Tuesday, 26 May 2015 08:25

ኢቫን አንድሪየቪች ክሪሎቭ

Written by  ፕርስፎራ ዘዋሽራ
Rate this item
(2 votes)

“በግጥሞቼ ፈገግ እላለሁ፤ በልቤ ግን ግፍን እያስታወስኩ አለቅሳለሁ”

   በዐሥራ ዘጠነኛው መቶ ክፍል ዘመን ላይ የሩሲያ መጽሔታዊ ሥላቅ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር፡፡ የመጽሔት ዝግጅት ክፍል ኃላፊ የነበረው ደግሞ ኢቫን ክሪሎቭ ነው፡፡ ካንቴሚር “በግጥሞቼ ፈገግ እላለሁ። በልቤ ግን ግፍን እያስታወስኩ አለቅሳለሁ” እንዳለው ክሪሎቭም የካንቴሚርን ይትበሃል ጠብቆ መጽሔት ያሳትም ነበር፡፡ ክሪሎቭ ተሣላቂ /ሣታየሪስት/ እና በጣም ርኅሩኅ /ሰብዓዊ/ ደራሲ እንደነበር ይነገርለታል፡፡

ክሪሎቭ “የደብዳቤው መንፈስ” በሚል ዓምዱ ቦሬይን የተባለው ጸሐፊ “እብደታቸውን ሳልመለከት ሰዎችን እወድዳቸዋለሁ” በሚል የጻፈውን ሐተታ በመጽሔቱ ላይ አሳትሞ ተደናቂነትን አግኝቷል፡፡

ኢቫን አንድሪየቪች ክሪሎቭ የተወለደው የካቲት 13 ቀን 1769 ሞስኮ ከተማ ውስጥ ነው፡፡ ቤተሰቦቹ ብዙም ሀብት አልነበራቸውም፡፡ ወላጅ አባቱ አንድሪየቪች የጦር ሠራዊት መኮንን ነበር፡፡ በ1774 አንድሪየቪች ጡረታ ሲወጣ ኑሮን ለመቋቋም ሲል ከዋና ከተማው ከሞስኮ “ትቮር” ወደ ተባለች አነስተኛ ከተማ ሲሄድ ክሪሎቭም ቤተሰቦቹን ተከትሎ ወደዚያው ሄደ፡፡ ትቮር በዘመኑ የሳይንስና የባህል ማዕከል ስለነበረች ለወጣቱ ክሪሎቭ መልካም አጋጣሚ ተፈጠረለት፡፡

ትቮር ከተማ የቴአትርና የሥነ ጽሑፍ ማዕከል ተቋቁሞ ትምህርት ለወጣቶች በሴሚናርና በውይይት ደረጃ ይሰጥ ነበር፡፡ ክሪሎቭም ወደ ማዕከሉ በመሄድ የሚሰጠውን ትምህርት በንቃት ተከታተለ። በተለያዩ ቴአትሮችና የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ላይ የሚደረገው ውይይት፣ ክርክርና በዐውደ ጥናቱ ላይ የሚሰጠው የማጠቃለያ ሐሳብ ወይንም አስተያየት ለወጣቱ ክሪሎቭ በእጅጉ ጠቃሚ ነበር። በዚህ ዓይነት ቴአትርንና ሥነ ግጥምን ለማጣጣም በመቻሉ ለኪነጥበብ ከፍተኛ ፍቅር አደረበት። መምህራንና ተማሪዎች በትምህርት ቤቱ ውስጥ በሥላቅ ላይ ያተኮረ ድርሰት ሲያነብቡና ድራማም ሲያቀርቡ ክሪሎቭ በየጊዜው መንፈሱ ይመሰጥ ጀመር። በተለይ የገጣሚ ፌዎዶር ሞዴስቶቭን ግጥም ከሰማ በኋላ መላ ሕይወቱን በኪነጥበብ ዙሪያ ተሠልፎ ለመኖር ወሰነ፡፡ የሞዴስቶቭ ግጥም የሚከተለው ነው፡-

