Saturday, 30 May 2015 12:20

ታዳሚዎች ልዩ የፋሽን ሃሳብ በላፍቶ ሞል ያቀርባሉ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

ዛሬ ምሽት በአገራችን ያልተለመደ ልዩ የፋሽን ሐሳብ (አይዲያ) ብሥራተ ገብርኤል በሚገኘው ላፍቶ ሞል በታዳሚዎች እንደሚቀርብ ተገለፀ፡፡

ሁሉም ሰው የራሱ የአለባበስ ፋሽን ስላለው ፋሽን የሚለው ቃል ሁልጊዜ በሞዴሎች ብቻ መገለጽ የለበትም ያሉት የካይሙ ኢትዮጵያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ተስፋ ገ/አብ፤ የዝግጅቱ ዓላማ የጋበዝናቸው እንግዶች ደስ የሚላቸውንና የራሳቸውን ፋሽን ይዘው መጥተው ፍላጎታቸውን ነፃ ሆነው እንዲናገሩ ነው ብለዋል፡፡

አቶ ተስፋ ትናንት በጽ/ቤታቸው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ አንዲት ሴት በአገራችን ባህል እብድ ናት እንዴ? በሚያሰኝ የሚያስገርምና የሚያስቅ ሁኔታ፣ “እኔ በጣም አጭርና ጥብቅ ያለ ሚኒስከርት መልበስ በጣም ያስደስተኛል” የሚል ሀሳብ ብታቀርብ መብቷ እንደሆነ ገልጸው፣ የተለያዩ ሰዎች ከእሷ የባሰ አስገራሚ የፋሽን ሐሳብ ሊያቀርቡ እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡ ካይሙ ኢትዮጵያ፣ በቅርቡ ማንኛውንም ቁሳቁስ (የፋሽን አልባሳት፣ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች፣ መጻሕፍት፣ ምግብና መጠጦች፣ የስፖርት፣ የቤትና የቢሮ ዕቃዎች ወዘተ) በኢንተርኔት በተመጣጣኝ ዋጋ የሚሸጥና ደንበኛው የገዛውን ዕቃ በአድራሻው የሚያስረክብ ድርጅት መሆኑን የጠቀሱት ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ፤ የዝግጅቱ ሌላው ዓላማ ካይሙን ከፋሽን ጋር በማያያዝ ማስተዋወቅ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ከምሽቱ 3፡00 እስከ ሌሊቱ 7፡00 የሚቆየውን የፋሽን አይዲያ (ሃሳብ) ፕሮግራም ያዘጋጁት ካይሙ ኢትዮጵያ ከኢጋኖፍ ቮድካ ጋር በመተባበር ሲሆን፣ በዝግጅቱ የተለያየ ጣዕም ያላቸው ቮድካና ሌሎች መጠጦች እንደሚቀርቡ፣ 4 ዲጄዎች (ሁለት ከውጭ፣ ሁለት ከአገር ውስጥ) ሙዚቃዎቻቸውን በማቅረብ ታዳሚውን እንደሚያዝናኑ፣ በዲዛይን ሥራቸው ታዋቂ የሆኑት አና ጌታሁን፣ አቡጊዳና አዶት ዲዛይነሮች፣ የሠሩትን አልባሳት ሞዴሎችን በማልበስ እንደሚያቀርቡና የዕለቱ ዝግጅት በኤፍ.ኤም 97.1 “ራዲዮ ሄሎ ሌዲስ” በተባለ ፕሮግራም ከ6-7 ሰዓት እንደሚተላለፍ አቶ ተስፋ ገ/አብ አስታውቀዋል፡፡

 

Read 1012 times