Saturday, 30 May 2015 12:18

በህንድ በተከሰተው ሃይለኛ ሙቀት የሞቱ ሰዎች ከ1ሺህ በላይ ደርሰዋል

Written by 
Rate this item
(4 votes)

 

 

 

        በ2003 በከፍተኛ ሙቀት ከ3ሺህ በላይ ሰዎች ሞተዋል

     በህንድ ሰሜናዊና ማዕከላዊ አካባቢዎች የተከሰተውን ያልተለመደ ሃይለኛ ሙቀት መቋቋም አቅቷቸው በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለሞት የተዳረጉ ሰዎች ቁጥር ከ1ሺህ በላይ መድረሱን ኢንተርናሽናል ቢዝነስ ታይምስ ዘገበ፡በያዝነው ሳምንት በተጠቀሱት አካባቢዎች የሙቀት መጠኑ እስከ 50 ዲግሪ ሴንቲግሬድ መድረሱን የጠቆመው ዘገባው፤ የአገሪቱ የሜቲዮሮሎጂ ባለስልጣንም የሙቀት መጠኑ መጨመር በታየባቸው የአገሪቱ ግዛቶች የከፋ ጥፋት ሊከሰት እንደሚችል ማስጠንቀቁን ገልጿል፡፡በአብዛኞቹ የህንድ ግዛቶች የሳምንቱ አማካይ የሙቀት መጠን 45 ዲግሪ ሴንቲግሬድ መድረሱ የተገለጸ ሲሆን፣ የሙቀት መጠኑ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር የሰዎችን ተፈጥሯዊ አደጋን የመከላከል የሰውነት ስርዓት እንደሚያዛባና ለድካምና ለሞት እንደሚዳርግ ሃኪሞች መናገራቸውን ዘገባው አብራርቷል፡፡

የአገሪቱ መንግስት ዜጎች በከፍተኛው ሙቀት እንዳይጠቁ ለመከላከል የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ ሲሆን፣ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የማቀዝቀዣ ውሃና ድርቀትን የመከላከያ ፈሳሾች እየተሰራጩ ነው ብሏል፡፡ ለሞት የተዳረጉት ሙሉ በሙሉ ለማለት በሚቻል መልኩ አረጋውያን እንደሆኑም ታውቋል፡፡ላልተለመደው የሙቀት መጨመር የተለያዩ ምክንያቶች እየተሰጡ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል ከፓኪስታን አቅጣጫ ወደ ህንድ የሚነፍሰው ሞቃት ንፋስ እንደሚገኝበት ዘገባው ጠቁሟል፡፡ህንድ በእነዚህ ወራት ሞቃት አየር እንደሚኖራት ቢታወቅም የዘንድሮው ሙቀት ግን ከተለመደው በ6 ዲግሪ ሴልሺየስ እንደሚበልጥ የዘገበው ኢንዲያን ኤክስፕረስ ጋዜጣ፣ አንድራ ፕራዴሽ በተባለችው የህንድ ግዛት ባለፈው እሁድ የተመዘገበው 48 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ሙቀት ባለፉት 68 አመታት በግዛቲቱ ታይቶ የማይታወቅ እንደሆነ ገልጿል፡፡

የህንድ የሳይንስ ኢንስቲቲዩት ጥናት እንደሚለው፤ ባለፉት 15 አመታት ከሙቀት መጨመር ጋር በቀጥታ በተያያዘ ሰበብ፤ በአገሪቱ በየአመቱ ለህልፈተ ህይወት የሚዳረጉ ሰዎች አማካይ ቁጥር 153 የነበረ ቢሆንም፣ በጊዜ ሂደት ግን ቁጥሩ እየጨመረ መጥቷል ተብሏል፡፡

ከአምስት አመታት በፊት አህመዳባድ በተባለው የህንድ አካባቢ የተከሰተውና 112 ዲግሪ ፋራናይት የተመዘገበው ከፍተኛ የሙቀት መጠን 1ሺህ 300 ሰዎችን ለህልፈተ ህይወት መዳረጉን ያስታወሰው ዋሽንግተን ፖስት በበኩሉ፣ እ.ኤ.አ በ2003 በአንድራ ፕራዴሽ ግዛት የተከሰተ ከፍተኛ ሙቀትም ከ3ሺህ በላይ ሰዎችን መግደሉን አክሎ ገልጿል፡፡

የሙቀት መጠኑ እስከ ወሩ መጨረሻ ይቀጥላል ተብሎ እንደሚጠበቅ የጠቆመው ዘገባው፣ የህንድ የሜቲዮሮሎጂ ባለስልጣን ሃላፊ ዴቬንድራ ሻርማም፤ ዜጎች ከቤታቸው እንዳይወጡና ብዙ ውሃ እንዲጠጡ ጥሪ ማቅረባቸውንና በሙቀት መጠኑ መጨመር የተነሳ በአገሪቱ ያለው አጠቃላይ እንቅስቃሴ መስተጓጐሉን ጠቁሟል፡፡

 

 

 

Read 2216 times