Saturday, 28 January 2012 11:34

ጉዞ ወደ ጐንደር “ጐንደር ርቃብን ተጨንቀናል”

Written by  አንተነህ ይግዛው
Rate this item
(2 votes)

(ክፍል ሁለት)

የጉዞ ማስታወሻ

***

“አባይ ቁልቁለቱን

እንባዬ እያነቀኝ፣

አባይ አቀበቱን

ላብ እያጠመቀኝ፣

መቅረትስ አልቀርም

እስከዚያው ጨነቀኝ…”                        (የአገሬ ዘፋኝ)

***

 

 

ይነድዳል…

እሳቱ ይነድዳል…

አጥንት እንደ ጉልጥምት

ከእሳት ይማገዳል

ይከስላል ያምዳል

ይጨሳል…

አርባ ሰው ይጨሳል

ህልም እንደ ጉም ሽቅብ፣ ወጥቶ እየበነነ

ይተናል ይነሳል

በንፋስ ይሳሳል

ይፈስሳል

ያው እንባ ይፈስሳል

ወገን ሲለበለብ ሲቃጠል እያየ

ወገንም ያለቅሳል

አባይም ይፈስሳል

እንባውም

ይሄዳል

አባይም ይሄዳል

“ውሃ ጠማኝ” ብሎ፣ ልጁ እየጠየቀው

“እሳት በላኝ” ብሎ፣ እየጨቀጨቀው

እሱ ምን ጨነቀው

እንኳን በቦይ ፈስሶ፣ እሳቱን ሊያጠፋ

ሰስቶ አንድ ጭልፋ

ለልጅ ጥም መቁረጫ

አባይ የወንዝ አባት

መች ለልጅ ይሳሳል፣

እነሱ ሲከስሉ

የራሱን ይፈስሳል

አሰቃቂው ትዕይንት ቀጥሏል፡፡ ሲያዩት የሚያሳቅቅ “ትራጄዲ” በረሃው ውስጥ እየተከናወነ ነው፡፡ አውቶቡሱ ምድጃ ሆኖ ከገደል ስር የአጥንት ፍም ታቅፏል፡፡ የበረሃው ንፋስ “እፍ” እያለ የሚያግለበልበው ፍም፣ የእሳት አለንጋ ፈትሎ ዙሪያውን ይወነጨፋል፡፡ ነበልባሉ ይጋረፋል፡፡ ወገነኑን ከምድጃ ነጥቆ ለማትረፍ ከአፋፍ ወደ ገደሉ የወረደውን ሁሉ “እንዳትጠጉኝ” እያለ ያስፈራራል፡፡

እሳቱ ይነድዳል…

ሩቅ

እንዲህ ዘግናኝ ነገር ታክሎበት ይቅርና፣ አባይ በረሃ ድሮም በፍርሃትና በጭንቀት የሚያርድ ቦታ ነው፡፡ እንኳን እሳት ነዶ ድሮም አባይ ቋያ ነው፡፡

ተፈጥሮ ከጐሃጽዮን ጓሮ እስከ ደጀን ደጃፍ አጥልቃ የማሰችው ጭው ያለ ገደል ነው - አባይ በረሃ!

እዚህ አስፈሪ ገደል ውስጥ አሰቃቂ ነገር የገጠመን መንገደኞች ነን፡፡ የፈራን መንገደኞች፡፡ ገደሉ ስር አመድ ሆነው የቀሩ 40 መንገደኞች ዕጣ እንዳይደርሰን የሰጋን መንገደኞች ነን፡፡

ስለሞታቸው ስናነባ ቆይተን፣ ስለሞታችን ማሰብ የጀመርን፡፡

ከግርጌያችን በአባይ ወንዝ ላይ የተዘረጋውን ዘመናዊ ድልድይ በጥርጣሬ የምናይ፣ አባይን ተሻጋሪ፣ እስከ ደጀን አፋፍ ያለው ጠመዝማዛ የአቀበት መንገድ የሚጠብቀን መንገደኞች ነን፡፡

የበረሃው ወለል ስር እየተጠማዘዘ ቁልቁል የሚፈሰውን አባይ አሻግሬ እመለከተዋለሁ፡፡ አባይን ፈራሁት፡፡ ክቡር ዶ/ር ሐዲስ አለማየሁ በፍቅር እስከመቃብር እንዲህ ሲሉ የገለፁትን አባይ…

“…አባይ በረሃ የሲኦልን ግርማ ተጐናጥፎ እስሩ የአባይ ወንዝ የአናቱና የጅራቱ መጨረሻ እንደማይታይ ዘንዶ ተጋድሞ…”

አባይን ፈራሁት፡፡ አሻግሮ የሚወስደውን መንገድ ተጠራጠርኩት፡፡ ልቤ መፍራት ጀምሯል፡፡ በወገኖቼ የደረሰ መከራ፣ እነሱን ጨርሶ ወደ እኔ ስላለመሻገሩ በምን እርግጠኛ መሆን እችላለሁ?

