Saturday, 16 May 2015 11:10

ሰው ሲቃና፣ ተዓምረኛ እንደሆነ... በአይፎን ታይቷል

Written by  ዮሐንስ ሰ.
Rate this item
(0 votes)

 ባለፉት አስራ ሁለት ወራት፣ ለገበያ ካቀረባቸው ሁለት መቶ ሚሊዮን አይፎኖችና ሌሎች ምርቶች 63 ቢሊዮን ዶላር ትርፍ እንዳገኘ አፕል ኩባንያ በቅርቡ ገልጿል። ሰላሳ ቢሊዮን ዶላር ከሚገመተው የኢትዮጵያ ጠቅላላ አመታዊ ምርት ጋር አነፃፅሩት። እጥፍ ገደማ ነው።
አፕል ኩባንያ፣ በአዳዲስ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች፣ የኮምፒዩተር ያህል አቅም ያላቸውና ለአጠቃቀም የተመቹ አይፎኖችን ለአለም ያስተዋወቀው የዛሬ ስምንት ዓመት ነው። በመጀመሪያው ዓመት አምስት ሚሊዮን ያህል አይፎኖችን የሸጠ ጊዜ ነው፤ “የሞባይልን ታሪክ የሚቀይር ስኬታማ ኩባንያ” ተብሎ የተሞገሰው። ብዙዎች አያስታውሱ ይሆናል እንጂ፣ ከጥቂት ጊዜ በፊት ኩባንያው በተደራራቢ ኪሳራዎች ከገበያ ለመውጣት የገደል አፋፍ ላይ ደርሶ ነበር። ከኩባንያው መስራቾች መካከል አንዱ የሆነው ስቲቭ ጆብስ፣ በየጊዜው አዳዲስ የፈጠራና የቢዝነስ ሃሳቦችን ቢያመጣም ባልደረቦቹ አልተቀበሉትም። ከነጭራሹም ኩባንያውን ለቅቆ እንዲወጣ አሰናበቱትና ኪሳራው ተባባሰ። ደግነቱ፣ “በቢዝነስ ሃሳብ ስላልተግባቡ ለመለያየት ወሰኑ” ማለት፣ “ዘላለማዊ የመጠፋፋት ቁርሾና ቂም ፈጠሩ” ማለት አይደለም።
ስቲቭ ጆብስ ተጠርቶ ኩባንያውን እንደገና እንዲመራ ሲደረግ፣ አክሳሪው የውድቀት አቅጣጫ ተለውጦ፣ ወደ ትርፋማ የስኬት ጉዞ ማንሰራራት ጀመረ። በሺ የሚቆጠር ዘፈን ለማከማቸትና በቀላሉ ለማጫወት የሚያስችሉ አይፖዶችን አምርቶ ሲያቀርብ፣ ገበያ ደራለት። አፕል፣ የቀድሞ ዝናውን አስመለሰ። ያኔ ነው፣ ትልልቅ ኩባንያዎች ወደሚፎካከሩበት የሞባይል ገበያ ለመግባት የወሰነው። የፉክክሩን ሃያልነት መቋቋም ይችል እንደሆነ ብዙዎች ቢጠራጠሩም፣ አፕል ገበያውን የተቀላቀለው ከቀድሞ የሞባይል ምርቶች በእጅጉ የላቀ የፈጠራ ውጤት በማቅረብ ነው - የአይፎን ምርትን።
በአይፎን ምርቶቹ ተወዳጅነት ለማትረፍ ጊዜ አልፈጀበትም። ግን፣ ‘ተሳክቶልኛል’ ብሎ መተኛት የለም። ለሚያንቀላፉ ቀርቶ፣  የገበያ ፉክክሩ ለታታሪዎችም ፋታ የሚሰጥ አይደለም። ያኔ የዛሬ 8 ዓመት በመላው ዓለም በብዛት ከተሸጡት አስር ምርጥ የሞባይል አይነቶች መካከል፣ የሰባቱ አምራች ማን ይመስላችኋል? ዝነኛው ኖኪያ ኩባንያ ነው። ነገር ግን፣ ኖኪያ በስኬት አልቀጠለም። ከወር ወር ወደ ታች እየተንሸራተተ ከምርጦች ግርጌ እንኳ መቆየት አቅቶት ከሰንጠረዡ ተሰናብቷል።
