Monday, 25 May 2015 08:55

‘ከፊት ለፊት ተኳኩሎ፣ ከጀርባ ተከልሎ…

Written by 
Rate this item
(6 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እነእንትና…‘ኢሌክሽን’ ምናምን እንዴት ነው! እንዴት ነው… ወደዛኛው ግቢ አጥር ዘለላችሁ እንዴ! አምስተኛው እንትንማ መጦሪያዬ መጦሪያዬ ምናምን ማለት ስለበዛው ነገረ ሥራህ ትንሽ ግራ ገብቶን ስለነበር ነው፡፡
ይቺን ነገር ሳናወራት አልቀረንም…ፖለቲከኛው የምርጫ ንግግር እያደረገ ነው፡፡ እናላችሁ…ምን ይላል… “ወገኖቼ ለአገራችን ተዋግቻለሁ፡፡ አልጋዬ ጦር ሜዳ ነበር፣ ጣራዬም ሰማዩ ነበር፣ እያንዳንዱ ዱካዬ በደም እስኪቀልም ድረስ ያልዋልኩበት የጦር ሜዳ፣ ያላቋረጥኩት በረሀ የለም፡፡ ስለዚህ ምረጡኝ…” ይላል። ይህን ጊዜ ከህዝቡ መሀል አንዱ ምን ቢል ጥሩ ነው…
“ለአገርህ ከሚገባህ በላይ ሠርተሀል፡፡ እቤትህ ሂድና አረፍ በል፡፡ ተወዳዳሪህ ደግሞ ገብቶ ይሞክረው፣” ብሎት እርፍ፡፡
ከዚህ የሚገኘው ‘ሌሰን’…ቦተሊከኞች ለምርጫ ስትወዳደሩ ‘ሲቪያችሁን’ ከልክ በላይ አታርዝሙትማ። አሀ… “እቤትህ ሂድና አረፍ በል…” ትባላላችኋ! ቂ…ቂ…ቂ…
ስሙኝማ…መቼም ዘንድሮ ፊት ለፊት የምንሰማው፣ የምናየውና ዘወር ስንል ደግሞ ያለው ነገር አልገጥም ብሎን ተቸግረናል፡፡ ፈረንጅ…‘ኋት ዩ ሲ ኢዝ ኋት ዩ ጌት’ የሚላት ነገር አትሠራም፡፡
እንትናዬዎች…“አድናቂሽ ነኝ…” ምናምን ስትባሉ ስትሰሙ አብራችሁ ዘወር ስትሉ ሊባል የሚችለውንም እያሰባችሁ፡፡ “እኔ እኮ አድናቂሽ ነኝ ያልኳት እሷም ሴት ሆና በሚኒስከርት በመሄዷ ነው…” ምናምን ሊባል ይችላል፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…
እንትናዬ ሸለል ብላ ወጥታለች፡፡ ዘንድሮ መቼም ሸለል ብሎ ለመውጣት የምትሞክር እንትናዬ መአት ነች፡፡ እናላችሁ…የሆነች እንትናዬ ሽልል ብላ ስትወጣ ምን ትባላለች መሰላችሁ… “አንቺ እንዴት ነው እንዲህ ያማረብሽ! እንዴ አንቺ እንዲህ ያብረቀርቅሽ የቤታችሁ የቅቤ ቅል እንዴት ሊሆን ነው!” አይነት ‘አድናቂሽ ነኝ’ ነገር ይቀርብላታል፡፡ እሷዬዋም ደስ ይላታል፡፡
እሷ ዘወር ስትል ምን ይባላል መሰላችሁ… “አገሩ ሁሉ በኮስሜቲክስ በሞላበት ምን አለ ትንሽ ለቅለቅ ብትል፡ “አላየሀትም እንዴ… ሥራ የበዛበት የዱቄት ወንፊት ትመስላለች እኮ፡፡”
እሱ ደግሞ ከአካሄዱ ጀምሮ… መንገዱን ተቆጣጥሮታል፡፡ “አንተ ምን አግኝተህ ነው…የእንግሊዝ ልዑላንን መሰልክ እኮ!” ምናምን ይሉታል፡፡ ይሄ እንግዲህ ዲፕሎማሲ ነው፡፡ ዘወር ሲል ምን ይባል መሰላችሁ… “እኔ እንደው ትከሻው ላይ ጃኬት ጣል ስላደረገ ነው እንጂ በልማት ምክንያት ይፍረስ የተባለ የማድቤት ግድግዳ ይመስላል…” ምናምን ይባላል፡፡
እናማ…‘ኋት ዩ ሲ ኢዝ ኋት ዩ ጌት’ ዘንድሮ አትሠራም፡፡
“አንተ! እንዴት ነው እንዲህ ትከሻ በትከሻ የሆንከው! የካምቦሎጆውን ሜዳ አከልክ እኮ?”