“…አባይ ለቆላው የመኪና መንገድ፣ ለወንዙ ድልድይ ሳይሰራለት ከጐጃም ወደ አዲስ አበባ፣ ከአዲስ አበባ ወደ ጐጃም የሚሄድ መንገደኛ ሁሉ ጐሃጽዮን ወይም ደጀን እስኪደርስ ድረስ ልክ የመከራ ትንቢት እንደተነገረበት ሰው ከአሁን አሁን መከራው ደረሰብኝ ብሎ ልቡ እየፈራና እየራደ የሚያልፍበት ቦታ ነበር፡፡…” ብለዋል ደራሲው፡፡

“ነበር” ባሉት አልስማማም፡፡

አባይ አሁንም እሳቸው እንዳሉት ሆኖብኛል፡፡

እሳቸው ያሉት የቀድሞው ድልድይ ከተሰራ በኋላ ነው፡፡ የ”ህዳሴው” ድልድይ ከጐኑ ከተነጠፈ በኋላ፣ ኮረኮንቹ በጃፓን እጅ አስፓልት ከለበሰ በኋላ …ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ አሁንም ለእኔ አባይ እንደዛው ነው፡፡

ድልድዩን አልፌ፣ ዳገቱን ተሻግሬ፣ አፋፍ እስክወጣ፣ ደጀን እስክደርስ እኔ፣ የመከራ ትንቢት እንደተነገረበት ሰው ነኝ፡፡

“ከአሁን አሁን መከራው ደረሰብኝ” ብሎ ልቡ እየፈራና እየራደ ቀጣይ ጉዞውን ሊጀምር ወደ ሚኒባሱ ገብቶ የተቀመጠ ፈሪ መንገደኛ ነኝ እኔ፡፡

ዝም ሚኒባሷ…12 ጋዜጠኞችን ይዛ ከአዲስ አበባ የተነሳችው ነጯ ሚኒባስ … ከፊቷ የነበረው አውቶቡስ የሄደበትን የገደል መንገድ በፍርሃት እያየች ዳር ይዛ ቆማ የቆየች ሚኒባስ፣ አስራ ሁለት ጋዜጠኞችን መልሳ የጫነች የእኛ ሚኒባስ፣ እንደገና ጉዞ ጀምራለች፡፡ አስራ ሁለት ዝምታ ጭና ቁልቁል በቀስታ ትጓዛለች፡፡

ሚኒባሷ ውስጥ ነን፡፡ የየግል ዝምታ ሆነን፡፡ የየራስ ፍርሃት፡፡ የየራስ ስጋት፡፡ የየራስ ጭንቀት ሆነን!

ሁሉም ወደ ራሱ ዛጐል ተከትቶ ዝም ብሏል፡፡

ከበረሃው መንጋጋ በቸር ስለመውጣቱ ይጨነቃል፡፡ የሚያየው ሁሉ ስጋት ሆኖበት ይሸበራል፡፡

ድልድዩ ላይ ደርሰናል፡፡

ከቁልቁለት ስጋት ወደ ዳገት ስጋት የምንሸጋገርበት ድልድይ ላይ፡፡ ይሄ ድልድይ እንደ ጋዜጠኛ እና እንደ መንገደኛ ትርጉሙ እየቅል ነው፡፡ ስንዘግብ “የህዳሴው” ልንለው እንችላለን ስንጓዝ ግን “የስጋቱ” እያልን ነው፡፡

