Print this page
Sunday, 10 May 2015 15:54

የዓለም የፕሬስ ነፃነት ክፉኛ አሽቆልቁሏል ተባለ!!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(12 votes)

ኤርትራ በፕሬስ ነፃነት 180ኛ ወጥታለች (ከ180 አገራት)
ኢትዮጵያ ደግሞ ከ180 አገራት 142ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች

    የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን ባለፈው እሁድ ሜይ 3 ቀን 2015 ዓ.ም በመላው ዓለም ታስቦ ውሏል፡፡ (እኛ አገር ደግሞ በመወቃቀስ!) አሳዛኙ ነገር ግን ምን መሰላችሁ? ያለፈው 2014 ዓ.ም ለዓለም የፕሬስ ነፃነት እንቅፋቶች የበዙበት ዓመት ነበር፡፡ በመላው ዓለም በመረጃ ነፃነት ረገድ ከፍተኛ ማሽቆልቆል መታየቱን “ሪፖርተርስ ዊዝአውት ቦርደርስ” የተሰኘው የሚዲያ መብት ተሟጋች ቡድን ገልጿል፡፡
እናላችሁ … ቡድኑ ባወጣው ሪፖርት፤ ባለፈው አንድ ዓመት በመላው ዓለም 25 ጋዜጠኞች የተገደሉ ሲሆን 158 ጋዜጠኞች ታስረዋል፡፡ መቀመጫውን ኒውዮርክ ያደረገው ሌላው የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ ቡድን (CPJ) በበኩሉ፤ ጋዜጠኞችን በማሰር ኢትዮጵያን በ2ኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል - 17 ጋዜጠኞችን አስራለች በሚል፡፡
በነገራችን ላይ ጋዜጠኞችን በማሰርና የህትመት ሚዲያም ሆነ ኢንተርኔትን በማፈን ከዓለም ቁጥር 1 የተባለችው ጎረቤታችን ኤርትራ ናት፡፡ (ሌላው ቢቀር ምናለ ከእሷ እንኳ ራቅ ብንል?!)  ጋዜጠኞች የመንግስት ክስና እስር በመፍራት ለስደት የተዳረጉባት አገር በሚልም ጦቢያ ተነቅፋለች፡፡ በ2014 ዓ.ም 30 ጋዜጠኞች ለስደት ተዳርገዋል ይላል - ሪፖርቱ፡፡  (መንግሥት አንድም የተሰደደ ጋዜጠኛ የለም ቢልም መብቱ ነው!)
ባለፈው እሁድ በመንግስት ኮሙኒኬሽን ፅ/ቤት አስተባባሪነት (ካልሆነ እታረማለሁ!) በተከበረው የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን ላይ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ፅ/ቤት ሚኒስትሩ አቶ ሬድዋን ሁሴን፤ የግል መፅሄቶች በእያንዳንዱ ዕትማቸው ሊያስከስስ የሚችልና ህዝብን ለአመፅ የሚቀሰቅስ ነገር ይፅፉ የነበረ ቢሆንም መንግስት በ“ሆደ ሰፊነት” ችሏቸው መቆየቱን ገልፀዋል። (በጅምላ የተዘጉትን መፅሄቶች ለማለት ነው፡፡) እኔ በበኩሌ መንግስት “ሆደ ሰፊ” አልሆነም የሚል ክርክር የለኝም (“ከባለቤቱ ያወቀ ቡዳ ነው” አሉ!) የእኔ ጥያቄ ግን የመንግሥት “ሆደ ሰፊነት” ምን ፈየደ? የሚል ነው። ከምሬ እኮ ነው … ሆደ ሰፊነቱ ምን በጎ ነገር አመጣ? ይሄን ያህል መስዋዕትነት የተከፈለውስ ምን ለማትረፍ ነበር? ሁላችንም እንዳየነው ሁሉም የማታ ማታ ተከሰው፣ የሚዲያ ተቋማቱም ተዘግተው፣ አሳታሚዎችና ጋዜጠኞች ለስደት ነው የተዳረጉት፡፡ እናም መንግስት “ሆደ ሰፊነቱን” በአግባቡ የተጠቀመበት አልመሰለኝም (Abuse ነው ያደረገው!)
