Tuesday, 26 May 2015 09:29

ጓደኛዬ ለመመረጥ ቆርጣለች!

Written by  ተአምር ተክለብርሃን
Rate this item
(24 votes)

 

 

 

ጓደኛዬ ቆርጣለች። ከዚህ ቀደም እንዲህ ቆርጣ ግን አታውቅም፡፡ ድንገት እኮ ነው ከመሬት ተነስታ (ለነገሩ ከመሬት አልተነሳችም፤ ወንበር ላይ ቁጭ ብላ ነው) “አንቀፅ 38 የሰጠኝን መብት እጠቀማለሁ” ያለችኝ። እኔ ደግሞ ሰው ከተንኮልና ከክፋት ሲፀዳ አይቼ በደህና ጊዜ ከእውቀት የፀዳሁ ስለሆንኩ፣ “አንቀፅ 38 ደግሞ ምንድነው?” ስል ጠየቅኋት፡፡

“ህገ - መንግስቱ የሰጠን መብት ነው። አንቀፅ 38 የመምረጥና የመመረጥ መብት!” አለችኝ ፍርጥም ብላ። አሃ! ምርጫ ደርሶ የለ? የምትለው በጥቂቱ የገባኝ መሰለኝ።

“ልትመርጪ አስበሽ ነው? ታዲያ ምን ታካብጃለሽ? ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ነቅሎ ወጥቶ እንደሚመርጥ ኢቢሲ በየቀኑ ይናገር የለም እንዴ!” አልኳት ኮስተር ብዬ።

“አንቀፁ የመምረጥ ብቻ ሳይሆን የመመረጥ መብትም ይሰጣል። እኔ መመረጥ ነው የምፈልገው፤ ፓርቲ አደራጅቻለሁ” አለችኝ:: 

እቺ ልጅ ምን ነካት? የቁንጅና ውድድር መሰላት እንዴ? (ብቻ ቁንጅናንም ሙያ አድርጋው ምረጡኝ እንዳትል አልኩ- በሆዴ!)

“ጓደኛዬ፤ ቁንጅናሽ በኢቢሲ ታየም አልታየም የሚያመጣው ለውጥ የለም። የኢትዮጵያ ህዝብ የሚፈልገው የሥልጣን አክሊል የሚደፋ እንጂ የውበት አክሊል የምትደፋ ቆንጆ አይደለም። ይልቅስ የፈላጊዎችሽን በር እንዳትዘጊ” ስል አስጠነቀቅኋት፡፡ እሷ ግን ማስጠንቀቂያዬን ከቁምነገር የቆጠረችው አትመስልም፡፡

“በምርጫው አሸንፌ ቀጣዩን አምስት ዓመት ሀገሬን ማገልገል እፈልጋለሁ።” አለችኝ አይቼባት በማላውቀው ድፍረት፡፡ አሁን እንዳበደች ገባኝ። በቃ አንዱ በውበቷ የነሆለለ ጎረምሳ ያሰራባት “መስተፋቅር” ዶዙ በዝቶ ጭንቅላቷ ላይ ወጥቷል ማለት ነው ብዬ ደመደምኩ፡፡

ጉዷን ልስማ ብዬ ድምፄ እየተርገበገበ፤ “እንደው ምርጫ ለመወዳደር ምን አሳሰበሽ?” ስል ጠየቅኋት።

ጓደኛዬ ተከዘች። ከንፈሯን ነከስ ነከስ እያደረገች ዮጋ እንደሚሰራ ሰው ተመሰጠች፡፡ ቀጣይ የሀገር መሪ ለመሆን ያለመችው ጓደኛዬ፣ ከስልጣኗም ባታካፍለኝ ቀጣዩ የሀገር ውስጥ ኑሮዬ ሰላማዊ እንዲሆን እንክብካቤ በተሞላበት ድምፀት፤ “እባክሽ ንገሪኝ፤ ተጨነቅሁ እኮ” አልኳት።

“ይኽውልሽ ---- ሀገር ለመምራት ያነሳሳኝ ያለፈው ታሪኬ ነው”

ኧረ ወየው ይቺ ልጅ ብሶባታል አልኩ - በሆዴ። የትኛው ታሪኳ ይሆን? እሷ እኮ መስተዋት ፊት ከመቆምና ወንዶች ከመቀያየር ያለፈ ታሪክ የላትም። ብቻ  በውስጤ ፈገግ አልኩ።

“ይኸውልሽ” አለች መጨረሻው ያማረኝ ወሬዋን ለመጀመር እየታሸች። “ሴት ነኝ” (“ወንድ ብትሆኚማ በዚህ ቁንጅናሽ እስከዛሬ እለቅሽ ነበር?” አልኩ ለራሴ) “ሴት ልጅ ደግሞ ክብረ ንፅህና ይኖራታል” (እንደው ምን ከዕውቀት የጸዳሁ ነኝ ብል ይችን ማወቅ ያቅተኛል?!) ግን ለምንድን ነው ሰው ወደ ፖለቲካ ሲገባ ነገር የሚያካብደው? በእርግጥ የቆንጆዋን ጓደኛዬን ወደ ፖለቲካ መግባት ገና አልተቀበልኩትም፡፡

ጓደኛዬ ቀጠለች ማብራሪያዋን፡፡ እኔም ጭንቅላቴን እየነቀነቅሁ ጉዷን ማዳመጥ ቀጠልኩ።

 “ታዲያ የድንግልና አካሄዱን ከውሃና መብራት አካሄድ ጋር አመሳስለው ቢሄድም ይመጣል በሚል ሴት እህቶቼ በከንቱ ውድ ንብረታቸውን እንዲያጠፉ አልፈልግም” አለች። (እቺ ጠጋ ጠጋ ያልወደቀ እቃ ለማንሳት ነው! አሉ) ብቻ የእኔም “ንብረት” አለ እንዳትለኝና ጉድ እንዳይፈላ። የፈለገ በምርጫ  እወዳደራለሁ ብትለኝም ልታገሳት ዝግጁ አልነበርኩም፡፡ (እየተዋወቅንማ አንታለልም!)