የአእምሮ ተዓምር
ስኬታማ መሆን ማለት ዛፍ ላይ እንደመውጣት ብንቆጥረው፤ ስኬታማ ሆኖ መዝለቅ ደግሞ ዛፍ ላይ እንደማደር ይሆናል። ለአፍታ የሚያንቀላፋ፣ ዛሬ ባይሆን ነገ አልያም ከነገ ወዲያ ቁልቁል መፈጥፈጥ አይቀርለትም። አፕል፣ ለጊዜው ከሁሉም የላቀ ምርት በማቅረቡ ብቻ አይደለም ስኬታማ የሆነው። ይልቅስ፣ ከሳይንስ ግኝቶች ጋር እኩል እየተራመደ፣ ምርቶቹን ሳያሰልስ በቴክኖሎጂና በዲዛይን የማሻሻል ብቃት በመላበሱ ነው በትርፋማነት መገስገስ የቻለው። (ልብ በሉ። ከሦስቱ የስኬት ምሶሶዎች መካከል አንዱ ይሄ ነው። የሳይንስ ግኝትና የቴክኖሎጂ ፈጠራ ማለት ሌላ አይደለም። ለእውነታ ክብር የመስጠት ቅንነትና፣ አእምሮን የመጠቀም ፅናት ነው - ቁልፉ ጉዳይ)። እናም፣ በዚሁ መንገድ አፕል በሁለተኛው ዓመት ከአስር ሚሊዮን በላይ አይፎኖችን በመሸጥ የስኬት ደረጃውን ከፍ አደረገ። በሦስተኛው ዓመትም እንደገና በ25 ሚሊዮን አይፎኖች ሽያጭ የራሱን ሬከርድ ሰብሯል። በአራተኛው ዓመት ደግሞ ሃምሳ ሚሊዮን ገደማ አይፎኖችን።
በአምስተኛው ዓመት ሽያጩን ወደ ዘጠና ሚሊዮን ያሳደገው አፕል፣ ምርቶቹን በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ከማሻሻል ስላልቦዘነ፣ የስኬት ገድል ማስመዝገቡን አላቋረጠም። አምና 150 ሚሊዮን አይፎኖችን፣ ዘንድሮ ባለፉት 12 ወራት ደግሞ ሁለት መቶ ሚሊዮን አይፎኖችን በመሸጥ የስኬታማነት ታሪኩን ቀጥሏል። አይፖዶችን፣ ማክ ኮምፒዩተሮችን፣ አይፓዶችን እና አይፎኖችን በመሳሰሉት ተወዳጅ ምርቶቹ፣ ባለፉት ሶስት አመታት ውስጥ ብቻ የምርቶቹን መጠንና ሽያጭ በእጥፍ አሳድጓል። ከሶስት አመት በፊት ሰማኒያ ቢሊዮን ዶላር የነበረው አመታዊ ሽያጭ፣ ዘንድሮ 160 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል። አርባ ቢ. ዶላር የነበረው አመታዊ ትርፍ ደግሞ፣ ዘንድሮ ከ60 ቢ. ዶላር በላይ ሆኗል።
ትርፋማነት - የሃብት ዝርፊያ ሳይሆን የሃብት ፈጠራ
