Monday, 25 May 2015 08:40

ዶ/ር አሸብር በሚወዳደሩበት ጊምቢ፣ ምርጫው ለሌላ ጊዜ ተላለፈ

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(1 Vote)

በነገው ዕለት የሚካሄደው 5ኛው አገር አቀፍ ምርጫ፣ በደቡብ ክልል ከፋ ዞን ቦንጋ ከተማ፣ ጊምቢ ምርጫ ክልል ላይ እንደማይደረግና ምርጫው ላልተወሰነ ጊዜ መተላለፉን ምርጫ ቦርድ አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መርጋ በቀና ከትናንት በስቲያ በሒልተን ሆቴል ጉዳዩን አስመልክቶ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፤ “በክልሉ ምርጫው በዕለቱ የማይካሄድ ሲሆን ላልተወሰነ ጊዜ እንዲተላለፍ ተደርጓል” ብለዋል፡፡ ምክንያቱን የተጠየቁት ፕሮፌሰር መርጋ፤ “ይህ በጣም ተራና ቁብ የማይሰጠው ጉዳይ ነው፤ ለጋዜጣዊ መግለጫም የሚበቃ አይደለም” ሲሉ መልሰዋል፡፡
ምርጫው እንዲተላለፍ የተወሰነበት የከፋ ዞን ቦንጋ ከተማ፣ ጊምቢ ምርጫ ክልል፤ የግል እጩ ተወዳዳሪው ዶ/ር አሸብር ወልደጊዮርጊስ፤ ከደህዴን ኢህአዴግ እጩ ተወዳዳሪ ዶ/ር መብራቱ ገ/ማርያም ጋር የሚፎካከሩበት እንደሆነ ይታወቃል፡፡
ምንጮች እንደሚሉት፤ ለፉክክር የቀረቡት የሁለቱ ወገኖች ደጋፊዎች ግጭት መፍጠራቸውና ግጭቱ እየተባባሰ መሄድ ለምርጫው መተላለፍ ዋና ምክንያት ሆኗል፡፡
የቦርዱ ሰብሳቢ ፕ/ር መርጋ በቃና፤ “በጥቂት ጊዜያት ውስጥ ችግሮችን ፈር አስይዘን ምርጫው ይካሄዳል” ብለዋል፡፡ ተፈጠረ ስለተባለው ግጭትም ሆነ ሌላ ምክንያት የቦርዱ ኃላፊ ከመናገር ተቆጥበዋል፡፡  

Read 2805 times