንጣፍ ለስላሳ አይደለም፤አባጣ ጎርባጣ አለው፡፡
ይሄን አቋርጦ ለመጓዝ፣ ችግሮችን ተጋፍጦ ለማለፍ ሲፈራ፣ ያን ጊዜ ወደ አምባገነንነት ነው የሚሄደው። ሃሳብ በሃሳብ እንዲሸነፍ የማይፈቅድ ከሆነ፣ በጥቂት የህግ እርማት ብቻ በሚያስፈልጋቸው ሃይሎች ምክንያት የብዝሃኑን አስተሳሰብ የሚጨፈልቅ ከሆነ ትክክል አይሆንም፡፡ አንድ ነገር እናስታውስ፡- ደርግ፤ ኢህአፓና አስተሳሰቡን ለማጥፋት ብዙ ህይወት ቀጥፏል፡፡ ሰዎቹን አጥፍቷል፤ የኢህአፓን አስተሳሰብ እና አላማ ግን አላጠፋም፡፡ ሰውን በመግደል ወይም በፍርሃት ውስጥ በማቆየት ሃሳብ አይጠፋም፤ ይዳፈን ይሆናል፤ጊዜውን ጠብቆ ይመጣል፡፡ እኔ አሁንም የምለው--- ለሃሳብ ቦታ ይሰጠው፤ ሃሳብ በሃሳብ ብቻ ይሸነፍ፡፡ ከጥላቻ ፖለቲካ እንውጣና የሃሳብን የበላይነት ለማረጋገጥ እንስራ ነው የምለው፡፡

Read 4522 times