Wednesday, 27 May 2015 07:46

የአፍሪካ ህብረት ታዛቢ ቡድን ምርጫው ሰላማዊና ተዓማኒ ነው አለ

Written by 
Rate this item
(9 votes)

*በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች ቅስቀሳ ሲካሄድ መታዘቡን  ጠቁሟል

የአፍሪካ ህብረት ታዛቢ ቡድን፤ ባለፈው እሁድ የተካሄደው የኢትዮጵያ አገራዊ  ምርጫ ከአንዳንድ ጥቃቅን ችግሮች በቀር ሰላማዊና ተዓማኒ ነው አለ፡፡  በአንዳንድ የምርጫ ጣቢዎች ለመምረጥ ከተመዘገበው ሰው በላይ ድምጽ የተሰጠባቸው ወረቀቶች መገኘታቸውን የጠቀሰው ታዛቢ ቡድኑ፤ በተወሰኑ የምርጫ ጣቢያዎች ደግሞ  ቅስቀሳ ሲካሄድ መታዘቡን ጠቁሟል፡፡የአፍሪካ ህብረት ታዛቢ ቡድን መሪ የቀድሞ የናምቢያ ፕሬዚዳንት ሂፊኬፑንዬ ፖሃምባ  በትላንትናው ዕለት በሂልተን ሆቴል የህብረቱን  የመጀመሪያ ዙር ሪፖርት ይፋ ባደረጉበት ወቅት እንደጠቆሙት፤ ከ23 የአፍሪካ አገራት የተውጣጡ 59 አባላት በገጠርና በከተማ በሚገኙ 356 የምርጫ ጣቢያዎች ተዘዋውረው የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱን ታዝበዋል፡፡

ህብረቱ በታዘባቸው 95 በመቶ ያህል  የምርጫ ጣቢያዎች፣ የመራጮች ምስጢራዊነት የተጠበቀ መሆኑን  የጠቆመው የቡድኑ ሪፖርት፤ በምርጫ ጣቢያዎች ምንም የጎላ ችግር አልተከሰተም ብሏል፡፡ በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች የመራጩ ህዝብ ቁጥር ከ1ሺ በላይ እንደነበር የጠቆመው የታዛቢ ቡድኑ፤ ይሄም በአንዳንድ ጣቢያዎች ለታየው  መጨናነቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን ገልጾ፣የምርጫ ህጉንም  ይቃረናል ብሏል፡፡

  ህብረቱ ከታዘባቸው የምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ 22.7 በመቶ በሚሆኑት የቅስቀሳ መልዕክቶችና ፖስተሮች ሲሰራጩ እንደነበር የገለጸው  ሪፖርቱ፤ 23 በመቶ በሚሆኑት ደግሞ በምርጫ ጣቢያ ውስጥ ቅስቀሳ ሲካሄድ መታዘቡን ጠቁሟል፡፡  በምርጫ ጣቢያው የተመዘገበው መራጭ ቁጥርና  ድምጽ የተሰጠባቸው ወረቀቶች አልተጣጣሙም ከተባሉባቸው አካባቢዎች መካከል ህብረቱ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ምርጫ ጣቢያ 10ን ለአብነት ጠቅሷል፡፡ በዚህ ጣቢያ የድምጽ ቆጠራ ሲከናወን፣ድምጽ ለመስጠት ከተመዘገበው መራጭ ቁጥር በላይ ድምጽ የተሰጠባቸው ወረቀቶች መገኘታቸውን  ህብረቱ ጠቁሟል፡፡ምርጫው የተረጋጋ፣ ሰላማዊና ተዓማኒ  ነው ያለው የአፍሪካ ህብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን፤ምክንያቱም የኢትዮጵያ ህዝብ የፈለገውን በድምጹ እንዲወስን ዕድል ሰጥቶታል ሲል ሪፖርቱን አጠቃሏል፡፡  59 ታዛቢዎችን ያሰማራው የአፍሪካ ህብረት የታዛቢ ቡድን፤ በአገሪቱ ካሉት 45ሺ የምርጫ ጣቢያዎች  በ356 ጣቢያዎች ብቻ ተዘዋውሮ መታዘቡን አስታውቋል፡፡

Read 2597 times