Tuesday, 26 May 2015 08:48

አንድነት፡- የራስ ወዳድነት መጠን ያለው ውበት ነው

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 

 

 

              “መንግስት፤ እኔ ነኝ የአገሪቱ ደራሲ ይላል”

    ይኼንን ያለው አልበርት ካሙ ነው፡፡ አንድነት ግን በተጨባጩ አለም ሊገኝ የሚችል ነገር ሳይሆን ሲቀር፣ አርቲስቱ ተጨባጩን እውነታ በማፈራረስ ከፍርስራሹ ውስጥ የራሱን የምናባዊ አለም አንድነት እንዳለው አስመስሎ ያቀርበዋል፡፡ ይፈጥረዋል፡፡

“አንድነት በተለዋጭ አለም ይኸው እንዴት ውብ እንደሆነ” ብሎ ያቀርባል፡፡ እናም የፈጠረው አንድነት የተሳካ ከሆነ ተቀባይነት ያገኛል፡፡ የፈለገ ምናባዊ ቢሆንም ግን ፈጠራው  ቀድሞ ከነበረው የእውነታ አለም የራቀ አይሆንም፡፡ ከራቀ የሚረዳውን አያገኝም፡፡ ካላገኘ፤ አንድነቱ የቱ ጋ ነው? የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡

ግን ተሳካለት እንበል፡፡ ማለትም የፈጠረው ምናባዊ ጥበብ አንድነትን በሰው እና በፈጣሪ መሀል ወይንም በሰው እና በማንነቱ … መሀል ያሉትን ቲዎሪያዊ ጥያቄዎች ሁሉ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ደፈነ፡፡ እና ምን ይከተል? ሲፈለግ የነበረው የፈጠራ ጥግ ተደረሰ ተብሎ ፍለጋው ይቆማል?

አይቆምም፡፡ የፈለገ አይነት ስኬታማ ድርሰት ቢዋቀር የሰው ልጅ የአንድነት ፍላጐት አይረካም። ደራሲው ራሱ እንኳን የመጨረሻው የውበት (አንድነት) ጥግን ነክቻለሁ ካለ በኋላ የራሱን መጨረሻ ለመብለጥ ሌላ ድርሰት ይጽፋል፡፡ ህይወቱ እስኪያከትም ድረስ ውድድሩን አይገታም። … የሚወዳደረው ከራሱ ጋር ነው፡፡ ወይንም ከራስ ወዳድነቱ ጋር፡፡

ምናልባት ጥበበኝነት ከራስ ወዳድነትም ጋር የሚጣመርበት ስፍራ ሊታየን የሚችለው እዚህ ላይ ሳይሆን አይቀርም፡፡

ማርሴል ፕሮስት፤ “In remembrance of the times past” በተባለው ዐብይ እና ትልቅ ስራው አንድነትን የፈለገበት መንገድ ወደራሱ የትዝታ አለም በመመነን ነው፡፡ ተጨባጩን አለም አፈራርሶ የእሱን ጠባብ የውስጥ ግዛት አለምን አሳክሎ በማብዛት ታላቅ ፈጠራን ሰራ፡፡ ከሰው ልጅ ጋር ራሱን “አንድ” ለማረግ የመረጠው መንገድ… የሰው ልጅን ሁሉ ወደ እሱ አተያይ በመቀየር ነው፡፡

ማርሴል ፕሮስት፤ ያደረገውን ያላደረገ ፈጣሪ በመሰረቱ የለም፡፡ የአንድነት ብቸኛ ፍቺ ነው የምንለው የሙሉኤ ኩሉው እውነታ ደራሲ (እግዚአብሔር) እንኳን… ሁሉንም ነገር የከወነው ከራሱ አልፋ እና ኦሜጋዊ አተያዩ አንፃር አይደል? የአንድነት ፍላጐት ከራስ ፍላጐት አንፃር እስከሆነ ድረስ ወደ ጠቅላይ ስምምነት የሚያደርስ ፈጠራ ሊኖር አይችልም፡፡

በዚህ ምክንያት የውበት ፍቅር፣ የእውነት ፍቅር ወይም የአንድነት ፍቅር ከራስ ወዳድነት ፍቅር ጋር ያልተከለሰበት ውበት ተሰርቶ  አያውቅም፡፡

