Monday, 11 May 2015 09:20

ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ የፈጀው የብስኩትና የፓስታ ፋብሪካ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

     በኦሮሚያ ክልል በቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪ መንደር በ36 ሚሊዮን ዶላር ወይም ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ካፒታል የተገነባው አሐዱክስ ፉድ ፕሮዳክትስ አክሲዮን ማኅበር  የብስኩትና የፓስታ ፋብሪካ ተመረቀ፡፡አሐዱክስ ፉድ ፕሮዳክትስ የኢትዮጵያዊ ኢንቨስተርና የእንግሊዝ ኩባንያ ንብረት ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ለ20 ዓመታት የሻይ ምርት በማቀነባበር፣ መድኃኒት በማስመጣት፣ በዘመናዊ እርሻ
ልማት፣ በሪል ኢስቴት፣ በፓኬጂንግና በትሬዲንግ ዘርፎች ተሰማርቶ ሲሰራ የቆየው አሐዱ ኃ.የተ.የግ ኩባንያ፤ በሴፕቴምበር 2013 ኩባንያውን የተቀላቀለው የእንግሊዙ ቫሰሪ ግሎባል ግሩፕ
በሽርክና ያቋቋሙት መሆኑ ታውቋል፡፡ ሊዝ በተገኘ 42 ሺህ ካ.ሜ ላይ የተገነባው የብስኩትና የፓስታ ፋብሪካ፣ በኢጣሊያ ታዋቂ የሆኑ 5 ድርጅቶች ያመረቷቸውና የዘመኑ ቴክኖሎጂ ያፈራቸው መሳሪያዎች የተገጠሙለት ፋብሪካ በዚህ
ሳምንት የተመረቀው በኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ክቡር ዶ/ር ሙላቱ ተሾመና በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዚዳንት ክቡር አቶ ሙክታር ከድር ነው፡፡ በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ ፋብሪካው ከየት ተነስቶ የት እንደደረሰ የገለፁት የአሐዱክስ ፉድ ፕሮዳክትስ የቦርድ አባልና ከቫሳሪ ግሎባል ግሩፕ ጋር የኩባንያው ባለቤት የሆኑት አቶ ሰለሞን
ወንድሜነህ፣በአሁኑ ወቅት ምርት የጀመረው የብስኩት ፋብሪካው እንደሆነ ጠቅሰው የፓስታ ፋብሪካውም ህንፃ ግንባታ ስለተጠናቀቀ በቅርቡ መሳሪያዎች ተገጥመውለት ምርት አንደሚጀምር ገልፀዋል፡፡ የብስኩት ፋብሪካው በቀን 500 ኩንታል ብስኩት የማምረት አቅም ያለው መሳሪያ ተተክሎለት ምርት መጀመሩን የጠቀሱት አቶ ሰለሞን፤ ተመሳሳይ የማምረት አቅም ያላቸው 5 መስመሮች
ይተከላሉ ብለዋል፡፡ የፓስታ ፋብሪካው እያንዳንዳቸው በቀን 900 ኩንታል ፓስታ የማምረት አቅም ያላቸው የማምረቻ መስመሮች እንደሚተከሉና ለሁለቱ ፋብሪካዎች በቀን ከ6, 500 ኩንታል በላይ ማምረት የሚችል የዱቄት ፋብሪካ ለመገንባት ማቀዳቸውን ተናግረዋል፡፡ የፋብሪካው ግንባታ 3 ዓመት መፍጀቱን፣ በአሁኑ ወቅት የተለያዩ ብራንድ ያላቸው ብስኩቶች
እንደሚያመርት፣ በቅርቡ የተለየ ጣዕምና ከፍ ያለ ጥራት ያላቸውን ብስኩቶች ለገበያ እንደሚያቀርብ ልጸዋል፡፡ በቀጣይ 3 ዓመት በሚደረገው የማስፋፊያ ሥራ 150 ሚሊዮን ዶላር
ወይም ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚፈጅ፣ አሁን ያለው 600 የሰራተኛ ቁጥር 3,000 እንደሚደርስ፣ 80 በመቶ የምርት ግብአት ከአገር ውስጥ እንደሚገኝ የጠቀሱት የቦርድ አባሉ።
