Saturday, 30 May 2015 11:57

“ሰውስ ምን ይለኛል?”

Written by 
Rate this item
(9 votes)

 

 

 

 እንዴት ሰነበታችሁሳ!

እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… “አንተ፣ እከሌ እኮ ሽበቱን ጥቁር ቀለም ግጥም አድርጎ ኑግ አያስመስለው መሰለህ!” ብለን ‘ጕድ’ የምንልበት ዘመን አለፈና አሁን፣ ‘ብሬስት፣’ አፍንጫ ምናምን ‘ሞዲፊክ’ የሚሠራበት ዘመን ደረስን አይደል! እኔ የምለው… ሙሉ ፊትን ‘ማሳመር’ ተጀመረ እንዴ! መጠየቅ አለብና… አንዳንድ ‘ኮመን’ የምንላቸው እንትናዬዎች በአንድ ጊዜ… “ደም ግባቷን አየህልኝ!” ምናምን የሚያስብል ‘ውበት’ ይይዙብን ጀምረዋላ!

ይቺን ስሙኝማ…ልጁ ለአባቱ “አባዬ ላገባ ነው…” ይለዋል፡ አባትም…

“ሸጋ፣  ሸጋ ነዋ! ለመሆኑ የምታገባት ምን አይነት ሴት ነች?” ይለዋል፡፡ ልጁም…

“አባዬ ቅር እንዳይልህ እንጂ የማገባት በዕድሜ የምትበልጠኝ ሴት ነች፡፡ የዘመኑ ወጣቶች ምንም አይመቹኝም፡፡ በዕድሜ ገፋ ያሉ ሴቶች የሚስብ ነገር አላቸው፡፡”

“ጥሩ፣ አንተን ደስ ካለህ ይሁን፡፡ ግን አንድ ነገር አለ…”

“ምን፣ አባዬ?”

“ነገ ተነገ ወዲያ ፊቷን ‘ማስተካከያ’ ለቀዶ ጥገና ገንዘብ አበድረኝ እንዳትለኝ!”

እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…በፊት እኮ አይደለም ጸጉር ማቅለም ምናምን ነገር ለየት ያለ ልብስ ለመልበስ እንኳን “ሰውስ ምን ይለኛል?” የጎረቤት ሀሜት ነው የሚዘለዝለኝ… ምናምን የሚባሉ ነገሮች ነበሩ፡፡ ዘንድሮ ‘ስልጣኔ’ እንዳለ ከእነተሳቢው ገባና…“ሰውስ ምን ይለኛል?” አይነት ነገር እየቀረ ነው፡፡

ግን እኮ… አለ አይደል… አንዳንዴ…“ሰውስ ምን ይለኛል?” ማለት ክፉ ነገር ላይሆን ይችላል፡፡ ገና ለገና… “በገዛ እንትኔ ማን ያገባዋል…” አይነት ነገር እየሆነ ህብረተሰቡን የሚያስቀይሙ፣ ከ‘አርአያነታቸው’ ይልቅ አፍራሽነታቸው የሚያመዝን ነገሮች ከማድረግ ሊጠበቀን ይችላል፡፡ ለምሳሌ ‘ሚኒስከርቷን’ና ‘ቦዲዋን’ ግጥም አድርጋ ማታ ለቅሶ ቤት ‘ለማስተዛዘን’ የምትሄድ እንትናዬ “በገዛ እንትኔ ማን ያገባዋል…” ብትል አሪፍ አይሆንም፡፡

ስሙኝማ…የሀዘን ነገር ካነሳን አይቀር… ብዙ ቦታ የሠልስት ስርአት መቅረቱ ጥሩ ነው፡፡ ሀዘንተኞቹ ከአላስፈላጊ መጉላላት ይተርፋሉ፣ ሰዉም ከመቸጋገር ያተርፈዋል፡ ግንላችሁ… ደግሞ ሠልስት መቅረቱ ብዙ እንትናዬዎች ውጪ የሚያድሩበትን ሰበብ አስቀርቶባቸዋል፡፡ ልክ ነዋ…“ሠልስት አዳር አለብኝ…” እየተባለ እንትን ሆቴል ክፍል ሠላሳ ሦስት ውስጥ የሚያድሩ እንትናዬዎች መአት ነበሯ! ቂ…ቂ…ቂ…

