Saturday, 30 May 2015 12:27

የድርብ ሃሳብ (Double think) አደጋ!

Written by  ሌሊሣ ግርማ
Rate this item
(5 votes)

 

 

 

 

ላለማሰብ እያሰብኩኝ

በጨለማ ተቀመጥኩ

የልቤን ሆደ ባሻነት ገሰፅኩኝ

ተስፋ መቁረጥን ተስፋ አደረኩኝ፡፡

    ይኼንን “የወሌፈንድ” ፍልስፍና ቁልጭ አድርጐ የሚያሳይ ግጥም የፃፈው ታላቁ ባለቅኔ ደበበ ሰይፉ ነው፡፡ “ተስፋ መቁረጥን ተስፋ ስለማድረግ” ለመረዳት ቀጥተኛ አስተሳሰብን መጠቀም አያገለግልም፡፡

ግጥሙ የዘመኔን መንፈስ ገላጭ ነው፡፡

ጆርጅ ኦርዌል በዓብይ ስራው “1984” ላይ ይኼንን የአስተሳሰብ መንገድ “Double think” ሲል ይገልፀዋል፡፡ ሁለት ጊዜ ስለ አንድ ነገር ማሰብ ማለት ነው፡፡ ግን ሁለት ጊዜ የታሰበው ነገር ሁለት ሊታረቁ የማይችሉ ተቃርኖዎችን ወደ በአንድ አጣምሮ ለማሰብ ቢያስችልም፤ ግን የእውነትን ማንነት ከውሸት ጋር ቀይጦ ሁለቱንም ወጥ ነገሮች የሚያጠፋም ነው፡፡

ደርቦ ማሰብ (double think) እንደዚህ ይገልፀዋል ኦርዌል፡- “To know and not to know, to be conscious of complete truthfulness while telling carefully constructed lies, to hold simultaneous two opinions which canceled out, knowing them to be contradictory and believing in both of them, to forget whatever it was necessary to forget…” እያለ ይቀጥላል፡፡

ይኼንን ፅንፍ ተቃርኖን የማቀላቀያ የአስተሳሰብ መንገድ (Double think) ለማስተናገድ የሰው ተፈጥሮ በጣም አመቺ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ውሸትን ከእውነት ጋር አቻችሎ የማሰብ ብቃት አለን፡፡ አጣምሮ የሚያስበው ግን ሁለቱንም ነጣጥሎ ትክክለኛ ባህሪያቸውን ለመረዳት ሲል ማጣመር እና የማጣመር አባዜ ስለተጠናወተው  ብቻ መሆን ትልቅ ልዩነት ይፈጥራል፡፡

በአጭሩ፤ “ተስፋ ማድረግ” መልካም መሆኑን አውቆ፤ ተስፋ መቁረጥን ለመቀነስ “ሁለቴ የሚያስብ” ከሆነ ይህ እውነተኛው አማራጭ መሆኑን መቀበል እናም ተግበር አንዱ (በእኔ እምነት ትክክለኛው አማራጭ) ነው፡፡ ላለማሰብ ማሰብን መርጦ… ተስፋ መቁረጥን ተስፋ ማድረግ ደግሞ ሌላው ነው፡፡

ከጀርመን እንዲያሊዝም በተለይም ከሄግል ያገኘነው አንዱ መጥፎ ነገር (እንደኔ እምነት)…የማይጣመሩ ነገሮችን የማጣመር ፍላጐትን ነው፡፡ ሄግል - Thesis (አዎንታዊ) ከUntithesis (አሉታዊ) ጋር ሲደመር አዎንታዊ እና አሉታዊውን ወደፊት የሚያሳድግ አዲስ የድብልቅ አማራጭ ይገኛል ባይ ነው፡፡ ይሄንኑ የሄግል ፅንሰ ሐሳብ (አይዲያሊዝሙን ወደጐን ትተው) የተጠቀሙበት የግራ ዘመም ርዕዮት ያላቸው ሃይሎች ናቸው፡፡

የማርክስ ዲያሌክቲካዊ ማቴሪያሊዝም… ከሄግል ዲያሌክቲካዊ አይዲያሊዝም የተወሰደ ነው፡፡

አዎንታዊ (ለምሳሌ እውነት፣ ተስፋ፣ ማወቅ፣ ማሰብ፣ ብርሃን) ከአሉታዊው ጋር ሲቀየጥ “ወሌፈንድ” ይፈጠራል፡፡ “ላለማሰብ ማሰብ” ፣ “ተስፋ መቁረጥን ተስፋ ማድረግ”… “Double think” የዚህ ውጤት ነው፡፡

