Tuesday, 26 May 2015 08:59

አሐዱና ሰባቱ እህት ኩባንያዎቹ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 

 

 

ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል አላቸው

ለ2,500 ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል

የአሐዱ ፒኤልሲ ዋና ሥራ አስኪያጅና ባለቤት  አቶ ሰለሞን ወንድሜነህ

ከዩኒቨርሲቲ የተመረቁት በደርግ ጊዜ ነበር። ያኔ ሥራ የሚመድበው መንግሥት ነበር፡፡ እናም በመንግሥት እርሻ ተመድበው በአትክልትና ፍራፍሬ ኮርፖሬሽን ሥራ ጀመሩ፡፡ እዚያ ለ5 ዓመት ከሰሩ በኋላ ለቀው በተለያዩ የግል ድርጅቶች በኃላፊነት ደረጃ በመሥራት ከፍተኛ ልምድ መቅሰማቸውን ይናገራሉ፡፡ በአገር ውስጥ ከሚሰጡ ሥልጠናዎችና በውጭ አገር ከወሰዷቸው አጫጭር ኮርሶች ያገኙት እውቀት ከፍተኛ በራስ መተማመን ፈጠረላቸው፡፡

ይኼኔ የራሴን ቢዝነስ ብጀምር‘ኮ ህይወቴን በተሻለ መንገድ መምራት፣ ለወገኖቼ የሥራ ዕድል መፍጠርና ለአገር ኢኮኖሚ አስተዋጽኦ ላደርግ እችላለሁ በማለት አሰቡ፡፡ እውቀትና ልምዳቸውን አቀናጅተው በግላቸው ለመሥራት ከተቀጠሩት መ/ቤት ለቀው፣ የዛሬ 23 ዓመት በ10 ሺህ ብር ካፒታል አሐዱ የግል ኩባንያን መሰረቱ፡፡ የአሐዱ ዋና ሥራ ከቡናና ሻይ ልማት ድርጅት ብትን ሻይ ቅጠል እየገዛ መሸጥ ነበር፡፡ ትንሽ ቆይቶም ሻይ ቅጠሉን በፋብሪካ አቀነባብሮና አሽጎ ለገበያ ማቅረብ ጀመረ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አንዳንድ ዕቃዎች ከውጭ እያመጡ ማከፋፈል ያዙ፡፡ ሌሎች ትናንሽ ቢዝነሶችንም ይሰሩ ነበር፡፡