“ሆደ ሰፊነቱ” በዘመቻ ጠራርጎ ለመዝጋት ወይም ለመክሰስ ከሆነ ከዚህ እርምጃ አገርና ህዝብ እንዲሁም የግል ፕሬሱ ምን ተጠቀመ? እንኳን ሌላው ራሱ ኢህአዴግ መራሹ መንግስትም እኮ የተጠቀመው ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡ (ለጊዜው እፎይ ብሎ ይሆናል እንጂ!)
እኔ የምለው … ከጦቢያ ወፈ ሰማይ ስደተኞች መካከል ስንቱ በድህነት፣ ስንቱ በፖለቲካ፣ ስንቱ በባዕድ አገር ናፋቂነት፣ … ወዘተ ለስደት እንደተዳረገ መረጃ ቢደራጅ ጥሩ ይመስለኛል፡፡ (ለመንግስት ተመቹም አልተመቹም እኮ ኢትዮጵያዊነታቸው አይፋቅም!!) በዚህ አጋጣሚ ለልማታዊ መንግስታችን የምመክረው ነገር ቢኖር (ደህና መካሪ ገጥሞት አያወቅማ!) ሁሉን “ጠላት” ከማድረግ እንዲቆጠብ ነው፡፡ (ከበቂ በላይ ጠላት እኮ ነው ያለን!)
እኔ እንደውም …. መንግሥት በኢትዮጵያ ምድር ከድህነት ውጭ ጠላት ባይኖረው እመርጣለሁ፡፡ (ማን መራጭ አደረገህ እንዳትሉኝ!?!) እንዴ መንግሥት እንዴት ሳር ቅጠሉን ጠላት ያደርጋል?! አንዳንዴ ሳስበው አበሻ “ምቀኛ አታሳጣኝ” እንደሚለው ሁሉ ኢህአዴግም “ጠላት አታሳጣኝ!” የሚል ይመስለኛል፡፡ (ጠብ ጫሪ ሆኖ እኮ አይደለም!) በቃ ጠላት ሲኖር ብርታት ይሆነኛል ከሚል ባህላዊ አስተሳሰብ! ነው (ግን እኮ ጎጂ ነው!) ለነገሩ ተቃዋሚዎችም እኮ ያው ናቸው! በሆነ ተዓምር ኢህአዴግ የባህርይ ለውጥ ቢያመጣ እኮ ግራ ነው የሚገባቸው፡፡ ምክንያቱም ለእነሱ የፖለቲካ 101 ኢህአዴግን እስኪበቃው መስደብ ነው፡፡ (ይሄም ኋላቀርነት ነው!)
በነገራችን ላይ አቶ ሬድዋን ስለመፅሄቶቹ ያነሱት፣ እኔም በዛሬ ፅሁፌ የደገምኩት የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀንን ሰበብ በማድረግ ስለሆነ ከነገር እንዳትቆጥሩብኝ። ደግሞም እኮ ውይይት አይከፋም፡፡ ማን ያውቃል አንደኛው ወገን እስካሁን ያልተየው ነገር ብልጭ ሊልለት ይችላል። ይታያችሁ … ኢህአዴግ አንድ ቀን (በቀኝ ጎኑ የተነሳ ዕለት መሆን አለበት!) ተነስቶ “በግል ፕሬሱ ጉዳይ እኔም ዘንድ ስህተቶች ነበሩ፤ ኢህአዴግ የመላዕክቶች ስብስብ አይደለም፤ አውቆ በድፍረት ሳያውቅ በስህተት ጥፋቶች ሊፈፅም ይችላል” ብሎ ቢናዘዝስ! (ማን ያውቃል አሉ!) ለጊዜው ግን ቅዠትና ህልማችንን ትተን ወደ ተጨባጩ እውነታ እንመለስ፡፡ እናላችሁ … ኢህአዴግ በመፅሄቶቹ ላይ አሳየሁት ያለውን “ሆደ ሰፊነት” አባክኖታል ባይ ነኝ፡፡ (“ሆደ ሰፊነት” መጥፎ ሆኖ እኮ አይደለም!)
