Saturday, 30 May 2015 11:50

የተቃዋሚዎች ያለ ውጤት መቅረት ያልተጠበቀ ነው ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

 

 

 

  • ዶ/ር ነጋሶ የህገመንግስት ማሻሻያ ያስፈልጋል ብለዋል
  • አቶ ሙሼ፤ ኢህአዴግ ያገኘው ድምፅ የስነልቦና ጫና ውጤት ነው ይላሉ

     በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ የማስተርስ ዲግሪ ተማሪ የሆነው አቤል አየናቸው፤ ኢህአዴግ በዘንድሮ ምርጫ እንደሚያሸንፍ ጥርጣሬ አልነበረውም፡፡ ነገር ግን ሙሉ በሙሉ ይጠቀልለዋል የሚል ግምት እንዳልነበረው ይናገራል፡፡ “ቢያንስ 20 እና 25 የሚሆኑ የፓርላማ ወንበሮች በተቃዋሚዎች ይያዛሉ የሚል ግምት ነበረኝ” ብሏል አቤል፡፡

በተለይ ሰማያዊ ፓርቲ፣ መድረክና ኢዴፓ በፓርቲዎች ክርክር ወቅት ባሳዩት ጥንካሬ ብዙ ትኩረትና ድጋፍ መሳባቸውን የሚናገረው አስተያየት ሰጪው፤ ከዚህም በመነሳት በርከት ያሉ እጩዎቻቸው የፓርላማ ወንበር ያገኛሉ የሚል ግምት እንደነበረው ተናግሯል፡፡

“ተቃዋሚዎች ሙሉ ለሙሉ ወንበር ማጣታቸው በምርጫው አሳታፊነትና ተአማኒነት ላይ ጥያቄ ማስነሳቱ አይቀርም” ብሏል አቤል፡፡ለቀጣይ 5 ዓመት የምናየው ፓርላማ አንድ አይነት ድምፅ የሚስተጋባበት መሆኑ ከፍተኛ ጉዳት እንዳለው የገለፀው አስተያየት ሰጪው፤ “ፓርላማው በማህበረሰቡ ውስጥ ያለውን ችግር የማስተጋባት አቅም አይኖረውም” የሚል ስጋት እንዳለው ይናገራል፡፡የለየለት አምባገነናዊ ስርአትን የሚከተሉ ሃገራት እንኳ በዚህ ደረጃ የምርጫ ውጤት አያስመዘግቡም ያለው አቤል፤ ኢህአዴግ ሁሉንም ጠቅልሎ ለመያዝ የሚያደርገውን ጥረት ረገብ አድርጎና የአውራ ፓርቲ ስርአት ለዚህች ሃገር እንደማይበጅ ተገንዝቦ፣ ብዝሃነትን ሊያስተናግድ የሚችል የምርጫ ፉክክር መፍጠር ይኖርበታል ሲል መክሯል፡፡

የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን መምህር የሆኑት አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው የምርጫውን ውጤት እንደጠበቅሁት አላገኘሁትም ይላሉ፡፡ የዛሬ ሳምንት ኢህአዴግ ያሸንፋል የሚል ግምቴን በዚሁ ጋዜጣ ላይ የሰጠሁ ቢሆንም ተቃዋሚዎች በተለይ ሰማያዊ ፓርቲ ጥቂት የፓርላማ ወንበር እንደሚያገኙ ጠብቄ ነበር ያሉት መምህሩ፤ የተነገረው የምርጫ ውጤቱ ለአገሪቱ የዲሞክራሲ ሥርዓት የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ኢምንት ነው ብለዋል፡፡ ውጤቱ ህብረተሰቡ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅና የፈለጉትን አመለካከት የመያዝ መብትን ሳያስተውለው እየተነጠቀ መሆኑን ያሳያልም ባይ ናቸው፡፡

የምርጫው ሂደት ላይ ጠንካራ ፉክክር አለመታየቱ፣ በተለይ ተቃዋሚዎች በሙሉ ልባቸው ወደ ምርጫው አለመግባታቸው ለዚህ አይነቱ ውጤት መመዝገብ አስተዋፅኦ ሳያበረክት አይቀርም ያሉት አስተያየት ሰጪው፤ ተቃዋሚዎች መራጮቻቸውን ሳያስመዘግቡ በምርጫው መሳተፋቸውና ገዥው ፓርቲ ይመርጡኛል ያላቸውን አስመዝግቦ ወይም እንዲመዘገቡ ቀስቅሶ በምርጫው መሳተፉ በውጤቱ ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል ብለዋል፡፡

ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከዚህ በኋላ የምርጫ አካሄዳቸውን በሚገባ ማጤን ይኖርባቸዋል ይላሉ -መምህሩ፡፡ በዘንድሮ ምርጫ ጥሩ ውጤት ያስመዘገቡ ሰማያዊን የመሳሰሉ ፓርቲዎች በሚቀጥሉት 5 ዓመታት ጠንካራ ዝግጅት ካደረጉና የህዝብ አመኔታን ካተረፉ በቀጣዩ ምርጫ ሙሉ በሙሉ የማያሸንፉበት ምክንያት አይኖርም ብለዋል፡፡

ፓርቲዎች በምርጫ ቦርድ ገለልተኝነት ላይ ጥያቄ ካላቸው ምርጫ ሳይደርስ ከወዲሁ አንስተው ከገዥው ፓርቲ ጋር ለድርድር መቀመጥ አለባቸው ያሉት መምህሩ፤ ይህን ሳያደርጉ በምርጫ ወቅት በምርጫ ቦርድ ገለልተኝነት ላይ ጥያቄ ቢያነሱ ህብረተሰቡን ከማሰልቸት ያለፈ ለውጥ አያመጡም ሲሉም ሃሳባቸውን ገልፀዋል፡፡በ2002 በተደረገው ምርጫ መድረክን ወክለው የተወዳደሩትና ራሳቸውን ከፓርቲ ፖለቲካ ያገለሉት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በበኩላቸው፤ በዘንድሮ ምርጫ ብዙ አዳዲስ ነገሮች ማስተዋላቸውን ይናገራሉ - እንግዳ ያልሆነባቸው የኢህአዴግ ማሸነፍ ብቻ መሆኑን በመግለፅ፡፡የተፎካካሪ ፓርቲዎች ቁጥር መቀነስና የምርጫ ጣቢያዎች መብዛት አዳዲስ ነገሮች ከሚሏቸው ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡ የምርጫ ጣቢያዎች መብዛት አዎንታዊም አሉታዊም ጎን አለው ያሉት ዶ/ር ነጋሶ፤ በአዎንታዊ ጎኑ ህዝቡ በአቅራቢያው ያለእንግልት ቶሎ እንዲመርጥና ወደ ጉዳዩ እንዲሄድ ይረዳል፣ በአሉታዊ መልኩ ደግሞ 45ሺ ጣቢያዎች መኖራቸው የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ታዛቢ የማሰማራት አቅም ይፈታተናል ብለዋል፡፡ “ፓርቲዎች ወኪሎቻቸውን ሳያስቀምጡ የሚካሄድ ምርጫ ደግሞ አጠያያቂ ሊሆን ይችላል” ይላሉ፤ ዶ/ር ነጋሶ፡፡ በእርግጥም ተቃዋሚዎች በብዙ የምርጫ ጣቢያዎች ታዛቢዎች እንዳልነበሯቸው ዘገባዎች ይጠቁማሉ፡፡

የአፍሪካ ህብረት ታዛቢ ቡድን ስለምርጫው ያወጣውን ሪፖርትና በተለያዩ ሚዲያዎች የቀረቡ ዘገባዎችን መከታተላቸውን የጠቆሙት ዶ/ሩ፤ ቡድኑ በዘንድሮው ምርጫ ከቀድሞው የተሻለ ጠንካራ ሪፖርት ማቅረቡን መገንዘባቸውን ገልፀዋል፡፡