ለምሳሌ በሀገራችን “አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች” የሚባሉ የጐሳ አየነቶች አሉ፡፡ በኦርዌላዊ “ጥምዝ ሃሳብ” የተካኑ ስለመሆናቸው አንዳችም ጥርጣሬ የለኝም፡፡ የሚሰጡት አስተያየት ውሸትም፣ እውነትም እንደሆነ በአንድ ቅፅበት አውቀው ነው በቴሌቪዥን ለመናገር የሚቀርቡት፡፡ በእውነተኛ ቁርጠኝነት ውሸትን ለመግለጽ ወይንም በእውነት እውነትን ለመቅበር ሃሳባቸውን አለማምደውታል፡፡

የሚናገሩት ነገር ውሸት እንደሆነም… እውነት ስለመሆኑም አውቀው ነው የሚናገሩት፡፡ እውነት እና ውሸትን ቀላቅሎ ማሰብ የተማረ አዕምሮ የተማረውን ቀላቅሎ መናገር መቻሉ አያጠያይቅም፡፡

“Double think” በውስጥ የሚዳብር የአስተሳሰብ መንገድ “Double Speak” ደግሞ በውጭ የሚቀርብ መገለጫው ነው፡፡ ሳይንሳዊ መንገድን በመጠቀም እውነትን መግለጽ፣ ሳይንሳዊ እውነታን መፍጠር ቀደም ብሎ ሲያስችል ቆይቷል፡፡ ሳይንሳዊ መንገድን በመጠቀም መዋሸት ግን ሳይንሳዊ እውነታን በሳይንሳዊ ውሸት አደናግሮ ለማሳመን ፍቱን መድሃኒት ነው፡፡

እውነትና ውሸትን በእኩል (በእኩይ) መንገድ መቀላቀል መቻል የሰውን አእምሮ ለማደንዘዝ በጣም አቋራጩ መንገድ ነው፡፡

ምሳሌ ልስጥ፤ “የሰው ልጅ በምንም አይነት በሌላ የሰው ልጅ መገደል የለበትም” የሚል ጽንሰ ሃሳብ በስነምግባር ፍልስፍናም ሆነ በሃይማኖት አስተሳሰብ ድጋፍ ሊኖረው ይችላል፡፡ እውነት ተብሎም ተቀባይነት አግኝቷል እንበል፡፡

“የሰው ልጅን ለመግደል የሚያሴሩ ስላሉ ለብዙሀኑ የሰው ልጅ ሲባል ጥቂቶቹ መገደል ይኖርባቸዋል” ከተባለ… አሁንም ብዙ ድጋፍ እና ጭብጨባ ይገኛል፡፡

አዎንታዊው ሃሳብ ከአሉታዊው ጋር በመቀላቀሉ የሰው ልጅን የሚጠብቅ እና የሚገድል አዲስ ሃይል ይፈጠራል፡፡ ይኸም ሀይል ባለስልጣን ሆኖ በመጠበቅ ስም የመግደል ሃላፊነትን በህጋዊ ቢሮ መልክ ይረከባል፡፡

ዣን ጃክ ሩሶ ከዘመናዊ የፖለቲካ ፈላስፎች መንገድ ጠራጊ አድርገው ምዕራባዊያን ይቆጥሩታል፡፡  በብዙሀን አንደበት ውስጥ በቀላሉ Popular የሆነ አባባል አለው፡፡ ምናልባት አባባሉ በመጽሐፉ (The social contract) የመጀመሪያው ገጽ ላይ በመገኘቱ ምክንያት ሊሆን ይችላል በቀላሉ የታወሰለት…

ለማንኛውም “Man is born free but every where in chains” ይላል፡፡ የሰው ተገቢ የማንነት ስፍራ ነፃነት ቢሆንም ያለ አግባብ በጭቆና ተጠፍሮ ዘወትር ይገኛል ማለቱ ነው፡፡ ሁለቱን ተቃራኒዎች አዎንታዊውን (ነፃነት) ከአሉታዊው (ባርነት) ጋር ቀላቅሎ ቢገልፃቸውም… ሁለቱን የቀላቀላቸው አትክክል የሆነውን ካልሆነው አንፃር አንጥሮ ለማውጣት እንጂ የማይደባለቁትን ሰይጣን እና መልአክ አጋብቶ ለማስማማት አይደለም፡፡

