Saturday, 16 May 2015 11:05

ቁጥጥርን መፀየፍ!

Written by  ሌሊሣ ግርማ
Rate this item
(2 votes)

እስቲ አስታውሱት ልጅነታችሁን፡፡ ትምህርት ቤት ያሳለፋችሁትን ዘመን፡፡ ምን አይነት ተማሪ ነበራችሁ? ስለ ትምህርት አቀባበላችሁ አይደለም የጠየኳችሁ፡፡ ጐበዝ ወይንም ሰነፍ ብሎ የሚመዝናችሁ ተቋሙ ነው፡፡
እኔ ለመመዘን የፈለግሁት በተፈጥሮአችሁ ምን አይነት አዝማሚያ እንዳላችሁ ብቻ ነው፡፡ ሰው ካልተቆጣጠራችሁ መረን የምትወጡ ነበራችሁ ወይንስ ራሳችሁን መግዛት ትችሉ ነበር?
እኔ ስለ ራሴ የማስታውሰውን ልንገራችሁ፡፡ አስተማሪ በሌለበት ፔሬድ በፀጥታ መጽሐፌን አነብብ ነበር፡፡ እንዲያውም ረብሽ ረብሽ የሚለኝ አስተማሪው ማስተማር ሲጀምር ነው፡፡ ምክንያቱ ያኔ አይገባኝም ነበር፡፡ አሁን ግን ሳስበው ምናልባት የሚያስተምረው ትምህርት በጣም ስለሚያስጠላኝ ሊሆን ይችላል። ከማስጠላቱም ባሻገር ግን አስተማሪው እንደ ፖሊስ አይነት ሰብዕና እየተላበሰ ሲያስፈራራን መዋሉ የብሽቀቴ መንስኤ መሆኑን እጠረጥራለሁ፡፡
በመሰረቱ አስተማሪው እና እኔ የስራ ባልደረቦች ነን፡፡ እሱ ወይንም እኛ ባንኖር የማስተማር ሂደቱ አይከናወንም፡፡ እኛም መማር ፈልገን ነው የመጣነው፣ እሱም ለማስተማር፡፡ ግን ስራችንን በአግባቡ ማከናወን አንችልም ነበር፡፡ እሱ የሚረብሸውን ለመግረፍ በተጋ ቁጥር እኛም ረባሽ እየሆንን ሄድን፡፡ አስተማሪነት ማለት ፈላጭ ቆራጭነት ከሆነ፣ ተማሪነት ደግሞ አመፀኝነት ነው። መምህራኖቹን በፊለፊት እየተሽቆጠቆጥን ከበስተኋላ እናንጓጥጣቸው ነበር፡፡
ከትምህርቱ በኋላ ፈተና ሲደርስ አስተማሪው ካስተማረን ይልቅ እርስ በራስ ተጠያይቀን ያጠናነው የፈተናውን ወንዝ ያሻግረናል፡፡ ፈተና ራሱ የቁጥጥር መሳሪያ በመሆኑ፣ ሳንሱሩን በጥሰን ማለፍ እንጂ ትምህርቱን መቅሰም ዋና ጉዳያችን አልነበረም፡፡ እና እንደኔ የሆናችሁ ካላችሁ እናንተ በተፈጥሮ አናርኪስቶች ናችሁ፡፡ ቁጥጥርን አለመውደድ በተፈጥሮአችን የተሰጠን ባህሪያችን ነው፡፡
አሁን ካፒታሊዝምን የምታቀንቀነዋን አሜሪካን የመሰረቷት የነፃነት አባቶች “The founding fathers” የያኔውን የእንግሊዝ መንግስትን ተቆጣጣሪነት፣ ፈላጭ ቆራጭነት ጠልተው ነው የራሳቸውን መንግስት ለመመስረት የተንቀሳቀሱት፡፡ ግን የእነሱ አናርኪስትነት በከፊል ስለነበረ ካፒታሊዝምን ወለደ፡፡ እነ ጄፈርሰን የእንግሊዝ መንግስት እንዳይቆጣጠራቸው ቢዋጉትም እነሱ ራሳቸው ግን በስራቸው የተቆጣጠሯቸው ብዙ ባሮች ነበሯቸው፡፡ “ከራሴ ባሪያዎች ያተረፍኩትን ለአንተ ባሪያ በመሆን አሳልፌ አልሰጥም” የማለት አዝማሚያ አለው አመፃቸው፡፡ ስልጣን እና የራስ ባለቤት መሆንን እስከ ግለሰብ ድረስ ማውረድ ባለመቻላቸው የአናርኪስት ገለፃ የማያጠቃልላቸው ሆኑ፡፡
