Monday, 25 May 2015 08:50

ለምርጫ ሲሰጥ የነበረው አለማቀፍ ትኩረት ለምን ቀነሰ?

Written by  ዩሃንስ ሰ.
Rate this item
(11 votes)

ከአሜሪካና ከአውሮፓ ይመጡ የነበሩ ታዛቢዎች ቀርተዋል። አለምክንያት አይደለም።
ምርጫዎች ምንም ቢሆኑ፣ በሰላም ከተጠናቀቁ በቂ ነው የሚል ተስፋ ቢስነት ሰፍኗል።
አለማቀፍ የሚዲያ ተቋማት በምርጫው እለት ካልሆነ በቀር ብዙም ቦታ አይሰጡትም።

    ለፖለቲካ ምርጫ ከፍተኛ ትኩረት ይሰጡ የነበሩ የአሜሪካና የአውሮፓ መንግስታት፣ ዛሬ ዛሬ ድምፃቸው ቢጠፋ አይገርምም። እንዲያውም፣ “ዋናው ሰላም ነው” በሚል ሃሳብ ምርጫዎችን በስጋት ወደ ማየት ያዘነበሉ ይመስላሉ። በቅርቡ እዚህ አዲስ አበባ መጥተው የነበሩት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር ምን እንደተናገሩ ታስታውሳላችሁ። ባለስልጣኗ ስለኢትዮጵያ ስኬቶች አዳንቀው የተናገሩትን ሰምታችሁ ከሆነ፣ የአሜሪካና የአውሮፓ መንግስታት ፍላጎት ወደ ምን ደረጃ እንደወረደ ለመገንዘብ አይከብዳችሁም። እንደ ድሮው አይደሉም። የፖለቲካና የፕሬስ ነፃነት፣ የንብረት ባለቤትነት መብትና ነፃ ገበያ፣ የህግ የበላይነትና ነፃ ምርጫ እያሉ “መራቀቅና መቀናጣት” ትተዋል። የተወሰነ የኢኮኖሚ እድገትና ሰላም ብቻ ይኑር። በቂ ነው። በጭራሽ የግጭትና የቀውስ ወሬ ከኢትዮጵያ መስማት አይፈልጉም። ወርደው ወርደው፣ “መንግስት ካለ፣ ችግር የለም” ወደሚል ደረጃ ለመድረስ ተቃርበዋል። ለምን? ዙሪያችንን እንመልከታ።
በዘረኝነት የተቧደኑ ጎራዎች የቆሰቆሱት የደቡብ ሱዳን ግጭት፣ ያለ መፍትሄ ከአመት በላይ መዝለቁ ሳያንስ፣ ወደፊትም ተስፋ ያለው አይመስልም። ለአመታት በቋፍ ላይ የቆየችው ቡሩንዲ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ መናጋት ጀምራለች። በተቃውሞ የዓመፅ እንቅስቃሴ መሃል የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ከማስተናገዷም በተጨማሪ፣ በዘረኝነት ግጭት እየተንተከተከች ነው። ከዘረኝነት ጋር የሃይማኖት አክራሪነትን በማዳቀል ከ20 አመታት በላይ ካስቆጠረው የሶማሊያ ቀውስ ሌላ፤ አሁን ደግሞ የየመን ተጨምሮበታል። ይሄም ተመሳሳይ ነው። በዘረኝነት ላይ የሃይማኖት አክራሪነት ታክሎበት፣ የሳዑዲ አረቢያ ጎራና የኢራን ደመኛ ባላንጣነት ተደምሮበት አካባቢው ተናውጧል። የማሊ እና የሴንትራል አፍሪካ ቀውስ መንስኤም ሌላ አይደለም - ዘረኝነትና የሃይማኖት አክራሪነት ነው። ናይጄሪያ፣ ቻድ እና ካሜሮንም እንዲሁ በዘር እና በሃይማኖት የመቧደን መዘዝ ነው የሚያተራምሳቸው።