“ጂም እሠራለሁ፡፡”
“የሚገርም ነው፣ የሆነ እኮ በቀራጺ የተቀረጽክ ነው የምትመስለው…” ምናምን ‘አድናቂህ ነኝ’ አይነት ነገር ይባላል፡፡
ይህ እንግዲህ ‘ዲፕሎማሲ’ መሆኑ ነው፡፡
ዘወር ሲል አጅሬው ምን ይባላል መሰላችሁ… “ይሄን ሰውዬ ግን በደንብ አይተኸዋል? ውፍረቱ ግን የጤና አይመሰለኝም! እኛ እኮ ስንትና ስንት ዓመት ጂም የሠሩ ጓደኞች አሉን፡፡ እሱ በሁለት ወሩ የሆነውን እነሱ ምነው በሁለት ዓመታቸው አልሆኑ!”
እናማ…‘ኋት ዩ ሲ ኢዝ ኋት ዩ ጌት’ ዘንድሮ አትሠራም፡፡
ቦተሊከኛው ለረጅም ሰዓት ሲደሰኩር ይቆያል፡ ሲጨርስ አዳራሹ በጸጥታ ይዋጣል፡፡ የተናገረው ነገር የህዝቡን ስሜት በከፍተኛ ደረጃ እንደነካው እያሰላሰለ ትኩር ብሎ ሲያይ ምን ቢያይ ጥሩ ነው…ለካስ ሰዉ ሁሉ እንቅልፉን ይለጥጣል፡፡
ከዚህ የሚገኘው ‘ሌሰን’ ቦተሊከኞች ለረጅም ደቂቃዎች አውርተው ሲጨርሱ ጸጥታ ከሰፈነ ሰዉ በሀሳብ ተመስጦ ሳይሆን በእንቅልፍ ሰምጦ መሆኑን ልብ ይባልማ!