አፕል፣ ለባለአክሲዮኖች የሚያከፋፍለው ዓመታዊ የትርፍ ድርሻ ሳይቆጠር፣ የኩባንያውን የአክሲዮን መጠን ብቻ ብንመለከት ከኢትዮጵያ ይበልጣል። ባለፉት አርባ ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ የተመረተና የተሰራ ነገር ሁሉ በገንዘብ ተሰልቶ ቢደመር፣ ከ700 ቢሊዮን ዶላር አይበልጥም። ከእነ ስቲቭ ጆብስ ጥበበኛ አእምሮና ሙያተኛ እጅ የተገኙ የስራ ፍሬዎችን ደግሞ እንይ። አርባኛ ዓመቱን ለመድፈን የተቃረበው አፕል ኩባንያ፣ ‘ሀ’ ብሎ ሲጀምር 3ሺ ዶላር የማያወጣ ኩባንያ ነበር። ዛሬ 700 ቢ. ዶላር የሚያወጣ የሃብት ፋብሪካ መሆኑን ስንመለከት፣... ለካ ‘ሚዳስ’ የእውነት ነው! ብንል አይገርምም። ሚዳስ በእጁ የነካው ነገር ወደ ወርቅ ይቀየራል እየተባለ የሚነገርለት በከንቱ አይደለም ማለት ነው።
ብሩህ አእምሮውን በመጠቀም፣... “የሙያተኛ እጅ ባለቤት” ለመሆን የበቃ ጥበበኛ ሰው፣ መልካም አላማውን ለማሳካት ከተጋ...  እውነትም ተዓምር ይፈጥራል - እንደ ‘ጀግናው ሚዳስ’። በድሮ የግእዝ አነጋገር ‘ቅዱስ ሚዳስ’ ልንለው እንችላለን። ለካ፣ የሚዳስ ታሪክ ተረት አይደለም። የሚዳስ ታሪክ፣ የእነ ስቲቭ ጆብስ ታሪክ ነዋ። እስቲ፣ ‘ክብር፣ ለሃብት ፈጣሪው የሰው ልጅ ይሁን!’ እንበል።
በጥበብ... በለምለም እጆቹ፣ ወርቅ እንቁ ሚያፈራ! አጃኢብ... እፁብ ድንቅ ጀግንነት፣ የአእምሮ ስራ!
(አሁንም ልብ በሉ። ሁለተኛውን የስኬት ምሶሶ በተግባር እያየን ነው። ምርታማነትና አትራፊነት ብለን ልንሰይመው እንችላለን። በቢዝነስና በነፃ ገበያ ላይ የተመሰረተ የካፒታሊዝም ምሶሶ ነው። በዝርፊያ ወይም በልመና ላይ የተመሰረተ፣ እናም አንዱ ሌላውን መስዋዕት የሚያደርግበት ስርዓት አይደለም። ይልቅስ፣ ከትናንሽ ነገሮች እጅጉን ጠቃሚ የሆኑ ትልልቅ ነገሮችን መገንባት፤ ከጥቂት ነገሮችም ብዙ ነገሮችን ማፍራትና መፍጠር... አትራፊነት ይሄ ነው፤ ምርታማነት ይሄ ነው)። እናም አፕል፣ ዘንድሮ ከ60 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንዳተረፈ ስንሰማ፤ የምርታማነቱን ልክ እንደሰማን ይቆጠራል። እውነትም ሰው በቀና ጎዳና ሲራመድ፣ ተዓምር ይሰራል።