የሰው ልጅ በተፈጥሮው ተቆጣጣሪን አይፈልግም። የሰው ልጅ በተፈጥሮው የተለያየ ዝንባሌ እና ፍላጐት ያለው ነው፡፡ የማወቅ እና የመበልፀግ አቅም በተፈጥሮው ተችሮታል፡፡ አለሚቷም ለሁሉም በቂ ናት፡፡ ግን አንዱ ተራ አስከባሪ አድርጐ ራሱን ይሾምና የቁጥጥርን አስፈላጊነት እንደ ተሞክሮ ያስለምዳል፡፡ የሰው ልጅ ተቆጣጣሪ ተሹሞለት መኖርን ከለመደ እና ከተዋጀው  ያለ ተቆጣጣሪ ጋጠወጥ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡
ምክንያቱም ያለተቆጣጣሪ ልጓም ገብቶለት መኖርን ብቻ ስለሚያውቅ ለራሱ ልጓም የማበጀት ተሞክሮ ሳያዳብር እድሜውን ገፍቷልና ነው፡፡
ከጠቀስኩላችሁ የትምህርት ቤት ትውስታዬ ሁልጊዜ የሚገርመኝ… የክፍል አለቃ ሆነው የሚመረጡት ልጆች ሀይለኛ፣ ተደባዳቢ እና ትምህርት የማይገባቸው አይነቶቹ የመሆናቸው ነገር ነበር፡፡ ተማሪው፤ አለቃ ምረጥ ሲባል የሚጠቁመው የሚፈራውን ልጅ ነው፡፡ ጐበዝ ተማሪ አለቃ ሲሆን አይቼ አላውቅም፡፡ ለነገሩ እውነታቸውን ነው፤ መጥፎውን ልጅ አለቃ በማድረግ ትንሽ ሃላፊነት እንዲሰማው ማኖ ማስነካት የተሻለ ብልጠት ነው፡፡
አስተማሪውም ተመሳሳይ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ፍተሻና ዱላ የሚያበዛ አይነት መምህር ትምህርት የማስተማር አቅሙ ደከም ያለ መሆኑን ነው የታዘብኩት። የሚያስተምረውን የሚያውቅና ለስራው ከፍተኛ ፍቅር ያለው አስተማሪ ረባሽ ተማሪን እንኳን ለመመለስ የሚሞክረው በማስተማር ነው፡፡ ከስራው ጋር የተያያዘ ስለሆነ በተማሪ ረብሻ ከአስተማሪነት ወደ “ፖሊስነት” በቅፅበት አይለወጥም፡፡
እና እኔም አናርኪስት ባህርይ በውስጤ በጥንትም አብሮኝ አድጓል፡፡ አናርኪስት ማለት ቁጥጥር የማይወድ ማለት ነው፡፡ የሰው ልጅ ራሱን መቆጣጠር ይችላል ብሎ የሚያምን ሁሉ ቃሉ ቢሰቀጥጠውም “አናርኪስት” ነው፡፡
ግንቡ ላይ ሄጄ ሽንቴን የማልሸናው “እዚህ ቦታ መሽናት የተከለከለ ነው” ተብሎ ስለተለጠፈ አይደለም። መሽናት ባይከለከልም ተገቢ እና የማይገባ ነገርን አስቀድሜ አውቃለሁ፡፡ እውቀቴ እኔን ራሴን፣ በራሴ እጅ እንዲያቅበኝ ማድረግ እንዳልችል ግን ብዙ አይነት ተቆጣጣሪ ይመደብልኛል፡፡ እና እራሴ መጠበቅ ከምችለው ነገር እንድጠበቅ ዘበኛ ሲያዋክበኝ አመፅ-አመፅ ይለኛል፡፡ ተቆጣጣሪው ፊቱን ወደ ሌላ ሲያዞር ጠብቄ ግንቡ ላይ እሸናለሁ፡፡