“ለመኖር ከፈለግህ በሰላም በርጋታ፣

ፈጣሪን ሳትሰለች አመስግን ጠዋት ማታ፣

ከመከራው ጉድጓድ ያወጣሃል ጌታ፡፡

ከክፉ አድራጊዎች ከየገበታቸው፣

እንዳትበላ ፍሬ ከጠረጴዛቸው፣

አብረህ እንዳትጓዝ በሰረገላቸው፡፡

ሰረገላቸውን እርሳው እንደ ሞተ፣

በእግርህ መንቀሳቀስ ይበጅሃል ለአንተ፡፡

ክፉ አድራጊዎቹ ጥሩ ወዳጅ መስለው፣

በውሸት ፈገግታ ልብህን አሙቀው፣

ያፈቀሩህ መስለው፣

መርዝ ያቀርቡልሀል በውሃ በርዘው፡፡

አንተም ምስኪኑ ሰው ያኔ ትወድቃለህ፣

ይህ ነው የእነርሱ ቅርስ የተላለፈልህ፡፡”

ለትቮር ነዋሪዎች በሴሚናር መልክ የሚተላለፈው የሥነጽሑፍ ትምህርት ታላቅ ጠቀሜታ ነበረው፡፡ በሴሚናሩ ላይ በየጊዜው በግምት ስድስት መቶ ሰዎች ይሳተፉ ነበር፡፡ እናም ክሪሎቭም ወደ ሥነ ጽሑፍ ክበብ በየወቅቱ መሄዱና ትምህርቱን መከታተሉ ላያስገርም ይችላል፡፡ በ1779 ታዋቂ መኮንን የነበረው አባቱ ሲሞት የመኖር ተስፋ ፈጽሞ ራቀው፡፡ ነገር ግን ወላጅ እናቱ በጣም ጠንካራና ታታሪ ስለነበረች ልጅዋን በተሻለ መንገድ ለማሳደግ ስትል ወደ ፔተርቡርግ ይዛው ሄደችና የመንግሥት ሥራ አስቀጠረችው፡፡ ክሪሎቭ ፔተርቡርግ ከተማ እንደገባ “ኮፌይኒሱ” የተሰኘ ኮሜዲያዊ ኦፔራ አዘጋጀ፡፡ ቆይቶም በተረትና በኮሜዲ ላይ ያተኮረ ድርሰት በመጻፍ ታወቀ፡፡ ወደ ፔተርቡርግ በሄደበት ዓመት ላይ ሌላ የኮሜዲ ድረስት ጽፎ ለአንድ የመጽሐፍ ባለመደብር ሸጦ በአገኘው ገንዘብ የእነ ሞሌርን፣ የእነራሲንንና የእነ ቦሌይን መጻሕፍት ገዛ። ወዲያው “ፊሎሜላን” የተሰኘ ድርሰቱን አሳተመ፡፡

በ1788 ጠንካራና ታታሪ የነበረችው ወላጅ እናቱ ስለሞተችበት እንደገና ሕይወት ጨለመችበት፡፡ ግን የጨለመ ሕይወቱን ለማፍካት ሲል መፍጨርጨር ጀመረ፡፡ ቆይቶ “ክሊዮፓትራ” እና “ፊሎሜላ” የተሰኙ ትራጄዲያዊ ቴአትሮችን ሠርቶ አቀረበ፡፡ በእነዚህ የኦፔራ ድርሰቶቹ አማካይነት በዘመኑ የነበሩ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮችን ለተመልካቾቹ አሳይቷል፡፡ አቀራረቡ ፋርሳዊ ነበር፡፡ ፋርስ የቴአትር ሌላኛው የአቀራረብ ስልት ነው፡፡ በ1786 “ቤሽናያ ሴማያ” የተሰኘ ኦፔራ ደረሰ። በኦፔራው ትዕይንት የሱምቡር አያት፣ እናቱና እህቱ፣ ፓስታን የተባለውን ሰውዬ ያፈቀረች ልጁ ይታያሉ፡፡ ሁሉም ቆንጆ ልጃቸውን ስለአላፈቀረ ከፓስታን ገንዘብ ለመቀበል ይፈልጋሉ፡፡ ሱምቡር ይህንን አስመልክቶ ሲናገር፡-

