Print this page
Tuesday, 26 May 2015 08:51

“...ስኬት የሚለካው .... በገንዘብ ትርፍ አይደለም...”

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 

 

 

በአዲስ አበባ እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር ማርች 23 እና 24/ በምህጻረ FIGO የተሰኘው አለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅት በ8ኛው አህጉራዊ ስብሰባው ጥንቃቄ የጎደለው ጽንስ ማቋረጥን በመከላከል ረገድ ምን ገጽታ አለ ወደፊትስ ምን መደረግ ይገባዋል የሚል ውይይት በአዲስ አበባ አድርጎ ነበር፡፡ በዚህ ስብሰባ ተሳታፊ ከነበሩት ውስጥ የደቡብ አፍሪካውንና የኡጋንዳውን ተወካይ በአገራቸው ስላለው ሁኔታ ሀሳብ እንዲሰጡ አነጋግረናቸዋል፡፡ በዚሁ አህጉራዊ ስብሰባ ላይ ከተነሱ ነጥቦች የምናስነብባችሁ እውነታ በዚህ እትም ተካቶአል፡፡ጥንቃቄ የጎደለው ጽንስ ማቋረጥ በተለይም በአፍሪካ አነጋጋሪነቱ ዛሬም እንደቀጠለ ነው፡፡ ምንም እንኩዋን ሀገራቱ እንደ አመቺነቱ የየራሳቸውን የአሰራር ደንብ ቢቀርጹም አሁንም በህብረተሰቡ ዘንድ ጉዳት ሲከሰት መስተዋሉ አልቀረም፡፡ ይህንን የሚመሰክሩት ከየሀገራቱ የመጡ ባለሙያዎች ሲሆኑ የኡጋንዳው ተወካይ የሚከተለውን ብለዋል፡፡“...ዶክተር ቺክ ጎምቸልስ እባላለሁ፡፡ የፅንስ እና ማህፀን ህክምና እስፔሸሊስት እንዲሁም በኡጋንዳ የፅንስ እና የማህፀን ሐኪሞች ማህበር ፕሬዝዳንት ነኝ፡፡ ፅንስ ማቋረጥ በኡጋንዳ በልማድ ሲሰራ የቆየ እጅግ ጎጂ ነገር ነው፡፡ በማህፀን ውስጥ የተለያዩ ነገሮችን በመጨመር እንዲሁም የተለያዩ ኬሚካሎችን በመውሰድ ጭምር የተፀነሰውን የመግደል ስራ ነው የሚሰሩት፡፡ ምንም እንኳን በተለያዩ ምክንያቶች ፅንስን ማቋረጥ የተለመደ ነገር ቢሆንም አብዛኛው ድርጊት ግን ጎጂ ሆኖ ነው የቆየው፡፡ በኡጋንዳ ሴቶች በተለያየ መንገድ ጥንቃቄ በጎደለው መንገድ ፅንስን ማቋረጣቸው በህይወት ላይ ከፍተኛ አደጋ ሲያስከትል ቆይቷል፡፡ በየአመቱም 300,000/ ያህል ጥንቃቄ የጎደለው ፅንስን ማቋረጥ የሚኖር ሲሆን ይህም  በምስራቅ አፍሪካ ከፍተኛው ቁጥር ነው፡፡ፅንስን ማቋረጥን በሚመለከት በኡጋንዳ በህግ የተደነገገ አሰራር አለው፡፡ ለዚያም መነሻ የሆነው አብዛኛው ፅንስን ማቋረጥ የሚሰራው ንፅህናውን ባልጠበቀ እና ጥንቃቄ በጎደለው መንገድ በመሆኑ ነው፡፡ አብዛኞቹ የጤና ባለሙያዎች ፅንስን በማቋረጡ ሂደት በቂ ግንዛቤ አላቸው የሚል እምነት የለኝም፡፡ ስለዚህ ጽንስን ማቋረጥ ግማሽ ያህሉ እውቀት ባላቸው ሰዎች የሚሰራ ሲሆን ግማሽ ያህሉ ግን በሴቶቹ በራሳቸው እንዲሁም በተለያዩ እውቀቱ በሌላቸው የቤተሰብ ወይንም የህብረተሰብ አባላት ነው፡፡ ጥንቃቄ በጎደለው መንገድ ፅንሱን በሚያቋርጡበት ግዜ ሴቶቹ ለተለያየ ጉዳት ይጋለጣሉ፡፡ ደም መፍሰስ፣ ኢንፌክሽን፣ የማህፀን መቧጠጥ፣ መቁሰል የመሳሰሉት ሁሉ ከሚደርሱት አደጋዎች መካከል ናቸው፡፡ በኡጋንዳ በቀን እስከ ስድስት ሴቶች ፅንስን በማቋረጥ ምክንያት ህይወታቸው ያልፋል። በአመትም እስከ 4,200/ ሴቶች ጥንቃቄ በጎደለው ፅንስ ማቋረጥ ምክንያት ህይወታቸው ያልፋል፡፡ አሁን ችግሩን ለመፍታት ጥረት በማድረግ ላይ ነን፡፡

