Print this page
Saturday, 16 May 2015 11:16

የብሩንዲ መፈንቅለ መንግስት ውጥረት ፈጥሯል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

በአገሪቱ በተቀሰቀሰው ግጭት ከ20 በላይ ሰዎች ሞተዋል
      አገር ጥለው የተሰደዱ ዜጎች ከ500 ሺህ በላይ ደርሰዋል

    የቀድሞው የብሩንዲ የደህንነት ቢሮ ሃላፊ ሜጀር ጄኔራል ጎዲፍሮይድ ኒዮምባሬህ ባለፈው ረቡዕ በአገሪቱ መዲና ቡጁምቡራ ከሚገኝ የጦር ካምፕ በሬዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት፣ የፕሬዚደንት ኑኩሩንዚዛ አገዛዝ ማክተሙንና አገሪቱን የመምራቱን ሃላፊነት የሚረከብ ጊዜያዊ ብሄራዊ ኮሚቴ መቋቋሙን ያስታወቁ ሲሆን አገሪቱ በከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ትገኛለች፡፡
የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ከሌሎች አገራት መንግስታት ጋር በጉዳዩ ዙሪያ ለመምከር ወደ ታንዛኒያ መሄዳቸውን ተከትሎ፣ ጄኔራሉ በአገሪቱ መፈንቅለ መንግስት መካሄዱን ማስታወቃቸውንና በሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በቡጁምቡራ አደባባይ በመውጣት ደስታቸውን እንደገለጹ የዘገበው ቢቢሲ፤ አገዛዙን የሚቃወሙ ወታደሮችም በሁለት የጦር ታንኮች ታግዘው ወደ መዲናዋ ማዕከላዊ ክፍል ማምራታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ተቃውሞው የበለጠ ተጠናክሮ መቀጠሉንና ከትናንት በስቲያም በመንግስት ጦርና በተቃዋሚ ሃይሎች መካከል በቡጁምቡራ ግጭት እንደተከሰተ የጠቆመው ዘገባው፣ ስርዓቱ ይፍረስ የሚለውን የተቃዋሚዎች አቋም በመደገፍ ተቃውሞውን ከተቀላቀሉት የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር ጋር በተደረገ ድርድር መፈንቅለ መንግስቱ መቆሙን አንድ የአገሪቱ ጦር መሪ ማስታወቃቸውንም ገልጧል፡፡
ፕሬዚዳንት ንኩሩንዚዛ፤ መፈንቅለ መንግስት እንደታወጀባቸው ሲያውቁ ከታንዛኒያ ወደ ብሩንዲ ቢመለሱም፣ ሜጀር ጄኔራል ጎዲፍሮይድ ኒዮምባሬህ አውሮፕላን ማረፊያውና የአገሪቱ ድንበሮች እንዲዘጉ በማዘዛቸው፣ ፕሬዚዳንቱ ወደ አገራቸው መግባት እንዳልቻሉና ወደ ዳሬ ሰላም መመለሳቸውን ያስታወቀው የቢቢሲ ዘገባ፣ ፕሬዚዳንቱ በትዊተር ገጻቸው በኩል ከትናንት በስቲያ ባስተላለፉት መልዕክት የተቃውሞ እንቅስቃሴው በቁጥጥር ስር ውሏል፣ ህገመንግስታዊ ስርአቱም ከአፍራሽ ሃይሎች ተጠብቋል ብለዋል፡፡
የመንግስት ጦር የፕሬዚደንቱን ቤተ መንግስት፣ የብሄራዊ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያውንና አውሮፕላን ማረፊያውን ጨምሮ በከተማዋ የሚገኙ ቁልፍ ቦታዎችን እንደተቆጣጠረ ቢያስታውቅም፣ የመፈንቅለ መንግስቱ መሪ ግን መዲናዋን ሙሉ በሙሉ በቁጥጥራችን ውስጥ አድርገናል ሲሉ አስተባብለዋል፡፡
የመፈንቅለ መንግስቱ ቃል አቀባይ ቬኖን ንዳባንዜ በበኩላቸው፤ “መንግስት ተቃውሞውን እንዲገቱ ያሰማራቸው ወታደሮችም ከጎናችን ቆመዋል፣ ድሉ የኛ ነው” ሲሉ ከትናንት በስቲያ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ተናግረዋል፡፡
ከሲቪል ማህበረሰብ ቡድኖች፣ ከሃይማኖት መሪዎችና ከፖለቲከኞች ጋር በመሆን በአገሪቱ የሽግግር መንግስት መቋቋም የሚችልበትን ሁኔታ እያመቻቹ እንደሚገኙም ሜጀር ጄኔራል ጎዲፍሮይድ ኒዮምባሬህ ተናግረዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ኑኩሩንዚዛ ህገ መንግስቱ ከሚፈቅድላቸው ውጭ ያለ አግባብ ለሶስተኛ ዙር በፕሬዚዳንትነት ለመወዳደር መዘጋጀታቸውን የተቃወሙ በርካታ የአገሪቱ ዜጎች አደባባይ ወጥተው ተቃውሟቸውን ከማሰማት ባለፈ፣ አገዛዙን ከስልጣን ለማውረድ መነሳታቸውን የገለጹት ጄኔራሉ፤ ጊዜያዊ ኮሚቴው ብሄራዊ አንድነትን መልሶ በመፍጠርና ምርጫው በፍትሃዊና ሰላማዊ ሁኔታ መካሄድ የሚችልበትን ሁኔታ ለማመቻቸት  እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡
ከሁለት ሳምንታት በላይ በዘለቀው ተቃውሞ ከ20 በላይ ዜጎች ለሞት መዳረጋቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ አገር ጥለው የተሰደዱ ብሩንዲያውያን ዜጎች ቁጥርም ከ500 ሺህ በላይ መድረሱን አመልክቷል፡፡

Read 2870 times
Administrator

Latest from Administrator