በእርግጥ፣ ምርታማነትና አትራፊነት የአፕል ብቻ አይደለም። ማሳው ላይ አንድ ኩንታል ጤፍ ዘርቶ 30 ኩንታል ጤፍ የሚያመርት ገበሬ ካየን፣ አትራፊነትን አየን ማለት ነው። ሳሙና ወይም ክብሪት ለመግዛት ወደ ፋብሪካ ማከፋፈያ አልያም ወደ መርካቶ የማንሄደው ለምንድነው? ጊዜያችንን ከማባከንና ለትራንስፖርት ገንዘብ ከማውጣት የሚያድነን የሰፈር ሱቅ ስላለ ነው። ከእነዚህ ጀምሮ፣... ማንኛውም በራሱ ጥረትና ስራ፣ የመተዳደሪያ ገቢ የሚያገኝ ሰው ሁሉ፣ እስከ ትልልቆቹ የፈጠራ ጀግኖች ድረስ፣ ሁሉም እንደየአቅማቸው አምራቾች ናቸው፤ ኑሮን የሚያሻሽል ነገር የሚያፈሩ ትርፋማዎች ናቸው። እንዲህ አምራች ከመሆን የላቀ ቅዱስ ማንነትና ክብር አለ? የለም። ከአምራችነት ውጭ ያሉት ሁለት አማራጮች፣ ዘራፊ ወይም ተመፅዋች የመሆን አማራጮች ብቻ ናቸው።
ከአነስተኛው ገበሬና ከአነስተኛ ጋራዥ ጀምሮ፣ እንደ ስቲቭ ጆብስና ቢል ጌትስ እስከመሳሰሉት ቢሊየነሮች፣ እንደ ጉጉልና ሳምሰንግ፣ እንደ ዩቱብና ፌስቡክ እስከመሳሰሉት ትልልቅ ኩባንያዎች ድረስ፣... እነዚህ በሙሉ፣ መልካም የስራ ፍሬ በማቅረብ በምላሹ ገቢ የሚያገኙ ምርታማ ሰዎችና ድርጅቶች ናቸው። ሁሉም እኩል ናቸው፣ ወይም ሰፊ ልዩነት የላቸውም ማለቴ አይደለም። በአንዱ ጥግ፣ ነባር ከእጅ ወደ አፍ ኑሯችንን ከመደገፍ ያላለፈ የዘልማድ አመራረት አለ። በሌላኛው ጥግ ደግሞ፣ ኑሮን በፍጥነት የሚያሻሽልና ከምንመኘውም በላይ (በውናችን ቀርቶ በሕልማችንም የማይመጣልን) አዲስ ምርትንና አገልግሎትን ይዞ በመምጣት ዓለምን ሁሉ የሚያዳርስ የፈጠራ ምርታማነት አለ - ዘር እና ሃይማኖትን ሳይለይ። ሶስተኛው የስኬት ምሰሶ ይሄ ነው - የትውልድ ሃረግንና ዘርን ወይም የሃይማኖት ተከታይነትን ሳይጠይቅ፤ አለምን ሁሉ የሚያዳርስ የስኬት ምሰሶ።
አዳሜ አለፈለት - በስልክ መስመር
የአዲስ አበባ ነዋሪ ከመቶ ዓመት በፊት፣... ሀረር፣ ጎንደር፣ ጂማ፣ መቀሌ ወይም  አሶሳ ከሚገኝ ሰው ጋር መልእክት የመለዋወጥ እድሉ ኢምንት ነበር። ለአገሪቱ ንጉስ እንኳ ቀላል አልነበረም። ፈረሰኞችን በማሰማራት አንዲት መልእክት ለማድረስና ምላሽ ለማግኘት ሳምንታት ይፈጅበታል። የስልክ መስመር፣ ይህንን ታሪክ እንዴት እንደቀየረው አስቡት። በቀጥታ፣ ድምፅ ለድምፅ እየተደማመጡ መልእክት መለዋወጥ... እንዲሁ ስታስቡት ትንግርት አይደለም? ለንጉሡ ሳይቀር እንደ ሩቅ ምኞትና እንደ ቅንጦት የሚታይ ነገር፣ ቀስ በቀስ ለብዙ ሰው ጭምር ሲዳረስ ይታያችሁ።
