Saturday, 16 May 2015 10:03

ታዋቂ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ነገ የዓይን ብሌን ልገሳ ያደርጋሉ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

ባጋጠመው ህመም ምክንያት ለ14 ዓመታት በጀርባው ተኝቶ በርካታ የስዕል ሥራዎችን ሲሰራ የቆየውና በቅርቡ “ታላቅ የምስጋና የስዕል ኤግዚቢሽን” ያዘጋጀው ሰዓሊ ብሩክ የሺጥላና ሌሎች ታዋቂ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ከህልፈታቸው በኋላ የዓይን ብሌናቸው ብርሃናቸውን ላጡ ወገኖች እንዲውል ለማድረግ በቃልኪዳን መዝገብ ላይ ሊፈርሙ ነው፡፡ ልገሳው ነገ ምኒልክ ሆስፒታል ቅጥር ግቢ ውስጥ በሚገኘው የኢትዮጵያ የዓይን ባንክ ቢሮ ይካሄዳል፡፡
“እኔ ያየሁትን ሌሎች እንዲያዩ” በሚል በተዘጋጀው የልገሳ ዘመቻ፣ የልደት በዓሉን ምክንያት በማድረግ የዓይን ብሌኑን የሚለግሰውን የወጣቱን ሰዓሊ ብሩክ የሺጥላ አርአያነት ተከትለው ሌሎች ታዋቂ የኪነጥበብ ባለሙያዎች በልገሣ ቃል ኪዳን መዝገቡ ላይ እንደሚፈርሙ የኢትዮጵያ የዓይን ባንክ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ደመቀ ከበደ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ ከተቋቋመ አስራ አንድ ዓመት ያስቆጠረው የዓይን ባንኩ እስከ አሁን በብርሃን አሳላፊ መስታወት መጎዳት ምክንያት ዓይነስውር ለሆኑ 1170 ወገኖች ንቅለ ተከላ መከናወኑን የገለፁት ምክትል ሥራ አስኪያጁ፤ ካለው የታካሚ ቁጥር አንፃር ይህ እጅግ አነስተኛ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ህክምናው የሚሰጠው ህብረተሰቡ በበጎ ፈቃደንነት ከህልፈት በኋላ በሚለግሰው የዓይን ብርሃን አሳላፊ መስታወቱ ሲሆን ይህን አካል የመለገሱ ባህል ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሎች ቢታዩበትም በቂ ሊባል የሚችል አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ በቅርቡ የሰርግ ስነስርዓታቸውን ያከናወኑት አቶ ዮሴፍ ገብረስላሴና ወ/ሮ ፀሐይ ቦጋለ የተባሉ ሙሽሮች በቃልኪዳን መዝገቡ ላይ የፈረሙ ሲሆን ባንኩ ሙሽሮቹ ባሳዩት አርአያነት ያለው ተግባር ምክንያት የበጎ ፈቃድ አምባሳደር አድርጎ የሾማቸው መሆኑን አቶ ደመቀ ተናግረዋል፡፡
እስከ አሁን ከ10 ሺ በላይ በጎ ፈቃደኞች የዓይን ብሌናቸውን ከህልፈት በኋላ ለመለገስ ቃል ገብተው የፈረሙ ሲሆን ከእነዚህ በጎ ፈቃደኞች ውስጥ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ፤ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴና አርቲስት ጀማነሽ ሰለሞን እንደሚገኙበት አቶ ደመቀ ገልጸዋል፡፡  

Read 1786 times