Monday, 25 May 2015 08:57

እናት ሀገር! (ብሔራዊ ዝንቅ)

Written by  መሐመድ ነስሩ
Rate this item
(19 votes)

ሀገር ምንድን ናት?! … ብለን እንጀምር፡፡
በድሉ ዋቅጅራ “ሀገር ማለት የኔ ልጅ” በሚለው ግጥሙ እንዲህ ይለናል፤
“ሀገር ማለት ልጄ ሀገር ማለት፣
እንዳይመስልሽ የተወለድሽበት ቦታ፣ የተወለድሽበት አፈር፣
እትብትሽ የተቀበረበት ቀድመሽ የተነፈሽው አየር፣
ብቻ እንዳይመስልሽ፡፡
ሀገር ረቂቅ ነው ቃሉ፤
ሀገር ውስብስብ ነው ውሉ፤…”
ሀገር እንዲህ ናት ብሎ መፈረጅ ከባድ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ነገር ግን ካለመፈረጅና በዝምታ ተሸብቦ ጥሬውን ከብስሉ ከመፍጨትና ከመፍጀት መበየንና መፈረጅ ሳይሻል አይቀርም፡፡
በድሉ ዋቅጅራ ይቀጥላል፡-
“… ሀገር ማለት ልጄ፣
ሀገር ማለት ምስል ነው፣ በህሊና የምታኖሪው፤
ከማማ ማህፀን ከወጣሽበት ቀን ጀምሮ
በጠባሽው ጡት፣ ወይም ጡጦ
በዳህሽበት ደጃፍ፣ በወደቅሽበት ፈፋ፤
በተማርሽበት ትምህርት ቤት፤
በተሻገርሽው ዥረት፤
በተሳልሽበት ታቦት፣ ወይ በተማፀንሽው ከራማ፤
በእውቀትሽና በስሜትሽ፣
በእውነትሽና በስሜትሽ፤
የምትቀቢው ምስል ነው፤ በህሊናሽ የምታኖሪው፤
ስትወጅ ሰንደቅ ታደርጊው፡፡
ቢያስጠላሽ የማትቀይሪው፡፡ …”
ሀገር የማንነት ማህተም፤ የምንነት ክታብ ናት፡፡ ሀገር መልካችን ናት፡፡ በሀገር መልክ እንጎላለን፡፡ በሀገር ገፅ እንኳ ላለን፡፡ ሀገር የማንነት አካል ብቻ ሳትሆን ፅኑ ማንነት ሆና ስለምትኖር መገለጫችን ሆና ትገኛለች፡፡ ስያሜያችንን ከሀገራችን ስም እንዋሳለን፡፡ ኢትዮጵያ፤ ኢትዮጵያዊ የሚለውን ስያሜ እንደምታትምብን ሁሉ፤ ሌላውም ሌላ ስምና ሌላ መጠሪያ ይኖረዋል፡፡
ኢትዮጵያዊነት ስንፈልግ የምናገኘው፤ ስንጠላ የምንፍቀው አይደለም፡፡ አይሰረዝም፤ አይደለዝም፡፡ አይካድም፤ አይፋቅም፡፡ ምክንያቱም ደም ነው፡፡
ከላይ በሰፈረው ግጥም በድሉ ዋቅጅራ ስለ ሀገር ሲገጥም ማዕከሉና እምብርቱ እንዲሁም የግጥሙ ሀሳብ መሽከርከሪያ ምህዋር እንዲሆን የፈለገው ሰውን ነው፡፡ የሀገር መገለጫዋ ሰው ነው የሚል አቋም ነው የሚያራምደው፡፡
ሌላው ሁሉ ግዑዝ ነውና ሀገርን ሀገር የሚያሰኘው መልከዓ ምድሩ፣ አፈሩ፣ ድንጋዩ፣ ተራራው፣ ዋሻው ሳይሆን “ዕድርተኛው” ነው ይላል፡፡
“…. መሬትማ የኔ ልጅ፣
በእምነትሽና እውቀትሽ፣ ከልለሽ ካላበጃጀሽው፣
ለእድገትሽ ውጥን ካልሆነ ለተስፋሽ ካልተመገብሽው፣
መሬትማ ባዳ ነው፣ ላለማው የሚለማ
ለተስማማው የሚስማማ፡፡
ዥረቱም ግድ የለውም፣ ቦይ ለማስላት ይፈሳል
ተራራውም ደንቆሮ ነው፤ ለቦረቦረው ይበሳል፡፡
መሬቱ አይደለም የኔ ልጅ፣ እድርተኛው ነው ሀገርሽ፤
ስትቸገሪ ታድጎ፣ ስትታመሚ አስታምሞ፣ ስትሞቺ አፈር የሚያለብስሽ፡፡
በእጅሽ ያለ ብሩህ ጽጌ፣ ሰው ነው ልጄ ሀገርሽ፡፡
ወገን ነው ልጄ ሀገርሽ፡፡”
ወጣቱ ገጣሚ አሌክስ አብርሃም በድሉን ይቀናቀናል፡፡ ሀገርን በተቃራኒው ለመግለፅ ስንኞችን ይደረድራል፡፡ ግጥሙ ለበድሉ የተፃፈ የመልስ ደብዳቤ ነው፡፡
“አገር ማለት ጋሼ” ይላል አሌክስ አብርሃም፡-
“….     አገር ማለት ወንዙ፤
አገር ማለት ጓዙ፣
አገር ማለት አፈር፡፡
ዓይናችን እስኪደክም ሽቅብ የምናየው፣
አገር ማለት ጠፈር፡፡ …”
ሀገር ማለት ስንወለድ የተቀበለን ምድር፣ በልጅነት የሮጥንበት ሜዳ፣ በክረምት ያቦካነው ጭቃ፣ በዳዴ የወጣነው ዳገት፣ ሸርተቴ የተጫወትንበት ቁልቁለት፣ ከብት ያገድንበት ማሳ፣ ቤት የለቀለቅነው እበት፣ አንድደን ያጨስነው ኩበት፤ ይሄ ነው ሀገር ማለት! …. (እንደማለት!) …
ከበድሉ በተቃራኒ ቦታ ላይ ቁሞ “ሰው ሀገር አይደለም” ይላል አሌክስ፡፡
“… የለም የለም ጋሼ … ሰው አገር አይደለም፣
እንደውም ያለርስት የሰው ግሳንግሱ
የሰው ጅምር ፅንሱ … አይቆነጠርም፣
አፈሩን የቀሙት …. እርምጃውን እንጂ … ማንነት አይቆጥርም ….
አገር ማለት አፈር፣
አገር ማለት ሜዳ፣ ሸለቆ ሸንተረር፣
አገር ማለት … ምድር፣
አገር ማለት… ጠፈር …”
የሀገር ትክክለኛ ትርጉም የሚገኘው በነጠላ ሳይሆን በድርብ ነው፡፡ በአንዱ ገጣሚ ግጥም ሳይሆን በሁለቱ ጥምር ገለፃ ነው፡፡ ሁለቱም በ‘ራሳቸው መንገድ ልክ ናቸው፡፡ ነገር ግን ሀገር ሰው ብቻ አይደለችም፡፡ ሀገር ተራራና ሸለቆ ብቻም አይደለችም፡፡ ሀገር የእነዚህ ውህድ የሚፈጥራት የራስዋ መልክና ቁመና ያላት፣ ህልው ማንነት የታደለች ገፀ-በረከት ናት፡፡ (ገፀ - በረከትነትዋም ለዜጎችዋ!)
ሀገር ውለታዋ እንደ እናት ብዙ ነው፡፡ ጉልበትዋን አሟጣ ትሸከመናለች፤ ሀብትዋን አፍስሳ ታስተምራለች። ዜጎችዋን ባንቀልባዋ አዝላ ወዲህ ወዲያ ትላለች፡፡ ከልጆችዋ ጋር ትዳክራለች፡፡
እናትና ሀገር ቦታ ሊቀያየሩ የሚችሉ ሁለት ነገር ግን ተመሳሳይ ነገሮች ናቸው፡፡ የሀገር ፍቅር የእናት ፍቅር አቻ ነው፡፡ እናት ሀገር የምንለው ለዚህ ነው፡፡ ሀገርና እናት እኩያማቾች ናቸው፡፡ (በዕድሜ ሳይሆን በአደራረጋቸው፡፡ እንጂማ በዕድሜ ሀገር መቅደሟ እውነት ነው፡፡ እናት ሀገር ኢትዮጵያም የዕድሜ ባለፀጋ ስትሆን ዕድሜዋ በሶስት ሺ ዓመታት የሚገመት ባልቴት ናት፡፡)
እስቲ ሁለቱን (እናትና ሀገርን) እናነፃፅራቸው፤
እናት አምጣ ትወልዳለች፡፡ ወልዳ ትመግባለች። መግባ ታሳድጋለች፡፡ ሀገርም እንደ እናት ናት፡፡ እንደ እናት አምጣ ትወልዳለች፡፡ እንደ እናት ወልዳ ትመግባለች፡፡ እንደ እናት መግባ ታሳድጋለች፡፡ እናት ሀገር አንድም ሁለትም ናቸው፡፡ አንድነታቸው ለልጃቸው (ለዜጋ) ባላቸው ፍቅርና እንክብካቤ ይገለፃል፡፡ ሁለትነታቸው እናት ስጋና ደም ያላት መሆንዋ ላይ ሲሆን፤ ሀገር ደግሞ መግቦትና ችሮት ለዜጋዋ በመለገስዋ ይገለፃል፡፡ ሀገርና እናት አንድም ሁለትም ናቸው፡፡
በዕውቀቱ ስዩም ስለ እናት የገጠመው ግጥም ትዝ አለኝ፡፡ እንደዚህ ይላል፡-
“በላዔ ሰብእ
ከፍልሰታ በፊት ቆረብኩኝ በእምዬ
ነጭ ደሟን ጠጣሁት ወተቷ ነው ብዬ
እውነት! እውነት! እውነት!