ያኔ ቢዝነሱ እንደ ዛሬ ውድድርና ትግል የበዛበት አልነበረም፡፡ “ገና ኢህአዴግ ሥልጣን ይዞ ነጻ ኢኮኖሚ የታወጀበት ጊዜ ስለነበር እንደ እኔ ያሉ ወጣት የቢዝነስ ሰዎች ያለ ብዙ ውጣ ውረድ ጥሩ የመስራት ዕድል ነበረን” ይላሉ፡፡ አሐዱ ሻይ በህብረተሰቡ ዘንድ ስለተወደደ ገቢያቸው ጨመረ። ሌሎች ቢዝነሶችም አትራፊ ሆነው ካፒታላቸው ሲያድግ፣ የዛሬ 20 ዓመት አሐዱ  ኩባንያ በ500 ሺህ ብር ካፒታል ፒኤልሲ ሆኖ ተቋቋሙ፡፡ብቸኛ የነበረው አሐዱ ዛሬ ወደ ጎን ተንሰራፍቶ 7 እህት ኩባንያዎች አፍርቷል፡፡ መድኃኒት እያስመጣ ያከፋፍላል፣ ዘመናዊ የእርሻ ልማት አለው፣ በሪል እስቴት ተሰማርቷል፣ ፋርማሲዎች አሉት፣ የፓኬጂንግ ፋብሪካና የትሬዲንግ (ንግድ) ድርጅቶች ባለቤት አለው፡፡ እነዚህ ብቻ አይደሉም። ወደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍም ገብቷል። ከእንግሊዙ ቫሳሪ ግሎባል ግሩፕ ጋር በእኩል 50፣ 50 የአክሲዮን ድርሻ በቢሾቱ ከተማ ያቋቋሙትና የዛሬ ሦስት ሳምንት የተመረቀው “አሐዱክስ ፉድ ፕሮዳክትስ ኩባንያ” የቦርድ አባል፣ የአሐዱ ፒኤልሲ ዋና ሥራ አስኪያጅና ባለቤት ናቸው - አቶ ሰለሞን ወንድሜነህ፡፡ ኢንቨስተሩ ለምን ወደማኑፋክቸሪንግ እንደገቡ ሲናገሩ፣ ግማሽ ምዕተ ዓመት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ ኢኮኖሚያቸው ያደገው ኮሪያና ቻይናም ሆኑ በኢንዱስትሪ የበለፀጉ ትላልቅ አገሮች የመጀመሪያ መነሻቸው አግሮ ፕሮሰሲንግ ነው፡፡ እኛም አሁን ያተኮርነው በእርሻ ምርቶች ማቀነባበር ነው፡፡ እሱን ማስፋፋት አለብን፡፡ ከአርሶ አደሩና ከሌሎች ኢንዱስትሪዎች ጋር ማስተሳሰርና ፕሮሰስድ የሆኑ የኢንዱስትሪ ምርቶችን ማውጣት ነው። ትልቁ ሀሳባችን በአግሮ ፕሮሰሲንጉ በብዛት ከሰራን በኋላ በሌሎች የቴክኖሎጂ ውጤቶች ላይ ማተኮር ነው ብለዋል፡፡ አቶ ሰለሞን በ1955 ዓ.ም በአሁኑ አርሲ ዞን በአሰላ ከተማ ተወለዱ፡፡ ያደጉትም ሆነ የመጀመሪያና የ2ኛ ደረጃ ትምህርት የተማሩት እዚያው ነው፡፡ 12ኛ ክፍል በ1972 ዓ.ም አጠናቀቁ፡፡ በቀጣዩ ዓመት ንግድ ሥራ ኮሌጅ (ኮሜርስ) ገብተው፣ በአካውንቲንግ (በሂሳብ አያያዝ) በዲፕሎማ ተመረቁ፡፡ በ1975 አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብተው፣ በ1980 የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በማኔጅመንት አገኙ። ወደ እንግሊዝ አቅንተው ሁለተኛ ዲግሪያቸውን (ኤምኤ) ከግሪንዊች ዩኒቨርሲቲ ተቀብለዋል፡፡

አሐዱ፣ የመጀመሪያ ማለት ነው፡፡ መስራቾቹ ይህን ስም የተጠቀሙት ከእግዚአብሔር ጋር ባላቸው የጠበቀ ቁርኝነት አሐዱ የመጀመሪያው አንድ አምላክ ለማለት ነው፡፡ አሐዱ መድኃኒቶችን ከአውሮፓ፣ ከመካለኛው ምሥራቅና ከአፍሪካ አገሮች እያስመጣ በተመጣጣኝ ዋጋ ያከፋፍላል፡፡ ለገሀር የሚገኘውን አክሱም ፋርማሲ ከመንግሥት ሁለት ሚሊዮን በማይሞላ ገንዘብ ገዝተው አሁን ቅርጫፎቻቸውን 12 አድርሰዋል፡፡ ቅርንጫፎቹም በሸበሌ፣ ሳሪስ፣ 22 አካባቢ፣ ቦሌ ሚካኤል፣ መገናኛ፣ ገርጂ፣ … የሚገኙ ሲሆን ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ መድኃኒት ያቀርባሉ ብለዋል አቶ ሰለሞን፡፡

በሪል እስቴት ዘርፍ መብራት ኃይል እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የሚገኘው ህንፃ በወቅቱ 47 ሚሊዮን ብር የፈጀ ሲሆን በዋና መ/ቤትነት እያገለገለ ነው፡፡ የተለያዩ ድርጅቶችም በቢሮነት ተከራይተውታል። በቦሌ መንገድ እየተሰራ ያለው ባለ 14 ፎቅ ህንፃ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ይፈጃል ተብሏል፡፡ ሕንፃው ለንግድ ማዕከልነትና ለመኖሪያነት የሚያገለግል ነው፡፡ ዘመናዊ እርሻው ያለው በምዕራብ ጎጃም አዊ ዞን፣ በግምጃ ቤት ወረዳ በኢንጅባራ ከተማ “አየሁ እርሻ ልማት” አካባቢ ሲሆን በ17.5 ሚሊዮን ብር በ1000 ሄክታር ላይ  የተቋቋመው ነው፡፡ እርሻ ልማቱ በቆሎ፣ በርበሬና ሌሎች ሰብሎችም ያመርታል፡፡ በአሁኑ ወቅት ቡና ማልማትም ጀምሯል፡፡