በእርግጥ ልንደርስ ካሰብንበት ቦታ ለመድረስ ገና ይቀረናል ነገር ግን የሴቶቹን ህይወት ለማዳን በምናደርገው እንቅስቃሴ የኡጋንዳ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ድጋፍ እያደረገልን ሲሆን ጥሩ ጥሩ ፖሊሲዎች ተቀርፀዋል፡፡ በህጉም በኩል እንደገና የሚታዩ  ሚሻሻሉ ነገሮች ስለአሉ ሁኔታው  እየተሸሻለ ነው፡፡ ስለዚህም በወደፊቱ አሰራር ጉዳቱ እየቀነሰ እንደሚመጣ እሙን ነው፡፡

የምጨምረው የግል አስተያየቴን ነው በማለት ዶክተር ቺክ ጎምቸልስ የሚከተለውን ሀሳብ ሰንዝረዋል፡፡

“”....ያልተፈለገ እርግዝና አንድ ወንድና አንንዲት ሴት በፍቅር ተግባብተው የሚፈጥሩት ሲሆን በኋላ ግን የሴቷ ችግር ይሆናል፡፡ ከስነልቦና ጉዳቱ ባሻገር ወደ አካል ብሎም ህይወት እስከ ማጣት ድረስ ጉዳት የሚደርሰው በሴቷ ላይ ነው፡፡ ይህንን እንደ አንድ ትልቅ የሀገር ጉዳይ መመልከት ይገባናል፡፡ ሴቶች በወሲብ ግንኙት ወቅት እንዲወስኑ፣ መቼና ምን ያህል ልጆች እንደሚያስፈልግ፣ እርግዝናው እንደማያስፈልግ ሲታወቅ ምን ማድረግ እደሚገባ ምርጫ እንዲኖራቸው እና ከሚደርስባቸው ጉዳት እራሰቸውን እንዲጠብቁ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡” ብለዋል፡፡

በማስከተል የጋበዝናቸው እንግዳ ከደቡብ አፍሪካ ናቸው፡፡  

“...ስሜ ኤኪ ሙስታንጋ ይባላል፡፡ የመጣሁት ከደቡብ አፍሪካ ነው፡፡ በደቡብ አፍሪካ ፅንስ ማቋረጥ ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን ጥረት እያደረግን ነው፡፡ የቀድሞው የጤና ጥበቃ ሚኒስትር የዛሬ አፍሪካ ዩኒየን ቼር ፐርሰን የሆኑት ሰው ሴቶች ደህንነቱ የተጠበቀ ፅንስ ማቋረጥ እንዲያደርጉ የተቻላቸውን ሁሉ አደርገዋል፡፡ ከዚህም በመነሳት ህብረተሰቡም መብቱን አውቆ በጤና ተቋማት እንዲገለገል ባለሙያዎችም የእናቶችን መብት በማክበር እና ሙያውን በትክክል በመተግበር የሚችሉበትን አቅም በስልጠና እና በመሳሰሉት መንገዶች እየገነባን ነው፡፡ ስለሆነም ደህንነቱ ባልተጠበቀ መንገድ በሚከናወን ጽንስ ማቋረጥ ምክንያት በደቡብ አፍሪካ ህይወታቸውን የሚያጡ ሴቶች ቁጥር እየቀነሰ ነው፡፡ አሰራሩን በህግ የተደገፈ ለማድረግ ሕግ የወጣው በ1996 ዓም/ ሲሆን ተግባራዊ ማድረግ የተጀመረው ግን በ1997 ዓም/ ነው፡፡ ቀደም ሲል ሴቶቹን በህክምና ለመርዳት የተስማሙት ሶስት ዶክተሮች ብቻ ሲሆኑ ህጉ ከወጣ በኋላ እና አሰራሩ ከተሸሻለ በኋላ ግን በርካታ ባለሙያዎች ህይወት እያዳኑ ነው፡፡

ባጠቃላይም በደቡብ አፍሪካ ከሚሞቱት እናቶች 30% የሚሆኑት ምክንያታቸው ደህንነቱ ያልተጠበቀ ፅንስ ማቋረጥ ነበር፡፡ አሁን ግን በዚሁ ምክንያት የሚሞቱት ሴቶች 8% ብቻ ናቸው፡፡ 

በስተመጨረሻም ኤኪ ሙስታንጋ የተናገሩት...