የኢንቨስትመንቱ ዕቅድ ሲጠናቀቅ አሐዱክስ፣ ከምስራቅ አፍሪካ አንዱና ቀዳሚው አግሮ ፕሮሰሲንግ እንደሚሆን እናምናለን፡፡ ምርታችንን ለዓለም ገበያ በማቅረብ ለአገራችን የውጭ ምንዛሪ እናስገኛለን ብለዋል፡፡ በተለያዩ የመንግሥት አካላት ድጋፍ አሁን ላሉበት ደረጃ ለመብቃት በመቻላቸው ድጋፍ ደረጉላቸውን አካላት ቢያመሰግኑም፣ ያቀዱት ዓለም አቀፍ ደረጃ ላይ ለመድረስ ችግሮች
እንዳሉባቸው አልሸሸጉም፡፡ የኢንዱስትሪው ዞን ኤሌክትሪክ ማሰራጫ ከፍተኛ መጨናነቅ አለበት።
በዚህ የተነሳ ተደጋጋሚ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ችግር እየገጠመን ስለሆነ አስተማማኝ
የኃይል አቅርቦት እንድናገኝ አመራር ይስጥልን ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ ወደ ፋብሪካው የሚያደርሰው መንገድ ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች በሚያደርጉት ምልልስ እየተበላሸና ችግር ስለፈጠረባቸው ቀደም ሲል የክልሉ መንግስት ፕሬዚዳንት አቶ ሙክታር፤ ፋብሪካውን በጎበኙበት ወቅት መንገዱ አስፋልት ይለብሳል በማለት የገቡትን ቃል እየተጠባበቁ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ እንዲሁም ፋብሪካቸው የሚገኘው በአግሮ ፕሮሰሲንግ ዞን ቢሆንም የኢንዱስትሩ ውጤት አምራች ፋብሪካዎች ቦታ ተሰጥቷቸው ምርት መጀመራቸውን ጠቅሰው ይህ ስብጥር ዓለም አቀፍ የምግብና ድራግ ቁጥጥር ሰርቲፊኬት ለማግኘት የምናደርገውን ጥረት ይፃረራል፡፡ ስለዚህ ፋብሪካዎቹ የሚፈጥሩት ብክለት፣ ለውጭ ገበያ በምናቀርበው ምርት ላይ
ከፍተኛ ተፅዕኖ ስለሚፈጥር ብክለቱ የሚወገድበት መንገድ በአፋጣኝ እንዲፈልጉ የክልሉን
መንግስትና የከተማ አስተዳደሩን ጠይቀዋል፡፡ ፋብሪካው ዓለም አቀፍ ብቃቱ የተረጋገጠ የምግብ ማምረቻ ተቋም መሆኑንና የምግብ ደህንነትን ዋስትና ለማረጋገጥ እየሰራ ነው። ሰራተኞችን ሲቀጥር ያሰለጥናል፣ የሥራ ላይ ሥልጠናም ይሰጣል፡፡ ለሰራተኞቹ መፀዳጃና መመገቢያ ክፍል፣ ቢታመሙ ምርመራ የሚያደርጉበት ላቦራቶሪ፣ ልብስ መቀየሪያ የመሳሰሉ አገልግሎቶች ተገቢውን የጥራት ደረጃ እንደሚያሟሉ ተደርገው ተሰርተዋል፡፡ የሰራተኞቹ ደሞዝ ከሌሎች የምግብ ማምረቻ የፋብሪካዎች ጋር ሲነፃፀር በእጥፍ እንደሚጨምር ቀደም ሲል በናስ ምግብ ፋብሪካ ይሠራ የነበረውና አሁን ፋብሪካው የሺፍት ኃላፊ ገልጿል፡፡ “ሁላችንም በሚከፈለን ደሞዝና በሚደረግልን ክብካቤ ደስተኞች ነን፡፡ ለምሳሌ ብስኩቱን በማሸግ
ሥራ የተሰማሩ ሴቶች ዝቅተኛ ደሞዝ 2000 ብር ነው” ብሏል፡፡ የአሐዱ ኃ.የተ.የግ. ኩባንያ ባለቤቶች አቶ ሰለሞን ወንድሜነህና በላቤታቸው ወ/ሮ ራሔል አሰፋ በፋብሪካው ግንባታ ወቅት የላቀ የስራ አፈፃፀም ላሳዩና ፋብሪካው ለደረሰበት ደረጃ ያበቁትን ሁለት
ሰራተኞች በግል ገንዘባቸው መኪና ገዝተው ሸልመዋል፡፡  ለፕሮጀክት ማናጀሩ ለአቶ እሱባለው ከፈለ በ900ሺህ ብር የቤት አውቶሞቢል ገዝተው ሸልመዋል፡፡ ለፕሮጀክት አስተባባሪው ለአቶ ገሠሠ አይኛው 1.7 ሚሊዮን ዋጋ ያለውን ፒክአፕ መኪና ቁልፍ አበርክተዋል፡፡ ኩባንያው ማኅበራዊ ኃላፊነቱን መወጣት ከአሁኑ የጀመረ ሲሆን፣ ለአካባቢው አርሶ አደሮች ከብት ውሃ ማጠጫና ለመስኖ አገልግሎት የሚውል ውሃ ማጠራቀሚያ በመገንባት በዕለቱ አስመርቋል። የትምህርት ጥራትን ለማበረታታት ከፍተኛ ነጥብ ያመጡ ተማሪዎችን ምስል የሚይዝ አደባባይ በቢሾፍቱ ከተማ እያስገነባ ሲሆን ለእነዚህ ስራዎች ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጉ ታውቋል፡፡

Read 2361 times