በለገጣፎ ከተማ በ32 ሚሊዮን ብር የተቋቋመው አዲስ አሐዱ ፓኬጂንግ ፋብሪካ፤ ለኤክስፖርት ከፍተኛ ድጋፍ የሚያደርግ ሲሆን በምርት ጥራቱና በቀጠሮ አክባሪነቱ በመንግሥት እውቅናና ምስጋና በማግኘቱ በቀድሞው ጠቅላይ ሚ/ር መለስ ዜናዊ መሸለሙንና ለ580 ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን ባለሀብቱ ተናግረዋል፡፡

አሐዱ ኩባንያ ከ20 ዓመት ያላሰለሰ ጥረትና ከፍተኛ ትግል በኋላ ከፍተኛ እውቅና ያገኘው ከሦስት ዓመት ወዲህ ሲገነባ በቆየውና ከሦስት ሳምንት በፊት በተመረቀው አሐዱክስ ፉድ ፕሮዳክትስ ኩባንያ ነው፡፡ አቶ ሰለሞን፣ ኢትዮጵያ፣ ጥራቱ በዓለም የታወቀ ስንዴ አምራች ሆና የስንዴ ውጤት የሆኑ የተለያዩ ብስኩቶች፣ ፓስታ፣ ማካሮኒ… ከውጭ አገራት ስታስገባ ማየት በጣም ያስቆጫቸዋል፣ ያማቸዋል፡፡ መቼ ነው ይህን ከውጭ የሚገባ የስንዴ ምርት ተክተን ለግዢ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ የምናድነው? መቼ ነው በአገራችን ስንዴ የተሰራ ምርት ወደ ውጭ አገር ልከን ለአገራችን የውጭ ምንዛሪ የምናመጣው? በማለት ብዙ ጊዜ አስብ ነበር ይላሉ፡፡

አሁን ወደ አግሮ ፕሮሰሲንግ በመገንባት ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ (36 ሚሊዮን ዶላር) በቢሾፍቱ ከተማ እጅግ ዘመናዊ የብስኩት፣ ፓስታና ማካሮኒ ፋብሪካ ገንብተው ራዕያቸውን በማሳካታቸው በጣም ደስ ብሏቸዋል፡፡ የጥራት ደረጃው ከፍተኛ የሆነ ለአገር ውስጥና ለዓለም ገበያ ምርት ለማቅረብ የዘመኑ ቴክኖሎጂ ውጤት የሆኑ ማሽነሪዎች ያስፈልጋል፡፡ እነዚህን እጅግ ዘመናዊ ማሽነሪዎች ከኢጣሊያ ለመግዛት ቢያዙም፣ ማሽነሪዎቹን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት መጠነኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ገጠማቸው፡፡ ስለዚህ አብሯቸው የሚሰራና የእውቀት ሽግግር የሚያመጣ ዓለም አቀፍ ኩባንያ ለማግኘት በራሳቸውና በአማካሪ ድርጅታቸው በዲዌይት በኩል ፍለጋ ጀመሩ፡፡

በደቡብ አፍሪካ በአግሮ ፕሮሰሲንግ ታዋቂ የሆነ ኩባንያ አብሯቸው ለመሥራት ፈቃደኛነቱን አሳየ። ከኩባንያው ጋር ውይይት ካደረጉ በኋላ እኔ ገንዘቡን እሰጣችኋለሁ፣ እናንተ ሥራውን ሥሩ አላቸው፡፡ የእውቀት ሽግግር የማያደርግ በመሆኑ ትተውት ሌላ መፈለግ ጀመሩ፡፡ ፍለጋቸው ሰምሮ በሰሜንና ደቡብ አሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በእስያና በአፍሪካ የካበተ ልምድና እውቀት ያለው የእንግሊዙ ኩባንያ “ቫሳሪ ግሎባል ፕሩፕ” በፈለጉት መንገድ አብሯቸው ለመሥራት ፈቃደኛ ስለሆነ፣ ከ7 ወር ድርድር በኋላ በ2013 (እኤአ) ቫሳሪ ግሩፕ አሐዱን ተቀላቅሎ አሐዱክስ ፉድ ፕሮዳክትስ አ.ማ ተቋቋመ፡፡

