Saturday, 28 January 2012 11:43

የላሊበላ የጉዞ ማስታወሻ ማመን ማየት ነው!

Written by  ነቢይ መኰንን
Rate this item
(0 votes)

“ማየት ማመን ነው” የሚለው አባባል በየማስታወቂያው እየገባ ረከሰ፡፡ ሳስበው፤ ለካ ግልባጩም ኃይለኛ ዕውነታን ያዘለ ነው - በተለይ እንደኔ ላሊበላን ላየና  -የዕምነት ምጡቅነትና ጥልቀት ለታየው! ገጣሚ ሰለሞን ዴሬሣ፤ “ይሄ ላሊበላ የሚባል ንጉሥ፤ እዚህኛው ተራራ ላይ ቆሞ፣”ያኛውን ተራራ ፈልፍዬ ቤተክርስቲያን አደርገዋለሁ” ብሎ እንዴት ሊያስብ ቻለ? ሀሳቡን ከየት አመጣው?  እያልኩ ሁሌ እገረማለሁ” ይላል፡፡ ይሄ አባባል በጣም የገባኝ ዛሬ ነው፡፡ ላሊበላ ሄጄ፤ ከነአየሩ፣ ከነመንገዱ ውጣ ውረድ፣ ከነመንፈሳውያኑ ጠንካራ ማተብ፣ ከነፈረንጁ ደፋ ቀና፣ ከነሥነ ህንፃው ጥበብ ሳስበው፡፡ ለካ ሰውን ካልተረዱ ተዓምረኛ ቦታን መረዳት አይቻልም፡፡ ቦታው፣ ኑሮውና ነዋሪው ተዋቅረው ነው ላሊበላን ተዓምረኛ የሚያደርጉት!

ባለፈው ሳምንት እንደጀመርኩላችሁ ጉዞዬን የጀመርኩት ከቡልጋሪያ አካባቢ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ገዳማትን በሚያስጐበኘው አውቶብስ ነው፡፡ “አበሻ ወግ ሲጀምር ወይ ከአዳምና ሔዋን በጣም ቀረበ ከተባለም ከአያት ቅድመአያቶቹ ነው ይል ነበር አሰፋ ጫቦ፡፡ ውነቱን ነው፡፡ ፈርዶብን ይሁን ሳይፈርድብን እንጃ፤ ተራኪ ማህበረሰብ (Story teller society) ነን፡፡ “ነገር - ከሥሩ” ዓይነት ባህሪ ነው ያለን፡፡ እኔም አበሻ ነኝ፡፡ ከሥሩ ልጀምር፡፡ መንገዳችን መንፈሳዊ ጉዞ በመሆኑ ባንተዋወቅም ተስማምተንና ተግባብተን እንደምንሄድ ነው የሚገመተው፡፡ ግን ገና በዕቃ መጫን ተጨቃጨቅን፡፡ ወንበሩ ትኬት የተቆረጠበትና ቁጥር ያለው ሆኖም ተጨቃጨቅን፣ ከወንበሩ አናት ያለው የዕቃ መስቀያም ላይ “የእኔ ይቅደም የእኔ” መጠነኛ ሽሚያ ነበር፡፡ ወደ መካከለኛው ወንበር ላይ የተቀመጥኩ ስለሆነ፤ ከሁዋላዬም ከፊቴም የቀመጡትን ሰዎች ለመቃኘት ተመችቶኛል፡፡ ሹፌሩ ቀልጠፍ ያለ፣ ትህትና ያለው ጐልማሳ ነው፡፡ ረዳቱ ባለፈው እንደነገርኳችሁ ሆንዳ (Honda) የሚል ቲ-ሸርት የለበሰ ወጣት ነው፡፡ የ”ሆንዳ”ው መልዕክት ስላልገባኝ እንደው በደፈናው ፈገግ አልኩኝ፡፡ አሁን 1.05 ሰዓት ነው ከጠዋቱ፡፡ በ11 ቢበዛ 11፡30 የተቀጠርን ይኸው አንድ ሰዓት አለፈ፡፡ የቀጠሮ ነገር አይሆንልንም፡፡ አንዳንዴ የቀጠሮ ነገር ከአንድ የጅጅጋ ወዳጄ ጨዋታ ጋር ይያያዝብኛል፡፡ ቆይቷል እንግዲህ፡፡ ወጉ ግን ይሄው፡-  ገበያ ይወጣና አንድ ሽርጥ ሊገዛ ነው፡፡ ሻጯ ሶማሌያዊት ተቀምጣለች፡፡ ዘና ለቀቅ ብላ፡፡

“ይሄ ሽርጥ ስንት ነው?”