“ይኼው ተገትረህ እንድትቆጣጠር የተቀጠርክለት ነገር ከቁጥጥር ውጭ ሆነ” ብዬ እንድዘባበትበት ይገፋፋኛል፡፡ በመሰረቱ እኮ ግንቡ ለእኔም ለእሱም … ለሀገሩም ንብረታችን ነው፡፡ ከቁሻሻ የፀዳውም ያለስፍራ በተጸዳዱት ጠረን መድረሻ ማጣቱ አይቀርም፡፡
በጣም የሚያሳዝነኝ ግን ቁጥጥርን ከትውልድ ትውልድ … ከመኖሪያ ቤት እስከ መስሪያ ቤት … ከመንግስት ባለስልጣን እስከ ቤተክርስቲያን ውግዘት … በቁጥጥር መንፈስ ተጀቡኖ የኖረ ማህበረሰብ … ቁጥጥር ሲላላለት በቀላሉ ወደ ጥፋት የመዞሩ ጉዳይ ነው፡፡ በቁጥጥር የተጠፈረ ህዝብ ያልለመደው መልአክ ሲሾምለት የእሱን ሰይጣን ያወጣበታል፡፡
ግን መንስኤው ተቆጣጣሪ አለመኖሩ አይደለም … ለስርዓት አልበኝነቱ፡፡ እውነተኛ ምክኒያት ራሱን መቆጣጠር እንዳይችል በሞግዚት በመጐልመሱ ነው፡፡ በሞግዚትነት ያደገ ስነምግባር የራሱን ጭንቅላት መሸከም አይችልም፡ አለመቻሉም የተቆጣጣሪ አስፈላጊነት የማይሻር ሀቅ ስለመሆኑ ማረጋገጫ ሆኖ ይቀራል፡፡
በራሱ ቤት ውስጥ ኮመዲኖ እና ሳጥን እየተቆለፈበት ያደገ ልጅ … ሳጥኑ አንድ ቀን ክፍት ቢተው፣ እጁን ወደ ሀጢአት መስደዱ አይቀርም። ምክኒያቱም ራሱን መግዛት ስላልተማረ ነው። አግባብ የሆነ እና ያልሆነውን መዝኖ ያልሆነው ስነምግባሩ ላይ ቁልፍ መቆለፍ የመቻል አቅም እንዳለው አያውቅም፡፡ ግዑዝ ሳጥን ላይ ቁልፍ እየተደረገ መኖርን ለመደ፡፡ ራሱን በራሱ መቆጣጠር መማር ያለበት ህያው ሰው ተትቶ፣ ግዑዝ ሳጥን በተንጠልጣይ ቁልፍ አማካኝነት ስነምግባር ተስተማረ፡፡
ትራፊክ ፖሊስ ተቆጣጣሪ ነው … ቁጥጥሩ ከግዜ ወደ ጊዜ መጨመሩ ይታየኛል፡፡ ግን ወንጀሉም የዛኑ ያህል ጨምሯል …፡፡ ቁጥጥሩ ትርፍ የሚጭኑትን ታክሲዎች ብቻ ሳይሆን … ትርፍ የሚጫነውንም ሰው መመዘኛ ሙሉ ለሙሉ አጥፍቶታል፡፡ በፊት ብዙ ቁጥጥር ሳይኖር ሁሉም ተሳፋሪ የታክሲውን ሹፌር ወይም ረዳት ምግባር “ተው አይሆንም” እያለ ይለካ ነበር፡፡ አሁን ልኬቱ ሙሉ ለሙሉ ሞግዚት ላይ ሲጣል ሰውም እንደ አንበጣ ተደራርቦ ይጫናል። ከሊቢያ ወደ ጣሊያን የሚሻገረው… በብዙ ሰው የታጨቀው ጀልባ አዲስ አበባ ውስጥም አለ። ቁጥጥር ከግለሰብ ወደ ባለመለዮ ፖሊስ በመዛወሩ ወንጀል ይሸፋፈን ይሆናል እንጂ አይወገድም፡፡
