Saturday, 30 May 2015 12:53

እቀጥን ብዬ ብሔድ … ወፍሬ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(17 votes)

 

 

 

ውፍረትን ለመቀነስ በሚል ሰበብ በርካቶች የጂም ቤቶችን ማዘውተራቸው አዲስ ክስተት አይደለም፡፡ ሸንቀጥ ያለ ሰውነት እንዲኖራቸው፣ ሰውነታቸውን እንደልባቸው ለማዘዝና ከተለያዩ ውፍረት አመጣሽ በሽታዎች ራሳቸውን ለመጠበቅ በሚል በሚያዘወትሯቸው ጂም ቤቶች አንዳንድ ጊዜ ኢላማቸውን ስተው ለክብደት መጨመር የተዳረጉ ሰዎች ጥቂት አይደሉም፡፡

 ብዙ ጊዜ ከሰው የምትቀላቀልባቸውን አጋጣሚዎች አትወዳቸውም፡፡ የሰርግና ሌሎች ግብዣዎች ጥሪ ባይመጡላት ደስታዋ ነው፡፡ እንዲህ ያሉ አጋጣሚዎች ውፍረቷን ክፉኛ እንድትጣላው ያደርጋታል፡፡

በውድ ዋጋ የተገዙ በርካታ ልብሶቿ ቁምሳጥኗን ያጨናነቁት ሲሆን ልብሶቿ እየጠበቧት፣ ክብደቷ በየጊዜው እየጨመረ መሄዱን ትናገራለች፡፡ “ምን አባቴ ላድርገው?” ትላለች፤ ሰውነቷን ዘወትር በመስታወት በተመለከተች ቁጥር፡፡

ከዓመታት በፊት ሁለተኛ ልጇን ወልዳ ስትነሳ ነበር ክብደቷ መጨመር የጀመረው፡፡ ከአራስ ቤት ስትወጣ ከቀድሞ ክብደቷ 12 ኪሎ ያህል ጨምራ ነበር፡፡ ይሄ ራሔልን እምብዛም አላስደነገጣትም ነበር፡፡ የአራስ ሰውነት ንፋስ ሲነካው ይቀንሳል በሚባለው ልማዳዊ አባባል እምነት ነበራት፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ቀድሞ ክብደቷ እንደምትመለስ እርግጠኛ ነበረች፡፡ ሆኖም ክብደቷ ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ፣ ውፍረቷ ለዓይን እያስጠላ መጣ፡፡ ችግሩ ሳይባባስ ጂም መግባት እንዳለባት ወሰነች፡፡ በወር 1240 ብር እንድትከፍል በተጠየቀችበት ጂምናዚየም ውስጥም ስፖርታዊ እንቅስቃሴዋን ጀመረች፡፡ በሣምንት አራት ቀን ጠዋት ጠዋት ለሁለት ሰዓታት ያህል ላቧ በጆሮ ግንዷ እስኪንቆረቆር፣ ድካም ልቧን እስኪያፈርሰው የምትሰራው ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ግን የፈለገችውን ለውጥ አላመጣም፡፡ በእርግጥ ሰውነቷን እንደ ልቧ ለማዘዝ አስችሏታል፡፡ ስፖርቱ የምግብ ፍላጎቷን የበለጠ ስለከፈተላት በየጊዜው እየጨመረ ከሚሄደው ክብደቷ አልታደጋትም፡፡ ጓደኞቹም “ያንቺ ውፍረት በጂም እምቢ ብሏል፤ እስኪ ደግሞ በጅብ አስሞክሪው፡፡” በማለት ያሾፉባት ጀመር፡፡ ሰውነታቸው ቀጠን ካሉ ጓደኞቿ ጋር መንገድ ላይ ስትሄድ ተላካፊ ወንዶች “እንትና… ከእሷ ላይ ተልጠሸ ነው? ልጣጯ ነሽ?” ይሏታል፤ አብራት የምትደድዋን ጓደኛዋን እያመለከቱ፡፡ ቀልዱ እሬት እሬት ቢላትም ፈገግ ትላለች - ላለመሸነፍ፡፡