“ስልሣ ብር”

ገዢው ወዳጄ ገረመው፡፡ ይሄ ሽርጥ አምሣ ብር መሆኑን አሳምሮ ያውቃል፡፡ ሐረርና አካባቢው፤ እሱ በሚያውቀው አስተዳደጉ ውስጥ አንድ ዋጋ ሁልጊዜ ያው ነው፡፡ አምሣ ብር የነበረው ሽርጥ ላይ አምሣ ሳንቲም አይጨምሩም፡፡ ይሄንን ዋጋ አገሩ ሁሉ ያቀዋል፡፡ በቃ አይዋሽም፡፡ ስለዚህ ገረመውና፤ “አቦ ይሄ አምሣ ብር አይደለም እንዴ? አሥር ብር ለምን ጨመርሽ? የታወቀ ዋጋ አይደል እንዴ?” ይልና ይጠይቃታል፡፡

ሶማሌዋም፤ “አቦ፤ እሱ ለሸዋ ሰው መከራከሪያ ነዋ” አለችና እቅጩን ነገረችው፡፡

“የሸዋ ሰውስ ቢሆን?” አላት ዝርዝሩን ለማወቅ ፈልጐ፡፡

“አቦ የሸዋ ሰው፣ ካልተደራደረ፣ “እርግጡን በይ” እያለ ካልተከራከረ አይገዛማ!”

ታዲያ አሁን አሁን እኔ ሳስበው ይሄ “የእርግጡን በል” ስሜት በብዙ ነገሮች ውስጥ ይታየኛል፡፡ ሠርግ ትሄዱና 6 ሰዓት ተጠርታችሁ 7 ሰዓትም ሙሽሮች ካልመጡ፤ ያው ሙሽራ ቶሎ አይመጣም - እርግጡን በል ካላችሁ - በ9 ሰዓት ከመጡም አሪፍ ነው፡፡

የፈለገውን ሰው በ4 ሰዓት ቀጥራችሁ 4.30 ቢሆን “ወይ ታክሲ አጥቶ ይሆናል ወይ መንገድ ተዘግቶበት ይሆናል” እንልና፤ ገና ሰውዬው ሳይመጣና ምክንያቱን ሳያቀርብ፤ እኛው ምክንያት እንደረድርለታለን፡፡ ከሶማሌዋ ምሳሌ እኛ እስከሰጠናቸው ምሳሌዎች ድረስ ተደራርበው የአርፋጁ ምክንያት ሲደመር ታላቁን ፎርሙላ (ቀመር) ይሰጠናል

“አበሻ ቀጠሮ አያከብርም!”

እንግዲህ በዚህ ቀመር ለተጓዘ፤ 47 ሰዎች ለሚጓዙበት አንድ አውቶቡስ፤ ሁለት ሰዓት ማርፈድ ይሄን ያህል ደም አያፈላም፡፡ የሚገርመው የምክንያት አሰጣጣችን ዘይቤ ራሳችንን አለመጨመሩ ነው፡፡ “ሰው መቼ በሰዓቱ ይመጣል? አበሻ መቼ ቀጠሮ ያከብራል?” እያልን ምክንያት ስላገኘን፤ “ቀስ ብለን እንደርሳለን” እያልን ራሳችን ማርፈዳችን ነው!!

