Saturday, 30 May 2015 12:04

ኢህአዴግ በተቃዋሚዎች “ባዶ ውጤት” አፍሯል ወይም ተፀፅቷል!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(22 votes)

 

 

 

ኢህአዴግ በተቃዋሚዎች “ባዶ ውጤት” አፍሯል ወይም ተፀፅቷል!

    የዘንድሮ 5ኛው አገራዊ ምርጫ በኢህአዴግ ጠቅላይ አሸናፊነት የተጠናቀቀ ይመስላል፡፡ (ቅድመ ትንበያ ተከልክሏል ለካ!) የእኔ ግን ቅድመ ትንበያ ሳይሆን መረጃ ላይ የተመሰረተ ድምዳሜ ነው፡፡ አያችሁ… ገና ያልተነገረ ውጤት ቢኖርም ተቃዋሚዎች ያሸንፋሉ ተብሎ የተጠበቁባቸው ቦታዎች በሙሉ ገዢው ፓርቲ ጠቅሎ ወስዷቸዋል - በምርጫ ቦርድ መረጃ መሰረት፡፡ (ተቃዋሚዎች ግን ተጭበርብሯል እያሉ ነው!) ኢህአዴግ በዚህ ምርጫ “ለተማሪ ዜሮና መቶ አይሰጥም” የሚለውን የት/ቤት ትውፊታዊ አባባል ተገዳድሯል፡፡ (ተቃዋሚ 0፤ ኢህአዴግ 100? ነው ያገኙት)

እንዲያም ሆኖ ግን ብዙዎቻችን እንደምናስበው ኢህአዴግ ባገኘው ውጤት እምብዛም የተደሰተ አይመስልም፡፡ ባደረኩት ምልከታዊ ጥናት (ሳይንሳዊ አይደለም!) ገዢው ፓርቲ በውጤቱ ወይ አፍሯል ወይ ተፀፅቷል፡፡ እናንተ ግን ከእስከዛሬው የአውራው ፓርቲ ባህርይ ተነስታችሁ በዚህ ድምዳሜዬ ላትስማሙ ትችላለሁ፡፡ ግን ምን መሰላችሁ? ሁሌ ልጅነት የለም፡፡ ኢህአዴግ አሁን ጎልምሷል፡፡  (የግማሽ ክ/ዘመን  የስልጣን ልምድ አለው እኮ!)

እናላችሁ … በምርጫው 100 ከመቶ ማግኘቱ፣ በኢኮኖሚ ዘርፍ ያስመዘገበው የባለ ሁለት አሃዝ ዕድገት ውጤት መሆኑን አሳምሮ ቢያውቅም በተቃዋሚዎች ያለ ውጤት መቅረት ተፀፅቷል ወይም አፍሯል፡፡ እንደዚያ ባይሆንማ በዝረራ (Landslide) አሸንፈሃል ሲባል እንዴት አይቀውጠውም?  (በፌሽታ ማለቴ ነው!) እሱ ግን አላደረገውም - ቢያንስ እስካሁን፡፡ የሚገርመው ምን መሰላችሁ? ገዢው ፓርቲ በውጤቱ መፀፀቱን ወይም ማፈሩን ተቃዋሚዎችም ራሳቸው ገና አላወቁም፡፡ “ምርጫው ተጭበርብሯል” እያሉ እየወነጀሉት ነው፡፡ ምርጫ ቦርድ ባለፈው ረቡዕ ውጤቱን ይፋ ሲያደርግ፣  የምርጫውን ድል በነጋታው ከግንቦት 20 ጋር ለማክበር ተመቸው ያሉም አልጠፉም ነበር፡፡   ግን ተሳስተዋል፡፡ እንኳን የምርጫው ድል፣ ግንቦት 20ም ራሱ እንደነገሩ ነው ያለፈው (ዝም ጭጭ ያለ በዓል ነበር!)

እንደወትሮው ቢሆን እኮ … EBC “የዘንድሮውን ግንቦት 20 ልዩ የሚያደርገው በምርጫው ማግስት በመዋሉ ነው” ሲለን ይከርም ነበር፡፡እናላችሁ …. እመኑኝ ኢህአዴግ በራሱ ውጤት ከተደሰተው በላይ በተቃዋሚዎች “ባዶ” መሆን አፍሯል ወይም ተፀፅቷል፡፡ ሳይናደድባቸውም አልቀረም፡፡ (ተቃዋሚ ባለበት አገር 100 በመቶ ማሸነፍ ተሰምቶ አይታወቅማ!) እነሰሜን ኮሪያና ሳዳም ሁሴን ነበሩ በዚህ ውጤት የሚታወቁት፡፡ አሁን ደግሞ ኢህአዴግ ሊሆን ነው፡፡ (በተቀሩት ቦታዎች ተቃዋሚዎች አንድ ሁለት መቀመጫ ቢያሸንፉ እኮ ይገላገል ነበር!) ግን ይሄውላችሁ… ተቃዋሚዎች ውጤት እንደሚያገኙ የሚያረጋግጥለት ቢያገኝ “ምርጫው ይደገም” ከማለት ሁሉ ወደኋላ የሚል አይመስለኝም!! (የምርጫ ቦርድ ምላሽ ባይታወቅም!) እርግጥ ነው ከምርጫው በፊት መረር ጠግነን ያለ (Aggressive) የምረጡኝ ቅስቀሳ አድርጓል፡፡ ያሰራቸው ቢል ቦርዶችና ፖስተሮች ብዛት፣ የቤት ለቤት ቅስቀሳው፣ የቡና ጠጡ ፕሮግራሙ፣ የEBC ዶክመንተሪ ፊልሞች… ከሁሉም በላይ ደግሞ የ1ለ5 ጥርነፋ ወዘተ … ኢህአዴግ በአገር ደረጃ ሳይሆን በአህጉር ደረጃ ለአፍሪካ የሚወዳደር ነበር ያስመሰለው፡፡ ፈርቶ ነበር ይላሉ - አንዳንዶች፡፡ (“አንዳንዴ ህዝብ አይታመንማ!”)