በቢሾፍቱ ከተማ የተሰራው ፋብሪካ ከኢጣሊያ የተገዙት ማሽነሪዎች ተገጥመውለትና ቫሳሪ ግሩፕ እውቀቱን ይዞ ማኔጅመንቱን ስለተቀላቀለ ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃ ያላቸው ብስኩቶች እያመረተ ነው፡፡ የአቶ ሰለሞን ዕቅድ የአገር ውስጥ ፍላጎት ካሟሉ በኋላ ምርቶቻቸውን ለዓለም ገበያ ማቅረብ ነው፡፡ ቫሰሪ ግሩፕ ዓለም አቀፍ የገበያ ልምድ ስላለው በቀላሉ ምርቶቻቸውን ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ያስችላቸዋል። ምርቶቻቸውን ኤክስፖርት ለማድረግ የአይኤስኦ እና ሀሳብ (Hasab) ዓለም አቀፍ ሰርቲፊኬት ያስፈልጋቸዋል፡፡ የአይኤስኦን ሰርቲፊኬት አግኝተዋል፡፡ የሀሳብን ሰርቲፊኬት ለማግኘት ደግሞ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አቶ ሰለሞን ባለትዳርና የልጆች አባት ናቸው። ከባለቤታቸው ከወ/ሮ ራሔል አሰፋ ጋር ትዳር የመሰረቱት የዛሬ 20 ዓመት ገደማ ነው፡፡ በትዳር ቆይታቸው አንድ ልጅ ወልደዋል፡፡ ነገር ግን ስንት ልጆች እንዳላቸው ሲጠየቁ መልሳቸው አምስት ናቸው የሚል ነው፡፡ አራቱ ከአብራካቸው እንደተገኙ ልጆች የሚያሳድጓቸው ናቸው፡፡ ጓደኛቸው በሞት ሲለይ፣ እናት ልጆቹን ለማሳደግ አቅም ስለተሳናት ልጆቹን ወስደው እንደራሳቸው ልጆች እያሳደጉ ነው፡፡

አቶ ሰለሞን ለወ/ሮ ራሔል ከፍተኛ ፍቅርና አክብሮት አላቸው፡፡ ብዙ ኢትዮጵያዊ ባሎች የማያደርጉትን እሳቸው ህዝብ ፊት ቆመው ሚስታቸውን አመስግነዋል፤ አሞግሰዋል፡፡ ሚስቴ ባለቤቴም የቢዝነስ ሸሪኬም ናት ይላሉ። “ሁሉንም የፕሮጀክት ሥራ የምትመራው እሷ ናት፡፡ እጅግ በጣም ጠንካራ፣ ጎበዝ፣ ደከመኝ ሰለቸኝ የማትል፣ የማቀርበውን አዲስ ሀሳብ ሁሌ የምትደግፍ ናት። እውነቴን ነው የምለው የህይወት ባልደረባዬ ብቻ ሳትሆን የቢዝነስ ባልደረባዬም ናት፡፡ ስለ እሷ ለመናገር ቃላት ያጥሩኛል፡፡ ስለ እሷ ከእኔ ይልቅ ሰራተኞቻችን ብዙ ማለት ይችላሉ፡፡ የእኔ ሥራ ከከፍተኛ አመራሮች ጋርና እውቀት ከሚያስተላልፉ ድርጅቶች ጋር ነው፡፡ ፕሮጀክቶችን እየተከታተለች ተግባራዊ የምታደርገው እሷ ናት፡፡ የዲዛይን መሠረታዊ እውቀት ስላላት ዕቃ መርጣ የምትገዛው፣ አስጭና የምታመጣው፣ ዲዛይኑ እንዲህ መሆን አለበት፣ እንዲህ ዓይነት ቀለም መቀባት አለባት …. የምትለው እሷ ናት፡፡ ….” በማለት አሞግሰዋቸዋል፡፡ወ/ሮ ራሔል ዋና መስሪያ ቤታቸው አሐዱ ኮምፕሌክስና የቢሾፍቱ ፋብሪካ ሲሰራ፣ ቱታ ለብሰውና ኬፕ አድርገው ከኮንስትራክሽን ሰራተኞች ጋር ይሰሩ እንደነበር ሰራተኞቻቸው ነግረውኛል። ከዚህም በላይ ሩህሩህና ደግ፣ ባልና ሚስቱ ሰውን በሰውነቱ፣ በእውቀትና በችሎታው እንጂ በጎሳ፣ በሃይማኖት በዝምድና የማይመለከቱ ስለሆነ በሁሉም ድርጅቶቻቸው ውስጥ የሁለቱ ዘመድ የሆነ አንድ ሰው እንኳ እንደሌለ መስክረዋል፡፡