እንደምንም 1.05 መንገድ ጀመርን፡፡ “አረፈድን ይቅርታ”፤ አላሉንም፡፡

አልጠየኳቸውም እንጂ “እኛምኮ አውቀን ነው በ11 ሰዓት ኑ ያልነው፡፡ አበሻ ማርፈዱ አይቀርም” እንደሚሉኝ አላጣሁትም፡፡

አባ “ፀሎት እናድርስ” አሉንና ፀሎት አድርሰን መንገድ ጀመርን፡፡ የደሴን መንገድ ተያያዝነው፡፡

ከሚካኤል ቤተክርስቲያን (ቡልጋሪያ - ሜክሲኮ - አብዮት - መገናኛ - ኮተቤ”) ቀጠልን፡፡ የመንፈሳዊ ጉዞው መንፈሳዊ መዝሙር አጀበን፡፡

“…ማሪያም ማሪያም ብዬ፣ ስምሽን ልጥራው

አይደክመኝም እኔ፣ ብደጋግመው…”

ቆየት ብሎ፤

“…ሚካኤል ወረደ፣ እኛም ከቤት ወጣን

በአውደ ምህረቱ፣ ቆሟል ሊባርከን”

ሰው መዝሙሮቹን ያውቃቸዋል፡፡ አብሮ ይላል፡፡ እንዲህ በጋራ የሚዘመር ነገር ብዙ ጊዜ አይዋጣም፡፡ የብሔራዊ መዝሙር እንኳ ሙሉውን ለመዘመር ያለው ዕድል ሙሉ አይመስለኝም፡፡ በአትሌቶችም፣ በኳስ ተጨዋቾችም፣ በፓርላማ አባሎችም በኮንፈረንሶችም ሁሉ ሰው ሙሉውን መዘመሩን እጠራጠራለሁ ደግነቱ ፈተና የለም፡፡ ለሥራ ኢንተርቪውም መሥሪያ ቤቶች አይጠይቁም! ዘምሩ አይሉም እንጂ ጉድ ይፈላ ነበር፡፡

ሰው ከዘማሪው ጋር ይዘምራል፡፡ ታድሎ! ነሸጥ ሲያደርገው የማያጨበጭብ የለም!

አባ ማስታወቂያ ተናገሩ፡-

“ላይ ለተጫነው፣ ሀላፊነቱ የእኛ ነው ውስጥ ያለውን እናንተ ጠብቁ” እንዳላመንናቸው ተጠራጠሩ መሰለኝ ቀጠሉ “ቁልቢ ስለተደረገ ነገር ኢንፎርሜሽን ስላለኝ ነው” አሉ፡፡ ምን ይሆን ቁልቢ የተደረገው አልኩ፡፡ ሌብነት መሆን አለበት፡፡ ራሴው መለስኩት፡፡

ለገጣፎ … ለገዳዲ … ሠንዳፋ … እያልን ሸኖ ገባን፡፡ “አንዴ ወጣ ብላችሁ ሸኖ ማሪያምን ተሳለሙ፡፡ አሥር ደቂቃ” አሉን፡፡ አሁን ሁለት ሰዓት ከ22 ደቂቃ ነው፡፡ ተሳልመን ተመለስን፡፡ አንድ ሃያ አምስት ደቂቃ ፈጀብን፡፡

ደብረ ብርሃን ሥላሴ 3፡34 ሰዓት ደረስን፡፡ በአሥር ደቂቃ ደርሳችሁ ተመለሱ“ አሉ፡፡ ከግማሽ ሰዓት በላይ ፈጅተን መጣን፡፡ ሳቅኩኝ፡፡ ነገሩ “መሳለም ምን ጊዜ ይፈጃል” ነው በተግባር ሲታይ ግን፤ ሱቅ የሚገባም፣ መንገድ ላይ የሚገበያይም፤ ንፋስ የሚቀበልም፤ የሚፀዳዳም፤ አንዳንዴ ቡና የሚጠጣም መኖሩ ነው፡፡ የፕሮግራም መሪዎቹም፣ ተግባሪዎቹም ሁሉም የሚያውቀው ሃቅ ግን ሁሉም “ያው ያበሻ ነገር” ብሎ የሚያስታምመው ዕውነታ ነው፡፡ መቻቻል መግባባት መታገስ “ካማረሩትማ ይጨምራል ደሞ” ማለት ደስ ይላል!!

