Saturday, 30 May 2015 12:16

ግማሹ የዓለም ህዝብ ዘንድሮ የኢንተርኔት ተጠቃሚ ይሆናል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 

 

 

      በ2000 የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች 400 ሚ. ብቻ ነበሩ

    የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አለማቀፉ የቴሌኮሙኒኬሽን ህብረት፤ ከዓለማችን ህዝብ ግማሽ ያህሉ እስከያዝነው የፈረንጆች 2015 አመት መጨረሻ የኢንተርኔት ተጠቃሚ ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅ ማስታወቁን ቢቢሲ ዘገበ፡ህብረቱ ባለፈው ማክሰኞ ባወጣው ሪፖርት እንዳለው፤ እስከ መጪው ታህሳስ ወር ድረስ በአለማችን የኢንተርኔት ተጠቃሚ የሆኑ ሰዎች አጠቃላይ ቁጥር 3.2 ቢሊዮን እንደሚደርስና ከዚህ ውስጥም 2 ቢሊዮን ያህሉ ያደጉ አገራት ዜጎች እንደሚሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

የሞባይል ብሮድባንድ አገልግሎት መስፋፋቱ በአብዛኞቹ የአለማችን አገራት የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር ለማደጉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል ያለው ሪፖርቱ፣ በአሁኑ ወቅት በኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ብዛት ቻይና፣ አሜሪካና ህንድ መሪነቱን ይዘው እንደሚገኙና በአመቱ መጨረሻ ግን ህንድ ሁለተኛ ትሆናለች ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጿል፡፡

የአለማችን ህዝብ የኢንተርኔት ተጠቃሚነት ባለፉት 15 አመታት ከ6.5 በመቶ ወደ 43 በመቶ ማደጉን ያመለከተው ሪፖርቱ፤ በቤታቸው የኢንተርኔት አቅርቦት ያላቸው ሰዎች ቁጥርም በ2005 ከነበረበት 18 በመቶ፣ ዘንድሮ 46 በመቶ ደርሷል ብሏል፡፡

እ.ኤ.አ በ2000 በአለማችን የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር 400 ሚሊዮን ብቻ እንደነበር ያስታወሰው ሪፖርቱ፣ በአሁኑ ወቅት የአለማችን 69 በመቶ የሚሆነው አካባቢ የ3ጂ ኢንተርኔት ተጠቃሚ መሆኑን ጠቁሞ፣ ይሄም ሆኖ ግን 29 በመቶ የሚሆኑ የገጠር አካባቢዎች ብቻ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጿል፡፡በሞባይል ብሮድባንድ ሽፋን ከአለማችን ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው አፍሪካ ስትሆን፣ በዘርፉ አህጉሪቱ ያላት ሽፋን 17.4 በመቶ ብቻ ነው ብሏል ሪፖርቱ፡፡

 

 

 

 

Read 1218 times