ከናቱ እቅፍ ወርዶ ምድርን እስኪቆፍር
ሰው በላዔሰብ ነው በደም የሚወፍር፡፡”
እውነት ነው፤ ሰው በላዒሰብ (እና በላዔ ሀገር) ነው፡፡ የእናቱን ደም ብቻ ሳይሆን የሀገሩን ስጋና አጥንት ጭምር ነጭቶና አድቅቆ የሚወፍር ወይም ቆሞ የሚሄድ ፍጡር፡፡
እናትና ሀገር ተመሳስሎ አላቸው፡፡ ልጆች የእናት ጡት ጠብተው እንደሚያድጉት ሁሉ፤ የሀገሩን አንጡራ ሀብት፣ የሀገሩን አፈር አለስልሰውና ልሰው፤ የሀገሩን ድንጋይ ፈልጠውና ተንተርሰው፣ የሀገርን ደም ጠጥተው፣ የሀገርን ስጋ በልተው ነው ዜጎችም ዜጋ ሊሆኑ የሚችሉት፡፡
እናት እንደ ሀገር ሆድዋ ሰፊ ሆኖ፣ ፍቅሯም ፅንን ያለ ነው፡፡ ሀገር እንደ እናት የፍቅር ልግስና የተቸረች ሆና ዜጋዋን አክባሪና መጋቢ ናት፡፡
እናት ማህፀን አላት፡፡
ሀገርም አፈር አላት፡፡
ሁለቱም ፍሬ ያፈራሉ፤ ዘር ይተካሉ፡፡
እናት ማህፀንዋ ልጅዋ የሚወጣበት፤ ወጥቶም ለእይታዋ ቅርብ የሚሆንበት በርዋ ነው፡፡ ሀገር አፈርዋ የተለያየ ዘር የሚዘራበት፤ ተዘርቶም ፍሬ የሚያፈራበት፤ አዝርዕት የሚቸርበት የልምላሜ መስክ ነው፡፡
እናት ልጅዋን፣ ሀገር ዜጋዋን አቅፈው አብረው ይኖራሉ፡፡ ሙቀት ይዋዋሳሉ፡፡ ፍቅር ይቀባበላሉ፡፡
ሀገር ሰፊ ናት፡፡
እኛ እሷ ውስጥ እንደምንኖረው፣ እሷም እኛ ውስጥ ትኖራለች፡፡ አንድ ደራሲ የተናገረው አንድ አባባል አለ፤ “የገጠርዋን ልጃገረድ ከገጠር ማውጣት ይቻላል፡፡ ገጠሩን ከልጃገረድዋ ልብ ማውጣት ግን አይቻልም፡፡”
በወንድዬ አሊ “ወፌ ቆመች” የግጥም መድበል ውስጥ “የባህር ማዶ ድምፅ” በሚል ርዕስ የተፃፈውን ግጥም ብናነበው የሚሰጠን ስሜት ይኖራል፡፡ ለማንኛውም እስኪ እናንብበው፡-
ውስጠ ባህሪዬ .. ሲሸምቅ
ባህረ - ሆዴ ሲባባ፣
ጨለማ ቀለም - ሲቀባ፣
በዝምታዎቼ - ኮለል አምባ ፣
አይሰማችሁም - ነውጡ!
ጉርምርምታዬ፣
አይታያችሁም - ድጡ!?
አጮልቆ ….
አወዳደቄን ለማፍጠን … ጀርባዬን ለመላላጡ፡፡
ቶሎ ይረግባል እንዴ … የደም ደጉ?
እንዲህ አጭር ነው እንዴ … እትብት ማጉ?
ጥቁር አፈሯ … ጣዝማ ማሬ፣
እንኮይ ሾላው … ያጋም ፍሬ፣
ገደል ዱሩ … ግርማ ክብሬ፣
ጫካ  - ጢሻው
    የሩቅ - ፍቅሬ፣
    ያሁን - ፍቅሬ፣
    የሩቅ - ፍቅሬ፣
    ያሁን - ፍቅሬ፣
የአገር ሰማይ - የአገር አድማስ፣
የአገር ታቦት - ታቦተ ንግሥ
የአገር ስራት - የአገር ዕድር
የሩቅ - ፍቅሬ
ያሁን - ፍቅሬ …”
ሀገር ግዙፍና ህያው ክስተት ወይም ፍጥረት ናት፡፡ ስለ ሀገር ለመፃፍ ጥቂት ቃላት አይበቁም። ለሀገርና ስለ ሀገር ድምፅን ከፍ አድርጎ መዘመርና መዝፈን ቢቻል እንኳ ለስሜታችን በቂ ሆኖ ላይገኝ ይችላል፡፡ ወይም እኛ ሀገርን በሚመጥን ደረጃ ብቁ ሳንሆን እንቀር ይሆናል፡፡ ይህ መጣጥፍ አንባቢን ለመኮርኮርና ለመተንኮስ እንጂ ሀገርን ለመግለፅና ስለ ሀገር ለመተንተን በቂ እንዳልሆነ አውቃለሁ፡፡ እኛም የተቀረውን እናንተ እንድትሞሉበት እጠይቃለሁ፡፡ 

Read 17490 times