ርዝመትና ስፋቱን ይሄን ያህል ነው ብለን ለመናገር አሁን ጊዜው አይደለም፡፡ “ምን ያህል ገንዘብ ፈጀ” እንዳትሉኝ፡፡

እንደ እኛ በፍርሃት ሲሻገሩት የድሮ ልኩ ይዛባል፡፡ ርዝመቱ ይጨምራል፡፡ ስፋቱ ይቀንሳል፡፡ ዋጋው ይጨምራል፡፡

አቀበቱ …

የማይገፋው አቀበት ከፊታችን ተገትሯል፡፡ ከሸለቆው ወለል አንስቶ እስከ ሰማይ ጥግ የጋራ አጥር ተዘርግቷል፡፡

እየፈራን እየተከዘን እየሰጋን የጋራውን መንገድ ተያያዝነው

ሚኒባሷ ጠመዝማዛውን መንገድ ተከትላ ጋራውን እየታከከች በዝግታ ትጓዛለች፡፡ ሙቀቱ እየጨመረ ነው፡፡ በረሃው መፋጀት ይዟል፡፡

ከህዳሴው ድልድይ አንስቶ እስከ ደጀን አፋፍ እየተጠማዘዘ ሽቅብ የሚያወጣውን መንገድ ለመጨረስ 25 ያህል ደቂቃዎች ፈጅቶብናል፡፡ ይሄን የምትለው ሰአቴ ናት፡፡ እኔ ግን እንዲህ አልልም፡፡ የአቀበቱ መንገድ ሰአቴ እንደምትለው 25 ደቂቃ አይደለም፡፡ ጉዞው በደቂቃም፣ በሰአትም፣ በቀን በሳምንት በወራት በአመታትም አይለካም፡፡ የዘመናትን ርዝማኔ ያለው ነው ጉዞው፡፡ በረሃው ውስጥ ጊዜ ቀርፋፋ ይሆናል፡፡

ከዘመናት ርዝማኔ በኋላ ነው ሚኒባሷ በረሃውን ጨርሳ ደጀን አፋፍ ላይ የደረሰችው፡፡

አፋፍ ላይ ሆኜ ወደኋላዬ ተመለከትኩ፡፡

ይሄው አባይ ይሉት ስምጥ፣ ይሄው አባይ ይሉት ምጥ፡፡

ከአፋፍ እስከ አፋፍ ተሰርጉዶ የሚታየኝ ይሄው አባይ፡፡

ጉዞው ቀጥሏል፡፡

አሁን በተወሰነ መልኩም ቢሆን ሚኒባሷ ውስጥ አንዣቦ የቆየው ዝምታ እየተገፈፈ ነው፡፡ አቀበት ቁልቁለት አልፎ ለጥ ያለ መንገድ መጥቷል፡፡ እሱን ተከትለን ከደጀን ወጀል፣ ከሉማሜ - አንበር እንጓዛለን፡፡

ግራና ቀኙን አገር ሙሉ የጤፍ ክምር ይታያል፡፡ የጐጃም ገበሬ የአመት ልፋቱን ውጤት ሊያፍስ አውድማ መለቅለቅ ጀምሯል፡፡

ሻፎ ጉዳልማ የተባለች የገጠር ቀበሌ ስንደርስ ከሚኒባሷ ወርደን ዘና ለማለት ተስማማን፡፡ የጐጃም ገበሬ እንዲህ አውድማ ጥሎ በራይ በጀመረበት ወቅት ማንም ይሁን ማን አልፎ የሚሄድን ሁሉ ከሩቅ እየጠራ እህል ውሃ የማቃመስ ልማድ አለው፡፡

አቶ ቢተውም ድንገት የደረሱባቸውን መንገደኛ ጋዜጠኞች በክብር ነበር የተቀበሉት፡፡ ከንፍሮ ከጠላው “እነሆ” ብለው ነው ያቋደሱት፡፡

“ቸር ያድርሳችሁ” ብለው ነው የሸኙን፡፡

“ቸር ያድርሳችሁ” ብሎ ምኞት ትርጉሙ የገባኝ አሁን ነው፡፡ “ቸር መድረስ” ምን ማለት እንደሆነ በትክክል ያወቅኩት ዛሬ ነው፡፡ መንገድ ላይ የቀሩ ባለክፉ ዕጣ መንገደኞች አባይ በረሃ ውስጥ አመድ ሆነው አይቻለሁ፡፡

አሁን የጥንቷ መንቆረር፣ የዛሬዋ ደብረማርቆስ ደርሰናል፡፡

ሻይ ቡና ለማለት ያረፍንባት ደብረ ማርቆስ ለዘመናት ተጭኗት የነበረውን ድብታ አራግፋ ቀና ቀና ማለት ጀምራለች፡፡

“ያስተዳድሯት የነበሩት ንጉስ ተክለሃይማኖት ከመቃብር ቢወጡ እንዳስቀመጧት ያገኟቷል” ይባልላት የነበረች “አይለወጤ” ደብረማርቆስ ለውጥ ለውጥ መሽተት ጀምራለች፡