ለዚህ ነው የብስኩት ፋብሪካው በተመረቀበት ወቅት አቶ ሰለሞን “በረጅሙ የሰነቅነውን አግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ግንባታ ሃሳብ ከማፍለቅ ጀምሮ ፕሮጀክቱ እስኪጠናቀቅ ድረስ ከአጠገቤ ሳትለይ የግልና የቤተሰብ ህይወቷን መስዋዕት አድርጋ ከጎኔ ለቆመችው ታታሪ፣ ብርቱና ሁለገብ ውዷ ባለቤቴ በህዝብ ፊት ቆሜ ስመሰክርላትና ሳመሰግናት በሥራ አጋሮቻችን ስም ነው” በማለት የተናገሩት፡፡

አቶ ሰለሞን የሥራና የውጤት ሰው ስለሆኑ ያቀዱት ነገር ውጤታማ ሲሆን ያስደስታቸዋል፡፡ አንድ ሥራ ውጤት ከሌለው ምን ተሰራ ይባላል? ድካም ነው ትርፉ ይላሉ፡፡ ለሥራ የሚመርጡት ሰዓት የለም፡፡ ስራ ከበዛ አምሽተውና ማልደው በመግባት እንደሚሰሩ ሰራተኞቻቸው ነግረውኛል። ሌላው ባህርያቸው ደግሞ ከማንኛውም ሰው ጋር ተግባብተው መስራታቸው ነው፡፡ ትልቁ ደስታቸው ደግሞ ለወገኖቻቸው የስራ ዕድል መፍጠራቸውና አገራቸው በዕድገት ጎዳና ላይ ሆና ማየታቸው ነው፡፡

የአሐዱ ኩባንያ ባለቤቶች በማህበራዊ ተሳትፎአቸውም ይታወቃሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በሚያዘው መሰረት ከሚያገኙት ትርፍ አስተዋጽኦ በማድረግ ነዳያንን ያበላሉ፤ ያለብሳሉ፡፡ በሚሰሩበት አካባቢ ላለው ህዝብ አገልግሎት የሚሰጥ ት/ቤት፣ ክሊኒክ፣ ንፁህ የመጠጥ ውሃ፣ መንገድ….. ይሰራሉ፡፡ በቅርቡ እንኳ በቢሾፍቱ ከተማ የብስኩት ፋብሪካው በተሰራበት አካባቢ ላሉ አርሶ አደሮች ከብት ማጠጫና ለመስኖ የሚሆን ውሃ ማጠራቀሚያ ገንብተዋል፤ መምህራን የወደፊቱን አገር ተረካቢ ትውልድ ቀራጭ በመሆናቸው ለእነሱ ትልቅ ክብር አላቸው፡፡ ስለዚህ ለመምህራንና ለተማሪዎች ክብር ሲሉ በቢሾፍቱ ከተማ በ12ኛ ክፍል ፈተና ከፍተኛ ነጥብ (4) ያመጡ ተማሪዎችን ፎቶግራፍ የያዘ አደባባይ አሠርተው ነገ ይመረቃል፡፡ ለሁለቱ ግንባታዎች ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ ማውጣታቸው ታውቋል፡፡ባለሀብቱ የቢሮክራሲ፣ የባንክ አገልግሎት፣ የመንገድ፣ የውሃ፣ የመብራት፣ የስልክ፣ የኢንተርኔት… የመሰረተ ልማት ችግሮች እንዳሉ ጠቅሰው ያሉትም በአገሪቷ በእኩል ደረጃ እንዳልተሰራጩ በመጥቀስ ለአብነት በቢሾፍቱ ከተማ ያለው የኢንተርኔት አገልግሎት አለ ለማለት እንደማያስደፍር ገልጸዋል፡፡የአሐዱ ኩባንያ ባለቤቶች በ10ሺህ ብር ካፒታል ጀምረው በአሁኑ ወቅት ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ አጠቃላይ ካፒታል አላቸው፡፡ ሰራተኞቹም 2500 ደርሰዋል፡፡ ምርቶቻቸውን የሚያከፋፍሉበት 40 መካከለኛና ትላልቅ መኪኖች ሲኖሯቸው፣ ወደፊትም ለወገኖቻቸውና ለአገር ዕድገት አስተዋጽኦ በሚያደርጉ መስኮች የመሰማራት ዕቅድ አላቸው፡፡ 

 

 

 

 

 

Read 3765 times