Saturday, 16 May 2015 10:51

‘የመገላበጥ’ ነገር…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(13 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…እኔ የምለው፣ ለሌላው ‘ምክር’ መስጠት ይህን ያህል የሚቀለን እንዴት ነው! አብዛኞቻችን የራሳችን ጉድ ‘ጓዳ’ ሆኖ…ለሌላው ምክር ሰጪዎች ሆነናል፡፡
እናላችሁ…የሆነ የምታወቁት ሰው አለ፡፡ እናላችሁ…ሲያያችሁ ሁልጊዜ ያው ናችሁ፡፡ የሆነ ንግርት ምናምን ያለባችሁ ይመስል ለሚሌኒየም የገዛችኋት ጫማ ቀለም አልቀበል ከማለቷ ሌላ…አሁንም እግራችሁ ላይ ነች፡ ታዲያላችሁ…ምን ይላችኋል…
“ስማ ብር ያለው አብሮ አደግ ጓደኛ ወይ ዘመድ የለህም?”
“ቢኖረኝስ!” ‘ቢኖረኝስ’ እንጂ ሌላ ምን ይባላል!
“አንድ ሁለት ሚሊዮን ስጠኝ በለውና የሆነች ኢንተርኔት ካፌ ነገር ክፈታ!” ይላችኋል፡፡ ወዳጆቼ ይሄ እናንተን አይመለከትም፡፡ ልክ ነዋ… እንኳን የምትሰጡት አንድና ሁለት ሚሊዮን ሊኖራችሁ ሚሊዮን የሚለውን ቁጥር የጻፋችሁት ስምንተኛ ክፍል ሚኒስትሪ ላይ ‘የናይጄሪያ ህዝብ ቁጥር ስንት ነው?’ ለሚለው ጥያቄ መልስ ስትሰጡ ነው። ቂ…ቂ…ቂ…
ደግሞ ሌላኛው ምን ይላችኋል…
“ስሚ ኤን.ጂ.ኦ. የምታውቂው ሰው የለሽም?”
“የማውቀው ሰው ቢኖርስ!” ‘ቢኖርስ’ እንጂ ሌላ ምን ይባላል!
“በቃ አንዱ ኤን.ጂ.ኦ. ሁለት ዓመት ብትሠሪ እኮ እኔ ነኝ ያለ ጂ ፕላስ ዋን ትሠሪ ነበር፡፡ ዘላለምሽን አሮጌ ሻንጣ ይዘሽ ሰፈር ለሰፈር ከምትዞሪ እወቂበት።”
እናላችሁ…አስቸጋሪ ነው፡፡ በእርግጥ ብዙ ሰው ለእናንተ በጎ ከማሰብ ይሆናል፡፡
“ምነው ጠፋህ?”
“ኧረ አልጠፋሁም፡፡”
“ጭራሽ አትታይም እኮ…”
“አለሁ ባንገናኝ ነው፡፡” በሆዳችሁ “ልጥፋ አልጥፋ ምን አገባው!” ምናምን ትላላችሁ፡፡
“አሁንም እዛው ድሮ መሥሪያ ቤትህ ነህ!”  ይሄኔ ነገር መጣ ማለት ነው፡፡
“አዎ…”
“አይ ዶንት ቢሊቭ ኢት! ገልበጥ ገልበጥ በል እንጂ!” በሆዳችሁ የእናቴ አባቴ አምላክ…” ብላችሁ እርግማን ቢጤ ትጀምሩና ትተዉታላችሁ፡፡
የምር ግን… አለ አይደል… አሁን ያለችሁበት ቦታ ለመኖራችሁ ችግሮቹ የውጪ ሳይሆኑ የእናንተ እንደሆኑ ሲያስመስሉት ቀሺም ነው፡፡
ደግሞላችሁ…ኮሚኩ ነገር ተሳክቶለታል የምትባሉ አይነት ከሆናችሁ ያው ሰው ምን ይላል… “አጅሬው አንተማ ምን ታደርግ፤ ላይ ያሉት በሙሉ ዘመዶችህ ናቸው አሉ…” ምናምን ይላችኋል፡፡
ደግሞላችሁ…ሌላውን ‘ሰው እንደ መምከር’ ቀላል የሆነ ነገር ዓለም ላይ እንደሌለ በማመሳከሪያነት ሊቀርብ የሚችል አይነቱ ይመጣና…
“አንተ… አሁንም እዚህ አገር ነህ!”