እንዲያም ሆኖ፣ ከበርካታ አስርት አመታት በኋላም፣ በኢትዮጵያ የተዘረጋው የስልክ መስመር ከጥቂት መቶ ሺዎች አይበልጥም ነበር። ለዚያውም ገሚሱ የመንግስት ነው። በሌሎች የአፍሪካ አገራት፣ ከኢትዮጵያ የተሻለ እድገት ቢታይም፣ የአህጉሪቱ የመቶ አመታት ድምር ውጤት፣ ከ10 ሚሊዮን የስልክ መስመር ብዙ ፈቅ አላለም። እናም፣ ስልክ ደውሎ “ከጎረቤት እገሌን፣ እገሊትን... እባክዎ...” ብሎ መሳቀቅና ማሳቀቅ የግድ ነበር። ለዚያውም፣ የተደወለለት ሰው በሰዓቱ በቦታው ከተገኘ ነው። ለዚያውም የየእለቱ የስልክ ብልሽት ሳይቆጠር ነው። ባይበላሽም፣ ከከተማ ከተማ ለመደወል፣ በቀጥታ መገናኘት ብርቅ ነበር - ቴሌ ማስመዝገብና ለሰዓታት መጠበቅ ያስፈልጋል። ወደ ውጭ አገር መደወልማ ተዉት። ለነገሩ፣ ዋጋውም አይቀመስም። በዚህ መሃል፣ ሳናስበውና ሳንመኘው... ሞባይል ስልክ መጣና፣ ታሪክ ተቀየረ።
የሞባይል ማዕበል
የስልክ መስመር ማስገባት አስቸጋሪና ውድ ምኞት እንዳልነበረ፤ ከአጠገባችን የማይለይና በኪሳችን የምንይዘው ሞባይል ስልክ እንደዘበት ከእጃችን ሲገባ ተዓምር አይደለም? ካሰኘንም ሁለት ሦስት የሞባይል መስመር! የተስፋፋበት ፍጥነትስ ብትሉ! የአለማችን የሞባይል መስመሮች ብዛት ከጠቅላላው ህዝብ ብዛት ጋር የሚመጣጠን ሆኗል - ከ7 ቢሊዮን በላይ።
የዛሬ ሃያ አመት ሞባይል ስልክ በኢትዮጵያም ሆነ በሌሎች የአፍሪካ አገራት አልነበረም። ዛሬ በአህጉሪቱ ከግማሽ ቢሊዮን በላይ የሞባይል መስመሮች አገልግሎት እየሰጡ ነው። በኢትዮጵያም ቢሆን፣ ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ወደ ኋላ ቢቀርም፣ የሞባይል መስመር ከ25 ሚሊዮን በላይ ደርሷል። አስታውሱ፣ የዛሬ ሃያ ዓመት፣ ሞባይል ስልክ ለኢትዮጵያዊያን ይቅርና በበለፀጉት አገራት ለሚገኙ ሃብታሞችም እንኳ ብርቅ ቅንጦት እንደነበር አትርሱ። ምን ይሄ ብቻ! ለሚሊዮነሮቹ ብርቅ ቅንጦት ከነበረውን የሞባይል ስልክ እና ዛሬ እጆቻችን ውስጥ የገቡ የሞባይል ስልኮችን እናነፃፅር ብንል፣ የፈረስ ጋሪን እና ጄት አውሮፕላንን እንደማነፃፀር ነው። በጣም አስገራሚው ነገር፣ የያኔው ‘ጋሪ’ ከዛሬው ‘አውሮፕላን’ መቶ እጥፍ ውድ ነበር።                      