አንድ እናት ጤና አዳም ሰጡኝ፡፡ ሽታው ደስ ስለሚለኝ የማስታወሻ አጀንዳዬ ዕልባት አደረኩት፡፡ ማስታወሻዬን ስጽፍ ጤና አዳም ጤና አዳም እንዲለኝ ነው፡፡

ደብረ ሲና ዋሻውን አቋረጥን፡፡ ከዋሻው በሰላም ስለወጣን “እልልል - ” አሉ ተሳፋሪዎቹ፡፡ ሰግተን ነበር ማለት ነው፡፡ የዕልልታ therapy (ማስታመሚያ) መሆኑ ነው፡፡

ይሄ ዕልልታ አውሮፕላን ማረፊያ ላይም ይገርመኛል፡፡ በነገራችን ላይ አውሮፕላን በሰላም ሲያርፍ ሲጨበጨብ (Soft –landing) የማውቀው በኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦሌ ስናርፍ ነው፡፡ የጭብጨባ ቴራፒ ነው፡፡ ተመስጌን ማለት ነው፡፡ በላሊበላ ጉዞ ደግሞ ዕልልታ ነው!

እነዚያ በሻንጣ ሰቀላ የሚነጫነጩ፣ በዕቃ ማስቀመጥ የሚጨቃጨቁና በወንበር የሚጣሉ አበሾች፤ አሁን ደሞ ያገኙትን ቆርሰው ካላካፈሉ የማይበሉ ሆነው ተገኙ፡፡ “አበሻ ግራ - ገብቶት ግራ ያጋባሃል፡፡ ስለዚህም ይጥምሃል” ይላል አንድ ወዳጄ፡፡ እንዲህ እንደኔ ሲሰማው ነው ማለት ነው!

የከተማ ሙዚቃ የዳንስ መዳረሻ (የፍቅር ዋዜማ) እንደመሆኑ ሁሉ፣ የመንፈሳዊ መዝሙር ወደ ገዳማቱና መካነ ቤተክህነቱ የመግቢያ ቪዛ ይመስላል፡፡ ከተማን ያስተዋል ያስረሳል፡፡ ያስመንናል፡፡ የከተማው ሽብሸባ ሳይሆን የሚያጨበጭብለት፤ መንፈስ ነው፡፡ ዕምነት ነው፡፡ ደስ ይላል፡፡ መነኮሳቱ፣ እናቶቹ በጭብጨባ ሊያጅቡት ሲሞክሩ የእጃቸው አቅም እስከዚህም ስለሆነ ድምፃቸውም ኮሰስ ስለሚል፣ መንፈሳቸው ብቻ ይሞቃል፡፡  ይሄ ደሞ ለገጣሚ ከማንም በላይ ደስ ይላል፡፡ በሀሳብ ያመጥቃል - ወደ ሌሎቹ ሰማያት!! (ግጥም፣ ቅኔ፣ መንፈሳዊ መዝሙር፣ ሙዚቃ ያላቸውን ረቂቅ ግንኙነት ወደፊት እመለስበታለሁ - በተለይ ሱባዔ፣ ፀሎት እና ምናኔ ከገጣሚ ንሸጣ (inspiration)፣ ምሳጤ (contemplation)፣ አይነኬ - ዳሰሳ (Imaginative journey or navigation) ጋር ያላቸውን ግንኙነት (ወደፊት የምመለከተውን) አቤት ያወቃችሁት ለታ እንዴት ደስ ይላችሁ? እኔስ እንዴት እረካ!)

ደብረ ሲና ደረስን፡፡ ለወትሮው ለቁርስ ይወረድ ነበር፡፡ አሁን ግን የገና ፆም ስለሆነ የትኛውም ሆቴል አንወርድም ተባለ፡፡ መንገድ ቀጠልን፡፡ በአግራሞት አንዱን መንገደኛ፤

“አሁን መብላት የሚፈልግ ቢኖርስ?” የሚል ጥያቄ ጠየኩ፡፡

“የገና ፆም አይደለም እንዴ? ማን መብላት ይፈልጋል?”