ለምሳሌ ፍቅር ሁሉ አንድነት ነው፡፡ ወንድ እና ሴት አንድ ለመሆን ወደ ፍቅር ይገባሉ፡፡ ግን አንድነታቸው ተዋረድ አለው፡፡ በተለምዶ ወንዱ አንድ አድራጊው ሀይል ነኝ ብሎ ሊያምን ይችላል፡፡ “የእኔ ነሽ … ባለቤትሽ ነኝ” ይላታል‘ኮ አፍ አውጥቶ። የፍቅራችን የአንድነት ደራሲ እኔ ነኝ ማለቱም ነው፡፡ ነገሩ ፍቅር ነው፣ ውበት ነው፤ ግን ውበቱ የተቀረፀበት አንፃር አለው፡፡

ማን ነበረ፤ “We are too small in mind and body to possess other people without pride or to be possessed without humiliation” ያለው እንደዚያ ነው ነገሩ፡፡

ነገሩ ደግሞ ሰው የሚፈጥራቸው ጥበባዊም ይሁን መንግስታዊ አንድነቶች ውስጥ ግዙፍ እውነት ሆኖ ይገኛል፡፡ “እኔ ነኝ የሀገሪቷ ደራሲ ይላል” መንግስት፡፡ ባልዬው፤ “እኔ ነኝ የቤተሰቡ እራስ” እንደሚለው፡፡

የመጽሐፍ ደራሲውም፤ “እኔ ነኝ የድሮውን እውነታ ፈታትቼ በአዲስ መልክ ፈጥሬ ያዋቀርኩት” ይላል፡፡ በራሱ ለመኩራት ሲል ፈጠራውን የሚከውነውን ያህል የአንድነት ፍላጐትም በተፈጥሮው አድሮ ውበትን ለመጨበጥ ያነሳሳዋል፡፡ ግን “እኔ አንድነቱን ካልፈጠርኩት ሳይፈጠር ይቅር! ወይንም ቢፈጠርም ተፈጠረ ሊባል አይችልም” የሚለው ምክኒያት ዋናው የተግባሩ የመነሻ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም፡፡

በአንድ ድርሰትም ሆነ በአንድ የመንግሥት አስተዳደር ጥንቅቅ ያለ የአንድነት ንድፍ ሊገኝ የማይችለውም ለዚህ ይመስለኛል፡፡ (ከመሰለኝ ደግሞ…!)

ህዝብና መንግስት መሀል ጭቆና የሚኖረው፣ መንግስት ራሱን እንደ ደራሲ ሲያይ ነው፡፡ መንግስትን የሚተካ ሌላ ደራሲ የሚነሳው ከበፊተኛው ድርሰት ራስ ወዳድነት ውስጥ ነው፡፡ ግን በዛው መጠን መዘንጋት የሌለበት አዲሱ ደራሲም አዲስ አንድነት ለማምጣት የሚጥረው ለህዝቡ ሲል ሳይሆን ከራሱ “Ego” (ፍላጎት) ተነስቶ ነው፡፡

ግን ማንም ደራሲ ቢመጣ፤ የቀደመውን ምናባዊ ድርሰት፣ በሌላ ምናባዊ አለም ቢለውጥ፣ ወይንም ተጨባጩን ቢሮክራሲ በሌላ አሻሻልኩ ቢል፣ ከራሱ እይታ አንፃር እስከሆነ ድረስ ጥቅሉ ውበት (አንድነት) አይጨበጥም፡፡

ባል ሚስቱ ጥላው ስትሄድ አልያም መንግስትን ህዝብ አልወድህም ሲለው…የፍቅሩ መቋረጥ ከሚቆረቁረው ይበልጥ ሚስት እሱን ትታው ሄዳ ሌላ ባል (ሌላ መንግስት) ማግኘቷ እንደማይቀር ማወቁ የስቃዩ እውነተኛ ምንጭ ነው፡፡

