Monday, 11 May 2015 09:04

“የቄሳር እንባ” እውነት ወይስ ልብወለድ?

Written by  በሰለሞን ጓንጉል አበራ
Rate this item
(2 votes)

የመጽሃፉ ርዕስ - የቄሳር እንባ
ደራሲው - ሃብታሙ አለባቸው
የገጽ ብዛት - 408
የታተመበት ጊዜ - 2007 ዓ.ም
የመጀመሪያው ስሜቴ
አስቀድሜ ያነበብኩት በመጽሃፉ የጀርባ ሽፋን ስለመጽሃፉ የተሰጡ አስተያየቶችን ነበር፡፡ አስተያየቶቹ ከአንዱ በስተቀር ደራሲው ከዚህኛው በፊት ላሳተሙት “አውሮራ” የተሰነኘ መጽሃፋቸው የተሰጡ አስተያየቶች ነበሩ፡፡ የአገላለጽ መንገድ ካልሆነ በቀር መጽሃፉ ባነሳው ታሪክ፣ በአጻጻፍ ዘዴው፣ በታሪኩ ፍሰት እኔም በእጅጉ ደስተኛ ነበርኩ፡፡ ፖለቲካ እና ፍቅር የአንድ ቤተሰብ አባል ሆነው በቀረቡበት “አውሮራ” መጽሃፍ ላይ የተፈጠሩ ገጸ ባሕሪያት፣ አንዳንድ ታሪኮች እንዲሁም የገጸባህሪያቱ ስያሜዎች በአብዛኞቹ በገሃዱ አለም የምናውቃቸው መሆን ይሕ መጽሃፍ ልቦለድ ነው? እውነተኛ ታሪክ? ወይስ ታሪክ ቀመስ ልቦለድ? የሚሉ ጥያቄዎችን አጭሮብኛል፡፡ ከዚህም ባለፈ ታሪክ ቀመስ ልቦለድ ቢባል በታሪኩ እና በልቦለዱ መካከል ያለው የእውነት ድንበር የቱ ነው? አንደኛው የአንደኛውን ድንበር ሲያቋርጥ የሚፈጠረውንስ ያለመረዳት እንዴት ማስታረቅ ይቻላል? የሚሉት ጥያቄዎች መልስ ያጣሁላቸው ተጨማሪ ጥያቄዎች ነበሩ፡፡ ጥያቄዎቼ መልስ
እንዳጡ ይልጥ መልስ ሊያሳጡኝ ደራሲው አሁን ደግሞ “የቄሳርን እንባ” ይዘው መጡ፡፡የቄሳር እንባ እና ፍቅር
እንደ አውሮራ ሁሉ ይህም  መጽሃፍ በአጻጻፍ ቴክኒኩ፣ በፖለቲካዊ ትንታኔው እና በገጸ ባሕሪያት አሳሳል ድንቅ ሆኖ ቀርቧል፡፡ እንደ ቀደመው “አውሮራ” ሁሉ በዚህም መጽሃፍ ፍቅር ከፖለቲካ ጋር እወዳጅ ብሎ ቁም ስቅል ሲያይ እና አንባቢንም ሲያሳይ አንብበናል፡፡ በምናባችን አይተናል። ሐምራዊት በተገለጸችባቸው ውብ አረፍተ ነገሮች ብቻም ሳይሆን በዚህ ጊዜ ብዙም ለስምነት ሲውል በማንሰማው መጠሪያዋ በቀላሉ የማትረሳ ሆና ቀርባልናለች፡፡ ደራሲው የሐምራዊትን እና የአፍቃሪዋን መቶ አለቃ በላይነሕ ደሴን (እርሱ የፕሬዝዳንት መንግስቱ ባለቤት የእህት ልጅ እና የመረጃ ምንጫቸው ሆኖ ቀርቧል) መጨረሻውን ሳያሳየን የራሳችሁ ጉዳይ ቢለንም ምርጥ የፍቅር ታሪክን በማቅረብ ግን አልጨከነብንም፡፡ ሊያውም ኢትዮጵያ በምትመራበት ቤተመንግስት ቅጽር ግቢ የቀረበው ይሕ የድብቅ የፍቅር ታሪክ (ፍቅር ሲደበቅ ደስ ይላል መሰል) አንባቢን ከመጽሃፉ ጋር አጥብቆ ለመያዝ አቅሙ አለው፡፡ ፖለቲካዊ ይዘት ያለው ስነጽሑፍ ብዙም የማይስባቸው ሰዎች ስለሐምራዊት ሲሉ ብቻ የቄሳርን እንባ እልፍ እልፍ እያሉም ቢሆን ማንበባቸው የሚቀር