የግብፅ የእለት ተእለት የሽብር ፍንዳታ፣ የቱኒዚያ ምስቅልቅል፣ “የሊቢያ ሶስት መንግስታት” እና በመቶ የሚቆጠሩ ታጣቂ ቡድኖች ጦርነት፣... ስንቱ ይቆጠራል። መካከለኛው ምስራቅ እንዳሁን ከዳር እስከ ዳር ተተራምሶ የሚያውቅ አይመስልም። ከሳዑዲና ከኳታር እስከ ሃማስና ሄዝቦላ፣ ከሊባኖስና ዮርዳኖስ እስከ ኢራንና ቱርክ የሚናከሱበት ጦርነት፣ አውድማውን በኢራቅና በሶሪያ ያደረገ ነው። ይሄም በዘረኝነትና በሃይማኖት አክራሪነት አማካኝነት የሚግለበለብ ጦርነት ነው። በኤሲያም የታይላንድ አመፅና መፈንቅለ መንግስትን፣ የማይነማር ቀውስን መጥቀስ ይቻላል።
በአውሮፓም እንዲሁ ዘረኝነትን የሚያራግቡ ፓርቲዎች እየገነኑ መጥተዋል - የሃይማኖትም እንዲሁ። ከራሺያና ከዩክሬን በተጨማሪ፣ ሰሞኑን በሜቄዶኒያ የተለኮሰው ዓመፅና ተቃውሞም የጤና አይደለም። ያው፣ “የአልባኒያ ተወላጅ” እና “የሰርብ ተወላጅ” በሚል በዘረኝነት ከመቧደን ጎን ለጎን፤ “ሙስሊም” እና “ክርስቲያን” በሚል የሃይማኖት አክራሪዎች የመቧደኛ ዘዴ፣ አገሪቱ ጦርነት አፋፍ ላይ ደርሳለች።
በየአቅጣጫው የሚታየውን የኢኮኖሚ ቀውስ እና የስደት ማዕበልንም ጨምሩበት። በተለይ ባለፉት ሃያ ዓመታት፣ የካፒታሊዝምን አሰራር እየሸረሸሩ በቅይጥ ኢኮኖሚ ወደ ሶሻሊዝም ሲንሸራተቱ የቆዩት አብዛኞቹ የአውሮፓ አገራት ይሄውና ከኢኮኖሚ ቀውስ ሳይገላገሉ ከ5 ዓመት በላይ ሆኗቸዋል። የድጎማ በጀት እያበጠ፣ የታክስ ጫናው ልክ እያጣ፣ የመንግስት እዳ እየተቆለለ፣ ኢንቨስትመንት እየተዳከመና የስራ እድል እየጠበበ ግራ ተጋብተዋል። የአፍሪካ አገራትም ከቀውስ አላመለጡም። ለጥቂት አመታት ወደ ነፃ ገበያ ትንሽ በመራመድ ኢኮኖሚያቸው ቢነቃቃም፣ እንደገና ወደ ሶሻሊዝም ቅኝት ማዝገም የጀመሩት አብዛኞቹ የአፍሪካ አገራት፣ ይበልጥ በሙስና እየተነከሩና በዋጋ ንረት እየተናጉ ኢኮኖሚያቸው የሥራ ዕድል መፍጠር አቅቶት የስደት ቀውስ ውስጥ ገብተዋል። ሁጎ ቻቬዝና ሉላ ዳሲልቫ በመሳሰሉ መሪዎች የሶሻሊዝም መፈክር የታወጀባቸው እንደ ቬኒዝዌላና ብራዚል አይነት አገራትም እንዲሁ፣ በኢኮኖሚ ቀውስና በሙስና ተተብትበዋል።
በኢኮኖሚ ቀውስ መነሻነት የሚናጉ አገራት፣ አብዛኛውን ጊዜ ማብቂያ ወደ ሌለው የዘረኝነትና የሃይማኖት አክራሪነት ግጭት እንደሚናጡ ደግሞ በተደጋጋሚ አይተናል። ምናለፋችሁ? የዛሬ 25 ዓመት ከአውሮፓ ፖላንድና ቼክ፣ ከአፍሪካ ሴኔጋል እና ጋና፣ ከላቲን አሜሪካ ቺሊ እና ሜክሲኮ... በርካታ አገራት ፊታቸውን ወደ ነፃ ገበያ የካፒታሊዝም ስርዓት በማዞር መልካም የፖለቲካ ለውጥ እውን ማድረጋቸውን እናስታውስ። ያኔ በሮናልድ ሬገን እና በማርጋሬት ታቸር አማካይነት ደህና ተቀባይነት አግኝቶ የነበረው የካፒታሊዝም ቅኝት ገና አልተዳከመም ነበር። እየተዳከመ ሲመጣ ነው ችግር የተፈጠረው። ባለፉት 10 ዓመታት፣ መልካም የፖለቲካ ለውጥ ማየት ብርቅ ሆኗል። የፖለቲካ ለውጥ ማለት፣ በሶሻሊዝም የኢኮኖሚ ቅኝት መናጋት፣ አልያም በዘረኝነት ተቧድኖ መጋጨት፣ ወይም በሃይማኖት አክራሪነት መጨፋጨፍ ማለት ሆኗል። አንዴ ተለኩሶ ከቁጥጥር ውጭ ከሆነ፤ መመለሻ ወደሌለው ጦርነትና ግጭት ይሻገራል። “ካልደፈረሰ አይጠራም” የሚለው አባባል፣ “ከደፈረሰ አይጠራም” በሚል ፈሊጥ ተቀይሯል።   