“ፓስታን ወርቅ ከአልሰጠኸኝ አንገትህን በሠይፍ ከልየ - እገድልሃለሁ” ይለዋል፡፡ በዚህም ንግግሩ ሴቶቹ በእጅጉ ይደሰታሉ፡፡ ሱምቡር ሐሳቡን እንዲህ እያለ በግጥም ፓስታንን ይሰድበዋል፡፡

“ጭንቅላት ባይኖርህ፣

ወርቅ ነው ካፖርትህ፣

አክብሮት ሳልሰጥህ፣

ስለዚህም ፈለግሁ ልዘባነንብህ፡፡

እኔ አለኝ መብቱ አንተን ለማንጓጠጥ፣

እንደልቤ ልዝለል እንደልቤ ልፍረጥ፡፡

እንዳላወራጭህ ቀንበር አሸክሜ፣

በካፖርትህ ብቻ እቀፈኝ ወንድሜ፡፡”

ሱምቡር አፉ እንደአመጣለት የሚናገርና ዓላማ ቢስ ሆኖ በተለምዶ የሚኖር ገጸባሕርይ ነው። ክሪሎቭ ከ1787 -1788  “ፊት  ለፊት” የሚል “ሪፍሞክራድ” “ሪፍሞህቫታ” ኮሜዲ አዘጋጀ። የኮሜዲው ይዘት የሚያተኩረው የሥነ ጽሑፍ ሥራው ተጻራሪው በነበረው ጸሐፌ ተውኔት ክንያዥኒን ላይ ነው። የክንያዥኒን ሚስት ደግሞ የጸሐፌ ተውኔቱ የሱማርኮቭ ልጅ ስትሆን በኮሜዲው ውስጥ የእርስዋን ባሕርይ የሚያንጻባርቅ ገቢር አለበት፡፡

የክሪሎቭ ኮሜዲያዊና ኮሚካዊ ኦፔራ ለሩሲያ ቴአትር ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ በሩሲያ የቴአትር ታሪክ ውስጥም የከበረ ቦታቸውን ለመያዝ የቻሉት የሙያውን ሳይንሳዊ አቅጣጫ ስላመለከቱ ነው። ለክሪሎቭ ዝና ከአተረፉለት ኮሜዲያዊ ሥራዎቹ ውስጥ ከ1798-800 የጻፋቸውና ለመድረክ ያበቃቸው “ቁንጥጫ” እና “ቀልዳቀልድ” የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡

እነዚህ ቴአትሮች የተጻፉት ለአንድ የቤተሰብ አባላት ሲሆን “የቤተሰብ ቴአትሮች” ይሰኛሉ። እነዚህ ቴአትሮች ለብዙ ጊዜያት ያህል ቤት ለቤት ሲታዩ የቆዩበት ዋናው ምክንያት የቀዳማዊ ጴጥሮስ መንግሥት ወደ ሕዝባዊ መድረክ ቀርበው እንዳይይታዩ ስለከለከለ ነው፡፡ ሥራዎቹ ለመድረክ እንዳይበቁ በተከለከለበት ወቅት ክሪሎቭ ለኪየቭ ቅርብ በሆነችውና የመስፍኑ የሰርጌይ ኤፍ ጋሌዚን የገጠር መንደር /ግዛት/ በሆነችው ካዛን ውስጥ የቤተመጻሕፍት ሠራተኛ ሆኖ ሠርቷል፡፡ ልዑሉ የሊቮንያ ወታደራዊ ገዥ በነበረበት ወቅትም ልዩ ጸሐፊው ሆኖ አገልግሏል፡፡ ሃያ ሦስት ያህል ፋቡላዎችን (በእንስሳት ሕይወት ላይ የተመሠረቱ ድርሰቶችን) ደርሶዋል፡፡ ከ1812-1841 የንጉሣውያን ቤተ መጻሕፍት ኃላፊና የሩሲያ መጻሕፍት ሥራ አስኪያጅ ሆኖ እንዲሰራም ተሹሟል፡፡ ክሪሎቨን የሩሲያ ሳይንስ አካዳሚ የክብር አባል አድርጐት ነበር። ሥራውን መዝኖም የወርቅ ሜዳልያ ሸልሞታል። በ1838 በንጉሣውያን ትእዛዝ በስሙ የተሰየመ ታላቅ ፌስቲቫል ተዘጋጅቶለታል፡፡ ከመሞቱ በፊት የሩሲያን ገበሬ ሕይወት የሚያንጸባርቁ ሥራዎች ሠርቶ 77 ሺህ ኮፒ የፋቡላ ድርሰቶች ተሸጠውለታል፡፡ የፋቡላ ድርሰቶቹ የኤዞፕንና የጂን ዶ. ላፎንቴንን ሥራዎች መነሻ አድርገው የተደረሱ ናቸው፡፡ ከዚህም የተነሣ ክሪሎቭ “ታላቅ የሩሲያ ፋቡሊስት” እየተባለ ይወደሳል፡፡ የሩሲያ ቴአትር ተመራማሪዎች “ቀልዳቀልድ” የሚለው ሥራው የቀዳማዊ ጳውሎስን ዘመን ፍንትው አድርጐ ያመለክታል ይላሉ፡፡ ዲ.ኢ ዛቫሊሽን የተባለ ታኅሣሣዊ (ዴካብሪስት ወይንም ዲሴምበር 7) ይህንኑ አስመልክቶ በጻፈው ሐተታ፤ ቁንጥጫና ቀልዳቀልድ ቴአትሮች ከላይ ከመንግሥቱ “ቁንጮ እስከ ዝቅተኛው የመንግሥት ባለሥልጣን እና መጥፎ መካሮች ድረስ የነበረውን ድርጊትና ክፋት፣ እንዲሁም ጭካኔ በሥላቃዊ አቀራረብ የሚያመለክቱ ናቸው” ብሏል፡፡

እነዚህ ሥላቃዊ ኮሜዲዎች /ቁንጥጫና ቀልዳቀልድ/ በ1924 ማለት ከታላቁ የጥቅምት ሶሻሊስት አብዮት በኋላ በሌኒን ግራድ፣ በ1944 ደግሞ በፔትሮዛቮድ ቴአትር ቤቶች ለመታየት ችለዋል፡፡ ፔትሮዛቮድ በቀዳማዊ ጴጥሮስ ስም የሚጠራ የአንድ ፋብሪካ ቴአትር ቤት ነው፡፡ የዐሥራ ስምንተኛው መቶ ክፍለዘመን የሩሲያ ድራማ ተመራማሪ የነበረው ፒ.ኤች ቤርኮቭ ስለፀሐፌ - ተውኔቱ በሰጠው አስተያየት “ክሪሎቭ ከክላሲዝም ቴአትር ተነሥቶ የሩሲያን ሕዝባዊ ድራማ ቅርጽ ያስያዘና ከሕዝባዊው ዘፈን ተነሥቶ የቴያትርን መመሪያ ያፈለቀ ደራሲ ነው፡፡” ብሏል፡፡

ድርሰቶቹ ፀረ - ፊውዳል አቋም ነበራቸው። እናም የሩሲያ ተራማጅ አስተሳሰብ ሕዝባዊነቱን ጠብቆ ወደፊት እንዲራመድና ዕድገት እንዲያሳይ ሆነው የተጻፉ ናቸው። ኮሜዲዎቹ እስከ ቀዳማዊ ጴጥሮስ ዘመነ መንግሥት ድረስ በሞስኮ የነገሡት ነገሥታትን ያወግዛሉ፡፡ ምሳሌ የሚያደርጉትም ዛር /ንጉሠ ነገሥት/ ቫኩልን ነው። በቫኩል ዘመነ መንግሥት በሕዝብ ላይ የደረሰውን መከራና ችግር እንደ መስታወት ወለል አድርገው ያሳያሉ።