ይሄውላችሁ … ለምሳሌ ምርጫ ቦርድ በምርጫው ሂደት መጀመሪያ ላይ ደጋግሞ “ሆደ ሰፊነትን” ሲጠቅስ ነበር፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ከፓርቲዎች ጀርባ ላለው ህዝብና ለዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው ሲል እንደሆነ መግለፁ ትዝ ይለኛል፡፡ (አንዳንዶች መጨረሻው አላማረም ቢሉም!)
እናላችሁ … ኢህአዴግ/መንግስት ለግል መፅሄቶች አሳየሁት ያለው “ሆደ ሰፊነት” የግል ፕሬሱን ህልውና ለመታደግ ቢሆን ኖሮ ዋጋውን ከፍ ያደርግለት ነበር። “ለግሉ ፕሬስ ማበብ በፅናት የታገለ ፓርቲ!” ተብሎም ሲወደስ በኖረ! (አሁንም የሚያወድሱት አይኖሩም አልወጣኝም!)
በእርግጥ ይሄ ያለልፋት አይገኝም፡፡ ግን አሁን ከደረሰው ኪሳራ አይብስም፡፡ ከግል ህትመቶቹ አሳታሚዎችና አዘጋጆች ጋር በልበ ቀናነት ቢወያይና ቢመካከር እርግጠኛ ነኝ ለውጥ ይመጣ ነበር፡፡ (ከኢቲቪ ዶክመንተሪ ውይይት ይሻል ነበር!)፡፡ እንዳለ መታደል ሆነና ግን ሆደ ሰፊነቱን ከንቱ ያደረገ ውጤት ተከሰተ፡፡ በአንድ ጊዜ 6 መፅሄቶችና ሁለት ጋዜጦች ተከረቸሙ። የሚብሰው ደግሞ 30 የሚደርሱ ጋዜጠኞች ለስደት መዳረጋቸው ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ዓለም አቀፍ የፕሬስ ነፃነት ተሟጋቾች ሪፖርት መነሻ ሆነናል፡፡ ከእነ ኤርትራና ሰሜን ኮርያ ጋር (አገራዊ ኪሳራ እኮ ነው!)
በእሁዱ የፕሬስ ነፃነት ቀን አንድ ጥናት አቅራቢ፤ CPJ የተባለው የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ተቋም ኢትዮጵያ ውስጥ ኤዲተር ላልሆኑ ሁሉ Best Editor of the Year እያለ ይሸልማል ሲሉ ወቅሰውታል፡፡ በነገራችን ላይ ይሄን ተቋም የሚተቹና የሚወቅሱ አብዛኞቹ ሰዎች “የተቋሙን ፕሬዚዳንት አውቀዋለሁ፤ ዳይሬክተሩ ወዳጄ ነው” ወዘተ … በማለት ነው የሚጀምሩት፡፡ (ነገሩን ማለቴ ነው!)
እኔ እንግዲህ CPJን በዝና እንጂ ብዙም አላውቀውም። ሽልማቱም … ስልጠናውም (ካለው ማለቴ ነው?!) አልደረሰኝም፡፡ ግን ቢያንስ ይሸልማል ተብሏል፡፡ እናም ነገር በሆዴ በላሁ፡፡ ኢህአዴግ ወይም መንግስት ባለፉት ዓመታት ስንቱን ጋዜጣና መፅሄት እንደዘጋ አስቡት - በ97 ምርጫ ማግስትና በተለያዩ ጊዜያት፡፡ ስንቱ የግል ፕሬስ ጋዜጠኛ እንደታሰረ፣ እንደተሰደደ አስቡት፡፡ ስንት ወቀሳና ውግዘት በኢቢሲ እንደወረደበትም አስቡት - የግሉ ፕሬስ!! ግን በ25 ዓመት የኢህአዴግ የስልጣን ዘመን አንድ የግል ጋዜጣ ወይም ጋዜጠኛ … ኤዲተር … ካርቱኒስት … ፎቶግራፈር እውቅና ወይም ሽልማት ሲሰጠው አላየንም አልሰማንም፡፡ (ማመልከቻ ከመሰለብኝም ይምሰልብኝ!)