“አዎ፣ ታዲያ የት ልሆንልህ ነው!”
“ወጣ በል እንጂ፣ ሰዉ ሁሉ አሜሪካ፣ አውስትራሊያ እያለ ዶላሩን ሲሰበስብ አንተ ከአገር እንዳትወጣ ተገዝተሀል እንዴ! ነው ወይስ አገሪቷ “አደራ በምድር በሰማይ…” ተብለህ የተሰጠችህ የስለት አገር አደረግሀት!”
ኮሚኩ ነገር እኮ ምን መሰላችሁ…ልክ እኮ ፓስፖርቱን አዘጋጅቶ የአንድ የአምስት ምዕራብ አገሮች ቪዛ አስመትቶ  “ይሄ ሰውዬ መጥቶ አይወስድም እንዴ?” ሲል የከረመ ነው የሚመስለው። እሱ ራሱ የፈረደባት አሜሪካ ለመሄድ ሲለፋ ጆርጅ ቡሽና ኦባማን አሳልፎ ሌላ ፕሬዚደንት እየጠበቀ ነው፡ ቂ…ቂ…ቂ…
እናላችሁ…አስቸጋሪ ነገር ነው፡፡ ብዙዎቻችን ያኛው ሰው የእኛን ያሀል ማሰቢያ ኩላሊት የሌለው እያስመሰልን ‘ምክር’ ብለን የምንሰጠው… በቃ፣ ቀሺም ነው፡፡ ደግሞላችሁ ዘንድሮ በተደጋጋሚ የሚሰማ ‘ምክር’ አለላችሁ፡፡
“አንተ ሰውዬ፣ ዘንድሮም ጠጋ አላልኩም እንዳትለኝ!”
“ወዴት ነው ጠጋ የምለው?”
“አንተ ሰውዬ!… ወዴት ነው ጠጋ የምለው ትለኛለህ! እኔ የምለው… መንግሥተ ሰማያት ለአንተ ብቻ ቃል የተገባልህ ይመስል ሀቀኝነት አታብዛ!”
“ያልከኝ ሳይገባኝስ…ወዴት ነው የምጠጋው?”
“ወደ ጨረቃ እንድልህ ነው፡፡ ወደ ሰዎቹ ነዋ!  እነእንትና እኮ ቶዮታ ኤክስኪዩቲቭና ያሪስ የሚለዋውጡት ሎተሪ ደርሷቸው መሰለህ፡፡ የእኔ ጌታ አውቀውበት ጠጋ ስላሉ ነው፡፡”
እናላችሁ… ‘ሰዎቹ’ የሚለው ትርጉም የማያሻማ ቢሆንም (ቂ..ቂ..ቂ…) የመጠጋት ‘ስትራቴጂዎች’ ግልጽ ይደረጉልን! ‘ወደ ሰዎቹ ጠጋ የመባያ አንድ መቶ አንድ አስተማማኝ ዘዴዎች’ የሚል መጽሐፍ ይውጣልን፡፡ ሰውየው ‘ምክሩን ሲያጠናቅቅ’ ምን ይላል መሰላችሁ…
“ጌታው ዘንድሮ ወይ ጠጋ ትላለህ፣ ወይም ጥግ ላይ እንደተለጠፍክ ባቡሩ ያመልጥሀል…” ይላችኋል።
እናላችሁ…አንዳንድ ጊዜ የምክሮቹ አይነት ይቺዋ ያለችውን ‘አይ.ቂዋችንን’  ስለሚቀንሱብን አንዳንድ ሰዎችን በሩቅ ስናይ መንገድ ብንሻገር አይፈረድብንም። ‘ሲደብሩንስ!’
