Saturday, 16 May 2015 10:46

የምርጫ ዋዜማ ወጋ ወጐች

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(37 votes)

“አሜሪካ - ሆሊዉድ
ህንድ - ቦሊውድ
ናይጄሪያ - ኖሊውድ
ኢትዮጵያ - ኑሮውድ!!”
እንግዲህ ወግም አይደለ…እስቲ 10 ዓመት ወደኋላ ተጉዘን ምርጫ 97 ላይ አረፍ እንበል፡፡ አይዟችሁ ምርጫውን ለመገምገም አይደለም፡፡ (ያኔ አልፏል!) ለመተቸትም እንዳይመስላችሁ፡፡ ለጨዋታ ነው፤ ለወጋ ወግ፡፡ እናላችሁ… ምርጫ 97 ከተጠናቀቀ ከጥቂት ወራት በኋላ (እስር፣ ስደት፣ ሞት፣ ወከባ መኖሩ ሳይረሳ ነው!) የቀድሞውን ጠ/ሚኒስትር (መሬት ይቅለላቸውና!) ጋዜጠኛ ይጠይቃቸዋል - ስለምርጫው፡፡
“ክቡር ጠ/ሚኒስትር፤ ምርጫው ትያትር ነበር ይባላል?”
በተረት፣ በሽሙጥ፣ በተረብ…ወዘተ የተኳሉ ምላሾች በመስጠት በእጅጉ የተካኑ የነበሩት የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር ምን ቢሉ ጥሩ ነው?
“ትያትር አልነበረም፤ ደበበ እሸቱ በምርጫው ላይ በመሳተፉ ቲያትር የመሰላቸው ካሉ ተሳስተዋል”
እውነቱን ለመናገር ይሄ ነገር በትክክል እሳቸው ይናገሩት ወይም ሌላ ሰው በስማቸው ይፍጠረው የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ (ለዚህች እንኳን አያንሱም!)
ጠ/ሚኒስትሩ ለጉብኝት ወደ ቤልጂየም ሄደው ነበር አሉ፡፡ (ከምርጫ 97 በፊት ይሁን በኋላ አልታወቀም!) እዚያ በነበረው ስብሰባ ከተጋበዙት ኢትዮጵያውያን መካከል አንዷ (የአውሮፓ ሞልቃቃ ሳትሆን አትቀርም!) ሃሳብ ለመስጠት ተነሳች፡-
“የእርስዎ መንግስት አስጠሊታ ነው፤ ሥርዓታችሁ አስጠሊታ፤ አካሄዳችሁ አስጠሊታ፤ ባለስልጣኖቻችሁ አስጠሊታ፤ ሁለመናችሁ አስጠሊታ ነው” (ሃገሩ ቤልጂየም መሆኑ በጃት!)
ጠ/ሚኒስትሩም፤ “ጥሩ ነው! አስጠሊታ ልንሆን እንችላለን፡፡ አሁን እዚህ የመጣነው ግን ለቁንጅና ውድድር አይደለም፡፡” (የጨረሰች እኮ ናት!)
በ97 ምርጫ ሰሞን 22 ማዞሪያ ላይ ቁጭ ብለው የሚለምኑ አዛውንት የእኔ ብጤ (የእኔ ቢጤ” የምንለው Modest ለመሆን እኮ ነው!) ትዝ ይሉኛል፡፡ ምርጫው እየተሟሟቀ ሲመጣ ታዲያ እሳቸውም አንድ ሁለት የግል ጋዜጦችን እያነበቡ ነበር የሚለምኑት (የቅንጅት ደጋፊ ነበሩ ልበል!) እኔ የምላችሁ ግን… ሰዎች ባኮረፉ ቁጥር ስደትና መኮብለልን የሚመርጡት እንዴት ቢመራቸው ነው? (የመኢአድ አባላት ኤርትራ ገቡ ሲባል ሰምቼ እኮ ነው!) ቆይ ግን ያኮረፉ ተቃዋሚዎች ወደ ኤርትራ የሚጎርፉት ወዲ አፈወርቂ “የማኩረፊያ ካምፕ” አላቸው ማለት ነው? (የእሳቸው ወደኛ፤ የኛ ወደሳቸው ሆነ እኮ!)
እናላችሁ ግን… ዜጐች የኑሮ ውድነትና ድህነት አስመርሯቸው ሲሰደዱ…. ዝም!! ጭጭ!! ጋዜጠኞችና አሳታሚዎች የፈሩትን ፈርተው ሲሰደዱ…ዝም!! ጭጭ!! ተቃዋሚዎች በፖለቲካ ምህዳሩ ወይም በራሳቸው መጥበብ አሊያም በኢህአዴግ ካድሬዎች ዕብሪት ተማረው ሲሰደዱ ዝም!! ጭጭ!! እኔ የምፈራው ምን መሰላችሁ? እንዲህ እንደ አሸዋ የበተናቸውን ዜጎቻችንን በኋላ መሰብሰቡ ጭንቅ እንዳይሆንብን ነው፡፡ (ነው ወይስ አንፈልጋቸውም?)