ቁጥጥር ከስልጣን ጋር እንደሚያያዝ ማንም ያውቃል፡፡  ስልጣን ደግሞ ከጥቅም ጋር የተያያዘ ነው። ጄፈርሰን የራሱን በነፃነት የመኖር … እና ሀብት የማፍራት መብት ያስከበረው … የእንግሊዝ መንግስት እና ቤተክርስቲያኑ ተባብረው በጉልበታቸው ቁጥጥር እያደረጉ ታክስ ስለሚቆርጡበት ነበር፡፡ የራሱን መብት ቢያስከብርም፤ ቶማስ ጄፈርሰንም ጆርጅ ዋሽንግተንም ሆነ ጆርጅ አዳምስ ብዙ ባሮችን የሚቆጣጠሩ ጌቶች ነበሩ፡፡ የእንግሊዝ መንግስት በስልጣኑ የአዲሲቷን እንግሊዝ (አሜሪካ) ዜጎች ተቆጣጥሮ የሀብት ተጠቃሚ መሆኑ ያልሰራበትን የሚያሳፍሰው ከበርቴነት ነው ብለው ተዋግተው ያስወገዱት፡፡ ካስወገዱት በኋላ ግን እነሱም ካፒታሊዝምን ለራሳቸው የጥቅም መቆጣጠሪያ አድርገው ሾሙዋት፡፡ ደሀው (ጥቁር) ዘንድሮም እንደ ጥንቱ ጥቂት ሀብታሞች ድህነቱን ተቆጣጥረውት ያካል፡፡
የሰው ልጅ በተፈጥሮው ቁጥጥርን አይሻም፡፡ የአናርኪስቶች ፍልስፍና የግለሰብ ነፃነት ከሁሉ ነገር በፊት ይቀድማል ይላሉ፡፡ ነፃነት የሚገኘው ማንም ለማንም ጥቅም የደሞዝ ባሪያ ሆኖ ሳይቀጠር፣ በማንም የኢኮኖሚ ፍልስፍና ቁልፍ ሳይቆለፍ፣ እውነተኛውን እና ትሩፋት ያለውን ህይወት በራሱ ቁጥጥር ስር አድርጐ እንዲኖር ስለሚመኝ ነው፡፡
አናርኪዝም ቁጥጥርን መጥላት ነው፡፡ ቁጥጥርን መጥላቱ ደግሞ የሚጀምረው ከታች ነው፡፡ ከጭቁኖቹ፡፡ ቁጥጥርም መኖር ካለበት ከታች ወደ ላይ የሚገነባ እንጂ ከላይ ወደታች የሚጫን መሆን እንደሌለበት ይሰብካል፡፡
መንግስት ማለት ማህበረሰብ ማለት ነው፡፡ ከግለሰብ ጀምሮ ብዙ ግለሰቦች እንደ አንድ ሆነው ትርጉም ያለው የህይወት መስተጋብር የሚፈጥሩበት ኩነት ማለት ነው። መንግስት ግን ራሱን የነጠለ፣ በጥቂት አካላት የተዋቀረ፣ ከላይ ወደታች ትዕዛዝ እና ቁጥጥርን የሚያስተላልፍ ተቆጣጣሪ ከሆነ ራሳቸውን ለመቻል አቅም የሌላቸው ጨቅላዎችን ተሸክሞ የመዞር ታሪክ ይፈጥራል፡፡
የመንግስት ባህሪ ደግሞ እስከ ትምህርት ቤትም ይወርዳል፡፡ አስታውሳለሁ… ኮሎኔል መንግስቱ ሀገሪቷን በሚመሩበት ዘመን እኛን ያስተማሩን ሰዎች እንደ እስር ቤት ገራፊ በዱላ የሚያመልኩ ነበሩ፡፡ በዱላ የቁጥጥር አምልኮ ያደገ ሰው፣ አንድም በጣም በመመታቱ ያምፃል ወይንም ጭራሽ ባለመመታቱም ጠግቦ ያምፃል፡፡
እንደ እኔ እምነት ወይንም እንደ እኔ አይነት ቁጥጥርን የማይወድ ሰው፤ በሞግዚት እጅ እንደ ህፃን እድሜ ልኩን እንደመኖር የሚፀየፈው ነገር የለም፡፡


Read 2342 times