ተቃራኒዎችን አነፃፅሮ ማሰብ የሰው ልጅ ተፈጥሮ ነው፡፡ ነጭ እና ጥቁርን ደምሮ እና ቀንሶ …በስተመጨረሻ ለያይቶ ፍቻቸውን ተረድቶ መግለጽ ጤናማ ተፈጥሯችን ነው፡፡ ጥበባችን፣ ፈጠራዎችን፣ ሳይንሳችን፣ የአስተውሎታችን መነሻ እና መድረሻ በዚህ ሂደት ውስጥ ያለ ነው፡፡

የሄግል ዲያሌክቲክስ እና የኦርዌል “Double think” ግን ከዚህ የተፈጥሮ ህጋችን ያፈነገጠ ነው፡፡ ጥቁር እና ነጭን ደባልቆ… ግራጫ ከጥቁር እና ከነጭ የበለጠ መሆኑን የሚናገር ነው፡፡ ማለትም “ተስፋ መቁረጥን ተስፋ ማድረግ” በተናጠል ማንነት ከነበራቸው “ተስፋ ማድረግ” እና “ተስፋ መቁረጥ” የበለጠ ነው እንደማለት፡፡

(ወይንም በሰሞኑ ሁኔታ ደግሞ በእርግጥ ከተገኘ ለውጥ ይበልጥ በእርግጥ የተገኘ የሚመስል የለውጥ ማስረጃ እድገት ነው እንደማለት ነው፡፡)

“Double think” በጥበብ አለም (በፈጠራ አለም) ስኬት ነው፡፡ በጣም እውነት የሚመስል ውሸትን መስራት የደራሲው ስኬት ነው፡፡ ገሃዱ አለምን ቁልጭ አድርጐ የሚያሳይ ነገር ግን በገሀዱ ተከስቶ የማያውቅ ፈጠራ “ውሸት ነው” ተብሎ ተአማኒነት አያጣም፡፡ ምክንያቱም፤ ጥበብ እውነትን የሚያጐላ ውሸት ነውና፡፡ እንዲያውም “መስታወቴ” ብሎ ተደራሲ የራሱን ውሸት በራሱ ጓዳ ከእውነቱ ጋር እያመሳከረ ህፀፁን እንዲያርም ያግዘዋል፡፡ (ወይንስ በጥበብ አማካኝነት የገሃድ አለምን ህመምን ማረም ወይንም መፈወስ የቻለ እስካሁን አንድም ከያኒ የለም? አከራካሪ ነጥብ ነው)

ያም ሆነ ይህ ጥበበኛው የራሱን ሃሳብ እና የገፀባህሪውን ሃሳብ ደብሎ መናገር እና ማሰብ ይችላል፡፡ ችግር የሚመጣው ከጥበብ ዘርፍ ውጭ ያሉት የገሃዱ አለም ግንኙነቶችም በዚሁ የጥበብ ውሃ ልክ በመሰለ ወለፈንድነት መመራት (መተግበር) ሲጀምሩ ነው፡፡

የትያትር መድረክ ላይ ትያትረኛው አንድን ገፀ ባህርይ ወክሎ ያስባል፤ ይናገራል፡፡ ከመድረክ ሲወርድ ግን እንደ እውነተኛ ማንነቱ ማሰብ እና መናገር መቻል አለበት፡፡ ጥበበኛው በፈጠራ ወቅት “Double think” ሲያደርግ ከሰውኛ የገሃድ ስነምግባሩ ጋር መጋጨትም የለበትም፡፡

ለመድረክ ላይ የሚጫወተውን ገፀ ባህርየ በገሀዱ አለም ላይም የሚደግም ሰው “የጥበብ ዲያሌክቲክስ” ፈጥሬአለሁ ካለ ችግር ነው፡፡ ልክ ድሮ የመድረክ ተዋናይ የነበረ ሰው በአጋጣሚ የአዕምሮ ጤናው ተቃውሶ በጐዳና ላይ ከወጣ እና ለብዙ አመታት ከተጐሳቆለ በኋላም “ፕርፎርመንስ አርት እየሰራ ነው” ብለው እንደተናገሩት ማለቴ ነው፡፡ እውነት እና ውሸት… ምክንያታዊነት እና እብደት የሚጣመሩበት ጊዜ እና የሚለያዩበት ወቅት ካልታወቀ ወለፈንድነት ለሙሉ ጊዜ በእውነታው አለም ላይ የማያቋርጥ ተውኔት ለማካሄድ ለባብሶ መድረክ ላይ ወጥቷል ማለት ነው፡፡ መድረኩ ደግሞ ትያትር ቤት ሳይሆን እለት ተለት ህይወት ትሆናለች፡፡