ጂም ሲሰሩ ቆይቶ ማቆም ክብደትን የበለጠ ይጨምራል ሲባል መስማቷ ጂሙን እንዳታቆም አደረጋት፡፡ “ግን ምንድነው የሚሻለኝ?” የሚለው ጭንቀቷም አልቆመም፡፡ ከስፖርታዊ እንቅስቃሴ ስትወጣ ምግብ መብላት እንደሌለባት አንዳንድ ጓደኞቿ ቢነግሯትም ይህን ማድረግ ግን አልቻለችም ሁልጊዜም ከስፖርት በኋላ አንጀቷ በረሃብ ይንሰፈሰፋል፡፡

ከቤት አላደርስ የሚላትን የረሃብ ስሜት ለማስታገስ ጂም ቤቱ አጠገብ ካለው ሬስቶራንት በርገር በቀዝቃዛ እርጎ መብላትን ልማድ አድርጋዋለች፡፡ ይህ ልማዷ ለውፍረቷ ምክንያት መሆኑ ቢነገራትም አምና ለመቀበል ተቸግራለች። “ሊሆን አይችልም፤ ቢገባም የሚቃጠል እኮ ነው” ትላለች፡፡ ላለፉት ሶስት ዓመታት እያፈረሰች የምትገነባው ሰውነቷ ፤በየጊዜው እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አለመሄዱ አሁን ተስፋ አስቆርጧታል፡፡

በሆቴል ዲአፍሪክ ሰሞኑን ያገኘኋት ይህች ራሄል፤ ክብደቷ 89 ኪሎ መድረሱንና ጂም ከመጀመሯ በፊት 76 ኪሎ እንደነበረች አጫውታኛለች፡፡ በጂም ቆይታዋ ያተረፈችው 13 ኪሎ ኢላማውን በሳተ መንገድ የተገኘ እንደሆነም ነግራኛለች፡፡

አላስፈላጊ ክብደትን ለማስወገድና ውፍረትን ለመቀነስ በሚል ሰበብ በርካቶች የጂም ቤቶችን ማዘውተራቸው አዲስ ክስተት አይደለም፡፡ ሸንቀጥ ያለ ሰውነት እንዲኖራቸው፣ ሰውነታቸውን እንደልባቸው ለማዘዝና ከተለያዩ ውፍረት አመጣሽ በሽታዎች ራሳቸውን ለመጠበቅ በሚል በሚያዘወትሯቸው ጂም ቤቶች አንዳንድ ጊዜ ኢላማቸውን ስተው ለክብደት መጨመር የተዳረጉ ሰዎች ጥቂት አይደሉም፡፡ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚነገረው ክብደትን ለመቀነስ ውጤታማ አለመሆኑ ለብዙዎች አሳሳቢ ጉዳይ እየሆነ መጥቷል፡፡

የሥነ ምግብ ባለሙያው አቶ ተረፈ እውነቱ ይህንኑ ጉዳይ አስመልክተው ሲናገሩ፤ “ስፖርታዊ እንቅስቃሴ በሰውነታችን ውስጥ የተጠራቀመውን ካሎሪ በማቃጠል፣ ሰውነታችን ውፍረትን እንዲቀንስ ማድረጉ የማይካድ ጉዳይ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ብዙ ጊዜ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች የመራብ ስሜትን በከፍተኛ ሁኔታ በመፍጠር ብዙ እንድንመገብና ክብደታችን እንዲጨምር ያደርጋሉ፡፡ ስፖርታዊ እንቅስቃሴን ስንሰራ በአንጎላችን የጡንቻዎች መቆጣጠሪያ ማዕከል የሥጋ ክምችቶች ይቀንሳሉ፤ ይሄኔ ከአንጎላችን የመራብ ስሜትን የሚገልፅ መልዕክት ይላክልናል፡፡ እናም ብዙ እንመገባለን፡፡ በዚህ ምክንያትም ክብደታችን እየጨመረ ይሄዳል” ብለዋል፡፡

ከባድ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን የሚያደርጉ ሰዎች የመብላት ፍላጎታቸው እየጨመረ እንደሚሄድና ይህም ለአላስፈላጊ የክብደት መጨመር እንደሚዳርጋቸው ባለሙያው ይናገራሉ። ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ከዳይት ጋር ካልታገዘ በስተቀር ክብደትን ለመቀነስ እንደማይረዳ የጠቆሙት ባለሙያው፤ ይልቁንም የረሃብ ስሜትን በከፍተኛ ሁኔታ በመፍጠር ብዙ እንድንመገብ ያደርገናል ብለዋል፡፡

በአገራችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተስፋፉት ጂምናዚየሞች ውስጥም የዚህ ዓይነቱን ቅሬታና እሮሮ መስማት የተለመደ ሆኗል፡፡ “ውፍረት ለመቀነስ ገብቼ በሁለት ወራት አራት ኪሎ ጨመርኩ”፣ “ክብደቴን እቀንሳለሁ ብዬ ገብቼ በየጊዜው እየጨመርኩ ሄድኩ” - የሚሉ እሮሮዎች በዝተዋል፡፡ በዓለም ሲኒማ፣ በላፍቶ ሞል፣ በሆቴል ዲአፍሪክና በደሳለኝ ሆቴል ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ አግኝቼ ያነጋገርኳቸው ደንበኞች፤ ጂም መስራታቸው ክብደት ከመጨመር አላዳናቸውም። ሆኖም ሰውነታቸውን እንደልብ ለማንቀሳቀስ አስችሏቸዋል፡፡

በከተማችን ከሚገኙት ታላላቅ ሆቴሎች በአንዱ ለደንበኞች የስፖርታዊ እንቅሰቃሴ ስልጠና በመስጠት ሥራ ላይ የተሰማራው እስከዳር አድማሱ እንደሚናገረው፤ ወደ ሆቴላቸው ለስፖርታዊ እንቅስቃሴ ከሚመጡት ደንበኞች አብዛኛዎቹ ዓላማቸው ክብደታቸውን መቀነስ አሊያም ከክብደት ጋር ተያይዘው የሚመጡ የጤና ችግሮች እንዳይከሰቱ መከላከል ነው፡፡ ይሁን እንጂ ይህንን ዓላማቸውን የሚያሳኩና ክብደታቸውን በመቀነስ ተያያዥ የጤና ችግሮችን ለማስወገድ የቻሉት በጣት የሚቆጠሩት ብቻ ናቸው፡፡ አብዛኛዎቹ ክብደታቸው በየጊዜው እየጨመረ በመሄዱ ምክንያት ይማረራሉ። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ከስፖርት እንቅስቃሴ በኋላ ውፍረት አምጪ የሆኑ ምግቦችን (እንደ ቅባትና ስኳርነት ያላቸው ምግቦችን) አብዝተው መመገባቸው ነው ብሏል ባለሙያው፡፡ 

“ታይም” መፅሔት በቅርቡ ባወጣው ዘገባ፤ ጂምን ከአመጋገባችን ጋር እየተቆጣጠርን ካልተገበርነው ለከፍተኛ ውፍረት እንደሚዳርግና አብዛኛዎቹ የጂም አዘውታሪዎች ውፍረት እየጨመሩ ለመሄዳቸው ዋንኛ ምክንያቱም አመጋገባቸው እንደሆነ ገልጿል። ሰዎች በተፈጥሮአቸው ሁለት ዓይነት የቅባት ቅንጣቶች እንዳሏቸው የጠቆመው ዘገባው፤ ከእነዚህ ነጭና ቡኒ የቅባት ቅንጣቶች ውስጥ ለሰውነት ክብደት መጨመር ተጠያቂ የሚሆነው ነጩ ቅንጣት እንደሆነና ቡኒው የቅባት ቅንጣት ሰውነታችን ከፍተኛ ኃይል ለማምረት የሚያስችለው ማይቶ አንድሪያን በማለዘብ፣ ለውፍረት የሚያጋልጡ የቅባት ለውጦች እንዳይኖሩ እንደሚያደርግ ጠቁሟል፡፡

ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ካደረጉ በኋላ ብዙ ውሃ መጠጣት የረሃብ ስሜቱን ለማስታገስ በእጅጉ እንደሚረዳ የጠቆመው ዘገባው፤ ቅባት ነክ የሆኑ ምግቦችን አለመወሰድ እንደሚገባም አመልክቷል። የጂም አዘውታሪዎች ከስፖርታዊ እንቅስቃሴው በበለጠ በአመጋገባቸው ላይ ጥንቃቄ ካላደረጉ እንደተመኙት ክብደት መቀነሳቸው ቀርቶ በየጊዜው እየጨመሩ እንደሚሄዱ ዘገባው ይጠቁማል፡፡

 

 

 

 

 

Read 16938 times