እንደሚመስለኝ ተቃዋሚዎች በቴሌቪዥን የፓርቲዎች ክርክር ላይ ትኩረት መሳባቸው ድንጋጤና ፍርሃት ሳይፈጥርበት አልቀረም፡፡ እናም አምርሮ ነበር፡፡ እልህ እንዳለበት ተማሪ ቀንና ሌሊት ምርጫው ላይ ቸክሎ አጠና፡፡ የማታ ማታ ኢህአዴግ - 100፤ ተቃዋሚዎች 0 ሆነ ውጤቱ! (አዲስ ሪከርድ እኮ ነው!) በመላው ዓለም እንኳንስ መቶ በመቶ … ከ50 በመቶ በላይ ማግኘት ብርቅ በሆነበት ዘመን ላይ እኮ ነው አውራው ፓርቲ ከ100 መቶ የደፈነው!! (በአሁኑ ወቅት በዓለም ብቸኛው ፓርቲ ሳይሆን አይቀርም!) እንዲህ ያለው ውጤት ደግሞ ከማሳጣትና ከአምባገነኖች ጐራ ከማሰለፍ ውጭ ምንም የሚፈይደው ነገር የለም፡፡ (መንግስት ለመሆን ይሄ ሁሉ ውጤት አያስፈልግም እኮ!!) እናም እመኑኝ … ኢህአዴግ የገዛ ራሱ ስኬት ሰለባ ሆኗል፡፡ (ማን ነበር “We are the victim of our own success” ያለው?)

ይኼውላችሁ … ምርጫ በመጣ ቁጥር እሱን ተከትሎ የሚከሰቱ ፖለቲካዊ ቀውሶችን ስመለከት፤ “ምርጫው ቢቀርብን ምን እናጣለን?” እያልኩ አበክሬ እቆዝማለሁ፡፡ (“ደፋር” እንዳትሉኝ!) የኒዮሊበራሊዝም አቀንቃኞቹ ሚዲያዎችና እነሂዩማን ራይትስዎች እንደሚሉት፤  9 የሚደርሱ ብሎገሮችና ጋዜጠኞች ወህኒ የወረዱት፣ 6 ገደማ መጽሔቶችና የሚዲያ ተቋማት የተከረቸሙት፣ 60 የሚደርሱ ጋዜጠኞች ከአገር የተሰደዱት እና ሌሎችም ውጥንቅጥጦች… ከፈረደበት ምርጫ ጋር ተያይዞ የመጣ ነው፡፡ (በምን ሂሳብ ይሄ ሁሉ አገራዊ ኪሳራ?)

የሚገርማችሁ ደግሞ በቅርቡ እንደተካሄደው የናይጄሪያ ምርጫ “ሰርፕራይዝ” ቢኖረው እንኳ ጥሩ ነበር፡፡ የጦቢያ ምርጫ ውጤት ግን ይታወቃል፡፡ እንኳን ተወላጆቹ የኒዮሊበራሊዝም አቀንቃኝ የሆኑት ሚዲያዎች ራሳቸው ገዢው ፓርቲ በዘንድሮ ምርጫ በዝረራ (Landside) እንደሚያሸንፍ የተናገሩት ከምርጫው በፊት ነው፡፡ ታዲያ የምን ልፋት ነው? በዚያ ላይ ለምርጫው የሚወጣው ወጪ ያሳዝናል (ብዙ ኮንዶሚኒየሞች አይሻሉንም!) ይሄ ብቻ አይደለም፡፡ ምርጫው ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ያለው ጭንቀት!