“Double think” የሚለውን የኦርዌል ሃሳብ ከሄግላዊ ማታፊዚክስ ጋር አንድ መሰረት አለው እያልኩ ነው፡፡ መሰረቱ ደግሞ ለአንባገነን ስርዓቶች እና ከብዙዎች ላብ አትርፈው ለተደላደሉት ጥቅም ይሰጣል ባይ ነኝ፡፡

በተጨማሪ የጥንቱ ካፒታሊዝም እና የጥንቱ ኮሚውኒዝም በዚሁ መንገድ ነው ተቀላቅለው የቻይናን ቴክኖሎጂ የፈጠረችውን ምዕራብ እና የምዕራብን ገበየ የፈጠረችውን ቻይና ወለፈንድ አድርገው ማስማሙት፡፡

“አለም ትያትር ናት ትያትር ደግሞ አለም”

ከትያትሩ የሚያተርፈው ተዋናዩ አይደለም ትያትር ቤቱ እንጂ፡፡ ሁሉም ትያትር ቤቶች የመንግስት ናቸው፡፡ በሁሉም ትያትር ቤት ተመርቀው የሚከፈቱ ፊልሞችን ህዝብ ራሱ ተውኖ ራሱ ይመለከታል፡፡ ራሱ ተውኖ ራሱ የተመለከተውን ራሱ ይከፍላል፡፡ የሚከፍለው በገንዘቡ ብቻ ሳይሆን በህይወቱም በቀጣይ የተስፋ ጭላንጭሉም ጭምር ነው፡፡ተዋናይ ነኝ ወይንስ ተመልካች?ደራሲ ነኝ ወይንስ ተደራሲ፣ ድራማው ተጠናቋል ወይንስ መጀመሩ ነው (ለሃያ አራት አመት መጀመሪያው ምዕራፍ ፈቅ የማይል ድርሰትም የወለፈንድ የድራማ ዘውግ ነው) ጭብጡ ጨለምተኛ ነበር ወይንስ ብርሃናማ? “አንዳንድ የአ.አ ከተማ ነዋሪዎች እነማን ናቸው? እኔ እና ማን ናቸው? “Man is born free but every where in chains በሚለው የሩሶ ሃሳብ እና በመሀመድ ስልማን “Man is borne in China but is found every where” በሚለው ሽሙጥ መሃል ምንም ለውጥ ይጠፋል፡፡

ግራ እና ቀኝ ሃሳቦች፣ እውነት እና ውሸት ተደባልቀው አንድ ይሆናሉ፡፡ እግዜር (Malevolent)፣ ሰይጣን (benevolent) በዴያሌክቲካዊ መንገድ ግራጫ ይሆናሉ፡፡ ግራጫ “Ambivalent” ነው፡፡ ላለማሰብ እንደማሰብ ነው ግራጫ ወይንም ስለሞት ሲባል መናር፡፡

የግራ ዘመም እና የቀኝ ዘመም ድብልቅ ወደየትም አይዘምም፡፡ ቢዘምም የዝመቱን አቅጣጫ የሚያነፃፅርበት… የማይለዋወጥ ቋሚ መለኪያ አይኖረውም፡፡ እርስ በራስ የሚጠፋፋ ሁለት ተቃራኒ ሃሳቦች አጋጭቶ እያስማማ… ሲስማማ እየጋጨ የድምር ዜሮ… የእውር ድንብር ጉዞ ማድረግ ብቻ ነው ውጤቱ፡፡

ገጣሚ ቢኒያም ዋሲሁን ግራና ቀኝ እጄ ተጣልተው ሲጋጩ “ጭብጨባ” ተብሎ ተተረጐመ እንዳለው… ግጭት ድጋፍ መስሎ ተቀባይነት ያገኛል፡፡

ይኼንን የወሌፈንድ አዝማሚያ “የሰው ልጅ ሞት” ብዬ ነው የምቆጥረው፡፡ ግን ወሌፈንድን ለመረዳትም የ “Double think”  አስተሳሰብን መከተል ያስፈልጋል፡፡

እየሞተ ያለው የሰው ልጆች አለም “እያደገ ነው” ሲባል ምን ማለት እንደሆነ በትክክል ለማወቅ… እውነት ከውሸት ጋር እንዴት ተቀይጦ በግራጫ ቀለም እንደፀደቀ መረዳት ግድ ይላል፡፡  

 

 

 

 

Read 1861 times