Saturday, 16 May 2015 11:14

የአይሲስ ምክትል መሪ ተገደለ

Written by 
Rate this item
(5 votes)

 የኢራቅ መከላከያ ሚኒስትር አይሲስ በመባል የሚጠራው ጽንፈኛ አራጅ የሽብር ቡድን ምክትል መሪ የሆነው አቡአላ አልአፍሪ በህብረቱ ሀይሎች በተካሄደ የአየር ጥቃት ባለፈው ማክሰኞ መገደሉ ይፋ ተደርጓል፡፡  
በዩቲውብ የተለቀቀው አጭር የቪዲዮ ፊልም እንደሚያሳየው፤ አቡ አላ አልአፍሪ የተገደለው በኢራቅ የታል አፋር ከተማ በሚገኝ አንድ መስጊድ ውስጥ ነው፡፡ አብዱራህማን ሙስጠፋ አልቃዱሊ በሚል ተለዋጭ ስም የሚታወቀውና በ1957 ሞሱል ከተማ ውስጥ የተወለደው አቡ አላ አልአፍሪ የኢራቅ የአልቃኢዳ ቡድን ምክትል መሪና የሞሱል ከተማ ክንፍ ዋና አዛዥ በመሆን አገልግሏል፡፡
የፊዚክስ መምህር የነበረው አቡ አላ አልአፍሪ፤ የኢራቅ የአልቃኢዳ ምክትል መሪ በነበረበት ወቅት በኦሳማ ቢንላደን  ዘንድ ከፍ ያለ ሞገስ ማግኘት የቻለና ለአይሲስ ከፍተኛ መሪነት በዋናነነት የታጨ ሰው ነበር፡፡ የቱርክሜን ብሔረሰብ አባላት ከሆኑ የአይሲስ ከፍተኛ መሪዎች ግንባር ቀደም የሆነው አቡአላ አልአፍሪ የአይሲስ ዋነኛ መሪ መሆን ያልቻለውና የመሪነቱ ስልጣን ለአቡበከር አልባግዳዲ የተሰጠው አቡበከር አልባግዳዲ የዘር ሀረጉ ከነብዩ ሞሀመድ የዘር ሀረግ ስለሚመዘዝ ብቻ ነው፡፡
አቡአላ አልአፍሪ ከመገደሉ በፊት በተፈፀመበት የአየር ጥቃት ክፉኛ ቆስሎ አልጋ ላይ የዋለውን የአይሲስ መሪ አቡበከር አልባግዳዲን ተክቶ ቡድኑን ሲመራ ነበር ተብሏል፡፡
አሜሪካ በቁጥጥር ስር ለማዋል በጥብቅ ከምትፈልጋቸው ዋነኛ አሸባሪዎች ውስጥ አንዱ መሆኑን በመጥቀስ “ጠቁሞ ላስያዘው” የ7 ሚ. ዶላር ወሮታ እከፍላለሁ ስትል የነበረ ሲሆን የአቡአላ አልአፍሪን መገደልን ገና አምና የተቀበለችው አትመስልም፡፡ የዚህን ነብሰ በላ አሸባሪ መሞት ባይኔ በብረቱ አይቼ ካላረጋገጥኩ በቀር የሰውየው መገደል ዜና ከሆዴ አይገባም ብላለች፡፡

Read 2574 times