Print this page
Tuesday, 26 May 2015 08:56

“ከዓመት በኋላ በየመንደሩ እንደ ማስቲካ የሚፈነዳ ትራንስፎርመር አይኖርም”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 

 

 

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የመብራት ችግር እየባሰበት መሆኑን መናገር ለቀባሪው አረዱት ይሆናል፡፡ በቀን ከሁለት እስከ አራት ጊዜ የሚቆራረጥበት ወቅት አለ፡፡ መብራት አለ ብለው እንጀራ ለመጋገር ሲዘጋጁ እልም ይላል፡፡ ይመጣል ብለው ሲጠባበቁ በዚያው ቀልጦ የሚያድርበት ጊዜ ብዙ ነው፡፡ በአንዳንድ አካባቢ ሁለትና ሦስት ቀን ከዚያም ሲብስ ሳምንት፣ አስር ቀንና ከዚያም በላይ ጠፍቶ ሲቀር ነዋሪዎች “የመብራት ያለህ” እያሉ በየሚዲያው ይጮሃሉ፡፡ ይህ ችግር በዓመት አንዴ የሚከበሩ በዓላትንም አይፈራም፡፡ ከሦስት ዓመት በፊት ለዘመን መለወጫ እንጀራ ለመጋገር አብሲት ተጥሎ መብራት እንደጠፋ በማደሩ በዓሉን በግዢ እንጀራ ማክበራችን ትዝ ይለኛል፡፡

መንግሥትና መብራት ኃይል ችግሩ ሲነገራቸው አንዳንድ ጊዜ “ዕድገት የፈጠረው ችግር ነው፤” ሌላ ጊዜ ደግሞ “የኃይል ማነስ አይደለም፣ የማሰራጫ መስመሮች እርጅና ነው፣ በዚህ አካባቢ ያለው ትራንስፎርመር ፈንድቶ ነው” ይላሉ፡፡ በየአካባቢያችንም ብዙ ጊዜ ትራንስፎርመር ሲፈነዳ ሰምተናል፣ አይተናል፡፡

ክቡር ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገ/ሚካኤል በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የመገናኛና ኮሙኒኬሽን ክላስተር አስተባባሪና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚ/ር፣ ባለፈው እሁድ የትራንስፎርመር ማምረቻ ፋብሪካን ሲመርቁ ባደረጉት ንግግር፤ ከዓመት በኋላ ትራንስፎርመር በየመንገዱ እንደ ማስቲካ እንደማይፈነዳ ገልፀዋል፡፡

ዶ/ር ደብረጽዮን ይህንን ያሉት በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን፣ በፓወር ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ የትራስፎርመር ፋብሪካ ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃ ያላቸው ትራንስፎርመሮች እያመረተ በመላ አገሪቱ ስለሚያሰራጭ ነው፡፡

በአንድ ዓመት ውስጥ የአገሪቱን የትራንስፎርመር ፍላጐት አሟልተው ምርታቸውን ለውጭ ገበያ እንደሚያቀርቡ የገለጹት የኢንዱስትሪው ዋና ሥራ አስኪያጅ ሻለቃ አሰፋ ዮሐንስ፣ በመላው ዓለም ቻይናም ሆነች አሜሪካ የሚጠቀሙት ትራንስፎርመር ፋብሪካቸው ከሚያመርተው ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በቡራዩ ከተማ አስተዳደር በታጠቅ ኢንዱስትሪ መንደር በ350 ሚሊዮን ብር የተሠራው ፋብሪካ ለኃይል ማመንጫ፣ ማስተላለፊያ፣ ማሰራጫና ለቁጠባ የሚያገለግሉ ልዩ ትራንስፎርመሮችን ያመርታል። በዓመት 10ሺህ ትራንስፎርመሮች ያመርታል፣ ይተክላል፡፡ የጥራት ደረጃው ዓለም አቀፍ መሆኑን ማን እንዳረጋገጠላቸው የተጠየቁት ሻለቃ አሰፋ፣ የጥራት ደረጃ የሚለካው በምርት ወቅት በሚጠቀሙት የግብአት ጥራት፣ በሚያልፍበት የምርት ሂደትና በዓለም አቀፍ የጥራት ማረጋገጫ ተፈትሾ (ቴስት) ተደርጐ እንደሆነ ጠቅሰው፣ የምርታቸው የብቃት ደረጃ 99.7 መሆኑን፣ አንዳንድ የአፍሪካ አገሮች ጥያቄ ስላቀረቡ ከዓመት በኋላ ለውጭ ገበያ እንደሚልኩ ተናግረዋል፡፡

ፋብሪካው 1‚200 ሠራተኞች ሲኖሩት አብዛኞቹ፣ ከዩኒቨርሲቲዎችና ከቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የተመረቁ ወጣቶች ናቸው፡፡ በፋብሪካው የኢንሱሌሽን፣ የዋይንዲንግ (ሽቦ መጠምጠም)፣ የአሴምቢሊንግ (መገጣጠሚያ) የኦይሊንግና ቴስቲንግ ወርክሾፕ የሚሠሩ አሉ፡፡

በእያንዳንዱ ወርክሾፕ የተመደቡት ወጣቶች ሁለት ሁለት ሆነው ነው የሚሠሩት፡፡ ሊዲያ ተስፋማርያምና ኢዮብ ዳና በኢንሱሌሽን ወርክሾፕ ሲሠሩ ነው ያገኀኋቸው፡፡ ሊዲያ የ21 ዓመት ወጣት ስትሆን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኬሚካል ኢንጂነሪንግ ተመርቃለች። ኢዮብ 23 ዓመቱ ሲሆን ከቲቪቲ ኮሌጅ የተመረቀ ቴክኒሻን ነው፡፡ የወጣቶቹ ሥራ በትራንስፎርመሩ የሚጠቀለሉት ኤሌክትሪክ አስተላላፊ ሽቦዎች እንዳይገናኙ በየመስመሩ ልዩ ዓይነት ኦርጋኒክ ወረቀት ማስገባት ሲሆን  ወረቀቱ ሌላም አገልግሎት አለው፡፡ በትራንስፎርመሩ የሚጨመረውን ዘይት ይመጣል፡፡

በኮኔክሽን ወርክሾፕ ሲሠሩ ያገኘኋቸው መቅደስና ታደሰ ጂጌ ኤሌክትሪሻኖች ናቸው፡፡ የ24 ዓመቷ መቅደስ ከወሊሶ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ነው የጨረሰችው፡፡ ታደሰም የ24 ዓመት ወጣት ሲሆን ከጂማ ዩኒቨርሲቲ በኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ተመርቋል፡፡ የወጣቶቹ ሥራ ከኃይል ማሰራጫ የሚመጣውን ኃይል ተቀብሎ ወደ ትራንስፎርመሩ የሚያደርሰውን ሽቦ መትከል ነው፡፡ በዚህ ዓይነት በሁሉም ወርክሾፖች ወጣቶች ተመድበው እየሠሩ ነው፡፡

 

 

 

 

 

Read 2579 times
Administrator

Latest from Administrator