“አየሽ ጓድ” አለችኝ እጩዋ ተወዳዳሪ (እየመጣሽ ተኚ… ጭራሽ ጓድ?) ግርም አለችኝ፡፡ በአንድ የትግል ሜዳ የተዋጋን ሁሉ ሳይመስለኝ አልቀረም፡፡

“አየሽ ጓድ፤ የድንግልናዬን አካሄድ ሳስብ በጎ ትዝታ የለኝም፡፡ ጣዕሙንና ምንነቱን ሳላውቀው ነው ድንገት የሄደው፡፡ እንደ ድንገተኛ አደጋ በይው! እናም እኔ ከተመረጥኩ ይሄ ዓይነቱ የድንግልና አካሄድ በሌሎች ኢትዮጵያውያን ሴቶች ላይ እንዳይደርስ ጠንከር ያለ ህግ አወጣለሁ”

በጓደኛዬ ነገረ ሥራ እየተገረምኩ፤ “ለመሆኑ የምርጫ ምልክትሽ ምንድነው?” አልኳት።

“ቀይ መሃረብ!” አለችኝ ፈጠን ብላ፡፡

“ቀይ እኮ የአደጋ ምልክት ነው!” ከምሬ ነበር።

“ታሪክ የመለወጥ አላማ ነው ያነገብኩት” አለችኝ ኮስተር ብላ፡፡

“ለነገሩ እኔ ምን አገባኝ”

“እኔ ምን አገባኝ ነው ሀገሬን የገደላት”

እቺ ናት ፖለቲከኛ! ገና ከአሁኑ “የኔ” ብላ እኔን ያለ ሀገር ታስቀረኝ?! (ስትመረጥማ ከሀገር ታሰድደኛለች!)

“ድንግልናችን በድንገት መሄዱ ሳያንስ ባል ተብዬው በስሙ ያወጣው ሲም ካርድ ይመስል የት አደረግሽው? ለማን ሰጠሽው ብሎ ያፋጥጠናል፡፡ በዚህ ጊዜ የእኛ ድንግልናችን ተመልሶ ያልመጣልን ሴቶች መከራና ጭንቀት አይጣል ነው፡፡ በዚያ ላይ እኮ ወንዱ ድንግል ይሁን አይሁን ማንም አይጠይቀው፡፡ ጫናው ያለው ሴቷ ላይ ብቻ ነው!”

“ይሄ እኮ የተፈጥሮ ጉዳይ ነው” አልኳት ጓደኛዬን፡፡ (ማለቴ እጩ ተወዳዳሪዋን!)

“አዎ ተፈጥሮ ነው፤ እኛ እንደ ሀገር መስራት የምንችለው ላይ ነው የምናተኩረው!”

“እሺ” አልኳት ደሞ ምን እንደምትቀጥል መገመት እያቃተኝ። ሰው እንዲህ በአንዴ ይለወጣል? (አይ ፖለቲካ! አይ ስልጣን! አይ ምርጫ! አይ ፓርቲ!)

 “ታዲያ ቅስቀሳውን ምን ላይ አተኩረሽ ልታደርጊ አሰብሽ?” ስል ጠየቅኋት፡፡

“የእኔ ፓርቲ ከተመረጠ ድንግልና ወይም ክብረ ንጽህና አዳኝ ወንዶችን በመከታተልና በመልቀም ሀገራችን ኢትዮጵያ በቀጣይ አምስት አመት የልጃገረዶች ሽፋንዋ በ30 በመቶ እንዲያድግ የሚሰራ ይሆናል። ድንግል መፈለግ ኢትዮጵያ ውስጥ ነዳጅ እንደ ማውጣት የሚታይበትን ዘመን በመቀየር፣ ኢትዮጵያ ነዳጅ አምራች አገር ባትሆንም ልጃገረድ አምራች ሀገር በማድረግ፣ በድንግል መሬቷ ብቻ ሳይሆን በድንግል ሴቶቿም ተመራጭ እናደርጋታለን። ቀድሞ የተወሰዱ ድንግልናዎችን ባናስመልስም በቀጣይ ይህ ታሪክ እንዳይደገም በቁርጠኝነት እንሰራለን!”

ለአፍታ ትንፋሽ ከወሰደች በኋላ ማብራሪያውን ቀጠለችበት፡፡ እንደ ከረመ ፖለቲከኛ ፕሮፓጋንዳ ሁሉ ሳትጀምር አልቀረችም፡፡ (ለነገሩ እሷስ ለፕሮፓጋንዳ ምን ይጎድላታል!?)

“በተጨማሪም የወንዶች ለከፋና ትንኮሳን በትጋት እንዋጋለን!” አለች፡፡

 

 

 

Read 11069 times