አይመስለኝም፡፡ደራሲው ደግ ነውአራት ኪሎ ቤተ መንግስት ይዞን ገባ፡፡ ሊቀ መንበር መንግስቱ ስለሚኖሩበት ቤት፣ ስለ ቤተ መንግስቱ ቅጽር ግቢ አጠቃላይ ስዕልም ሰጠን። ይበልጥ ደግ ሆነናም ፕሬዝዳንቱ እንደ ባል እና እንደ አባት ሆነው ሲኖሩ ሊያሳየን ባለቤታቸው ውባንቺን ካወቁበት ቀን አንስቶ ሶስቱን ልጆቻቸውን ትምሕርት፣ ትዕግስት እና አንድነትን ከነየባሕሪያቸው አስተዋወቀን፡፡ ስለአባትዋ ቪኦኤ እና የያኔው የወያኔ ራዲዮ በተናገሩ ቁጥር ልጃቸው ትምሕርት በር ዘግታ ስታዝን አሳየን፡፡ ማትሪክ ያመጣች ጊዜም ኮረኔል መንግስቱ አራት ኪሎ ዩኒቨርስቲ ይሻልሻል ወይስ ጥቁር አንበሳ እያሉ ሲያስመርጧት አስነበበን፡፡ በጥቅሉም ስለ ቤተሰባዊ ሕይወታቸው ቤተ መንግስት እና ቤታቸው አስገብቶ አሳየን፡፡ እኛን ስለሚመሩን ሰዎች ቤተሰባዊ ሕይወት ብዙ በማናውቅበት እና እንድናውቅም በማይፈቀድልን ሃገር ነዋሪ ነንና ነው የደራሲውን ይሄንን ተግባር በእርግጥ የእውነቱን ነው የጻፈውን እየጠየቅሁ? ደግ ነው ያልኩት፡፡ ሳንተዋወቅ መሪና ተመሪ መሆን ግን ያሳዝናል፡፡ኮረኔል መንግስቱ ውባንቺን በአራዳ ቋንቋ የጠበሱበት መንገድም ደስ ይላል፡፡ እግራቸው ለወታደርነት ሥራ ጎጃም የደረሰው ሰውየው፣ የእህል እገሃባቸውን ሊያስታግሱ በገቡበት አነስተኛ የገጠር ምግብ ቤት ነበር ውባንቺን ያገኙት፡፡ ርሃብ በጣፋጭ ጥብስ፣ መጠማትም በጥሩ ጠጅ ተሸነፉ፡፡ የሥጋ ፍላጎትን እየሞሉ ሳሉ ማደላደያውን ቡና ሊያፈሉ አይናፋርዋ ውባንቺ ከመንግስቱ ፊት በቀረቡ ጊዜ የልባቸውን ሙላት የሚሰጧቸውን የትዳር አጋር አገኙ፡፡ መቼም ግጥምጥሞሹ ሸጋ ነበር፡፡ በዚህ ሁሉ አስደሳች የታሪክ ጉዞ ግን ዘና ብዬ እያነበብኩ እኚህ ደራሲ የጻፉት እውነት ነውን? ስል እጠይቃለሁ፡፡ ከተጻፈው ሁሉ የትኛው ልቦለድ? የትኛውስ እውነት ነው ስል እጠይቃለሁ፡፡የኮሎኔሉ የሥልጣን ጉዞ
የጉዟቸው ማለፊያ እና ማረፊያ ሁሉ ሞት፣ አጃቢያቸው ደግሞ ግትርነትና የጦር መሳሪያ ሆኖ በስልጣናቸው የዘለቁት መንግስቱ፤ ከውስጥ ወደ ውጭ ማየት የማይችሉ ሆነው ቀርበዋል። ሁልጊዜም ራሱን ብቻ የሚያዳምጥ፣ እንወያይ ብሎ እንኳን ሰብስቦም ለሌሎች ሃሳብ ተግባራዊነት ጊዜ የማይሰጠው አምባገነንታቸው ሞትን ከቤተ መንግስት ቅጥር እስከ ጦር ሜዳ ሲጠራና ሲያመጣ የሥልጣን ዘመናቸው ያልቃል፡፡ የቅርብ ሰው ሆኖ ግደል ያሉትን ሁሉ ሲገድልና ሲያስገድል የነበረው አስር አለቃ፣ ኋላ መቶ አለቃ የሆነው ምስጋናው በማዕረግ እድገቱ የደስ ደስ የግድያ ጀብዱውን ሲያወራ በልጃቸው መሰማቱ እርሳቸውም ጆሮ ደርሶ እንዲገደል መደረጉ አንባቢን ያስደነግጣል፡፡ ግን ይሄስ ነገር እውነት ነውን? ስል እጠይቃለሁ፡፡የሚሰወድባቸውን አብዮታዊ እርምጃ አንደግፍም ለምን በጡረታ አይሰናበቱም? የሚል የውሳኔ ሃሳብ እየቀረበላቸው ውሳኔውን ወደ ጎን አድርገው በጄነራሎቻቸው ላይ ሞትን ሲፈርዱና ሲያስፈጽሙ የኖሩት መንግስቱ፤ በቅጡ አልገባቸውም በተባሉበት የሶሻሊዝም ርዕዮተ አለም ሲዳክሩ እንደኖሩ የጻፈልን ደራሲ፤ መንቃታቸውን እና የመጨረሻ  ዕንባቸውን እየናፈቀ በልግመተ ኢትዮጵያ ሃሳቡ መቶ አለቃ በላይነህን ተራኪ አድርጎ ያስነብበናል፡፡ የታሪኩ ዋና ማጠንጠኛ የሆኑት ፕሬዝዳንት መንግስቱ እና ባለስልጣኖቻቸው  (እያንዳንዳቸው ከነእውቀት እና ባሕሪያቸው በመጽሃፉ ቀርበዋል፡፡) ኢትዮጵያን የመሩበትን የጦር መንገድ፣ ሶማሊያን ድል የመቱበት ብርታት፣ ያለፍንባቸውን የድርቅና የእርስ በእርስ ጦርነትን ጊዜ በቄሳር እንባ ላነበበ የዛሬ ትውልድ እንኳንም ያንን ጊዜ አልኖርኩበት ብሎ ቀድሞ መመኘቱ የሚቀር አይመስለኝም፡፡እባክዎ ደራሲው ይንገሩኝ
በመጽሃፉ ላይ አብዛኞቹ የተሳሉት ገጸ ባህሪያት በገሃድ አለም የሚታወቁ ናቸው፡፡ በመቶ አለቃ በላይነህ ደሴ ሲቀርብ የነበረው የፖለቲካ ትንተናም ንድፈ ሃሳባዊ ብቻም ሳይሆን በተግባራዊ እውቀት የተደገፈ ስለመሆኑ በግልጽ ይታያል፡፡ ገጸ ባህሪያቱን ከፖለቲካ ትንታኔው ጋር ላዋደደ ሰው የሚያነበው ሁሌ እውነት ነው ብሎ ለማመን የሚገደድ ይመስለኛል፡፡ እኔ እንደዚያ ተሰምቶኛል፡፡ ከስሜት ባለፈ ግን እውነ ትመሆኑን ለማረጋገጥ ደራሲው ይሄንኑ በመጽሃፉ በመግለጽ እውነቱን እንድናውቅ እድሉን አልሰጡንም፡፡ በመጽሃፉ የተገለጹ ድርጊቶችን እና ቁጥሮችን ለሌላ ስራ በማጣቀሻነት ለማቅረብ የሚፈልግ አንባቢም ሆነ የታሪክ ባለሙያ በዚህ ረገድ የሚቸገር ይመስለኛል፡፡ ደጋግሜ እንዳነሳሁት አቶ ሃብታሙ መጽሃፉን ድንቅ አድርገው አቅርበውታል፡፡ በዚህ ላይ ጥያቄ የለኝም፡፡ ምርጥ መጽሃፍ ነው፡፡ ጥያቄዬ መጽሃፍዎት እውነተኛ ታሪክ ነው ወይስ ልቦለድ? ምን ያህሉስ እውነት ነው? የሚለው ነው፡፡ ጥያቄዬ መጽሃፍዎት እውነት እና ልቦለድን
አጋብቶ ያቀረበም ከሆነ እንደ እኔ ያለ አንባቢዎ ይሄንን ለመለየት ድንበሩን ለማወቅ አይቸገርምን? የሚል ነው፡፡ ከዚህ በተረፈ ግን ሌሎች ሥራዎችዎንም ለማየት ከሁሉም የሚበልጠው የአዕምሮ ሰላም ከእርስዎ ጋር
እንዲሆን ከልቤ እመኝልዎታለሁ፡፡

Read 2753 times