ሳር አምባ ደብረ ገነት ኪዳነ ምሕህረት ገዳምን ልንሳለም ወረድን፡፡ ከፍቅር እስከ መቃብር ንባቤ በኋላ የቆሎ ተማሪ ሳገኝ ዛሬ፤ እዚህ ነው፡፡ በጣም ደስ አሉኝ፡፡ ዋናውን መጽሐፍ (በእኔ እይታ ዳጐስ ያለ ዲክሽነሪ የሚያክል መጽሐፍ) የያዘው ተማሪ ይመራል፡፡ ሌሎች ይቀበላሉ፡፡ ፎቶ አነሳሁዋቸው፡፡ የተሰጠንን ጊዜና የቆሎ ተማሪዎቹን ትምህርት የማጤንበትን ጊዜ ሳስብ ሳቄ መጣ፡፡ “አይ የከተማ ሰው” ያሰኛል፡፡ የምችለውን ያህል ሰማሁ፡፡ ቁምጣቸው፣ ኩታቸው፣ ደበሏቸው ገረመኝ፡፡ “Why do  they wear shorts? Their scarff is dirty, Their overcoat is fur!” ያለችውን  አሜሪካ ያደገች አበሻ አስታወሰኝ፤ (አጭር ሱሪ ለምን ይለብሳሉ፣ ሻርፓቸው ቆሻሻ ነው፣ ካፖርታቸው ፀጉራም ነው፤ ማለቷ ነው)

ምሣ ሸዋ ሮቢት ሆነ!

እዚሁ እያለን ጐማ ተበላሸ፡፡ አንድ ሰዓት ተኩል አቆየን፡፡

ከዚያ ወደ ደሴ ልንገሰግስ ሆነ፡፡ሹፌሩ ውነቱን ነው፡፡ “Place we can recover, time we can’t” `(ቦታን መልሰን እንይዛለን፡፡ ጊዜን ግን አንችልም) ይላል ናፖሊዮን ቦናፓርት፡፡

እዚህ ሠፈር አንድ ትዝታ አለኝ፡፡ ማሰላሰል ጀመርኩ፡፡ አንድ ሰዓት ተኩል ጀመርኩ፡፡

አጣዬ! ሰውዬው፤ መቶ አለቃ ናቸው - ያለፈው ሥርዓት፡፡ አንድ ውለታ ለሊቀመንበሩ ሠርተው ኖሮ ይህን ቦታ ያስተዳድራሉ ይባላል፡፡ የፖለቲካ ቅስቀሳ የሚካሄድበት ዕለት ነው፡፡ አገሬው ሁሉ ተጠርቷል፡፡ ሰብሳቢው መቶ አለቃ ናቸው፡፡ ከህዝቡ ጥያቄ  እንዲመጣ በተጠየቀው መሠረት በትናንሽ ወረቀቶች ጥያቄ ይላካል፡፡

መቶ አለቃው፤ የሴቶች ጥያቄ ሲመጣ ለሴቶች ተጠሪ፣ የወጣቶች ጥያቄ ሲመጣ ለአኢወማ (ለወጣት) ተጠሪ፣ የመንግሥት ፖለቲካ ንቃት ጥያቄ ሲመጣ ለካድሬው ሲሰጡ ይቆዩና እሳቸውን የሚመለከተውን ጥያቄ ለራሳቸው ያስቀራሉ፡፡ ሁሉም በየፊናቸው የደረሳቸውን ጥያቄ ይመልሳሉ፡፡ ቀሪው የመቶ አለቃ ጥያቄ ይሆናል - መቶ አለቃ ጥያቄውን ይገልፁና እንደሚከተለው ያብራራሉ፡-

“ጓዶች፤ ለእኔ የደረሰኝ ጥያቄ፤ የፓሪስ ኮሚዩን ለምን ፈረሰ? የሚል ነው፡፡ ይሄ ምን ያነጋግራል ፈረሰ! ፈረሰ! የምን ጭቅጭቅ ነው?!

መልሱ ይሄው ነው” አሉ፡፡

ትዝታዬን የኋሊት ዳስሼ ፈገግ አልኩኝ፡፡ ኮምቦልቻ ደረስን፡፡ ከሐረር መስመር ወደ አዲስ አበባ ስመጣ፤ ዱከም ስደርስ አዲስ አበባ የገባሁ ይመስለኛል፡፡ ወደ ወሎ ስሄድ ከአዲስ አበባ፤ ኮምቦልቻ ስደርስ ደሴ የገባሁ ይመስለኛል፡፡ ያባከነውን ሰዓት ለመተካት አውቶብሱ ወደ ደሴ ይበርራል፡፡ የምናርፈው ደሴ ገብርኤል ቤተክርስቲያን አጠገብ በተዘጋጀልን ማረፊያ ውስጥ ነው!