በአጭሩ፣ በ10ሺ ዶላር ለትልልቅ ባለሃብቶች የተሸጡ የያኔዎቹ ሞባይል ቀፎዎች፣ ዛሬ በ10 ዶላር የሚገዛቸው አይገኝም - እንደ ‘ቅርስ’ ካልታዩ በቀር። የመጀመሪያው ሞባይል ስልክ፣ ሁለት ኪሎ ግራም ክብደት እንደነበረው ታውቃላችሁ? ሁለት ሊትር ውሃ አንስታችሁ ሞክሩት። በዚያ ሁሉ ክብደቱና ትልቅነቱ ግን፣ ስልክ ከመደወል ያለፈ አገልግሎት አልነበረውም። የፅሁፍ መልዕክት መለዋወጥ እንኳ ብርቅ ነበር። የሚያኮራ ካሜራማ ከጊዜ በኋላ ነው የመጣው። ደረጃውን የጠበቀ የሙዚቃና የቪዲዮ ማጫወቻ ያለው፣ ኢንተርኔት ውስጥ እንዳሻን እየተንሸራሸርን ያሰኘንን መረጃ የምናስስበት፣ የየራሳችን ድረ ገፅ በፌስቡክ የምንከፍትበትና የሚሊዮኖችን የምንከታተልበት ሞባይል ስልክ (ስማርትፎን) ከመጣኮ ገና አስር ዓመት አልሞላውም። ግን በዚህች እድሜው፣ እንደገና አጃኢብ የሚያሰኝ አዲስ ጉደኛ ታሪክ ሲፈጠር አየን።
የስማርትፎንና የኢንተርኔት አብዮት
የስማርትፎን ሽያጭ በአመት ከ1 ቢሊዮን በላይ መብለጡን ይገልፃል ዘኢኮኖሚስት። ከዘመናዊ ኮምፒዩተር ያልተናነሰ አቅም ያላቸው ስማርትፎኖች፣ ከ30 አመት በፊት የሲአይኤ እና የናሳ መመኪያ ከነበሩት ድንቅ ኮምፒዩተሮች ጋር ሲነፃፀሩ፣ በመቶ እና በሺህ እጥፍ የሚበልጥ አቅም አላቸው። ዋጋቸው ደግሞ የዚያኑ ያህል በብዙ እጥፍ ያንሳል። የስማርትፎን ምርቶች በአማካይ በመቶ ዶላር እየተሸጡ እንደሆነ የዘገበው ዘኢኮኖሚስት፤ ማይክሮማክስ እና ሌሎች አዳዲስ ኩባንያዎች ደግሞ የስማርትፎንን ዋጋ እስከ 40 ዶላር እያወረዱት ነው ብሏል። ከ8 ዓመት በፊት ስማርትፎን አልነበረም። ዛሬ ግን ሕፃናትን ሳይጨምር ከአለማችን ህዝብ ግማሹ (2 ቢሊዮን ያህሉ) የስማርትፎን ባለቤትና ተጠቃሚ ሆኗል። የቤት ስልኮች በቁልፍ ሲከረቸሙ ትዝ ይላችኋል? የወላጆች ትልቁ ስጋት፣ በተለይ ወደ ውጭ አገር እንዳይደወልበት ነበር - ከተደወለበት ክፍያው መዓት ነዋ። የበርካታ መቶ ብሮች ሂሳብ ይመጣባቸዋል። ዛሬ፣ በነፃ ወደ ማውራት ተቃርበናል። የፅሁፍ፣ የፎቶ፣ የድምፅ፣ የቪዲዮ መረጃዎችን መቀላሉ እንለዋወጣለን። ‘የፈለግነውን አይነት ዜና፣ መረጃ እና እውቀት ማግኘት እንችላለን’ ብንል የተጋነነ ይመስላል። ግን ፈፅሞ አልተጋነነም።
ከሃያ አመት በፊት፣ ኢንተርኔትን የመጠቀም እድል የነበራቸው፣ ከመንግስት ጋር ግንኙነት የፈጠሩ ጥቂት “ትልልቅ” ሰዎች ብቻ ናቸው። ዛሬ እዝበ አዳም እየተንሸራሸረበት ነው - ከ3 ቢሊዮን በላይ የአለማችን ሰዎች በኢንተርኔት እየተጠቀሙ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥም እንደአቅሚቲ፣ በስማርትፎን መበራከትና በፌስቡክ ሰበብ ከኢንተርኔት ጋር ለመተዋወቅ የበቁ ሰዎች ከአንድ ሚሊዮን ቢበልጡ እንጂ አያንሱም። መረጃና እውቀት የማግኘት እድልም የዚያኑ ያህል በርክቶላቸዋል - ያንን እድል ለመጠቀም ፈቃደኛ እስከሆኑ ድረስ። እንዴት በሉ።