እናላችሁ … ምርጫው ቢቀርስ እላለሁ!! ለምን መሰላችሁ? ኢህአዴግ ዝም ብሎ ከሥልጣን አይወርድም፡፡ አምባገነን ሆኖ እኮ አይደለም፡፡ ልማታዊ ስለሆነ ነው፡፡ በቃ የጦቢያን ህዝብ ባለመካከለኛ ገቢ የማድረግ ህልም አለው፡፡ (ከድህነት ካልተላቀቅን አይለቀንም!) እናላችሁ… ይሄን ይሄን ሳስብ ሁሌም  “ምርጫው ቢቀርብን ምን እናጣለን?” እላለሁ፡፡ የዲሞክራሲና የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ጠላት ሆኜ እንዳይመስላችሁ፡፡ ከዲሞክራሲ በፊት ዳቦ፣ ከምርጫ በፊት ልማት ብዬ ነው፡፡ አያችሁ … የምንበላውን መምረጥ ስንጀምር የሚገዛንንም ልንመርጥ እንችላለን፡፡ ያኔ የ1ለ5 አደረጃጀት፣ ኮንዶሚኒየም ቤቶች፣ ጥቃቅንና አነስተኛ ወዘተ… በምርጫው ላይ ተፅዕኖ አያመጡም፡፡ (ባለመካከለኛ ገቢ ሆነናላ!)

በነገራችን ላይ መንግስት በ97 ምርጫ የአውሮፓ ታዛቢ ቡድን አባል በነበረችው አና ጐሜዝ የተነሳ ዓለምአቀፍ የምርጫ ታዛቢዎችን “ዓይናችሁን ለአፈር” ማለቱ ተገቢ አይደለም (ነገር አካበደ እኮ!) የአፍሪካ ህብረት ታዛቢ ቡድን ሰሞኑን ባወጣው የመጀመሪያ ሪፖርቱ ላይ፤ በየጣቢያው በርካታ የህዝብ ታዛቢዎችን መመልከቱን ጠቁሞ ለምርጫው ግልጽነት እንዲሁም በሂደቱ እምነት ለማሳደር የተለያዩ ዓለምአቀፍ ታዛቢዎች መገኘታቸው ወሳኝ ነገር መሆኑን ገልጿል፡፡ የአና ጐሜዝ ጦስ የአውሮፓ ህብረትን ብቻ አይደለም ፊት ያስነሳው፡፡ የአሜሪካ መንግስትም ዲፕሎማቶቹ ምርጫውን እንዳይታዘቡ መከልከላቸውን ሰሞኑን በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡

የጦቢያ መንግስት አጋር ምናምን አያውቅም እንዴ? (አቦ! ኢህአዴግ አንዳንዴ ያበዛዋል!) ግን እኮ ዓለም አቀፍ ታዛቢ ቡድን ቢኖር … ተቃዋሚዎች ምርጫ ተጭበረበረ፣ ኮሮጆ ተገለበጠ ወዘተ… ሲሉ…. ብቻ ተውት! የቅድሙ ሃሳቤ ይሻላል፡፡

ከምሬ ነው … ይሄ የምርጫ ነገር ቢቆየን ነው የሚሻለው፡፡ አንድያውን መካከለኛ ገቢ ላይ ስንደርስ ምርጫውን ብንጀምር ምን ይመስላችኋል? እስከዚያው ግን “ሁሉ ነገር ወደ ልማት!” የሚለውን መፈክር ጠበቅ ብናደርግ ይመረጣል፡፡

የሚገርማችሁ እኮ በአንድ በኩል ገዢው ፓርቲ፤ በዓለም አስገራሚ የሚባል የ100 ፐርሰንት ውጤት አግኝቶ ድሉን በአደባባይ ለማክበር እንኳ አልቻለም - በተቃዋሚዎች “ባዶ ውጤት” ተፀፅቶ፡፡

በሌላ በኩል ተቃዋሚዎች ውጤቱን አንቀበልም ብለዋል፡፡

ምርጫ ቦርድ ደግሞ “የተጭበረበረ ነገር የለም፤ መሰረተቢስ አሉባልታ ነው” ይላል፡፡ (ግን በምኔው መረመረው??) ቆይ አሁን እውነት ማን ጋ ናት? ለእውነታ ዋጋ የሚሰጥ ባህል ሳንፈጥር እንከን የለሽ ምርጫ ለማካሄድ መሞከር ከንቱ ነው፡፡ ከምሬ ነው… ምርጫው ትንሽ ይቆየን!!

በነገራችን ላይ ተቃዋሚዎች በ97ቱ ምርጫ 147 መቀመጫዎችን አሸንፈው ነበር - ባይቀመጡበትም፡፡ በ2002 ምርጫ አንድ መቀመጫ ብቻ አሸነፉ፡፡ ዘንድሮ ደግሞ እንዳየነው ነው፡፡ (ኢህአዴግን ለፀፀትና ለሃፍረት የሚዳርግ ውጤት አስመዘገቡ!) ለማንኛውም ግን እንኳንም ምርጫው በሰላም ተጠናቀቀ፡፡

አንድ በዕድሜ የገፉ አዛውንት፤ ኢህአዴግ ምርጫውን ጠራርጐ ማሸነፉ ሲነገራቸው ምን አሉ መሰላችሁ?” “እናቴን ያገባ ሁሉም አባቴ ነው” (ኢህአዴግም ተቃዋሚም ለውጥ የለውም እያሉን ነው!) አሁን ምርጫው አልቋል፤ ወደኑሯችን እንመለስ!! (“አረረም መረረም ማበሬን ተወጣሁ” ነው ነገሩ!)

 

 

 

 

 

Read 4629 times