ደሴ ገባን!

ደሴ የማይታመን ብርድ ነው ያለው! ያረፍንበት ቦታ ደግሞ የባሰ ቅዝቃዜ አለው፡፡ የቆርቆሮ አዳራሽ! ጣራው ቆርቆሮ ነው፡፡ ግድግዳው ቆርቆሮ፡፡ ላዩ ታቹ ዙሪያው አጥሩ ቅዝቃዜ ነው! አዳምና ሄዋን ተንቀጠቀጡ፡፡ ሁሉ በየስሊፒንግ ባጉ (የመኝታው ከረጢት) ገብቶ የገዛ እግሩ፣ የገዛ እጁ እየበረደው፣ እየቀዘቀዘው እትትትት ይላል፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሥጋው ከመንፈሱ ሲዋሃድ የደሴን ብርድ እየተቋቋመ ለጥ አለ፡፡

“ከንጋቱ 10 ሰዓት ተነስተን ነው የምንጓዘው” ብለውናል አባ - የፕሮግራሙ መሪ!

ደሴ እቃችንን አራገፍን፡፡ በተዘጋጀው የቆርቆሮ አዳራሽ ውስጥ ቦታ መረጥን፡፡ ካጠገባችን አንድ ወጣትና አንዲት ወጣት ቦታ ይዘዋል፡፡ ሰው ገና መተዋወቅ አልጀመረም፡፡ ገና ብዙ ጊዜ አለን ለመተዋወቅ!

ራት ፍለጋ ወደ ደሴ ከተማ ወጣን፡፡

“ፒያሳ ናችሁ” ይላል ወያላው፡፡ ወደ ገብሬል ለመመለስ የሚያመቸን ፒያሳ መሆን አለበት፤ አልን፡፡ “አራዳ ናችሁ” አለ ሌላው፡፡ መቼም አራዳ የከተማ ዕምብርት መሆን አለበት፤ አልን፡፡

በአራዳው ተሳፍረን ፒያሳ ወረድን፡፡ አንድ ባርና ሬስቶራንት ገባን፡፡ “የአዲስ አበባው ቅርንጫፍ እንዳይሆን” ተባባልን፡፡ ምግብ አዝዘን ማወራረጃ አደረግን፡፡ ቡና ቤቱ ውስጥ ግርግር ተነሳ፡፡ “ግርግር ካለ ወንድና ሴት አሉ ማለት ነው” አልን፡፡ ዕውነት ነው፡፡ ግርግር፤ አዲስ አበባም ደሴም ያው ነው፡፡ “እንውጣ እንውጣ” ስንባባል፡፡ ጋብ አለ፡፡ እንደማንኛውም ግርግር!

ወደ መኝታችን ስንመለስ አገር ተኝቷል፡፡ የዘበኛው ንጭንጭ ጠበቀን፡፡

“ወንድሞቻችሁና እህቶቻችሁ ተኝተው፣ ከነሱ ተለይታችሁ ለምን አመሻችሁ?” አለ፡፡

እንዳንለያይ ህግ አለ? እሱ የዚህ ጉዳይ አላፊ ነው ወይስ እንደዓለም ብናስበው የሆነ ጉርሻ ነገር ፈልጐ ይሆን? ብቻ ይሄንኑ እያሰላሰልን ወደ መኝታችን ገባን፡፡ ብርዱም እንቅልፉም እኩል ስራውን ጀመረ፡፡ ወደ ላሊበላ ፊታችንን አዙረን ተኛን፡፡

 

ስምንት ሰዓት ተኩል ነቃሁ፡፡ ጉዟችን በ10 ሰዓት ነው፡፡ ስለዚህ እስካሁን ከላይ የፃፍኩትን ፃፍኩ - መንገድ እስከምንጀምር!