አሁን ያልኳት ነገር የመንግስት ወይም ኢህአዴግ ሥራ ነው አልወጣኝም፡፡ ጋዜጦችንና ጋዜጠኞችን የሚሸልሙና የሚያነቃቁ የግል ተቋማት ግን የግድ ያስፈልጋሉ፡፡ (የፕሬስ ካውንስል መቅደም እንዳለበት አልጠፋኝም!) ሆኖም ባለቤቶቹ ለየቅል ናቸው ብዬ ነው፡፡
እንግዲህ በዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን ሰበብ የጀመርኩትን የዓለም ፕሬስ መረጃዎች ጥቂት ላስቃኛችሁና ወጌን ልቋጭ፡፡ በነገራችን ላይ CPJ የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀንን ምክንያት በማድረግ ባወጣው ዓመታዊ ሪፖርቱ 10 በሳንሱር የታነቁ አገራትን ዝርዝር ይፋ አድርጓል፡፡ (ከቻይናም እንብሳለን እንዴ?) እናላችሁ … 1ኛ ኤርትራ፣ 2ኛ - ሰሜን ኮሪያ፣ 3ኛ ሳኡዲ አረቢያ፣ 4ኛ - ኢትዮጵያ፣ 5ኛ አዘርባጃን፣ 6ኛ - ቬትናም፣ 7ኛ - ኢራን፣ 8ኛ - ቻይና፣ 9ኛ ምያንማር፣ 10ኛ ኩባ …. ናቸው ተብለዋል፡፡ ሪፖርቱ ላይ እንደተገለፀው መንግስታት ሳንሱርን በተለያዩ መንገዶች ሊፈፅሙት ይችላሉ፡፡ አፋኝ የፕሬስ ህግ በማውጣት፣ ጋዜጠኞች ራሳቸውን ሳንሱር የሚያደርጉበት (Self Censorship የሚባለው ነው!) ስጋት በመፍጠር፣ ከአገር በማሰደድ ወዘተ እንደ CPJ ሪፖርት!በነገራችን ላይ በዚህ የCPJ ሪፖርት ውስጥ ኢትዮጵያ ብቻ አይደለችም የተገመገመችው (የኒዮሊበራሎች አሻጥር አይደለም ማለት ነው!) እናም በመላው ዓለም 180 አገራት በጥናቱ ወይም በግምገማው ውስጥ የተካተቱ ሲሆን ኤርትራ ከ180ኛ አገሮች 180ኛ ወጥታለች፡፡ (በፕሬስ ነፃነት ከዓለም ውራ ናት!) እኛስ? ጦቢያ 142ኛ ደረጃ ላይ ናት ተብሏል፡፡ በፕሬስ ነፃነት ላለፉት 5 ዓመት በተከታታይ 1ኛ የወጣችው ፊንላንድ ናት፡፡ ቀናሁባት! (በናታችሁ ቅኑባት!)
ከመለያየታችን በፊት ከኢንተርኔት ያገኘሁትን ቀልድ ልንገራችሁ፡፡ ሶቭየት ህብረት ከመበታተኗ በፊት ነው አሉ፡፡ የአሜሪካ ውሻ፣ የፖላንድ ውሻና የሶቭየት ህብረት ውሻ በአንድ ላይ ተቀምው ያወጋሉ፡፡
የአሜሪካው ውሻ፡- “በእኔ አገር ብዙ ከጮህክ ይሰሙህና ጥቂት ስጋ ይሰጡሃል”
የፖላንድ ውሻ፡- “ሥጋ ምንድን ነው?”
የሶቭየቱ ውሻ፡- “መጮህ ምንድን ነው?”
(በሶቭየት ህብረት የመናገር ነፃነት አለመኖሩን ለመጠቆም የተቀለደ ነው!)

Read 3454 times