Monday, 25 May 2015 08:35

ጠ/ሚኒስትሩ በምረቃና የመሰረት ድንጋይ በመጣል ተወጥረው ሰነበቱ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

በአንድ ሳምንት 20 የሚደርሱ ፕሮጀክቶች ሲመረቁ፤ ከ10 በላይ የመሰረት ድንጋይ ተጥሏል


ያለፉት ጥቂት ሳምንታት ለኢህአዴግ ከፍተኛ ባለስልጣናት የውጥረት ጊዜ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ከመደበኛ ሥራቸው ውጭ ከምርጫ ጋር የተገናኙ እንቅስቃሴዎችንም ሲያከናውኑ ሰንብተዋል። የኢህአዴግ ሊቀመንበርና የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ለሆኑት አቶ ኃይለማርም ደሳለኝም ሁኔታው የተለየ አልነበረም፡፡ ያለፉትን ሳምንታት ለአዳዲስ ፕሮጀክቶች የመሰረት ድንጋይ በመጣልና የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶችን በመመረቅ ተወጥረው ነው ያሳለፉት። በአዲስ አበባና ክልል ከተሞች በአንድ ሳምንት ውስጥ 20 የሚደርሱ ፕሮጀክቶች የተመረቁ ሲሆን ከ10 በላይ ለሚሆኑ አዳዲስ ፕሮጀክቶች የመሰረት ድንጋይ ተቀምጧል፡፡
ባለፈው ሰኞ ማለዳ በአዳማ ከተማ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በ340 ሄክታር መሬት ላይ ለሚገነባው የኢንዱስትሪ ፓርክ የመሰረት ድንጋይ ያስቀመጡ ሲሆን የአዲስ አበባ ሚኤሶ የባቡር መንገድ ግንባታ የሃዲድ ዝርጋታ ፕሮጀክትንም መርቀዋል፡፡ የዚያኑ እለት ረፋዱ ላይ ደግሞ 102 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሃይል ያመነጫል የተባለውን የአዳማ ቁጥር 2 የንፋስ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት እንደመረቁ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ፅ/ቤት ድረ ገፅ ይጠቁማል፡፡
በነጋታው ማክሰኞ ጠ/ሚኒስትሩ ወደ ጂማ በማምራት ለጅማ የኢንዱስትሪ መንደር ግንባታና ለጅማ ባቡር ጣቢያ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ አኑረዋል፡፡ በዚህ ብቻ አላበቁም፡፡ የጅማ ቦንጋ 110 ኪሎ ሜትር የአስፓልት ኮንክሪት መንገድን እንዲሁም ከ250 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተከናወነውን የጅማ አባጅፋር አውሮፕላን ጣቢያ የማስፋፊያ ፕሮጀክትም መርቀዋል፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ የዚያኑ እለት ወደ ድሬደዋ ተሻግረውም በ1 ቢሊዮን ብር ይገነባል ለተባለው ዘመናዊ ስታዲየም እንዲሁም ለኢንዱስትሪ መንደር ግንባታ የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል፡፡
ከሳምንት በፊት ረቡዕና ሐሙስ ደግሞ አምቦ ነቀምት ነበሩ፡፡ በአምቦ የባቡር ጣቢያ የመሰረት ድንጋይ ያስቀመጡ ሲሆን በነቀምት የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ አኑረዋል፡፡ ከዚያው ከነቀምት ሳይወጡም የብረት ማዕድን አውጥቶ ብረት ለሚያመርት ፋብሪካ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል፡፡
ባለፉት ሳምንታት ሜጋ ፕሮጀክቶች ብቻ አልነበሩም የተመረቁት፡፡ ከት/ቤት አንስቶ እስከ የመጠጥ ንፁህ ውሃ ድረስ ተመርቋል፡፡ ባለፈው ማክሰኞ የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ያስገነባቸውን የአንደኛ ደረጃ ት/ቤት፣ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የገበያ ማዕከላት እንዲሁም የወጣቶች ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ያስመረቀ ሲሆን የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ በበኩሉ፤ በጀሞ 1 እና በቦሌ ሳይት ኮንዶሚኒየም ቤቶች አካባቢ ያስገነባቸውን ት/ቤቶች ረቡዕ እለት አስመርቋል፡፡
በደቡብ ክልል ሲዳማ ዞን በ149 ሚሊዮን ብር የተገነባው የአዋዳ - ቦርቻ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የተመረቀ ሰሆን የንፁህ ውሃ ፕሮጀክቱ በ43 ቀበሌዎች የሚኖሩ 257 ሺህ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሏል፡፡ በዚያው በደቡብ ክልል በስልጤ ዞን፣ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን እና የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈርጌሣ፤ የጠጠር መንገድ እና የሆስፒታል ግንባታ ፕሮጀክቶችን መርቀዋል፡፡   
በአዲስ አበባ በአዲስ ከተማ ክ/ከተማ ለሚገነባው ዘመናዊ ሆስፒታል የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠ ሲሆን አዲስ ለሚገነባው የብሔራዊ ቲያትር ህንፃም እንዲሁ የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠው በእነዚሁ ሳምንታት ነው፡፡  
በሌላ በኩል ተቃዋሚዎች፤ በምርጫው ዋዜማ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ በርካታ ፕሮጀክቶች መመረቃቸውና የመሠረት ድንጋይ መጣሉ የኢህአዴግ የምርጫ ቅስቀሳ ስትራቴጂ አካል ነው ሲሉ ይተቻሉ፡፡ የኢህአዴግ ጽ/ቤት የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሃላፊ አቶ ደስታ ተስፋው በበኩላቸው፤ “የፕሮጀክቶቹ መመረቅም ሆነ ለአዳዲስ ፕሮጀክቶች የመሠረት ድንጋይ መጣሉ ፈጽሞ ከምርጫው ጋር የሚገናኝ አይደለም፣ የመንግስት የእለት ተእለት ተግባር አካል ናቸው” ብለዋል፡፡
መንግስት የሠራቸውን ፕሮጀክቶች ቀደም ብሎም በተከታታይ ሲያስመርቅ ነበር ያሉት ኃላፊው፤ ህዝቡ ኢህአዴግን የሚመርጠው በተመረቁት ፕሮጀክቶች ብቻ አይደለም፤ በተከታታይ ያከናወናቸውን ጠንካራ ስራዎች መዝኖ ነው ብለዋል፡፡ “ምርጫውን ማንም ቢያሸንፍ ልማት አይቆምም” ያሉት የኢህአዴግ ጽ/ቤት ሃላፊው፤ “የምርጫው ውጤት እስኪታወቅ ድረስ መንግስት እጁን አጣጥፎ እንዲቀመጥ መፈለግ ትክክል አይደለም፤ ለምርጫ ተብሎ የሚመረቅ ፕሮጀክት የለም፤ ምርጫ ነው ብለንም ልማት አናቆምም” ብለዋል፡፡
በርካታ ፕሮጀክቶች ከዚህ ቀደምም ተመርቀዋል፤ የመሠረት ድንጋይም ተጥሎላቸዋል ያሉት ኃላፊው፤ በአጋጣሚ በምርጫው ሰሞን የተመረቁትን ብቻ አጉልቶ ወደ ሌላ ትርጉም መውሰድ ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡

Read 3563 times