የሆነ ተናጋሪ ቀሺም ስለነበር አዳራሹ ውስጥ ማጉረምረም በዝቷል፡፡ እናማ...ድምጹን ከፍ አድርጎ ምን ይላል… “እባካችሁ ጆሯችሁን አውሱኝ…” ይላል። ይሄን ጊዜ ከተሰብሳቢዎቹ አንዱ ምን ቢለው ጥሩ ነው… “የእኔን ውሰድ፡ ቢያንስ ቢያንስ ያንተን ንግግር አልሰማም፡፡”
ተናግረናል…ዘንድሮ ‘ኋት ዩ ሲ ኢዝ ኋት ዩ ጌት’ አይሠራም፡፡
የንግግርን ነገር ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ… ሰውየው ለመናገር ሲሞክር ጫጫታው ያስቸግረዋል። ይሄን ጊዜ ይናደድና… “እዚህ አዳራሽ ውስጥ በአንድ ጊዜ አንድ ደደብ ቢናገር ደስ አይላችሁም!” ይላቸዋል፡፡ ከሰዉ መሀል አንዱ ምን ቢለው ጥሩ ነው… “መጀመሪያ አንተ ተናግረህ ጨርሳ!”  አሪፍ አይደል፡፡
ስሙኝማ… ሰዋችን በአደባባይ መናገር ጀምሯል፡፡ በፊት፣ በፊት ከአሥሩ አንዱ ሰው “አሁንስ መከራችንን በላን…በግራ በቀኝ አላስኖር አሉን እኮ…” ምናምን ሲል ዘጠኙ ሰው “ጎበዝ እንዳትበላ፣ ከተናግሮ አናጋሪ ይጠብቀን…” አይነት የጎሪጥ ይተያያል፡፡ ዘንድሮ አሥር ሰው ኖሮ አንዱ ሰው “አሁንስ መኖር አቃተን…” ሲል ስምንቱ “እነሱ ምን ቸገራቸው አትክልት ተራ አይሄዱ፣ እህል በረንዳ አይሄዱ…ወፍጮ ቤት አሻሮ ተሸክመው አይሄዱ…” ምናምን እያለ ይጨምርበታል፡፡
አስቸጋሪ ጊዜ ውስጥ ነን፡፡ በጣም አስቸጋሪ ጊዜ ውስጥ ነን! የምንስማማበት አንድ ርዕስ ቢኖር ‘የኑሮ መወደድ’ ነው፡፡ አንድ ፍርፍር ለሁለት የምንበላውም፣ አንድ ኪሎ ጥሬ ሥጋና ሁለት ስፔሻል ክትፎ ለብቻችን የምንበላውም እኩል… “ኑሮ አቃተኝ እያልን ነው፡፡”
የምግብ ነገር ከተነሳ አይቀር… ሰውየው ዶሮ አሮስቶ ያዛል፡ ዶሮዋ ስትመጣ ሲያያት ይጎመጅና ሲቀምሳት ምንም የዶሮ ጣእም የላትም፡፡ መቼም የሚወጣባት ገንዘብ ነውና እንደምንም ይጨርሳታል፡፡ ሂሳቡ ሲመጣለት ሁለት መቶ ሀያ ሁለት ብር ይሆናል፡፡ ምን አለፋችሁ…በንዴት ጣራ ይነካላችኋል፡፡
”ምንድነው ይሄ!”
”ሂሳቡ ነዋ፣ ጌታዬ፡፡”
“ሙሉውን የዶሮ እርባታ የሰጣችሁኝ መሰላችሁ እንዴ! ሁለት መቶ ሀያ ሁለት ብር! ዶሮዋ እኮ ቆዳና አጥንት ብቻ ነበረች...” ሲል አሳላፊው ምን ቢል ጥሩ ነው…
“ጌታዬ ላባዋንም ፈልገው ከነበረ ለምን አልነገሩንም!” ብሎት እርፍ፡፡
እናም አሪፍ መልክ ያላት ዶሮም ይሁን ሽፋኑ ዓይንና ቀልብ የሚስብ አብዛኛው ነገር እንዳሰቡት የማይገኝበት ዘመን ነው፡፡
እናማ…ዘንድሮ ‘ኋት ዩ ሲ ኢዝ ኋት ዩ ጌት’ ብሎ ነገር አይሠራም፡፡
ባል ሆዬ ገና ‘ፉከራውን ያልጨረሰ’ ሹሮ ወጥ ይቀርብለታል፡፡ “ዛሬ ገና ሹሮ ልትበላ ነው…” እያለ የመጀመሪያውን ጉርሻ ሲጎርስ… አለ አይደል… አንድያውን የሹሮ እህሉን ሳይከካ ቢያቀርቡለት ይመኛል፡፡
ብሽቅ ብሎ ምን ይላል… “ይሄን ወጥ የሠራው ማነው?”