ይሄን ሁሉ የዓለም ቀውስ የተመለከቱትና መፍትሄ ያጡት የአሜሪካና የአውሮፓ መንግስታት፤ “ዋናው ሰላም ነው፤ መንግስት እስከኖረ ድረስ ችግር የለም” ወደሚል ግራ የመጋባት ተስፋቢስነት የወረዱት በዚህ ምክንያት ነው። ምንኛ ያሳዝናል!   
አሳሳቢው ነገር ምን መሰላችሁ? የአገራችን ሁኔታ ግራ ከመጋባትም የባሰ ነው። ጨርሶ የአደጋውን መጠን የተረዳነው አይመስልም። የምርጫ ክርክሮችን ተመልክተናል። የብዙ ፖለቲከኞች ዲስኩር ሰምተናል። ግን፣ አንዳቸውም የአደጋውን ምንነትና መጠን እንድንገነዘብ የሚረዱ አይደሉም። በርካታ አገራትን ለትርምስ ከዳረጉ የቀውስ ምንጮች እንዴት መዳን እንደምንችል፣ ቁምነገረኛ ሃሳብ ሲቀርብ አልሰማንም። እነዚያ የቀውስ ምንጮች... ሌሎች አገራትን እንጂ ፈፅሞ ኢትዮጵያን የማይመለከቱ ነገሮች ናቸው እንዴ? ውስጥ ለውስጥ እየተንተከተኩ ያሉ ችግሮች አይደሉም እንዴ?
አዎ፣ ከዛሬ 14 ዓመት በፊት አልቃይዳ በአሜሪካ ከተሞች ላይ በአረመኔ የሽብር ጥቃት በሺ የሚቆጠሩ ሰዎችን ሲገድል፣ በርካታ “አዋቂ ነን” ባዮች፣ ነገሩን የአሜሪካና የኦሳማ ቢንላደን ፀብ አስመስለው ሲያቀርቡ እንደነበር እናስታውሳለን። የዛሬ 50 ዓመት የቬትናም እና የኩባ ኮሙኒስቶች ከአሜሪካ ጋር የነበራቸውን ፀብ፣ በርካታ የኢትዮጵያ ምሁራን እንደ ሩቅ ወሬ ነበር የሚቆጥሩት። ሶሻሊዝምና ኮሙኒዝም፣ ጨርሶ ለኢትዮጵያ አደጋ የሚሆንበት እድል እንደሌለው ነበር የሚያስቡት። አንዳንዶቹ የዘመኑ አብዮተኞች ደግሞ፣ የቬትናምና የኩባ ኮሙኒስቶችን በማድነቅ፣ የኋላ ኋላ ለሆቺሚኒ እና ለቼ ጉቬራ የውዳሴ መዝሙር እስከማዜም ደርሰዋል። ብዙም አልቆየም። ኮሙኒዝምን በሚያውለበልቡ ምሁራን ቆስቋሽነት ሶሻሊዝምን የሚያውጅ ደርግ መጣና፣ አገሪቱ በቀይ ሽብርና በረሃብ መከራዋን አየች። የኮሙኒዝም ፍቱን መድሃኒቱ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚን ማስፋፋት ቢሆንም፣ ካፒታሊዝምን በፅናት እየደገፈ የሚከራከር ይቅርና የኮሙኒዝምን አደገኛነት በግልፅ የሚያስረዳ ምሁርና ፖለቲከኛ በወቅቱ አልነበረም።
ለጭፍን እምነት ጥብቅና የሚቆም የሃይማኖት አክራሪነት በየአገሩ ሲበራከት እናያለን። ለአእምሮና ለሳይንስ መከራከር ጨርሶ አልተለመደም። እንደ ቁምነገርም አይቆጠርም። በየእለቱ ስለ ሃይማኖት አክራሪነትና አሸባሪነት ሲነሳ ብንሰማም፤ የጭፍን እምነት መድሃኒቱ ለአእምሮና ለሳይንስ ክብር መስጠት መሆኑን የሚናገር ምሁር፣ ፖለቲከኛ፣ ፓርቲ ወይም የመንግስት ባለስልጣን አጋጥሟችኋል?  
