Saturday, 16 May 2015 11:01

አዲስ የጤና አገልግሎት ማውጫ ተመረቀ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

በሀገሪቱ በጤናው መስክ የሚታየውን የመረጃ ክፍተት ለመሙላት፣ በዘርፉ ያለውን የእርስ በርስ ግንኙነት ለማጎልበትና ለጤና አገልግሎት ተጠቃሚዎች አመቺ የመረጃ ምንጭ እንዲሆን ታስቦ የተዘጋጀው “ኢትዮ ሄልዝ ዳይሬክተሪ” የተሰኘ የጤና አገልግሎት ማውጫ ከትናንት በስቲያ ተመረቀ፡፡
በዘርፉ በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነው ይህ የጤና አገልግሎት ማውጫ፣ በይዘቱ ምሉዕ እና ከሁለት አመት በላይ በፈጀ የመረጃ ስብሰባ የተዘጋጀ ሲሆን መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ የጤና አገልግሎት ሰጪዎችን፣ የሆስፒታሎችን፣ የመድሃኒትና የሕክምና መገልገያ መሳሪያዎች አስመጪዎችን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን አድራሻ የያዘ ነው፡፡
በደብሊው ኤ ኤች አሳታሚ የተዘጋጀው የጤና አገልግሎት ማውጫው፤ ተደራሽነቱን ለማስፋት ሲባል በመጽሃፍ መልክ ከመቅረቡ በተጨማሪ በድረ ገጽ እና በሞባይል አፕሊኬሽን አማካይነት ተዘጋጅቶ ለተጠቃሚዎች መቅረቡን አዘጋጁ በተለይ ለአዲስ አድማስ ጠቁሟል፡፡  
ማውጫው በአዲስ አበባ እና በመላ የአገሪቱ ክልሎች ለሚገኙ የጤና ተቋማት በነጻ የሚሰራጭ ሲሆን  ለጤና ተቋማት የመረጃ ምንጭ በመሆን የርስ በርስ ግንኙነትን ከማጎልበት ባለፈ፣ ለጤና አገልግሎት ተጠቃሚዎችም የማንኛውም የጤና ነክ መረጃ ምንጭ በመሆን ያገለግላል፡፡
አዘገጃጀቱ ለተጠቃሚዎች ምቹ በመሆኑና መረጃዎቹ በየጤና ዘርፉ ተከፋፍለው የቀረቡ መሆናቸው፣ የጤና አገልግሎት ተጠቃሚው ህብረተሰብ እንደፍላጎቱና እንደችግሩ የሚበጀውን መረጃ በቀላሉ ለማግኘት እንደሚያስችለው አዘጋጁ ገልጸዋል።
በዝግጅቱ የኢፌዲሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እና የመድሀኒት የምግብ እና የጤና ክብካቤ ባለስልጣንን ጨምሮ በጤናው ዘርፍ የሚሰሩ መያዶች፣ ሌሎች ባለድርሻ አካላትና በዘርፉ ለአመታት የሰሩ አንጋፋ የህክምናው ዘርፍ ባለሙያዎች፣ ተቋማትና የመንግስት አካላት የተሳተፉ ሲሆን፣ በሚቀጥሉት እትሞችም ተደራሽነቱን በስፋት ለማሳደግ እየተሰራ ነው ተብሏል።
በዘርፉ የሚታየውን የመረጃ ክፍተትን በመሙላት ረገድ ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነ የተነገረለት የጤና አገልግሎት ማውጫው፣ የኢፌዲሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር ልዩ ጽ/ቤት ሃላፊ ዳይሬክተር ጀነራል፣ የጤናው ዘርፍ ባለድርሻ አካላትና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ባለፈው ሃሙስ በኢትዮጵያ ሆቴል በተዘጋጀ ፕሮግራም ላይ በይፋ ተመርቋል፡፡


Read 3694 times