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…የመደባበር ነገር ካሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ፡፡
እሱና እሷ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው የተገናኙት፣፣ እና እራት ይጋብዛታል፡፡ ግንላችሁ እራት እየተመገቡ… አለ አይደል… ትንሽ ደቂቃ አብረው እንደተቀመጡ ትደብረዋለች፡፡ (ወንዶች… “ጧት ከእንቅልፏ ስትነቃ እያት…” እንደሚባባሉት ማለት ነው፡ ቂ…ቂ…ቂ…) እናማ… እንደምንም ብሎ ትቷት ለመሄድ ይፈልጋል። ቀደም ሲል ለጓደኛው “ለክፉ ለደጉም አይታወቅምና መሀል ላይ ደውልልኝ…” ብሎት ነበር፡፡ ጓደኛውም እንደተባለው ይደውልለታል፡ እሱዬው ሞባይሉ ላይ ትንሽ አዳመጠና “እውነትህን ነው!” ሲል ይጮሀል። “በቃ አሁን መጣሁ…” ይላል፡፡ ለእሷዬዋም “መሄድ አለብኝ፣ አያቴ ሞተች አሉ…” ይላታል፡፡  እሷ ምን ብትለው ጥሩ ነው… “ተመስገን፣ የእኔም አያት ልትሞት ትንሽ ደቂቃ ነበር የቀራት…!” እንዲህም አይነት መደባበርም አለ፡፡
እራት የምትጋበዙ እንትናዬዎች ሰውያችሁ ሞባይሉ ላይ… አለ አይደለ… “እውነትህን ነው!” ብሎ ከጮኸ አያቱ ሞተዋል ማለት ነው፡ ቂ…ቂ…ቂ…
ደግሞ ሌላ ‘መካሪ’ አለላችሁ..
“አንቺ አሁንም ከእሱ ጋር ነሽ?”
“ምነው፣ አሁንም ከእሱ ጋር ነሽ ማለት ምን ማለት ነው?”
“አሁንም መንግሥት መሥሪያ ቤት ምናምን ነው የሚሠራው?”
“አዎ፣ ችግር አለው እንዴ?”
“ያንቺ ነገር እኮ… የምትኖሪው ለነፍስ ነው እንዴ! ይሄን የመሰለ መልክ ይዘሽ ዘላለሙን ሞዴል ስድስት ምናምን እያለ ከሚሰለፍ ምስኪን ጋር ምን ያዳርቅሻል! የእኔ እመቤት ገልበጥ ብትይ ይሻልሻል፡፡ አለበለዛ ዓለም ላይሽ ላይ ትገለበጥብሻለች፡፡”
እና እነኚህ ‘ገልበጥ በል’ና ‘ገልበጥ በይ’ ነገሮች ግራ እያጋቡን ነው፡፡ እኔ የምለው…ገልበጥ ሲባል ‘ከአልጋ መውደቅ’ አለ አይደል እንዴ! ነው ወይስ ከ‘አልጋ መውደቅም’ አንዱ ገልበጥ መባያ መንገድ ነው!
ስሙኝማ…እግረ መንገዴን የሆነች ነገር ትዝ ብላኝ ነው፡፡ ትንሽ ትልቁ ከ‘አልጋ መውደቅ’ ለምዶበት ወደፊት ‘ኃጢአታችንን’ መናዘዝ የምንፈልግ ሰዎች በማህበር ተደራጅተን መምጣት የሚኖርብን ይመስለኛል፡፡ አሀ… እያንዳንዳችንን በተናጥል የሚያናዝዙ በቂ የኃይማኖት አባቶች አይኖሩማ! ሰው በጉዱ ስለማይስቅ አልሳቅሁም፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…
ገልበጥ በል፣ ገልበጥ በይ የሚለው ምክር ለትንሽ ጊዜ በስምምነት ይታገድልንማ፡፡ አሀ…ልጄ ስንት ‘የሚያገላብጠን ነገር’ እያለ...
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 2516 times