እንዲያውም፤ የሃይማኖት አክራሪዎች በኒውዮርክና በዋሺንግተን ጥቃት በፈፀሙ ማግስት፤ የሃይማኖት አክራሪነት ኢትዮጵያን የሚነካ አደጋ እንዳልሆነ ለማስመሰል የባጥ የቆጡን እየጎተቱ የሚለፍፉ ምሁራን ጥቂት አልነበሩም። አንዳንዶች ደግሞ፣ ከነጭራሹ የኦሳማ ፎቶ የተለጠፈበት ቲሸርት እስከመልበስ ደርሰው እንደነበር እናስታውሳለን። ሌሎች አገራትም፣ እንደዚሁ ራሳቸውን ሲያታልሉ ነበር - እነ ሊቢያና ግብፅ፣ እነ ናይጄሪያና ማሊ፣ እነ ሶሪያና እነ የመን ... እንደ ፈረንሳይ የመሳሰሉ አገራትም ሳይቀር፣ ከዳር ሆነው ለመመልከት ነበር የሞከሩት። ዛሬ ግን ብዙዎቹ የቀውስ መናሃሪያ ሆነዋል። ኢትዮጵያውያንም የሃይማኖት አክራሪነት ነበልባል ሰለባ እየሆንን ነው። ዋና ዋና አደጋዎችን በቅጡ አለመለየት፣ በጊዜ መፍትሄ አለማበጀትና አለመዘጋጀት... ውሎ መዘዝ አለው። ይህንን ያልተገነዘቡ የአገራችን ፓርቲዎች ግን፣ የሃይማኖት አክራሪነትን የፖለቲካ ቁማር መጫወቻ ሊያደርጉት ሲሞክሩ ይታያሉ። ወይ አላዋቂነት። በርካታ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ደግሞ፣ “ስለ ሃይማኖት አክራሪነትና ስለ አደጋው መናገር፣ ኢህአዴግን ለማጥላላት የሚያገለግል የመጫወቻ ካርድ አይደለም” ብለው ስለሚያስቡ ይተናነቃቸዋል። ገዢው ፓርቲ፣ “አክራሪ” እና “አሸባሪ” የሚሉ ቃላትን እንደዘበት በዘፈቀደ እየደጋገመ፣ ተራ የፖለቲካ መጫወቻ ካርድ ያደርጋቸዋል - አብዛኛውንም ጊዜ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ለማዋከብ ይጠቀምባቸዋል።
በአጭሩ፤ ከሃምሳ አመት በፊት ኢትዮጵያ ለኮሙኒዝም የተዳረገችበት የአላዋቂነት ስህተት፤ ዛሬም በሃይማኖት አክራሪነት ላይ እንዳይደገም ያሰጋል። ለመሆኑስ፣ የፖለቲካ ምርጫዎችና ክርክሮች፣ ዋና ዋና አደጋዎችን ለመከላከል ቁምነገረኛ ሃሳቦች የሚቀርቡበት አጋጣሚ እንዲሆኑ በማድረግ ካልተጠቀምንባቸው፣ ፋይዳቸው ምንድነው? ታዲያ፣ በአለማቀፍ ደረጃ ለምርጫዎች ሲሰጥ የነበረው ትኩረት መቀነሱስ ምን ይገርማል?

Read 4531 times