ክሪሎቭ የሕዝቡን ድህነትና የቫኩልን መንግሥት ጭካኔ “ቁንጥጫ” በተሰኘ ኮሜዲው አቅርቦታል፡፡ የቫኩል ሴት ልጅ እንዲህ ትላለች፡-

“አባባ ለምን ነው ሕዝቡ ተሰብስቦ፣

ስምህን የሚያጠፋው እየበላ ዳቦ፡፡”

አባትዋ ቫኩል ደግሞ እንዲህ ሲል ይመልስላታል፡-

“እጄ ዐመድ አፋሽ ነው ሐሜት ነው ቀለቤ፣

እንጀራ በአበላሁ ሕዝቦቼን ሰብስቤ

ዛሬ በጥጋቡ በደስታው ወራት፣

ሕዝቦቼ አነደዱኝ ጠበሱኝ እንደእሳት፡፡

የእኔን ታላቅነት ወደፊት ያያሉ፣

በችጋሩ ዘመን በቀጠና ወራት ስሜን እየጠሩ ያመሰግናሉ፡፡”

ክሪሎቭ በዚህ ዓይነት በዛሩ መንግሥት ዙሪያ ያሉ መሳፍንት፣ መኳንንትና ባላባቶች መልካም አስተሳሰብ የሌላቸው፣ አርቆ ማስተዋል የማይታይባቸው፣ ድድብና የበዛባቸው፣ ነባራዊውን እውነታ ለመገንዘብ የተሳናቸው መሆናቸውን በጥበቡ አድምቆ ያስረዳናል፡፡

“ከነገሥታቱና ከመሰሎቻቸው ይልቅ ድልድይ ሥር ተቀምጣ ኮፔክ የምትለምን አንዲት የጂፕሲ ሴት ከእነሱ ትበልጣለች፡፡ ምክንያቱም ከአንድ መቶ ዓመት በኋላ በሩሲያና በዓለም ጭምር የሚሆነውን ስለምትተነብይ ነው” እናም “ከእነርሱ ጂፕሲይቱ ለማኝ መቶ ጊዜ ትበልጣለች፡፡” ይላል ክሪሎቭ፡፡

ክሪሎቭ “ቁንጥጫ” በተሰኘ ቴአትሩ ላይ፤

“ንጽሕና ከሌለ ይቆሽሻል ገላ

ከንፈር ከወፈረ

ጢም ከተከመረ

ይይዛል አተላ፣

ራስ ከቆሸሸ ያስጠላል ቁንዳላ፡፡

ነፋስ አያስጥልም የረዘመ አፍንጫ፣

የትም አያደርስም የዳክየ ሩጫ፡፡

አሁን በእኛ ዘመን አይ ጉድ አይ ጊዜ ብሎ እማያማርር፣

ከሴቶች ከወንዶች አለ ወይ ልመሥክር፡፡” ይላል፡፡

ክሪሎቭ “ሸሚዜ መሥክሪ” የሚል ባለ ሁለት ቤት ስንኝም አለው፡፡

“ሸሚዜ መሥክሪ ቅርብ ነሽ ለአካሌ፣

የተሳካ አይደለም የመኖር ዕድሌ፡፡”

ክሪሎቭ በሩሲያ የመጽሔት ሥላቅ ታላቅ ሥራ በመሥራቱ ስሙ ለሁልጊዜም ይጠቀሳል፡፡ ከ1769 -1774 የቢኮቭ ሥላቃዊ መጽሔት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ በኋላ እየቀነሰ ቢሄድም በ1780 “ምን አዲስ ነገር አለ?” በሚል በለዛ /ሒዩመር ላይ/ ያተኮሩ መጣጥፎችን ከነ ኖቪኮቭና ፎንቪዚን ጋር በማቅረብ የመጽሔቱን ተወዳጅነት ከፍ አድርጐታል፡፡

ማስታወሻ፡- በፅሁፉ ውስጥ የተጠቀሱት ዓ.ም በሙሉ እ.ኤ.አ ናቸው)

Read 2037 times