እናላችሁ… የጎረቤቱ እንትናዬ ላይ ቀልቡ የወደቀው እንትና ወደ ‘ስትራቴጂ ቀረጻ’ና ወደ ‘ተግባራዊ እርምጃ’ ከመግባቱ በፊት መጀመሪያ የሚመጣበት “ጎረቤትስ ምን ይላል?” አይነት ነገር ነበር፡፡ የኮተቤዎቹ እሱና እሷ ሸጎሌ የሚቃጠሩት እኮ… አለ አይደል… “መንደረተኛው አብረን ቢያየን ምን ይላል?” በሚል ነበር፡፡ (‘ነበር’ የሚለው ‘ኃላፊ ጊዜ’ ልብ ይባልልንማ! ቂ…ቂ…ቂ…

ዘንድሮማ ምን ችግር አለ! ከኮተቤ ሸጎሌ የለ… ከቦሌ ጉለሌ የለ…ከፒያሳ መካኒሳ የለ…ምን አለፋችሁ… እንዲህ ሁሉም ነገር ‘ግልጥ በግልጥ’ ሆኖ… ብቻ፣ ‘አገር አናት ላይ ምን እንደወጣ’ እሱ ይወቀው! ቂ…ቂ…ቂ…

ኮንዶሚኒየምን የመሰለ መብራት የሌለው ‘ሬድ ላይት ዲስትሪክት’ እያለ…ማንስ አየ አላየ ግድ ሊሰጠን ነው! እኔ የምለው…ይሄ የኮንዶሚኒየም ነገር…በቃ መኖሪያ ብቻ መሆኑ በሰርኩላር ምናምን ነገር ተሰረዘ እንዴ! አሀ…የምንሰማውና ወዳጆቻችን የሚነገሩን ነገር ሁሉ…የሆነ የሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ‘ሶዶምና ገሞራ’ ምናምን የሆነ ይመስላል፡፡ ኮንዶሚኒየም የሚኖሩ ወላጆች ለሴት ልጆቻቸው በሰላም መውጣትና መግባት ቢጨነቁ አይገርምም! እናላችሁ… “ሰውስ ምን ይለኛል…” የማይባልበት ነገር ሆነና ‘ለመኖሪያነት’ እየተሠሩ ያሉት ኮንዶሚኒየሞች ኑሮን የሚያሳጥሩ ነገሮች እየበዙባቸው ነው፡፡

እናላችሁ…እነኚህ ነገሮች ሁሉ የበዙብን… አለ አይደል…ስልጣኔ እየተባለ ነው፡፡ (ለ‘ፖርኖው’ና ለምናምኑ ‘ሽግግር’ የምንጨነቀውን አንድ አሥረኛ ለቴክኖሎጂና እውቀት ሽግግር ብንጨነቅ ይሄኔ የት በደረስን!)

ስሙኝማ…ድሮ በ‘ሪቮዎች’ ምናምን ዘመን… አለ አይደል… “በኢምፔያሊስት ባህል በከሉን…” እየተባለ… አለ አይደል… “ያንኪ ጎ ሆም!” ይባል ነበር፡፡ ልጄ፣ ዘንድሮ… “ጎ ሆም…” ምናምን ብሎ ነገር የለም፡፡ መፈክር አስጽፈን አደባባይ አንውጣ እንጂ…“ያንኪ ካም ሆም!” የምንል ነው የሚመስለው፡፡ ብቻ በየምኗና በየምናምኗ ያየናትን ነገር ለቀም አድርገን ‘አዳብረን’ና ‘አገሪኛ ቀለም ሰጥተን’ (ቂ…ቂ…ቂ…) ጣራ እናደርሳታለን፡፡ እናላችሁ… ዘንድሮ በተለይ በ‘እነሆ በረከት’ ጉዳይ “ሰው ምን ይለኛል!” ምናምን ብሎ ነገር የለም፡፡

ስሙኝማ…እግረ መንገዴን የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ፡፡ ጥያቄ አለን… ያሁኖቹ ወዳጆቻችን ‘ያስቀየሙን’ ጊዜ “ጃኪ ቻን ጎ ሆም!” ልንል ነው? ቂ…ቂ…ቂ… ልክ ነዋ…በኋላ መፈክርም ለመጻፍ ካሁኑ ብናውቀው አሪፍ ነው፡፡ 

“ምን አለ በሉኝ ከጥቂት ዓመታት በኋላ የአባቶቻቸው ማንነት የሚያከራክሩ ልጆች ባይበዙ…” ያልከን ወዳጃችን…እውነት ብለሀል፡፡ አዝማሚያው ምንም ደስ የሚል ነገር የለበትም፡፡ የአባትነት ነገር ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ…