ሚስትም ሥራዬ ተወደደልኝ ትልና ኮራ ብላ “እኔ ነኛ…ድሮስ ማን ሊሆን ነው…” ትላለች፡፡”
ባል ምን ቢል ጥሩ ነው… “በይ ቁጭ በዪና ራስሽ ብያት!”
ሚስቶች “በይ ቁጭ በዪና ራስሽ ብያት!” ከመባል ያድናችሁማ!
እናማ…መልክ ብቻ የሆነ ሹሮ ለሚቀርብላችሁ አባወራዎች ምክር ቢጤ… ሚስቶቻችሁን “ለወደፊቱ ጣት የሚያስቆረጥም ሹሮ የመሥራት ዓላማሽን ለማሳካት ትኩረት ሰጥተሽ ልትንቀሳቀሺ ይገባል…” በሏቸውማ፡፡ አሀ ልክ ነዋ…ራሳቸው ይኳኳሉ እንጂ ሹሮ ወጥን መኳኳል ምን የሚሉት ሙያ ነው!  ቂ…ቂ…ቂ…
እናማ…ዘንድሮ ‘ኋት ዩ ሲ ኢዝ ኋት ዩ ጌት’ ብሎ ነገር አይሠራም፡፡
ስሙኛማ…እግረ መንገዴን የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ…እኛ ባሪያቶ ነው ምናምን የሚሏቸው ሰውዬ ተሰናበቱ አይደል! የምር እኮ… አንዳንዶቻችን ስንወርድባቸው የከረምነው…አለ አይደል…የስፖርት ጉዳይ ሳይሆን የሚስትና የርስት ጠብ ያለብን ነበር የሚመስለው፡፡
ስሙኝማ…አንድ ጊዜ “ግማሽ ሚሊዮን የሚሆን ብር እየዛቁ…” የሚባል ነገር ሰማሁ መሰለኝ! እንዲህ ተብሎ ነው እንዴ የሚታሰበው! ግራ ስለገባኝ ነው… እኚህ ሰውዬ የውጪ ዜጋ ናቸው፡፣ ደረጃቸው ምንም ይሁን ምን ዓለም አቀፍ አሰልጣኝ ናቸው…ደሞዛቸው አሥራ ስምንት ሺህ ዶላር ምናምን ‘ነች’፡፡ በኢንተርናሺናል አሰልጣኝነት ደግሞ ይቺ የመጨረሻዋ ቀሺም ክፍያ ትመስለኛለች፡፡ “...እየዛቁ…” የምትለዋ ግራገብታኝ ነው፡፡ ስፖርት ጋዜጠኞቻችንም እኮ “የስፖንሰር ገንዘብ እየዛቁ…” አይነት ነገር እየተባላችሁ ነው!  
የምር ግን እሳቸው ሰውዬ ላይ በሚዲያ የተወረደባቸውን ግማሹን ያህል ‘መከራ የሚያበሉን’ ባለወንበሮች ላይ የሚወረድባቸው ዘመን ይመጣ ይሆን!  አሀ…ልክ ነዋ! እኔማ አንዳንዴ ወገባችንን ይዘን ልክ ልካቸውን ስንነግራቸው… አለ አይደል… “እኚህ ሰውዬ የጀኔራል ደቦርሚዳ ዘመድ ናቸው እንዴ?” ልል ምንም አይቀረኝም ነበር፡፡
አዲሱን አሰልጣኝ ከዚህ ይሰውረውማ፡፡
እናማ…ላይ ላዩን እያያን ዘወር ሲባል የሚባለውን መርሳት አሪፍ አይደለም፡፡ ዘመኑ እንዲህ ነው፡፡
ዘንድሮ… ‘ኋት ዩ ሲ ኢዝ ኋት ዩ ጌት’ ብሎ ነገር አይሠራም፡፡
እናማ… ‘ከፊት ለፊት ተኳኩሎ፣ ከጀርባ ተከልሎ…’ ዘመንን ርዝመት ያሳጥርልንማ!
ደህና ሰንበቱልኝማ!

Read 2457 times