Monday, 11 May 2015 09:16

ንግድ ባንክ የዘጠኝ ወር የዕቅድ አፈጻጸሜ አጥጋቢ ነው አለ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

       የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዘጠኝ ወር የዕቅድ አፈጻጸሙን ለመገምገም ከሚያዝያ 15-17 በባህርዳር
ከተማ ባደረገው ስብሰባ የአፈጻጸም ክንውኑ አጥጋቢ እንደነበር አስታወቀ፡፡ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተቀማጭ ሂሳብ ዕድገትን ለማሳደግ ባደረገው እንቅስቃሴ 27.5 ቢሊዮን ብር
ተጨማሪ ተቀማጭ ማሰባሰቡን አመልክቷል፡፡ ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር
የተሻለ መሆኑንና የባንኩ ጠቅላላ ተቀማጭ ሰኔ 30 ቀን 2006 ከነበረበት 139.3 ሚሊዮን  ብር ወደ 220.8 ቢሊዮን ብር ከፍ ማለቱን አመልክቷል፡፡ የባንክ አገልግሎትን ተደራሽ ከማድረግ አኳያ በዘጠኝ ወር እንቅስቃሴው 107 አዲስ ቅርንጫፎች
በመክፈት፣ የቅርንጫፎቹን ጠቅላላ ቁጥር 939 ማድረሱን፣ ከአዳዲስ ደንበኞቹ 1.1 ቢሊዮን ብር ተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰቡን፣ የ1.9 ሚሊዮን አዳዲስ ደንበኞች ሂሳብ በመክፈቱ የአስቀማጮች ጠቅላላ ብዛት 10.1 ሚሊዮን መድረሱን አስታውቋል፡፡
ባለፉት ዘጠኝ ወራት የውጭ ምንዛሪ ለማሰባሰብ ባደረገው ጥረት ከተለያዩ ምንጮች 4.4 ቢሊዮን
ዶላር ማሰባሰቡን ጠቅሶ፣ ከዚህ ውስጥ 3.63 ቢሊዮን ዶላር በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የተላከ መሆኑንና ቀሪው 756.1 ሚሊዮን ዶላር ከወጪ ንግድ መገኘቱን
አመልክቷል፡፡ አዳዲስ ብድሮች ለመስጠትና ብድሮችን ለማስገባት ባደረገው ጥረት፣ 62.9 ቢሊዮን ብር ለብድርና ለቦንድ ሽያጭ አቅርቦ፣ 28 ቢሊዮን ብር ከብድር መሰብሰብ መቻሉን ገልጿል፡፡ ወደ ጥሬ ገንዘብ አልባ የግብይት ሥርጭት ለመሸጋገር በሚያደርገው እንቅስቃሴ የባንክ ካርድ፣
የሞባይልና ኢንተርኔት የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆን አስፈላጊ ነው፡፡ በዚሁ መሰረት ንግድ ባንክ በተከላቸው 627 ኤቲኤም ማሽኖች በተደረጉ 11.1 ሚሊዮን ግብይቶች 9.6 ቢሊዮን ብር መገኘቱንና ከ33 ሚሊዮን ዶላር ጋር የሚመጣጠን የውጭ ምንዛሬ ልውውጥ መደረጉን አስታውቋል፡፡ በተለያዩ የገበያ ቦታዎች 1,162 POS ማሽኖች በማስቀመጥ 553.1 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው
228,903 ግብይቶች መደረጋቸውን፣ በአሁኑ ወቅት በደንበኞች እጅ ከሚገኙ ካርዶች 654, 641 አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን፣ ለሞባይል ባንኪንግ ከተመዘገቡት ውስጥ 144,588 ደንበኞች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን፣ የሞባይል ባንኪንግ ተጠቃሚዎች 39 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ 9,877 ግብይቶች መፈፀማቸውን፣ በሞባይል ባንኪንግ 49,728 ግብይቶች ተደርገው 173.3 ሚሊዮን ብር ማስተላለፍ መቻሉን፣ በአሁኑ ወቅት 1,127 የኢንተርኔት ባንክ ተጠቃሚ ደንበኞች ማፍራት መቻሉንና በኢንተርኔት ባንክ በተከናወኑ 5,895 ግብይቶች 42.5 ሚሊዮን ብር ማስተላለፉን አብራርቷል፡፡ የባንኩ አዳዲስ የባንክ አገልግሎቶች አፈጻጸም ስንመለከት፣ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት 69,217 ሂሳቦች ተከፍተው 807 ሚሊዮን ብር መቀመጡን፣ በሴቶች ልዩ ቁጠባ 422,482 ደንበኞች ተመዝግበው ያስቀመጡት ገንዘብ 3 ቢሊዮን ብር መድረሱንና በታዳጊዎች የቁጠባ ሂሳብ 273,560 ወጣቶች ተመዝግበው 353 ሚሊዮን ብር መቆጠባቸውን አስታውቋል፡፡ ንግድ ባንክ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 4,312 አዳዲስ ሰራተኞች የቀጠረ ሲሆን የሰራተኞቹ ጠቅላላ ብዛት 22,475 መድረሱን፣ የባንኩ ጠቅላላ ሀብት 276.3 ቢሊዮን ብር መሆኑን፣ በዘጠኝ ወር ውስጥ ጠቅላላ ገቢው 15.9 ቢሊዮን መድረሱንና በዚሁ ጊዜ ከታክስ በፊት 9.05 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማግኘቱን አስታውቋል፡፡  

Read 1639 times