የአፍሪካ ህብረት ታዛቢ ቡድኑ በ356 የምርጫ ጣቢያዎች ብቻ ታዝቦ ያወጣው ሪፖርት በምርጫው ላይ ጥያቄ የሚያስነሳ እንደሆነ የጠቀሱት ዶ/ር ነጋሶ፤ በምርጫ ጣቢያዎች የቅስቀሳ ፖስተሮች ተለጥፈው መገኘታቸው፣ የምርጫው እለት ቅስቀሳ ሲካሄድ ማየቱና ከታዘባቸው ጣቢያዎች 21.4 በመቶ በሚሆኑት ኮሮጆዎች ሳይፈተሹ ወደ ምርጫ መገባቱን መታዘቡ በቀላሉ የሚታይ አይሆንም ብለዋል፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ታዛቢዎች አለመኖርና የምርጫ ወረቀት እጥረት መከሰቱ በቡድኑ መጠቆሙም ምርጫው ጉድለቶች እንደነበሩበት ያሳያል ብለዋል - ዶ/ሩ፡፡በ1987 በተረቀቀው ህገ-መንግስት ላይ ጉልህ ተሳትፎ የነበራቸው ዶ/ር ነጋሶ፤ በኢትዮጵያ የሚከናወን ምርጫን በተመለከተ ህገ መንግስቱ ጭምር መሻሻል አለበት ይላሉ፡፡ የተመጣጣኝ ድምፅ አሰራር የሚተገበርበትን አካሄድ መከተል እንደሚሻል ጥናት ላይ የተመሰረተ ሃሳብ ማቅረባቸውን የጠቆሙት ምሁሩ፤ የተመጣጣኝ ድምፅ ስርአት ብንከተል የሀገራችንን ብዙሃነት በተገቢው ሁኔታ አሳታፊ አድርጎ ድምፅ ታፍኖ እንዳይቀር፣ ዜጎች ከማንኛውም ተሳትፎ እንዳይገለሉና ድምፃቸው ሙሉ ለሙሉ ዋጋ እንዲኖረው የሚያደርግ ስርአት ለመዘርጋት ያስችላል፤ ይህን ተግባራዊ ለማድረግም የህገ መንግስት ማሻሻያ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

መድረክ የምርጫውን ውጤት አልቀበልም ማለቱን እንደሰሙ የጠቆሙት ዶ/ር ነጋሶ፤ እንዲህ ያለ ችግር ሲያጋጥም ወደ ፍ/ቤት በማምራት ፋንታ ገለልተኛ አካል ይቋቋምና የምርጫው ውጤት ይጣራ ብሎ መጠየቁ ግራ እንዳጋባቸው ተናግረዋል፡፡የአለማቀፍ የህግ ባለሙያው ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለማርያም  በበኩላቸው፤ “ምርጫውን ምርጫ ብዬ ስለማልቀበለው አስተያየት ለመስጠት እቸገራለሁ” ሲሉ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ 

የቀድሞው የኢዴፓ ፕሬዚዳንት አቶ ሙሼ ሰሙ፤ የምርጫው ውጤት እንደተገለፀው ሊሆን እንደሚችል ብዙ ጠቋሚ ነገሮች ነበሩ ሲሉ ያስታውሳሉ፡፡ ያለፉት 5 ምርጫዎች ከሂደት፣ ከዲሞክራሲ ባህሪና ከውጤት አኳያ ሲገመገሙ ብዙ ችግሮችና ምስቅልቅሎች የነበሩባቸው እንደሆኑ የጠቆሙት አቶ ሙሼ፤ በየጊዜው ምርጫ ተጭበርብሯል የሚለው የፓርቲዎች እሮሮ የሃሳብ ጥራት ወይም የችግሩን ምንጭ በጥናት ላይ ተመስርቶ ያለመፈተሽ ችግር ይታይበታል ይላሉ፡፡“ምርጫው ሲጀመር አንስቶ ድምፅ ሊጭበረበር ይችላል እየተባለ፣ ያንን ለማረም የሚያስችል ስራ ሳይሰሩ ወደ ምርጫ መግባት በራሱ ትርጉም የለውም” የሚሉት አቶ ሙሼ፤ ፓርቲዎች በአንድ በኩል በሂደቱ ላይ እምነት እንደሌላቸው እየተናገሩ፣ መሻሻል ሳይኖር ዝም ብለው በምርጫው መሳተፋቸው በራሱ አግባብ ነው ወይ ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡

ህዝብ ስለምርጫው ያለው አመለካከትና ፓርቲዎች በህብረተሰቡ ያላቸው ቅቡልነት አለመጠናቱም አንድ የምርጫ ሂደቱ ችግር ነው ይላሉ፤ አቶ ሙሼ፡፡ ገዥው ፓርቲም ሆነ ተቃዋሚዎች ህዝቡ ከኔ ጋር ነው ሲሉ ይደመጣል የሚሉት የቀድሞው የተቃዋሚ አመራር፤ ነገር ግን ተቃዋሚዎችም ሆነ ገዥው ፓርቲ ምን ያህል የህብረተሰብ ክፍል ይደግፋቸዋል? የትኛው የህብረተሰብ አካልስ ተቀብሏቸዋል የሚለውን በጥናት ለማረጋገጥ አለመሞከሩ በኢትዮጵያ የሚካሄዱ ምርጫዎች ችግር ነው ባይ ናቸው፡፡ ፓርቲዎች በማህበረሰቡ ያላቸውን ቅቡልነት በጥናት ማረጋገጥና ለምርጫ ሲዘጋጁም ይሄን ያህል ህዝብ ሊመርጠን ይችላል፣ ይሄኛው ላይመርጠን ይችላል የሚለውን አስቀድመው ቢያውቁ እንደዘንድሮ አይነት የምርጫ ውጤት ሲያጋጥም መደናገጥ ላያጋጥም ይችላል ሲሉ አስረድተዋል፡፡በዘንድሮው ምርጫ የታዘቡትን ሲናገሩም፤ ምርጫውን የማጭበርበር ሂደቶች እንደ ምርጫ 97 ኮሮጆ በመቀየር፣ ካርድ በማሰራጨት ሳይሆን የስነ-ልቦና ጫናዎች ናቸው ይላሉ፡፡ ኢህአዴግ ያገኘው ውጤት የስነ - ልቦና ተፅዕኖ ድምፅ ነው የሚሉት አቶ ሙሼ፤ ማህበረሰቡ በሚሰጠው ድምፅ ኢህአዴግ ሲለወጥ ላለፉት 5 ምርጫዎች አለማየቱ፣ ተቃዋሚዎችን ቢመርጥ በስራ ቦታውና በማህበራዊ ህይወቱ የሚያጋጥመውን ተግዳሮት ሽሸት የስነ - ልቦና ተፅዕኖ ያሳድራል ይላሉ፡፡ ኢህአዴግን ወዶና ፈቅዶ የሚመርጥ የመኖሩን ያህል የሚደርስበትን ማህበራዊ ምስቅልቅል ሰግቶ ኢህአዴግን ሳይወድ የሚመርጥም አለ የሚሉት አቶ ሙሼ፤ ተቃዋሚን ብመርጥም ለውጥ አይመጣም ብሎ አስቀድሞ ማሰብም ሌላው የስነ - ልቦና ተፅዕኖ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡

“አርሶ አደሩ ተገዶ የምርጫ ካርድ እንዲወስድ መደረጉ ሳያንስ ተገዶ እንዲመርጥም ይደረጋል” የሚሉት አስተያየት ሰጪው፤ ወጣቱም ቢሆን ምርጫውን ተከትሎ ሊፈጠር የሚችልን እስርና እንግልት ስለማይፈልገው ድምፁን ለኢህአዴግ ሊሰጥ ይችላል ብለዋል፡፡

በቀጣይ ተቃዋሚዎች ምርጫው በደፈናው ተጭበረበረ ከማለት ይልቅ የችግሮቹን ስረ መሰረት የሚፈትሹ ጥናቶችን ሰርተው የሚያገኙትን የጥናት ውጤት እንደ ግብአት በመጠቀም ለእውነተኛ የፖለቲካ ትግል ራሳቸውን ሊያዘጋጁ ይገባል ብለዋል፡፡

የኢህአዴግ ጽ/ቤት የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ ደስታ ተስፋው በበኩላቸው፤ “ህብረተሰቡ በድጋሚ ለኢህአዴግ ሙሉ ለሙሉ ኃላፊነት መስጠቱን ከምርጫው ውጤት አረጋግጠናል” ይላሉ፡፡

ገና የሚቀር ውጤት ቢኖርም ኢህአዴግ ሙሉ ለሙሉ ምርጫውን ቢያሸንፍ እንኳ አንዳንድ ተቃዋሚዎች እንደሚሉት፣ የምርጫውን ዲሞክራሲያዊነት አይቀይረውም ያሉት አቶ ደስታ፤ “መራጮች የተሻለው አማራጭ ይሄ ነው ብለው በሙሉ ፈቃደኝነት ከመረጡ የግድ ተቃዋሚ መግባት አለበት ተብሎ ከህግ አግባብ ውጪ ይሰራ ማለት ነው?” ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ ዲሞክራሲ ማለት የህዝብ ውሳኔ ማለት ነው ያሉት ኃላፊው፤ ተቃዋሚዎች አይመሩኝም ብሎ ህዝቡ ከወሰነ ውሳኔው መከበር አለበት ብለዋል፡፡ እንዲያም ሆኖ አንዳንድ ተቃዋሚዎች ጠንካራ ተፎካካሪ ሆነው፣ በርካታ ድምፅ ያገኙበት አጋጣሚም እንዳለ አቶ ደስታ በመጥቀስ፤ ምርጫው በሚገባ አሳታፊና በምቹ የመወዳደሪያ መድረክ የተካሄደ ነው ብለዋል፡፡ 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

Read 3144 times