የስደት ነገር ከተነሳ አይቀር አንዲት ሃሳብ ጣል አድርጌ ልለፍ፡፡ ዜጐች ከስደት ይልቅ አገር ውስጥ ሰርተው እንዲለወጡ መቀስቀስ፣ ማነቃቃት፣ ግንዛቤ መፍጠር… ሸጋ ነው፡፡ ግና ሁሉምን እየተነሳ ሹማምንት ያሉትን እንደበቀቀን መድገም ያሳፍራል። ያሳዝናል፡፡ ያስተዛዝባልም፡፡  (መፍትሄም አይሆንም!)
“ከሰው አገር ስደት እናት ጉያ ስር አሹቅ እየበሉ መኖር በስንት ጣዕሙ…” የሚሉት የጦቢያ ዝነኞች (Celebrities) ሲሆኑ ደግሞ ያናድዳል፡፡ (አሹቅንም… ስደትንም… ድህነትንም…. አያውቁትማ!)
አሁን ወደ ምርጫ ወጋ ወጋችን እንመለስ፡፡ እንዳልኳችሁ የምርጫ ዋዜማ ላይ ስለሆንን ገራ ገሩን ነው የምንጫወተው፡፡ ወጋ ወጉን!! (በህግ ዕውቀት ማነስ የሥነ ምግባር ጥሰት እንዳንፈጽም እኮ ነው!)
በነገራችን ላይ በ97 ምርጫና በዘንድሮው ምርጫ መካከል ያየሁት አንድ ጉልህ ልዩነት ምን መሰላችሁ? በ97 የፖለቲከኞች ስደት …. ኩብለላ …. እስር … ወዘተ የተከሰተው ከምርጫው በኋላ ነበር፡፡ በዘንድሮው ምርጫ ግን ከምርጫው በፊት ሆኗል፡፡ (ከተሳሳትኩ እታረማለሁ!)
ከምሬ እኮ ነው … አንዳንድ የመኢአድ አባላት “የሰላማዊ ትግል ጫማቸውን ሰቀሉ!” ሲባል ሰምቻለሁ፡፡ (ጥሩ ምልክት ባይሆንም እንደ መረጃ ተቀብለነዋል!) እኔ የምላችሁ ግን ሰዎች እያኮረፉ ለስደት ሲዳረጉ (ፈልገውም ይሁን ተገደው!) የሚያግደረድር እንኳ ይጥፋ እንዴ! (እመኑኝ! 8ኛው ሺ ማለት አሁን ነው!)
አንዳንዴ ለምን እንደሆነ እንጃ … እዚህች አገር ላይ ሁሉ ነገር ድብልቅልቅ ይልብኛል፡፡ ለምሳሌ የሃይማኖት መሪዎችና የመንግስት ባለሥልጣናት፣ ቤተክህነትና የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር … ወጣትና የአገር ሽማግሌ … ድብልቅልቅ! (እኔ ብቻ ነኝ ልበል?!) ከመደበላለቅ ይጠብቃችሁ!! (የሃይማኖት መሪዎቹ ባለስልጣን ቅላፄ ሲናገሩ ምን ልበል?!)
ወደ ምርጫ ተመልሼአለሁ፡፡ ምን ሰማሁ መሰላችሁ… የእኛ አገር ፓርቲዎች አሁንም (እንደ 60ዎቹ) በአ“ቸ”ናፊ እና በአ“ሸ”ናፊ (በ“ቸ” እና “ሸ” እኮ ነው) መወዘጋገባቸውን አልተውም ይባላል? ሁለት ተቃዋሚ ፓርቲዎች የዘንድሮ የምርጫ ቅስቀሳ ሂደት ጅማሮ ላይ “የአዲሱ ትውልድ ፓርቲ” የምትለዋ አባባል ‹የእኔ ናት› በሚል መነታረካቸውን ሰምቼ ተስፋ ቆረጥኩ… በሆዴ! (ሌላው አብሮኝ ተስፋ እንዳይቆርጥ እኮ ነው!)
የቅስቀሳ ሳንሱር ደግሞ ትዝ አለኝ፡፡ (የ2007 ምርጫ ትውስታዬ ነው!) ቅሬታው የቀረበው ከኢዴፓ ነው፡፡ እናላችሁ … ኢዴፓ “መንግስት ሆኜ ከተመረጥኩ የፖለቲካ እስረኞችን በሙሉ እፈታለሁ” የሚል የቅስቀሳ መልዕክት ለEBC ይልካል፡፡ “የለም …. አይተላለፍም” ተባልኩ - ብሏል ኢዴፓ፡፡ (ከርቸሌ ውስጥ አመፅ ይቀሰቅሳል ተብሎ ይሆን?)
ሰሞኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት የምርጫ ሂደቱን የመገምገምያና የመቋጫ መድረክ በሒልተን ሆቴል አዘጋጅቶ ነበር፡፡ (ከስር ከስሩ መገምገም ዕዳ ያቃልላል!) እናላችሁ …. በግል ለመወዳደር አስበው በዕጣ የተጣሉት ወ/ሮ ሰሎሜ ታደሰ (የቀድሞ የኢቲቪ ሥራ አስኪያጅ!) በፕሮግራሙ ላይ የሰጡት የሰላ ሂስ አስደስቶኛል፡፡ (አንዳንዶች “Feminist” ናቸው ሊሉ ይችላሉ!)
እናላችሁ… ወ/ሮ ሰሎሜ የምርጫው ፍትሃዊነትና አሳታፊነት ላይ ነው ዱብዕዳ አስተያየት የሰነዘሩት። (የደነገጠ ግን የለም!) የምርጫ ቦርድ አባላት … በአዳራሹ ያሉት ተሳታፊዎች … ሚኒስትሩ …. ወዘተ ሁሉ ነገሩ በወንዶች የተሞላ መሆኑን ጠቁመው ሴቶችን የቱ ጋ ነው ያሳተፈው? ሲሉ ከአዳራሽ ሙሉ ወንድ ጋር ተገዳድረዋል፡፡ (የሰሎሜ ዓይነት ሃቀኛና ደፋር ያብዛልን!) የሚያሳዝነው ግን ወንዱ ሁሉ ቀልድ (Joke) እንደተነገረው ሰው ነው በሳቅ የፈረሰው፡፡ (አሳታፊነት ላይ ጥያቄ ማንሳት በየት አገር ነው የሚያስቀው?) በነገራችን ላይ እንደ ሰሎሜ ያሉ ጀግኖች ከምርጫ በዕጣ መገለላቸው ፌር አይደለም (ህግና ደንቡ ቢሆንም!)
ወደ ምርጫ ገራገር ልመልሳችሁ፡፡ ሰሞኑን በፌስ ቡክ ላይ ቀልቤን ከሳቡኝ ከምርጫ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች መካከል አንድ የኢህአዴግ ደጋፊ “ፌዝቡከር” ፖስት ያደረገው ምስል (ከንፈሯን ንቦች የከበቧት ሴት ናት!) ይገኝበታል፡፡ ከምስሉ ስርም፡-
“ማር ማር ይላል ከንፈርሽ
ለካስ ኢህአዴግ ነሽ” ይላል በግጥም፡፡
 የሰማያዊ ፓርቲ ደጋፊዎች ደግሞ “ግራም ነፈሰ ቀኝ ምርጫችን ሰማያዊ ነው” የሚል መፈክር ለጥፈዋል፡፡ (የፌስ ቡክ ጌታ ማርክ ዙከርበርግ ውሎ ይግባልን!!)
ከምርጫ ጋር ብዙም ግንኙነት የሌለው፣ ፈገግም ጨፍገግም የሚያደርግ ነገር ልንገራችሁና ልሰናበት (ምንጩ ፌስ ቡክ ነው!)
“አሜሪካ - ሆሊዉድ
ህንድ - ቦሊውድ
ናይጄሪያ - ኖሊውድ
ኢትዮጵያ - ኑሮውድ!!”
(አይገርምም… ጦቢያ በዓመት ይሄን ሁሉ ፊልም እያወጣች የፊልም መንደር የላትም!!)
በመጨረሻ በቴክስት ያለፍላጐታችን ከሚደርሱን መልዕክቶች ሰሞኑን የተላከልንን ለመሰናበቻ እነሆ፡፡
“Cheating in Examination is Killing a Generation!” ይላል (National Educational Assessment and Examination Agency) ከተባለ የመንግስት ተቋም የተላከው መልዕክት!)
እርግጥ ነው መኮረጅ ሃጢያት ነው (መንግሥት የሚኮርጀው ለፈተና ሳይን አገር ለመምራት ነው!) ግን እኮ Cheating   በፈተና ብቻ ሳይሆን በትዳርም (አመንዝራ ይባላል) በሥራ ቦታም፣ በጓደኝነትም፣ በምርጫም (ማጭበርበር ይባላል!) ወዘተ … ነውር ስለሆነ እናስወግደው!!
ስናሳርግ …. ምርጫው ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊና፣ ፍትሐዊ (ፍቅርም የሞላበት!) እንዲሆንልን አበክሬ እመኛለሁ፡፡ (በፀሎት የታገዘ ምኞት መሆኑን ልብ በሉ!)
ኢትዮጵያ ለዘላለም ታፍራና ተከብራ ትኖራለች። (ድንገት ብቅ ያለውን አርበኝነቴን ቻሉት!!)

Read 6653 times