 

ከደሴ ወደ ወልዲያው ያደረግነውን ጉዞ፣ ከዚያም የላሊበላ መዳረሻችንን በሚቀጥለው ሳምንት አሳውቃችኋለሁ! ለማሳረጊያ ግን አንዱን ግጥሜን ላቅርብላችሁ! ቁጥር ሁለት በሉት ብትፈልጉ፡፡

ላሊበላ ማለት…

ላሊበላ ማለት፣ ህዝቡ ኖሯል ለካ

ላሊበላ ማለት፣ ዕምነቱ ነው ለካ

ላሊበላ ማለት ፣ ሰማያት ነው ለካ

ሰባቱን ሰማያት በምስል የሚያሳይ

የኤረር፣ የራማ፣ የኢዮር ጣራ ላይ

ሰማይ የሩሳሌም፣ ውዱድ ህዋ ርዕይ

እስከ ፅርሐ አርያም፣ ሰባተኛ ሰናይ

“በአባቴ ቤት ብዙ፣ መኖሪያ አለ”፣ ያለው

ይሄ ኖሯል ለካ፣ መጨረሻው ሰማይ፡፡

የሚታየው ገነት፣ ከማይታየው ጋ

የተናበረበት፣ የአለታት ውብ - ገላ፣ የድንጋያት ሸጋ

እሱ ኖሯል ለካ!

ላሊበላ ማለት መንገዱ ነው ለካ!

ጠመዝማዛው ዳገት - ሸርተቴው ቁልቁለት

የስቃይ መለኪያው፤ የፃድቃኑ ብርታት፡፡

ላሊበላ ማለት መከራው በረከት!

ላሊበላ ማለት ንጉሱ ነው ለካ

ቅዱሱ ነው ለካ!

ግዛቱን በመንፈስ በለታት የለካ፡፡

ማር ገላው ነው ለካ፡፡

ላሊበላ ማለት፣ ሙዚየም ነው ለካ

የአለታት ማህፀን፣ የቋጥኞች ጫካ፡፡

ላሊበላ ማለት፣ መንፈሳዊ ዜማ

ሙዚቃ ነው ለካ፤

ህንፃ እሚዘምረው፣ የጡብ ልሣን ዲካ

የያሬድ ዝማሬን በህንፃ የተካ፡፡

ላሊበላ ማለት፣ ድንጋይ - ዛብ ነው ለካ

የአለት ቋር ነው ለካ

ቋጥኝ ቋድ ነው ለካ

የአለት ኦርጅናሌ፣ የአለት ቀንጃ ኖሯል፣

መንፈስ መቀነቻ

ከአለት ተፈልፍሎ

ከአለት ተነጥሎ፤ ያላጋር ያላቻ

አጣማጅ ሳይኖረው፣ የቆመ ለብቻ!

የአለት ድግ

የአለት ድግ፤ ዲብ አካል ነው ለካ

ውበትን ከግዝፈት፣ በውል ያለካካ፡፡

ኖሯል የአለት ወጪት

ኖሯል የብር ቋጥኝ፣ ኖሯል ደንጊያ ዳካ

የቄጤማ ምንጣፍ፣ የወለላት ዳውጃ

የውሃ ላይ ኬሻ፣ የድንጋያት ገሣ

የድንጋያት ድሪ፣ ታሪክ ተናጋሪ

እሱ ኖሯል ህያው፣ እሱ ኖሯል ኗሪ፡፡

የመላዕክት ልሣን፣ የቅዱሳን ዱካ

የምድር ሁደት ዛቢያ፣ የስበት መለኪያ

የሰማይ ዙር ማሣ፣ ከዋክብትን መዝሪያ፡፡

ያለት ቅርጽ

የአለት ቅጽ

ያልታጠፈ መጽሐፍ፣ ያልተገለጠ ገጽ፡፡

ላሊበላ ማለት …

መልኩና ገበሩ፣ ያለት ቅጥ ያለት ባጥ

ይቆጡኛል ያለ፣ ያመት - ምጥ የ’ለት ቁርጥ

ላሊበላ ማለት የመንፈስ አቅም ነው

የዋሻዎች ፍልፍል፣ የአለት ውቅር ዱካ

ልብ ያልነው ነገር ነው፤ ልባችን ሲነካ!!

ታህሳስ 28, 2004 ዓ.ም

(ላሊበላና ለመንፈስ ጽናታችን)

 

 

 

Read 3371 times Last modified on Saturday, 28 January 2012 11:51