“...በአፍሪካ ያለን ሰዎች ሁሉ ለሴቶች ክብር እና ከፍ ያለ ግምት ልንሰጣቸው ይገባናል፡፡ እነዚህ ሴቶች ትውልድን ለመተካት የሚችል ተፈጥሮ ያላቸው ብርቅዬዎች ናቸው፡፡ የሚጠቅማቸውን እና የሚጎዳቸውን ለይተው ስለሚያውቁ ሌሎች ሊወስኑላቸው አይገባቸውም፡፡ ስለዚህ እንስማቸው፡፡ ምርጫቸውንም እንጠብቅላቸው ሊያደርጉ የሚፈልጉት ነገር ካለም እንደግፋቸው፡፡” ብለዋል፡፡  

ጽንስን በመድሀኒት ማቋረጥ ጠቀሜታው በተለያየ መንገድ ሊመዘን ይችላል የሚለን  ኮንሰፕት የተሰኘው በ1989 ዓ/ም የተቋቋመው በተለይም የመካከለኛና ዝቅተኛ ደረጃ  ባላቸው አገሮች የስነተዋልዶ ጤና በጥሩ ሁኔታ እንዲጠበቅ ለማድረግ ከየሀገራቱ ጋር የሚሰራ ድርጅት ነው፡፡

በመድሀኒት አማካኝነት ጽንስን በተገቢው መንገድ ማቋረጥ በተለይም በታዳጊ ሀገሮች ያለው ጠቀሜታ የጎላ ቢሆንም ይላል ኮንሰፕት አንዳንድ አመቺ ያልሆኑ ነገሮች መከሰታቸው አልቀረም፡፡ ለምሳሌም የመድሀኒቶች ውድነት ከሚጠቀሱ መካከል ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ጥራትና አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ላይሆን ይችላል እንደ ኮንሰፕት እማኝነት፡፡ ከአምራቾች አኳያ ጉዳዩን ስንመለከተው ይላሉ መድሀኒቱን ለማዘዝ የፍላጉት መቀዝቀዝ ፈቃደኝነት ማጣትና በመድሀኒቱ ተጠቅሞ ተገቢውን አገልግሎት የማዳረስ ችሎታ በታዳጊ ሀገራቱ እየታየ አይደለም፡፡

በመድሀኒት አማካኝነት የሚደረግ ጽንስን ማቋረጥ ከ96-99% ውጤታማ ነው። ምናልባትም ውጤት አልባ ነው ቢባል 5% ብቻ ነው፡፡ በተጨማሪም ጎጂ ጎኑ መጠነኛ እና በፍጥነት ያልተፈለገውን ጽንስ ለማስወገድ ይረዳል፡፡ ስለዚህ ህ/ሰቡ በቂ ግንዛቤው እንዲኖረው ማድረግና አገልግሎቱን ምቹ ማድረግ ተገቢ ይሆናል፡፡

በስብሰባው ላይ ከተሳተፉት ድርጅቶች ፓስ ፋይንደር አንዱ ሲሆን ልምዱን እንዳካፈለው ከሆነ ከ55 አመት በላይ ጽንስን በማቋረጥ ረገድ በሁለቱም  ማለትም ሕግ ባወጡም ባላወጡም ሀገራት ስራዎችን በመስራት ላይ ነው፡፡

እንደፓስ ፋይንደር እማኝነት ጽንስን ማቋረጥ ትኩረት ሊደረግበት የሚገባው በቀጥታ ከእናቶች ሞታ ጋር ስለተያያዘ ብቻ ሳይሆን ከሴቶች የስነተዋልዶ ጤና ጋር በተገናኛ መሰረታዊ መብታ ቸው ሊከበር ስለሚገባውም ጭምር ነው።

በአለማችን ወደ 220/ሁለት መቶ ሀያ ሚሊዮን ሴቶች ዘመናዊ የሆነውን ያልተፈለገ እርግዝና መከላከያ አያገኙም፡፡ የእርግዝና መከላከያውን ቢያገኙ ኖሮ፡-

ያልተፈለገ እርግዝና ከ60% በላይ ይቀንሳል

የጨቅላ ሕጻናት ሞት በ44% ይቀንሳል

150,000 ያህል የእናቶች ሞት ይቀንሳል

600,000 ህጻናት እናቶቻቸውን በሞት አይነጠቁም፡፡ ይህ መረጃ ከ Women Care Global (WCG) የተገኝ ነው፡፡

ድርጅቱ እንደገለጸውም፡-

“...ስኬት የሚለካው በሴቶች ሕይወት መሻሻል እንጂ በገንዘብ ትርፍ አይደለም...”

በአለም አቀፍ ደረጃ በአመት በአማካይ 40/ ሚሊዮን የሚሆን ጽንስን የማቋረጥ ተግባር የሚፈጸም ሲሆን ከዚህም ከግማሽ በላይ ደህንነቱ የተጠበቀ አይደለም፡፡

ወደ 90% የሚሆነው ደህንነቱ ያልተጠበቀ ጽንስ ማቋረጥ የሚፈጸመው በታዳጊ ሀገራት ነው፡፡

ደህንነቱ ያልተጠበቀ ጽንስ ማቋረጥ ለእናቶች ሞት በዋና ምክንያትነት ከሚጠቀሱት ከ5ቱ ገዳዮች አንዱ ነው፡፡

 

 

 

Read 3981 times
Administrator

Latest from Administrator