ዛሬ፣ በብዙ የአገራችን ዩኒቨርስቲዎች እንደተለመደው፣ ሰላሳ አርባ አመት ያስቆጠሩ የመማሪያ መፃህፍትን ሳይሆን፣ የ21ኛው ክፍለዘመን መፃሕፍትን ማግኘት ቀላል ሆኗል - ከኢንተርኔት። በ10 ሺ የሚቆጠሩ ዲጂታል መፃሕፍትን ከኢንተርኔት በመሰብሰብ፣ እያንዳንዱ ሰው በአንዲት ኮምፒዩተር የትልቅ ቤተመፃሕፍት ባለቤት መሆን ይችላሉ - ካወቀበት። አለማቀፍ ሚዲያዎችን እያማረጠ፣ ዜናዎችን መቃኘትም ሆነ በጥልቀት መመርመርም፣ ስማርትፎን ላይ አንድ ሁለት ጣት ከማንሸራተት ያለፈ ድካም አያስፈልገውም። በጀርመንና በስዊድን አልያም በስፔንና በጃፓን ቋንቋዎች የሚቀርቡ ዜናዎችን፣ እዚያው ኢንተርኔት ውስጥ በሴኮንዶች ውስጥ ወደ እንግሊዝኛ አስተርጉሞ ማንበብ ይቻላል። እዚሁ እየኖረ፣ በኢንተርኔት ለውጭ ኩባንያዎች የመስራት እድልን ጨምሮ፣ በስማርትፎን እና በኢንተርኔት አማካኝነት የተፈጠረው ልዩ ታሪክ ተዘርዝሮ አያልቅም።
ይህንን እውነት በንፅፅር ለማየት፣ የሲአይኤ ዳሬክተር ሊዮ ፓኔታ ከሃላፊነታቸው በተነሱ ማግስት ያሳተሙትን መፅሐፍ ሳነብ ያገኘሁትን መረጃ ልጥቀስላችሁ። (አሜሪካና አውሮፓ የታተሙ አዳዲስ መፃህፍትን አግኝቶ ማንበብ፣ በተለይ ለኢትዮጵያውያን ምንኛ ብርቅ እንደነበር ሳስበው ይገርመኛል። ከነጭራሹ፣ ምን ምን አዳዲስ መፃህፍት እንደታተሙ ማወቅ እንኳ አይቻልም ነበር)። ለማንኛውም ሊዮ ፓኔታ፣ ስለ መረጃ እንዲህ ይላሉ። “በዓለማችን ውስጥ ብዙ መረጃዎችን እንዳሻቸው የማግኘት ሰፊ እድል ያላቸው ሰዎች እነማን ናቸው?” ቢባል፣ በቀዳሚነት የሚጠቀሱት የአሜሪካ ፕሬዚዳቶች ናቸው ይላሉ ፓኔታ። ለምሳሌ ያህል የቀድሞው ፕሬዚዳንት ክሊንተንን እንውሰድ። በስልጣን ዘመናቸው ብዙ አይነት ዜና፣ መረጃና እውቀት ለማግኘት የነበራቸው እድል ሲታይ በአለም ተወዳዳሪ አልነበረው። ዛሬስ? ዛሬማ ከአሜሪካ እስከ አፍሪካ፣ ከኤስያ እስከ አውሮፓ፣ ስማርትፎን ወይም ኮምፒዩተር ያለው ማንኛውም ሰው፣ ፕ/ት ክሊንተን ከነበራቸው የመረጃ እድል የላቀ የመረጃ አማራጭ እድሎች ተከፍተውለታል ይላሉ ፓኔታ። ትንግርት ነው!

Read 1644 times