ብዙ የአንድነት አይነት አለ፡፡ ግን የራስ ወዳድነቱ አይነት አንድ ነው፡፡ “ሳዲስት” ከ “ማሶቺስት” ጋር አንድነት ይፈጥራሉ፡፡ ፍቅር ይመሰርታሉ፡፡ ህዝብን የሚሰድብ ደራሲን መጽሐፍ የሚገዛ፣ መሰደብ ከሚወድ ህዝብ … የገበያም ሆነ የመናበብ ትስስር ይፈጥራል፡፡ የፍቅር አይነት ነው፡፡ ሌላው ደግሞ እንክብካቤ እና ጥሩ ህይወት በምትፈልግ ሚስት እና ፍላጐቷን በሚያሟላ ባል መሀል የሚፈጠር አንድነት አለ፡፡ ግን አንድነቱ በጥል እና ባለመስማማት ይፈታል፡፡ አለመስማማት ማለት ሁለቱም የአንድነት መስራች አካሎች ራሳቸውን ማስቀደማቸው ግልፅ ሲወጣባቸው፣ አንድ የሚያደርጋቸው ነገር ሳያሳምን ሲቀር ነው፡፡

እስካሁን የተሰራው የሰው ልጅ የድርሰት መፅሐፍ ለምን አንድ ላይ ተደምሮ ትልቅ ውበት ማግኘት አልተቻለም? የሚል ጥያቄ ከመጣ መልሱ፡- የማንም የራስ ወዳድነት ንድፍ ከሌላው ጋር ቢደመር ትልቅ ራስ ወዳድነት እንጂ ትልቅ ውበት ወይንም ፍቅር አይወጣም፤ የሚል ይመስለኛል፡፡

ትልቅ ራስ ወዳዶች ትልቅ ጥበብን ይፈጥራሉ። በጥበቡ የሚስማማላቸው፣ በእነሱ እይታ መነፅር አለምን ለማየት ህዝቡ ወይንም ተደራሲያቸው እስከፈቀደላቸው ድረስ ሳይፈቅድ ሲቀር ሌላ ደራሲ የድሮውን አንድነት በራሱ አዲስ አተያይ ለውጦ እንዲያሳያቸው ይፈቅዳሉ፡፡ ሲፈቅዱ የወጣውን አውርደው የወረደውን አዲስ የአንድነት ደራሲ ያነግሳሉ፡፡

ትልቅ ራስ ወዳዶች ጥበብን ይፈጥራሉ፡፡ ራሳቸውን ከፈጣሪ፣ ከተፈጥሮ፣ ከስነምግባር ልዕለ ትርጉም ጋር ለማስተሳሰር ሲሉ፤ … ግን ለማሰር የሚሞክሩት በድርሰታቸው የደረሱትን ህዝብ ነው። ህዝብም ራስ ወዳድ ነው፡፡ ህዝብም ሰው ነው፡፡

ህዝብ ለመንግስት እንደ ሚስት ይመስላል፡፡ ባል ስልጣኑን ሲጭንባት ሚስት አሜን ብላ ትቀበላች፡፡ … ግን ጭነት ሲበዛባት ፍቅሯን (አንድነቷን) መጠርጠር ትጀምራለች፡፡ ጀምራ ከቀጠለች ባሏን ጥላ መሄዷ አይቀርም፡፡

ሚስቱ ጥላው የምትሄድ ባል፣ ህዝቡ ጥሎት የሚሄድ መንግስት ይበግናሉ፤ ይቃጠላሉ። የሚያቃጥላቸው ከህዝቡ ጋር የነበረው ፍቅር ከልባቸው አልወጣ ስለሚላቸው አይደለም፡፡ የሚያብከነክ ናቸው፡፡ ጥላ የሄደችው ሚስት ሌላ ባል ማግኘቷ እንደማይቀር በማወቃቸው ነው፡፡

በራስ ወዳድነት ላይ ተመስርተው የሚፈጠሩ አንድነቶች ሁሉ … አንድነት ሆነው የሚቆዩት ለተወሰነ ጊዜ ነው፡፡ የተወሰነው ጊዜ ሲያልቅ … ሁሉም ፈጣሪ ነን ባዮች ወደ ተራነት ይመለሳሉ። መንግስትም ይቀየራል፣ ትዳርም ይፈርሳል፣ የገነነ ድርሰትም ከመፅሐፍ መደርደሪያ ላይ ወርዶ በሌላ ግነት ይተካል፡፡ የአንድነት ፅንሰ ሀሳብ ገናና የሚሆነው … የግለሰብ ራስ ወዳድነትን መጠን ያህል ነው፡፡

 

 

 

Read 2848 times