ቀጣይ ነው ጉዞው…

450 ኪሎ ሜትር መንገድ ከፊታችን ይጠብቀናል፡፡

ስለዚህ መፍጠን አለብን፡፡ መፍጠን አጉል ነገር ሊያመጣ እንደሚችል ባናጣውም መፍጠን ፈልገናል፡፡ ወደፊት መገስገስ…

ወደ አማኑኤል፣ ወደ ደንበጫ፣ ወደ ጅጋ፣ ወደ ፍኖተ ሰላም ወደፊት በምትፈጥን ሚኒባሳችን መስኮት አሻግሬ እመለከታለሁ፡፡ ማንኩሳ በሚኒባሳችን ፍጥነት ወደኋላችን ስትሮጥ አያታለሁ፡፡ የፍቅር እስከ መቃብሩ በዛብህ የተወለደባት ማንኩሳ!

ቡሬ ልንገባ ጥቂት ሲቀረን ከመንገድ ዳር ቆመው ኮክ የሚሸጡ ህፃናት አገኘን፡፡ ቆም ብለን የሚበቃንን ያህል ኮክ ሸምተን ጉዞ ስንጀምር፣ እኔ ስለ ኮክ ማሰብ ጀመርኩ፡፡

“ኮክ አሁንም በህይወት አለ እንዴ?” እያልኩ፡፡

“ኮክ” የሚባል ነገር ካየሁ ረጅም ጊዜ አልፎኛል፡፡

እውነት ግን እንዲህ እንደ ኮክ፣ ዘመን ቀስ በቀስ እያጠፋቸው ያሉ ብዙ ነገሮች እንዳሉ አስባችሁ ታውቃላችሁ? በቃ ልብ ሳንላቸው ቀስ በቀስ እየተረሱ የቀሩ ብዙ ነገሮች አሉ’ኮ፡፡ አንድ ወዳጄ በአንድ ወቅት እንዳጫወተኝ እርግጥም ብዙ እየጠፉ ያሉ ነገሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ እፉዬ ገላ፣ ኪሮሽ፣ ሰደርያ፣ ካራቴ ጫማ፤ ቀጭቀጭ እስክርቢቶ፣ እጅ የሚመስል እጀታ ያላት የብረት ሚዶ፣ ዘመሚት፣ መሐረብ፣ ቶንዶስ፣ ካፌኖል፣ እከክ፣ ቅጫም፣ ሙጀሌ፣ እንቁራሪት፣ ቅንጬ፣ ስኩየር ሉክ፣ ተልባ…

እውነት ግን እነዚህ እነዚህ ሁሉ አሁንም በአገር አሉ?

ምን እነዚህ ብቻ! ጐንደር የምትባል አገርስ በአገር አለች?

ምን ላድርግ ጠፋችብኝ እኮ! ብንሄድ ብንሄድ የማንደርስባት የት ሄዳ ነው?

አዎ ደርሰናል፡፡

እዚህ “የበሬን ምስጋና

ወሰደው ፈረሱ” ብሎ ነገር አይሰራም፡፡

የአዊ ፈረስ ቀድሞ መድረስ ብቻም ሳይሆን ተጠምዶ ማረስም ያውቅበታል፡፡

ይሄ አገር ምድሩን የሞላው የእህል ክምር ፈረስ ባረሰው ማሳ ላይ የበቀለ ነው፡፡

ከመሸ ነው ባህርዳር የገባነው፡፡ ለአይን ያዝ ማድረግ ከጀመረ፡፡ እራት ባህርዳር በልተን ለቀጣዩ ጉዞ ስንዘጋጅ ከምሽቱ 1 ሰዓት ከ45 ደቂቃ ሆኖ ነበር፡፡

ቀጣዩ ጉዞ በጨለማ ነው፡፡

በድቅድቁ ጨለማ ውስጥ…

በስተግራ ጥቁር አባይ በጥቁር ጣና ላይ ይፈስሳል፡፡ ነጯ ሚኒባስ በጥቁር ድልድይ ተሻግራ ወደ ጐንደር ምድር ትጓዛለች፡፡ የዛሉ ጋዜጠኞችን ይዛ፣ የታከታቸው መንገደኞችን አሳፍራ… ወደ ወረታ… ወደ ሐሙሲት… ወደ አዲስ ዘመን… ወደ ሌላው የጨለማ ጠመዝማዛ መንገድ… ወደ ጣራ ገዳም… ዝም ብለናል…

ጐንደር ርቃብን ተጨንቀናል፡፡

እውነት ግን ጐንደር የት ሄዳ ነው?

(ይቀጥላል)

 

 

 

Read 3336 times Last modified on Saturday, 28 January 2012 11:43