Print this page
Saturday, 02 May 2015 12:09

በሱዳን ምርጫ አልበሽር በ94.5 በመቶ ድምጽ አሸነፉ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

- ዋና ዋናዎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በምርጫው አልተሳተፉም
- ምዕራባውያን አገራት ምርጫው ነጻና ፍትሃዊ አይደለም ብለዋል

 ዋና ዋናዎቹ የሱዳን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ነጻና ፍትሃዊ አይሆንም በሚል ራሳቸውን ባገለሉበት የአገሪቱ ምርጫ የተወዳደሩት ፕሬዚዳንት ኡመር ሃሰን አልበሽር፤ 94.5 በመቶ ድምጽ በማግኘት በቀጣይም አገሪቱን በፕሬዚዳንትነት እንዲመሩ መመረጣቸውን ቢቢሲ ዘገበ።የአገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን ሃላፊ ሙክታር አል አሳም ባለፈው ሰኞ ከካርቱም በሰጡት መግለጫ፣ ናሽናል ኮንግረስ ፓርቲን በመወከል ለፕሬዚዳንትነት የተወዳደሩት አልበሽር፤ ከ5 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ድምጽ በማግኘት ማሸነፋቸውን ያስታወቁ ሲሆን የአፍሪካ ህብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን በበኩሉ፤ ድምጽ ለመስጠት ከተመዘገቡት 13.3 ሚሊዮን ዜጎች ውስጥ ድምጽ የሰጡት አንድ ሶስተኛ ያህሉ ብቻ መሆናቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡ አልበሽር በዘንድሮው የሱዳን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ይህ ነው የሚባል ፉክክር እንዳልገጠማቸው የዘገበው ዘጋርዲያን በበኩሉ፣ ከተፎካካሪዎች መካከል የተሻለ ድምጽ ያገኙት ፌደራል ትሩዝ ፓርቲን ወክለው የተወዳደሩት ፋደል አልሳይድ ሹያብ መሆናቸውንና ያገኙት ድምጽም 1.43 በመቶ ብቻ መሆኑን አስታውቋል።ከሚያዝያ 5 ቀን ጀምሮ ለአራት ተከታታይ ቀናት በመላ አገሪቱ በተቋቋሙ 11 ሺህ የድምጽ ጣቢያዎች በተከናወነው የድምጽ አሰጣጥ ስነስርአት ላይ ድምጽ ለመስጠት ከተመዘገቡት ውስጥ ሁለት ሶስተኛው ድምጽ አለመስጠታቸውንና ለፕሬዚዳንታዊ ምርጫው በተፎካካሪነት የቀረቡት 15 እምብዛም እውቅና የሌላቸው ዕጩ ተወዳዳሪዎች ብቻ እንደነበሩም አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡ አሜሪካ፣ እንግሊዝና ኖርዌይን ጨምሮ በርካታ ምዕራባውያን አገራት፣ ላለፉት 25 አመታት ሱዳንን በፕሬዚዳንትነት የመሩት አልበሽር፤ በከፍተኛ ድምጽ ያሸነፉበትንና ባለፈው ሰኞ የተከናወነውን የአገሪቱ ምርጫ ድምጽ አሰጣጥ ነጻና ፍትሃዊ አይደለም፣ እውቅና አንሰጠውም ሲሉ የተቹት ሲሆን፣ የቻይናው ፕሬዚደንት ዢ ጂፒንግ በበኩላቸው፤ ለአልበሽር የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት ልከዋል፡፡
ስቲስ ኤንድ ኢኳሊቲ ሙቭመንት የተባለው የአገሪቱ አማጺ ቡድን ባለፈው እሁድ በደቡብ ዳርፉር አካባቢ በሱዳን መንግስት ጦር ላይ በከፈተው ወታደራዊ ጥቃት የጦር ካምፕ ማውደሙንና የጦር መሳሪያዎችን መማረኩን ያስታወቀ ሲሆን፣ የአገሪቱ የጦር ሃይል በበኩሉ አማጽያኑ በሚንቀሳቀሱበት አካባቢ ባደረገው ድብደባ ከፍተኛ ውድመት ማድረሱን አስታውቋል፡፡ በአየር ድብደባው 16 ሲቪል ዜጎች መሞታቸውንና ከ11 በላይ የሚሆኑ ደግሞ መቁሰላቸውን የዘገበው አይቢታይምስ ነው፡፡
በዳርፉር ግጭት የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽመዋል በሚል በአለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ክስ የቀረበባቸውና የእስር ማዘዣ የተቆረጠባቸው የ71 አመቱ አልበሽር፣ ድርጊቱን አልፈጸምኩም ሲሉ ተቃውሟቸውን ማሰማታቸውን ዘገባው ጨምሮ አስታውሷል፡
ፕሬዚዳንት አልበሽር እ.ኤ.አ በ1989 በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን ከያዙበት ጊዜ አንስቶ አገሪቱን እየመሩ ሲሆን ሱዳንን ለረጅም ጊዜ በመምራት ቀዳሚው ሰው እንደሆኑ ይታወቃል፡፡

Read 1461 times
Administrator

Latest from Administrator