ሆሊዉድ ውስጥ ነው አሉ፡፡ እናማ… ልጅየው ትምህርት ቤት ውስጥ እየበጠበጠ ያስቸግራል፡፡ ርዕሰ መምህሩም ያስጠራውና፤ 

“በሚቀጥለው ወር እናትህ ትምህርት ቤት እንድትመጣ ንገራት፣” ይለዋል፡፡ ልጅዬውም…

“ለእናቴ መንገር አልችልም፡፣” ሲል ይመልሳል፡፡ ርዕሰ መምህሩም…

“ማለት እናትህ የሚቀጥለው ወር የት እንደምትሆን አታውቅም ማለት ነው?” ብሎ ሲጠይቀው ልጁ ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው…

“አይ፣ በሚቀጥለው ወር አባቴ ማን እንደሚሆን አላውቅም፡፡”

አሪፍ አይደለች፡፡ እኛ ዘንድ እናት ለማምጣት የወር ቀጠሮ የሚሰጡ መኖራቸውን እንጃ እንጂ በሚቀጥለው ወር ‘ተባባሪ አባቱ’ (‘አሶሺዬት ፐሮፌሰር’ እንደማለት፡ ቂ…ቂ…ቂ…) ማን እንደሚሆን የማያውቅ መአት ልጅ ባይኖር ነው! ቂ…ቂ…ቂ… እናላችሁ…አንዳንድ ጊዜ ነገሩ ሁሉ ግራ፣ ግራ ሲሆንባችሁ፤ “ሰውስ ምን ይለኛል?” የሚሏት ነገር የሆነ መልካም ነገር ነበራት ትላላችሁ፡፡ ቢያንስ፣ ቢያንስ ድርጊቶች እኛ ደስ ስላለን ወይ ስላለን ሳይሆን ህብረተሰቡ ላይ ስለሚፈጥረው ነገርም እንጨነቅ ነበር፡፡ ለህብረተሰብ ማሰብ ደግሞ ለትውልድም ማሰብ ይሆናል፡፡ ስሙኝማ…አንዳንዷ እንትናዬ ዕድለኛ አይደለችም፡፡ ዶክተሩ የሚሠራበትን የአእምሮ በሽተኞች ሆስፒታል ለጓደኛው እያስጎበኘው ነው፡፡

“እዛ ጋ ያለው ሰውዬ ይታየሀል?” ሲል ዶክተሩ ይጠይቃል፡፡“አዎ፣ ይታየኛል፡፡ ምን ሆኖ ነው እዚህ የገባው?”

“የሠርጉ ዕለት ማታ ሙሽራው ክዳው ከሌላ ጋር ኮበለለችበት፡፡”

“አትለኝም! በጣም ያሳዝናል፡፡”

ጉብኝታቸውን ይቀጥላሉ፡፡ አንድ በብረት የታጠረ ክፍል ውስጥ ጭንቅላቱን ብረቱ ላይ በሀይል የሚደበድብ ሰው ያያሉ፡፡

“ያ ማን እንደሆነ ታውቃለህ?” ሲል ዶክተሩ ይጠይቃል፡፡“አላውቅም፣ ማነው እሱ?”

“እሱ ደግሞ የኮበለለችውን ሙሽራ ያገባው ነው፡፡”

አጅሪት…ሁለቱንም ፉዞ አድርጋቸው አረፈች! እኛ ዘንድ በመጡ…ሀያ ሁለቱን ‘ፉዞ’ ማድረግ የምትችል መአት አለች፡፡

ከዚች አይነቷ ሙሽራ ይሰውራችሁ፡፡

ስሙኝማ…አንድ ሰሞን የሠርጋቸው ዕለት ማታ ከሚዜ ጋር እነሆ በረከት ሲባባሉ የነበሩ ሙሽሮች እንዳሉ ይወራ ነበር፡፡ ነገርዬውማ ምን መሰላችሁ…ይሄ የሰው እንትናዬ እነሆ በረከት መባባል ከመብዛቱ የተነሳ አንድ ቤተ መጻሕፍት ሙሉ የሚወጣ ታሪክ አለ አሉ፡፡ እናማ… “ሰውስ ምን ይለኛል?” በአጉል ይሉኝታ መሥራት ያለብንን ነገሮች እንዳንሠራ ቢያግደንም አንዳንድ ጊዜ ደግሞ መሥራት የሌለብንን ነገሮች ከመሞከር ይከላከለን ነበር፡፡

ነገሮችን እያመዛዘንን የምንሠራበትን ዘመን ያቅርብልንማ!

ደህና ሰንብቱልኝማ!

 

 

 

 

Read 4657 times